ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
በህይወት ለሌሉ ሰዎች መታሰቢያ የሚሆን አንዳች ነገር ማቆም የተለመደ ነገር ነው።በሀገር ደረጃ እውቅና የተሰጣቸው ለመታሰቢያቸው ተብሎ መንገድ፣ ህንጻ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግፋ ሲልም በስማቸው ተቋም የተሰየመላቸው ግለሰቦች አሉ፡፡
አንድ ቀን በመንገዴ ላይ ትኩረቴን የሳበው የግሮሰሪ ስም የዚህ ጽሁፍ ርእስ እንዲሆን ፈቀድኩ።ግሮሰሪው “እከሌ መታሰቢያ ግሮሰሪ” ይላል።የግሮሰሪ ተጠቃሚ ባልሆንም ግሮሰሪ ውስጥ የሚሰጠውን አገልግሎት ስለማውቅ በግሮሰሪው ቤት እንዲታወስ የተፈለገው ሰው መታሰቢያነቱ እንዴት ይታይ ይሆን? ስል ራሴን ጠየኩ።የአልኮል ማስታወቂያን ለመገደብ እንዲቻልና በሀገራችን ሚዲያ ውስጥ እንዳሻው እንዳይሆን ለማድረግ ህግ እንዲወጣለት ድረስ መድረሱን አስታወስኩና የግሮሰሪ መታሰቢያነት በአሉታዊነት ወደ መታየቱ ማዘንበሉ የግድ ነው ብዬ ከራሴ ጋር የጀመርኩትን ወሬ አቆምኩት፡፡
አጋጣሚው ግን ስለ መታሰቢያ እንዳስብ አደረገኝ።መታሰቢያ ስለሚሰራላቸው ግለሰቦችና ጥለውት ስለሚያልፉት ሌጋሲ።
በዓላማ ዙሪያ የሚጻፉ ጽሁፎች ላይ አንድ ሰው ዓላማዬ ብሎ የሚኖርለት ጉዳይ በእለተ-ህልፈቱ የህይወት ታሪኩ ሲነበብ ሊሰማ የሚፈልገው ቢሆን ይመከራሉ።“እኔ በእለተ-ህልፈቴ ምን ተብሎ ታሪኬ ቢነበብ እፈልጋለሁ?” የሚለውን ጥያቄ መነሻ አድርገው የህይወት ጉዟቸውን የሚጓዙ ሰዎች በዓላማ-መር ህይወት ውስጥ መሆናቸው ይታመናል። በዚሁ መንገድ የምንራመደው እያንዳንዱ እርምጃ ተደማምሮ ደግሞ ሌጋሲን ይፈጥራል፤ ጥለን የምንሄደው መታሰቢያችን።
የትላንት ጉዟችን ወደድንም ጠላንም የምንታወስበት ሆኖ የሚቀጥል መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም።ሰዎች እኛን በተግባር ባዩበት መልክ ያስታውሱናል።ሌጋሲ በተግባር በኖርንበት ኑሮ አንጻር ትርጉሙ የሚገኝ በመሆኑ የዛሬ ኑሮ የነገ ሌጋሲ ነው።
በዓለማችን ላይ ያሉ ፋውንዴሽን በሚል ተቀጥያ የሚጠሩ ተቋማት መስራቾቻቸው ወይንም የተመሰረቱበት ግለሰብ ሌጋሲ የህይወት ጉዞ ወይንም ኑዛዜ አንጻር በእጅጉ ይቆራኛሉ።የፋውንዴሽኑ ሰራተኞችም መታሰቢያ ይሆንለት ዘንድ በተመሰረተው ሰው ሌጋሲ ላይ ተመስርተው ይሰራሉ፤ ለደመወዝ ቢሰሩም በዙሪያቸው ባሉት ዘንድ ግን እነርሱም የራሳቸውን ሌጋሲ እያስቀመጡ ያልፋሉ።በምንኖረው፣ በምንናገረው፣ በምንሰጠው፣ ጆሯችን ለሌሎች ችግር በተከፈተበት መጠን፣ ልባችን በቅንነት በተቃኘበት ቅኝት ወዘተ ውስጥ መታሰቢያችን በሌሎች ውስጥ ይገነባል።
ሰው ለወደደው በሌጋሲው ልቡን ለሰጠው በወደደውና በቻለው መጠን መታሰቢያውን ለማስቀመጥ ይጥራል።ዛሬ ጥለን ስለምናልፈው ሌጋሲ በማንሳት እያንዳንዱን ቀን ልንኖር እንደተገባው ኖረን እንድናልፍ ማሰቡ የግድ ነውና፤ ስለ እያንዳንዱ እርምጃ በማንሳት እንዝለቅ፡፡
እያንዳንዱ እርምጃ፣
ሌጋሲ የእያንዳንዱ እርምጃ ውጤት ነው።ሌጋሲ የአንድ ጠብታ ውሃ ጥርቅም የሆነው ጅረት ማሳያ ነው።ሌጋሲ በሽርፍራፌ ማይክሮሰከንድ ውስጥ የምንኖረው ኑሮ ተደምሮ የሚሰጠን የህይወት ዘመን መልክ ማሳያ ነው፡፡
የእያንዳንዱ እርምጃ ውጤት የህይወት ዘመንን መልክ የመበየን አቅም እንዳለው ከተረዳን የህይወታችን እያንዳንዱ ጉዞን በጥንቃቄ መምራት አስፈላጊ ይሆናል።ዛሬ ሀገራችን የምትገኝበት ገጽታ የአንድ ቀን፣ የአንድ ወር ወይንም የአንድ ዓመት ውጤት መሆኑን ካሰብን የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረሳችን አይቀሬ ነው።እውነታው ያለፉት የበረከቱ ዓመታት ድምር ውጤት ዛሬን መሆኑ ሲሆን፤ በመዝራትና ማጨድ ህግም እንደተደነገገው።
በሰላም ግንባታ ቢሆን በልማት መስፋፋት የዛሬው መልካችን የትላንት እያንዳንዱ እርምጃ ውጤት ማሳያ ነው።በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የጦርነት ታሪክ ለዛሬው ገጽታችን አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡
በግለሰብ ደረጃ እርምጃችንን እንዴት እንወስን የሚለውን ለመናገር ስንነሳ መዳረሻው በግለሰብ ውስጥ ይሆናል ማለት ግን አይደለም፤ በፍጹም! በግለሰብ ደረጃ የሚሆነው እያንዳንዱ እርምጃ ከጎረቤት ጋር ሆኖ በማህበረሰባዊ መልክነት ተንጸባርቆ በስተመጨረሻ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ሆኖ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ የሚታይ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡
ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያን ሲያዩ የሚታያቸው መልክ ውስጥ የእያንዳንዳችን የተናጥልም ይሁን የጋራ እርምጃ ውጤት ይገኝበታል።የግል እርምጃችን ለግላዊ ሌጋሲ ትርጉም ቢኖረውም፤ የሀገራዊ እርምጃችን ግን በእያንዳንዳችን እርምጃ ድምር ውስጥ ትርጉም ኖሮት የጋራ መልካችን ሆኖ ይታያል።
ለውጥ ሁልጊዜ የሚኖር ስለሆነ ማህበረሰባዊ ለውጥን በምናስብበት ጊዜ ማሰብ ከሚኖርብን ነገሮች መካከል ለውጡ ከየት ጀምሮ የት ድረስ ሊዘልቅ ይገባዋል የሚለውን ጥያቄ ነው።እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በእድሜ ጠገብ ሀገራት ውስጥ በዓመታት ውስጥ የዘለቀ ማህበረሰባዊ እሴት ያለው ቦታ ቀላል አይደለም።ታላላቆችን ማክበር፣ የበኩርና ቤተሰባዊ ሃላፊነት፣ በሸንጎ ፊት የሚኖር ስርዓት፣ በደቦ አብሮ በመሰለፍ ለጋራ ውጤት መስራት ወዘተ በዓመታት ውስጥ በዘለቀው ማህበረሰባዊ እውቀት ውስጥ ከግለሰብ ሌጋሲ ማህበረሰባዊ ሌጋሲን መፍጠር የሚያስችሉ እሴቶች ናቸው።
በእያንዳንዱ እርምጃ ውስጥ ስለሚፈጠር ሌጋሲ በምናስብበት ጊዜ የግለሰብ ሌጋሲ ወደ ማህበረሰብ ሌጋሲ እየተሸጋገረ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ በማህበራዊ ወረት ላይ እንደሚፈጥር ማሳየት ይገባል።ትላንት የኖሩ አባቶቻችንና እናቶቻችን ጥለውልን ያለፉት ሌጋሲ የሚያሳየን በማህበራዊ ወረት ላይ ከተሰራበት ብዙ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ነው።ማህበራዊ ወረት ተሸርሽሮ የእሴት ትርጉም ሚዛኑን ሲያጣ ግን መታሰቢያ እንዲሆን በምንመርጠው የመታሰቢያ ምልክት መረጣችን ለግምት የሚጥለን ይሆንና ባልተገባ ስፍራ መታሰቢያን እንሰራለን።
ሰዎች ገንዘብን ጥለው ሊሄዱ ይችላል፤ ንብረትን እንዲሁ በአይነት በአይነቱ ጥለው ሊሄዱ ይችላሉ ለሁላችን የሚጠቅም ሌጋሲ ግን ሰላምን ትተው የሚሄዱ መሆናቸው ነውና ሌጋሲን ከሰላም አንጻር ማየት የግድ ይለናል። ሌጋሲ በእያንዳንዱ ግለሰባዊ እርምጃ ውስጥ ተጽንሶ የሚወለድ መሆኑን አስምረንበት በዓመታት ውስጥ ዓላማ ባደረጉት ነገር ሊታወሱ የሚፈልጉ ሰዎች ስለ ሌጋሲ ሲያስቡ ማሰብ ካለባቸው ነገሮች መካከል በቅድሚያ መቀመጥ ያለበትን የሰላም ጉዳይ እናንሳ።ከሁሉም ስለሚቀድመው ውስጣዊ ሰላም ግን በቅድሚያ!
ቀዳሚው የውስጥ ሰላም፣
ስለ ሰላም ብዙ ተዘምሯል።ሰላም ያላት ዋጋ ውድ መሆኑን ለማሳየት ሰዎች ከልዩነቶች ባሻገር በመሄድ በተመሳሳይ ቃል ሰላምን ገልጸዋታል።ሰላም ግን እንደ ታሰበው በለስላሳ ዝማሬዎች የምትገኝ አልሆነችም።ከእያንዳንዱ ጓዳ እስከ አደባባይ ሰላም እንዲሁ በቀላሉ የምትገኝ እንዳልሆነች የተስማማንም ይመስላል።ሰላም መቀበልን ብቻ አስቦ በሚራመድ መስመር ውስጥ በስሌት የማትገኝ በመሆኗ በብዙ የራቀችንም ትመስላለች።ሰላም በመሞት ውስጥ የሚገኝ ህይወት መሆኑን መረዳት ባለመቻል በብዙ አጥተናታል።ሰላም ለሌላው በመኖር ውስጥ ራስን ማግኘት መሆኑ ደጋግሞ ቢሰበክም ሰላምን ማእከል አድርገው የሚኖሩት መጠሪያቸው ሞኝነት ሆነና ከህይወት ገበያ ውስጥ ሊሸምታት የሚወድ ብዙ ሳይሆን ቀረ፡፡
በታሪክ ፊት መታወስ፣ በአካባቢ መታወስ እንዲሁም በሰዎች ልብ ውስጥ በመልካም መታተም የብዙ ሰው ፍላጎት ሆኖ የሚታይ ቢሆንም የፈለግነውን ለምን እንዳጣን ስንፈልግ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጹእ ነው” ከሚለው መፋታታችንን አሳየን፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ በሚከተሉን ሰዎች ቁጥር በሆነበት ሁኔታ የተከታይ ቁጥር የእርምጃችን ታላቅነትን የሚያሳይ ሆኖ በእንክርዳዱ ሁሉ ላይ የሌጋሲ ትርጉም መፈለግ ተጀመረ።ሰላም መፍጠር መቻል፤ የሰላም ሰው መሆን፤ በውስጥ ሰላም ውስጥ ህይወትን ማካፈል በመቻል ውስጥ ከሚታይ ህይወት የሚቀዳ ሌጋሲነት ቦታውን እያጣ ሽብር ፈጣሪና ሰላምነሺነት ቦታውን የያዘ መስሎም በጉልህ ታየ።
የቤት ሰላም፣
ግሮሰሪ አምሻሽቶ ልጆቹ እንቅልፍ ከጣላቸው በኋላ ወደ ቤቱ የሚገባ አባት በልጆቹ ውስጥ የሚፈጥረው ስሜትና የሚሰራው መታሰቢያን ለማሰብ እንሞክር።ግሮሰሪ ቀማምሶ ካልተደባደብኩ የሚለውንም አባት እንዲሁ እናስበው። ልጆች በእንቅልፍ ድባብ ውስጥ ሆነው እናትና አባት በሚያደርጉት ንትርክ ውስጥ ሰላማቸው ደፍርሶ የሚያልፏቸው ሌሊቶች የሚሰሩት የመታሰቢያ ድንኳንስ ምን ይመስል? በተቃራኒው ከስራ መልስ በጊዜ ከቤቱ ተገኝቶ ለልጆቹ ከተጣበበው ጊዜ ውስጥ ሰዓት መድቦ ያለውን ለመስጠት የሚጥረውስ አባት? የእናት ሌጋሴ መቼም የትም በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን በቃላት የማይገለጽ በመሆኑ ስለ እናት ለማስረዳት መድከም የለብንም በማለት የቤት ውስጡን ሰላም በተወሰነ በአባቶች በኩል አድርገን ለማየት ሞከርን፡፡
በቤት ሰላም የሚፈጠር ሌጋሲ ወደ አደባባይ ወጥቶ ሃውልት የሚቆምለት ቢሆን ምን ያህል መታሰቢያዎች ይገኙ ይሆን? አንባቢው አባት ራሱን ሲመረምር ምንስ ወደ ልቦናው ይዘልቃል? ሌጋሲን በብዙ አቅጣጫ ማስረዳት ቢቻልም ሰላምን ማእከል አድርገን እየተጓዝን መሆኑን አንባቢው ልብ እንዳለ አስባለሁ፡፡
ከቤት ሳንወጣ በቤተሰብ ውስጥ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ውስጥ የሰላም ሚናውን የሚጫወት የቤተሰብ አባል ሌጋሲ በምን ቃላትስ ይገለጹ ይሆን? ጥያቄዎችን እያብላላን መታሰቢያ የተገባቸውን ሰዎች በውስጣችን እናመላልሳቸው፡፡
በሀገራችን የለቅሶ ሥነ-ስርዓት ውስጥ የሟቹን ሰው መልካምነት የሚያሳዩ ቃላት ከለቀስቶኛው ዘንድ መደመጡ የተለመደ ነገር ነው።በለቅሶ እለት ሟቹ ሁሉ ጻድቅ ወይንም ለመላእክትነት ሩብ ጉዳይ እንደሆነ ማሰብ ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም።
የቤት ሰላም መታሰቢያ ይገባው እንደሆን በማሰብ ወደ ቤተሰብ ዘልቀን እንግባና አልጋ ለይተው ዓመታትን ያስቆጠሩቱ፣ አንዳቸው በሌላላቸው ላይ ስልት የሚያነሱትን፣ አልጋቸውን ለሌላ የሚያጋርቱን ወዘተ አስበን ከትዳር የሚሸሹትን የሚያቀርቡትን መከራከሪያ ወደ ጎን ለማድረግ እንድንችል በበጎ መታሰቢያ የሚታወቁትን ከሚዛን አድርገን እንመዝን።በትዳር ውስጥ ልጅ ማግኘት እንደታሰበው መሆን ባልቻለ ጊዜ ትዳርን ማፍረስ እንደ ቀላል በሚመክሩና እስከ እለተ ሞታቸው ልጅ ባይኖረም ቃሌን አላጥፍም ብለው በንጽህና የዘለቁ የእውነት ሰዎችን በሚዛን አድርገን እንዴት በሌጋሲ መጻህፍት ውስጥ እኒህ ምርጦች ምእራፍ ተነፈጋቸው? ብለን እንጠይቅ፡፡
እከሌ ግሮሰሪ መታሰቢያ አልኮል እየቸረቸረ እከሌን ለማስታወስ የሄደበት እርቀት ግለሰቡ ምን ቢሆን ብለን እንድንጠይቅ እንዳደረገን፤ እንዴት መልካሞቹ የቃላቸው ሰዎች በማህበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ ተደንቀን የምንማርባቸው ህያው መጻህፍት መሆናቸውን ዘነጋን።
የቤተሰብ ሰላም መሰረቱ የግለሰቡ ሰላም ሲሆን ሰላምን ማእከል ያደረገው ጉዞ ውስጥ ያለው ሌጋሲ ደግሞ አስተማሪነቱ ጉልህ ነውና አቅሙ ሃያል ነው።አስተማሪነቱ ወደ ጉርብትና የሚያልፍ መሆኑ ጥርጥር የለውም።
ጉርብትናችን ትርጉም ሲኖረው፣
በኢትዮጵያ አውድ ጉርብትናን በቀላሉ መግለጽ መቻል አስቸጋሪ ነው።ጉርብትና አንድ ሁለት ነገር ብቻ አይደለምና።በጉርብትና ውስጥ የጎደለን እየተሞላ እንኖራለን፣ ልጆች በቤተሰብ ብቻም ሳይሆን በጎረቤት እይታ ውስጥም ሆነው ያድጋሉ፣ ግጭት ሲገጥም ወደ መፍትሄው ለመድረስ ሽማግሌዎች ይሰየማሉ፣ ደስታን ለመካፈል፣ ክፉ ቀንንም በጋራ ለመወጣት በጉርብትና ውስጥ የሚሆነው በሂሳብ መግለጫ ላይ ትርፍና ኪሳራ ተሰልቶ የሚደረስበት ቁጥር አይነት አይደለም።በጉርብትና ውስጥ ትዝታቸው በበጎ የሚነሳ ለሁሉም ምሳሌ የሚሆኑትን ፍለጋ ካለንበት አካባቢ የተወሰኑ ሜትሮችን ሄደን የሰፈሩን ነዋሪዎች መጠየቅ ብቻ ሊበቃ ይችላል።
ዛሬ ዛሬ በጉርብትና እሴትን ወዝ የሚቀንሱ ወፋፍራም አጥሮች በየቀዬው የበረከቱ ቢሆንም አሁንም ለጉርብትና ሰፊ ቦታን በምትሰጥ ሀገር ውስጥ መኖራችንን ልንክድ አንችልም።ጉርብትናችን ትርጉም እንዲኖረው ከግለሰባዊ እሴት ወደ ቤተሰባዊ ገጽታ የሚያልፈው መልካችን አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።በጉርብትና ሌጋሲያቸው የጨመሩት ዋጋ እጅግ የገዘፉት ላይ ጥናት አድርጎ መታሰቢያ ሊቆምላቸው የሚገቡትን መዘርዘር ብንጀምር ስንት ላይ ማቆም እንደምንችል እርግጠኛ አይደለንም።የጦር መሪዎችን አስቀድሞ መታሰቢያቸውን ለማቆም በብዙ በምንተጋበት ልክ ጦርነት እንዳይኖር ሰላምን በማውረድ የሚታትሩ የጉርብትና አዋቂዎችን መዘከሩ ትርጉሙ ከፍ ባለ ነበር፡፡
ጉርብትናችን ትርጉም ያለው ባልሆነበት ጊዜ ሰላምን የሚያሳጣ አንዳንዴም ህይወትን የሚጠይቅ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።በጉርብትና ውስጥ በሚያጋጥሙ አሉታዊ ገጠመኞች በመነሳት አጥርን ማጥበቅ የዘመናዊነት ምልክትም መስሏል።እውነታው ግን የሴኩሪቲ ካሜራ ከሚሰጠው አገልግሎት በላይ በጉርብትና እሴት ውስጥ ያለው እጅጉኑ ይገዝፋል።መቀበልን ሳይሆን መስጠትን ታሳቢ አድርገን የምንከተለው የጉርብትና ህይወት በየት በኩል ዋጋችንን እንደሚከፍለን አናውቅም።በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ከአንድ ነጋዴ ጋር ከምናደርገው የንግድ ልውውጥ ከምናገኘው ዋጋ በገንዘብ ስሌት ውስጥ ካለ ልውውጥ ዋጋው የበዛና ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ወረት መሆኑን ነው።
ለእከሌ ግሮሰሪ መታሰቢያ ያደረገው ሰው/ያደረገችው ሰው የራሷ ምክንያት እንዳላት ብንገምትም ስለጉርብትና መታሰቢያ ማቆም የሚገባው ምክንያት ያለው እንደሚበዛ አንጠራጠርም።አንዳንዱ መታሰቢያ በግልጽ የማይታይ ሊሆን ይችላል፤ በልብ ውስጥ ብቻ ከፍ ብሎ የሚሰቀል።
እያንዳንዱ የግለሰቡ እርምጃ በሰላም ውስጥ ለማየት እንደሞከርነው፤ በቤተሰብ ውስጥ ያለውም ህይወት በሰላም ሚዛን ስንመዝነው የሚሰጠን ውጤት ጤናማ ከሆነ ሌጋሲ ፈጣሪ ከሆነ ያለጥርጥር ጉርብትናን በመዋጀት ረገድ አቅም ያለው ነው።የጉርብትናችንን ጤንነት ሊያውክ የሚችል ቢሆንም የተመሰከረለት ሰላማችን ማሸነፍ የሚችልበት አቅም አለውና ለውጥ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
ጉርብትናውን አልፈን እንዝለቅ …
ከደመወዝ ያለፈው መታሰቢያ፣
ከጉርብትና እልፍ ብለን ወደ ስራ ቦታችን እንሂድ።በስራ ቦታ የተገኘነው ደመወዝን ፍለጋ ሊሆን ይችላል።ሙያችንን ሸጠን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ለማግኘት።ይህ መሆኑ ችግር ነው ብዬ አላምንም።የስራ ቦታ የምንታወስበትን እያሰቡ የስራን አካሄድ መተለም ግን ይገባል።ለደመወዝ መከፈል የሚገባውን ስራ በመስራትና ሌጋሲ ፈጣሪን ስራን በመስራት መካከል ባለው ልዩነት ላይ መስራት ይገባል።በተቋም ውስጥ በስራ ምዘና ስርዓት ውስጥ ሲያልፉ የሚጠበቅባቸውን ተወጡ የምንላቸው ነገር ግን ሌጋሲያቸው ሰላም ፈጣሪ ያልሆነ፤ ሌጋሲያቸው ለሌሎች ትምህርትን የሚሰጥ ያይደሉ ሰራተኞች ይገጥሙናል።
በሚገባ የተደራጁ ተቋማት አዳዲስ ሰራተኞችን ሲቀጥሩ ከቀደመው ድርጅታችው ውስጥ ምስክርነትን ይጠይቃሉ።የሚያገኙት ምስክርነት ውስጥ መካከል አዲሱ ድርጅት ሊቀጥረው ያለውን ሰራተኛ የቀደመው ድርጅቱ ዳግም የመቅጠር እድል ቢኖረው ሊቀጥረው የሚፈልግ መሆኑን አለመሆኑን የሚጠየቅበት ጥያቄም ይገኛል።አብሮን ይሰራ የነበረን ሰው ከእኛ ተለይቶ ዳግም ልንቀጥረው እንድንፈልግ የሚያደርገን የኖረው ኑሮው እርሱ ትቶልን የሚሄደው ሌጋሲው ነው።በሰዓት ስራ የሚገቡ፣ በሰዓት የሚወጡ፣ የሚጠበቅባቸውን የሚወጡ፣ ነገር ግን ሌጋሲን ከማይፈጥሩ መማር ይገባናል።ሌጋሲ የሚጠበቀውን በመስራት ሳይሆን ከሚጠበቀው በላይ በአዎንታዊ ልብ በመስራት የሚገኝ ነውና።በስራ ቦታ ይህ መሆን የሚችለው ከደመወዝ ያለፈን እይታ ማየት ሲቻል ነው።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ተቋማት ውስጥ ሊመጣ የምንፈልገውን ለውጥ በመናገር ረገድ የበረቱ አስተያየት ሰጪዎች ያሉንን ያህል ተቋማትን በመገንባትና ከሚጠበቀው በላይ በመሄድ ሌጋሲን መፍጠር በመቻል ረገድ ግን ያሉን ሰዎች እጀግ ጥቂቶች ናቸው።ይህ የሚሆነው ከደመወዝ ሆነ ከስልጣን ባለፈ ውጤትን ታሳቢ ያደረገን ሥራ በመስራት ውስጥ ስለሆነ ነው።ውጤቱም ሰላምን ለሥራው ተጠቃሚ መፍጠር ሲችል አድርገን ብናየው ደግሞ የበለጠውን ምስል ይሰጠናል፡፡
እከሌ መታሰቢያ ግሮሰሪ ስራውን እየሰራ ግብሩንም እየከፈለ ሲኖር በድርጅቱ ስም ላይ እንዲታወስለት የወደደውን ግለሰብ ስም አኑሯል።እኔ በህልፈቴ እለት ታሪኬ ወደ ኋላ ተጠንጥኖ ሲታይ ሰዎች ሊያስቡኝ የሚወዱት በምን ይሆን? ብለን በመጠየቅ የህይወት እርምጃችንን እንመልከት።ከውስጥ ሰላም በሚነሳ፣ በቤተሰብ ውስጥ በተገለጠ፣ በጉርብትናችን ውስጥ ቦታ የተሰጠውና ወደ ሥራ-ቦታችን የመጣ የሰላም ሰውነት ውስጥ ያለው ሌጋሲ ግን የከበረው ነውና እኒህ ሁሉ ቃላት ሰላም ፈጣሪ ለሆነ ሌጋሲ መታሰቢያ ሆኑ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013