ዘላለም ግርማ
ሰምሃል ጉዑሽ የካባና የዲዛይን መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ናት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ አርክቴክቸር፣ የሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኮሌጅ (EiABC) ውስጥ የአርክቴክቸር ትምህርትን ከተማረች በኋላ ከስዊድን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በዘላቂ ሥራ አመራር ዲፕሎማ ተቀብላለች።
ሰምሃል በፋብሪካ ቁጥጥር ዘርፍ ከስካይላይን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት (LIDI) የምስክር ወረቀት ተቀብላለች፡፡ በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በአመራርነት እና በኢንተርፕርነርሺፕ ስልጠናዎች ከአሜሪካን ኤምባሲ ወስዳ ሰርተፊኬት ተቀብላለች። በያሊ ፌሎውሺፕ የሚሰጠውን የዘላቂ ቢዝነስ ማኔጅመንት ስልጠና ወስዳለች። በሌሎች ፕሮግራሞችም በመሳተፍ የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን አግኝታለች፡፡
ሰምሃል ከተመረቀች በኋላ ወዲያውኑ በአርክቴክት ቢሮ ቢ.ኬ.ደብዩ አርክቴክቶች (BKW Architects) እና በሌሎች የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ውስጥ ለጥቂት ወራቶች ሰርታለች። ከዛም ለሁለት ዓመታት በአርኪቴክቸርና ኢንጂነሪንግ ድርጅቶች ከሰራች በኋላ የፕሮግራም ዝግጅት አቅራቢ ድርጅት ውስጥ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት አገልግላለች።
የራሷን ድርጅት ለመመስረትና ፍላጎቷን ለማሳካት ሙሉ ጊዜዋን ለስራ ማዋል እንዳለባት ከተገነዘበች በኋላ ማህበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ የተመሰረተውን የቆዳ ውጤቶች አምራችና ላኪ የሆነውን ቀበና ቆዳ ፋብሪካ ለማቋቋም በቅታለች።
በቅርቡ የኢትዮጵያዊን ሄራልድ ጋዜጣ ከዚህች ቆራጥ ወጣት አንተርፕርነር ጋር በጉዞዋ እና በተሞክሮዎቿ ዙሪያ አጭር ቆይታ አድርጎ ነበር። ለዚህ ዝግጅት ክፍል በሚመጥን መልኩ አዘጋጅተን እነሆ ብለናል። መልካም ንባብ።
እባክዎን ስለ ድዛይን የሥራ ጉዞዎ እና በዚህ ዘርፍ ለመግባት ምን እንዳነሳሳዎ ትንሽ ይንገሩን?
ዲዛይን የእኔ ፍላጎት ከሆነ ቆየት ብሏል። በሕይወቴ ውስጥ ምንም ያህል እንቅፋቶች ቢያጋጥሙኝም ከመስራት የሚገድበኝ ምንም ነገር የለም፤ ይህ የእኔ የሁል ጊዜ ስሜቴ ነው። የካባና ቡድን የአስደናቂ እና ጠንካራ ሴቶች እውነተኛ ስብጥር መሆኑ በሙያዬ ለእያንዳንዷ እርምጃዬ ወደ ፊት እንድራመድ የሚገፋፋኝ ሌላኛው ምክንያት ነው።
ከሰራተኞቼ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችንም ሊያነቃቃ የሚችል በርካታ ታሪኮች አሉኝ። የቀበና ቆዳ በንግዱ ዘርፍ አዎንታዊ ተፅእኖን እያመጣ ከመሆኑ ባለፈ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል እየፈጠረ በመሆኑና በዚህም ህይወታቸው ሲቀየር ሳይ በፊቴ ላይ ፈገግታ የሚጭርብኝ ነገር ሆኗል።
በኩባንያዎ ውስጥ ምን ዓይነት ሸቀጦች እየተመረቱ ነው? በወጪ ንግድ ላይ የሄዱበት ርቀት እንዴት ይገለፃል?
ከ90 በመቶ በላይ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም የጉዞ ሻንጣዎችን፣ የሻንጣ ከረጢቶችን፣ የላፕቶፕ እና የኪስ ቦርሳዎች እንዲሁም እንደ ቀበቶ ያሉ የቆዳ ቦርሳዎችን እናመርታለን።
ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ምርቶቻችን ለኤክስፖርት ገበያ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ሩዋንዳ ያሉ ጥቂት የአፍሪካ አገራት ወደ ውጭ ቢሄዱም፤ እኛ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ገበያም ጭምር ተሰማርተን እንገኛለን።
የእርስዎ ትልቅ ፈተናዎች የሚሏቸው ምን ምን ነበሩ? ከሂደቱስ ምን ትምህርት ተማሩ?
የ“ኮቪድ-19” ወረርሽኝ መከሰት ለእኔ፣ ለቡድኔ እና ለካባና ቆዳ ምርት ትልቅ ፈተና ሆኖ ነበር። በመላው ዓለም እንደ አብዛኞቹ የንግድ ድርጅቶች እንደገጠማቸው እኛም ብዙ መሰናክሎች ነበሩብን እና የተዘጉ ሱቆች ማለት ይቻላል። በወቅቱ ደንበኞቻችን ትዕዛዞቻቸውን ስለሰረዙ በጣም ከባድ ሆኖ ነበር። ነገር ግን ንግዱ ከተመለሰ በኋላ ሁሉም ተሰርዘው የነበሩ ትዕዛዞች በትላልቅ ቅናሾች ተልከዋል።
በወቅቱ የተከሰተው ወረርሽኝ ከዚህ በፊት የማናውቀው ነገር በመሆኑ ጊዜያዊ ሠራተኞቼን አሰናብቼ ባሉት ጥቂት ቋሚ ሰራተኞች ብቻ ጭምብሎችን እና ሌሎች የግል መከላከያ መሣሪያዎችን ለማምረት ፋብሪካውን እንደገና ለመጠቀም ተገደድኩ። ምስጋና ለማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ይሁንና ሰራተኞች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ እና አጠቃላይ ስራውም ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን አስችሎናል።
በተጨማሪም፣ ይህንን ኩባንያ ከመመሥረቴ በፊት ካሳለፍኳቸው ውድቀቶች ውስጥ በርካታ የሕይወት ትምህርቶችን ወስጃለሁ፤ እናም አማካሪዎቼ ከሆኑት ጠንካራ ሴቶች ጋር መገናኘቴ ዕድለኛ አድርጎኛል።
የሥራና ሌሎች ማህበራዊ ሕይወትዎን እንዴት ሚዛናዊ ያደርጋሉ? ከሠራተኞችዎ ጋርስ ያልዎት ግንኙነት እንዴት ይገለፃል?
እኛ በፈጠርነው ሥራ ከመቶ በላይ ሰራተኞች ያሉን ሲሆን ከ300 በላይ ቤተሰቦችንም እንደግፋለን። ምንም እንኳን እስካሁን ትዳር ባልመሰርትም ሰራተኞቼን እንደ አንድ ቤተሰብ በመቁጠር በእርግጠኝነት ለራሴ እውነተኛ ቤተሰብ አፍርቻለሁ።
ሰራተኞች ልጆቻቸውን ወደ ስራ እንዲያመጧቸው እና የስራ-ህይወትን ሚዛን እንዲጠብቁ የሚያስችል የልጆች እንክብካቤ ማዕከል ከፍተናል። ከስራ ህይወቴ ውጭ፣ ከእኔ በጣም የሚቀራረቡ አንድ አህት እና ታናናሽ ወንድሞች አሉኝ። ከእነሱ ጋር ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ እሞክራለሁ። በሕይወቴ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር በቂ ጊዜ ለማሳለፍ እፈልጋለሁ። ለራሴም በቂ ጊዜ መስጠቴን አረጋግጣለሁ።
ቤት ውስጥ ጊዜ ማሳለፍ፣ መፅሃፍ ማንበብ እና ምግብ ማብሰል ያስደስተኛል። ነገር ግን፣ አሁንም የጊዜን ሚዛናዊነትን እየተማርኩ ነው፤ ይህም ቀጣይ ሂደት ነው ብዬ አምናለሁ።
የእርስዎ ትልቁ ስኬትዎ ምንድነው?
እኛ፣ እንደ ካባና ቡድን፣ በፋብሪካችን ውስጥ ወደ 250 የሚጠጉ ሰዎችን አሰልጥነን አንድ መቶ እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለናል። ለዚያም ለምሳሌ በዩ.ኤን.ዲ.ፒ በሚዘጋጀው “ወጣት ሴት ሥራ ፈጣሪ በ2018” ዓይነት ሽልማቶችን መቀበል ችለናል። በተመሳሳይ እኛም ከ2020 ማንዴላ ፌሎውሺፕ፣ ከአህጉራዊ ኢንተርፕረነር 2020/21 ሽልማት፣ እንዲሁም የ2021 የአመራር ሽልማትን ወስደናል።
የራስዎን የተሳካ ኩባንያ የምትመራ ሴት እንደመሆንዎ መጠን ለአንባቢዎቻችን ምን ምክር መስጠት ይፈልጋሉ?
ምንም እንኳን አሁንም እየተማርኩኝ እና በኩባንያዬ ውስጥ የተሻሉ ውጤቶችን ለማምጣት እየተጓዝኩ ቢሆንም፣ ለሚታገሉት ሴቶች ሁለት ነጥቦችን ማንሳት እፈልጋለሁ። አንደኛው በጭራሽ ተስፋ አለመቁረጥን፣ ፍላጎትን መከተል እና በዙሪያቸው አዎንታዊ ተፅእኖ ለማምጣት ሁል ጊዜ መጣር የሚሉት ናቸው።
ለሴቶች ያለኝ ሌላው ምክር ደግሞ ሴቶች በተሰማሩበት በማንኛውም መስክ ምርታማነታቸው እንዲጨምር፣ ተነሳሽነታቸው እንዲመጣ፣ እና ብቃታቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ እንደ “የሴቶች ንግድ ማህበር (AWiB)” ያሉ ማህበራትን መቀላቀል እንደሚኖርባቸው ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2013