መልካምስራ አፈወርቅ
ትውልድና ዕድገቱ ምዕራብ ጎጃም ልዩ ስሙ ‹‹መራዊ›› ከተባለ ስፍራ ነው። እንደማንኛወም የገጠር ልጅ በግብርና ስራ ሲሰራ ቆይቷል።በትምህርቱ እምብዛም አልዘለቀም።የቤተሰቦቹ ችግር ከእሱ ፍላጎት ማጣት ተደምሮ ርቆ አልተራመደም።ለእርሻ ካሉት ግን ትጉህ ገበሬ ነው።በሬዎቹን ጠምዶ መሬቱን ሲገምስ ይውላል።ምርት ሰብስቦ ጎተራ ሙሉ ያገባል፡፡
በላይነህ ደረሰ በዚህ የህይወት ጉዞ ዓመታትን በብርታት ዘለቀ።ቆየት ብሎ ግን ያልተለመደ አመል ታየበት።ግብርናውን ተወት አድርጎ በሀሳብ ናወዘ።ዓይምሮው አርቆ እያሰበ ብዙ ማቀድ፣ ብዙ ማለም ያዘ ።ውሎ ሲያድር ይህ ልማድ ጠናበት።ግብርናው ሰለቸው።ከበሬዎቹ ጋራ ተራራቀ።በቁዘማው ቀጠለ፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን በላይነህ ለውስጡ ጥያቄ ምላሽ አገኘ።ይህኔ ጓዙን ሸከፈ፣ ገንዘቡን ቋጠረ፣ ማልዶ ተነሳ።ጉዞው ወደ አዲስ አበባ ሆነ።አዲስ አበባ ለበላይነህ የልጅነት ህልሙ ነች።ስለከተማዋ ድምቀት ስለሰዎቿ ብዛትና ዘመናዊነት አስቀድሞ ሰምቷል፡፡
ከመንደሩ ያሉ ወጣቶችና የቅርብ ዘመዶቹ ሸገር ሄደው ተለውጠዋል።አብዛኞቹ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ኑሮ መለወጥ ምክንያት ናቸው።በላይነህ ይህን ጠንቅቆ ያውቃል።እነሱ ባለፉበት መንገድ እሱም ቢከተል የሚያገኘውን ጥቅም ካሰበበት ቆይቷል፡፡
አዲስ አበባ ሲደርስ ከተማዋ በቸር ተቀበለችው።በላይነህ የናፈቀውን ስፍራ ከጠበቀው በላይ አገኘው።እሱ ካደገበት፣ ከኖረበት ባህልና ልማድ በእጅጉ ይለያል።ይህ መሆኑ አላስከፋውም።ከሁሉም ጋር ቀርቦ ሁሉን ለመደ።ከተሜነት በእጅጉ ገባው፡፡
ከሰዎች ሲግባባ በርካታ የስራ አማራጮች እንዳሉ አወቀ።ካያቸው ከለያቸው ስራዎች ሁሉ ንግድና ገበያ ልቡን ማረከው።ያሰበውን ለማድረግ አላመነታም።ከአንድ የገበያ ስፍራ ተገኝቶ ስራውን ሞካከረ።ሁኔታው በወጉ እስኪገባው ግራ ተጋባ።ቆይቶ ግን ከሌሎች ብዙ ተማረ፤ መውጣትና መውረዱ አልከበደውም፡፡
መሾለኪያ ያለው የሀዲድ ገበያ በላይነህን የእህል ነጋዴ አድርጎ ሾመው፤ ፈጥኖ ከብዙ ደንበኞች ተወዳጀ።ከሌላ ስፍራ የሚገዛውን እህልና ጥራጥሬ በትርፍ ሲሸጥ የሚያዋጣው ሆነ።ጆንያ አቁሞ፣ በሚዛን ለክቶ የሚሸጥበት ስፍራ ከደንበኞቹ አግባብቶ ገቢ አመጣለት፤ ስፍር እየሞላ ዋጋ እየተመነ ገበያ መዋልን አወቀ፡፡
የእህል ንግዱ መልካም መሆን ሲይዝ በአቅሙ ቤት ተከራይቶ ራሱን ቻለ።የእህል ነጋዴው በላይነህ አንዳንዴ ገበያው እንዳሰበው ሆኖ አይቀናውም።በስፍራው እሱን መሰል ነጋዴዎች አብረውት ይውላሉ።አብዛኞቹ በንግዱ ዓለም አመታትን ቆጥረዋል።እንደእሱ ያሉ ጥቂቶች ደግሞ ለስራው ጀማሪ ናቸው።የአካባቢው ነጋዴዎች መክሰርና መክበርን ያውቁታል።ገበያ በጠፋ ጊዜ ካስቀመጡት ጥሪት ያወጣሉ።ቀኑ አለፍ ብሎ ገበያው ሲመለስም ተመልሰው ይተጋሉ፡፡
በላይነህ ጀማሪ ነጋዴ ነው፤ እንደነእሱ የንግዱን ውጣውረድ አልቻለውም።የዕለቱን ከሸጠ ስለነገው እርግጠኛ አይደለም።ያም ሆኖ መትጋት መሮጡን አልተወም።የዛሬን አጣርቶ የነገን ለመሙላት ይታትራል።ገበያው ከፍና ዝቅ ባለ ጊዜ ግን ይጨንቀዋል።የጀመረው እንዳይቋረጥ፣ ያሰበው እንዳይሰናከል ሲተክዝ ይውላል፡፡
ድንገቴው ኪሳራ
በላይነህና የእህል ንግድ አብረው ናቸው።እሱ በብርታት ንግዱ በልማድ እየተጓዙ ነው።አሁን ግን በላይነህ ድካም ይሰማው ይዟል።በየቀኑ የሚሮጥበት ስራ እያከሰረው ትካዜ ገብቶታል።ስራው እንደመጀመሪያ አለመሆኑ ነጋዴውን ለብድርና ዕዳ እየዳረገው ነው።ይህን ሲያውቅ ከወደቀበት ለመነሳት ቀናትን ቆጠረ።አልቻለም፤ ሙከራው የትም ሳያደርሰው ቀርቶ ስራውን ሊያቆም ግድ አለው፡፡
በላይነህ አዲስ አበባን በወጉ ያወቀበት የንግድ ስራ አብሮት አልዘለቀም።ለብደር ዳርጎት ለኪሳራ አድርሶት በዶውን ቀረ።ትናንት እንደአቅሙ ገንዘብ የቆጠረው ሰው አሁን ህይወት ከበደው።መላና ዘዴ የጠፋበት በላይነህ በትካዜ ቆዘመ።ተመልሶ ወደስራው እንደማይገባ እያሰበ ሌሎች አማራጮችን ፈላለገ።በላይነህ ለመተዳደሪያው የሚሆን እንጀራ አላጣም።ከተገኙለት የጥበቃ ስራዎች የተሻለውን መርጦ በአንዱ ስፍራ ተቀጠረ።ስራው አልከበደውም።ጠዋት ማታ በፈረቃ መዋል ማደርን ለመደ።
በላይነህ አንዳንዴ የነበረበትን የንግድ ዓለም አሁን ካለበት ስራ ጋር እያወዳደረ ይተክዛል።ትናንት በእጁ ሲቆጥረውና ሲያዝበት የነበረው ገንዘብ ዛሬ ወር ጠብቆ መምጣቱ ያስገርመዋል።እሱ እንደለፋው ንግዱ ቀጥሎ ቢሆን የሚደርስበትን ያስባል።ሕይወቱ እንደሚለወጥ፣ በቂ ገንዘብ እንደሚኖረው እያለመ ይቆጫል፣ ይናደዳል፡፡
አንዳንዴ የሚከፈለው ገንዘብ የልቡን አያደርስም።እንዲህ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ይናደዳል፤ ዓመሉ ከፍቶም ያለምክንያት ከሰዎች ጋር ይጋጫል።የገንዘብ ችግሩን ለመፍታት በትርፍ ሰዓት የሚሰራው ተጨማሪ የጥበቃ ስራ መፍትሄ ሆኖታል። በሌሎች ድርጅቶች ትርፍ ጊዜውን ሰውቶ የሚያገኘው ገንዘብ ጎዶሎወን ሞልቶ ለችግሩ ደርሷል።
የትናንትናው ነጋዴ የዛሬው ጥበቃ በሌላ የህይወት መንገድ ላይ ነው።አሁን እህል ለመሸመት አገር አቆርጦ አይሄድም።ያመጣውን ልሽጥ፣ ልለውጥ ሲል አያስብም።ዛሬ ላይ ትርፍና ኪሳራ ይሉት ጣጣ አብሮት አይደለም።ግዴታውን ከውኖ ወደቤቱ ይመለሳል።ጠዋት ማታ በሚተጋበት አዲስ ስራው ቀን ቆጥሮ፣ ጊዜ ጠብቆ የሰራበትን ይቀበላል።አሁን በላይነህ እየተረጋጋ ነው።የትናንቱን ረስቶ ዛሬን በበጎ ያስባል።ይህ ሀሳቡ መልካም ነገር እያመጣለት ነው።መረጋጋት መጀመሩ ቁምነገረኛ አድርጎታል፡፤
አዲስ ህይወት…
በላይነህ በጥበቃ ስራ ዓመታትን ቆጠረ።ዕድሜው ሲበስልና ጊዜው ሲጨምር ግን ብቸኝነት አስጠላው።በየቦታው በስራ መሮጡ የተሻለ ገንዘብ አስይዞታል።አሁን ነገን በመልካም እያሰበ ነው።ይህ አሳቤው ሚስት እንዲያገባ ትዳር እንዲይዝ ገፍቶታል።ትዳር መያዝ እንዳለበት ውስጡ ከነገረው ወዲህ ውጥን ዕቅዱ ቁምነገርን ማሰብ ሆኗል፡፡
ጎልማሳው በላይነህ አሁን የልቡ ሞልቷል።ጠዋት ማታ የሚያስበው ዕቅድ ዕውን ሆኖ ለትዳር በቅቷል።የትዳር አጋሩ የእሱ ወይዘሮ ከሆነች ወዲህ ህይወቱ ሙሉነት እየተሰማው ነው።ከቤቱ ሌላ የሚያባክነው የሚተረፈው ጊዜ የለም።ጠዋት ማታ የሚለፋበትን በወጉ ይዞ ወደ ጎጆው ይመለሳል፡፡
ውሎ ሲያድር አዲሱ የትዳር ህይወት በልጅ ጸጋ ተባረከ።ይሄኔ በላይነህ የልቡ ሞላ ፣ ህይወቱን የተለየ ሀሴት ጎበኘው።ባለትዳሩ የጥበቃ ስራውን እየከወነ የጎደለ ጎጆውን በላብና በጉልበቱ ወዝ መሙላት ያዘ።በፍቅር የዘለቀው ጎጆ በመተሳሰብ በመግባባት ዘለቀ፡፡
ዓመታት አለፉ።የሞቀው ጎጆ ሁለተኛውን ልጅ ተቀበለ።የቤተሰቡ ቁጥር ሲጨምር ኑሮ መወደድ መክበድ ያዘ።የልጆች ትምህርት ቤት፣ የቤት ኪራይ፣ የምግብና የሌላም ፍላጎት እየናረ ህይወትን አከበደው።ያም ሆኖ አባወራው በላይነህ በጥንካሬው ዘለቀ።የልጆቹን፣ የእሱንና የሚስቱን ህይወት ለመሙላት ጥረቱን ቀጠለ፡፡
አንዳንዴ አስር ዓመታትን የዘለቀበት ስራና የሚያመጣው ገቢ አልጣጣም ሲል ብስጭት ይገበኘዋል።በየሰበቡ ከባልደረቦቹ እየተጋጨም ለጠብ ይዳረጋል።ኑሮ ሲፈትነው፣ እጅ ሲያጥረው አርፎ አልተቀመጠም።የተሻለ ነው ባለው የኮንስትራክሽን ድርጅት ለመቀጠር ስራውን ቀየረ፡፡
በላይነህ በድርጅቱ ስራ ሲጀምር ውጣውረድን አላየም።በቂ ልምዱን ያስተዋሉት አሰሪዎች ፈጥኖ ስራ እንዲጀምር ፈቀዱለት።አዲሱ ጥበቃ በድርጅቱ ተቀጥሮ ደመወዝ ማግኘት ጀመረ።ከትናንትናው ገቢ የዛሬው ሻል ማለቱ ለጊዜው እፎይ አሰኘው፡፡
በላይነህና አዲሱ የጥበቃ ስራ በወጉ ተግባቡ፣ በድርጅቱ ስራን አያይዞ የሚከፈለው ጥቅማ ጥቅም ከደመወዝ ሲዳመር የጎጆን አቅም ይደጉማል።በታላቅ ድካም ዋጋ በሚከፈልበት ግቢ በርካቶቹ በላባቸው ወዝ ሰዓታትን ይለፋሉ።ጥበቃዎቹ፣ የቀን ሰራተኞቹ፣ ስራ አስኪያጆችና ሌሎችም ዕረፍት ይሉትን አያውቁም፡፡
አዲሱ አለቃ…
አሁን በላይነህ በዚህ ድርጅት አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል።ዛሬም የትናንቱ ብርታት አብሮት ነው።በሰራው መጠን ልክ የሚከፈለውን ይዞ እንደአቅሙ ቤተሰቦቹን ያሳድራል።ዓመታትን በገፋበት የኮንስትራከሽን ድርጅት አልፎ አልፎ ከሰዎች አለመግባባትን አስተናግዷል።ከሁሉም ግን ከድርጅቱ የሂሳብ ክፍል ሀላፊ ጋር የፈጠሩት ቅሬታ ባስ እያለ ነው፡፡
ሀላፊው በድርጅቱ ከተቀጠረ ወዲህ የሰራተኞችን የግል ማህደር እየመረመረ ችግር አለበት የሚለውን ሰራተኛ ያነጋግራል።መስተካከል ይገባዋል የሚለውን እያጣራም ማረሚያና ዕልባት ይሰጣል።በላይነህን በቢሮው ባስጠራው ጊዜ ማህደሩን እየመረመረ ነበር።በላይነህ ለምን እንደተጠራ ጠየቀ።ሀላፊው እንዲቀመጥ ነግሮት ሲቀጠር ለምን ዋስ እንዳላመጣ ጠየቀ፡፡
ተጠያቂው ለጥያቄው ምላሽ ሰጠ። ወደ ስራው የገባው በዕምነት እንደሆነና እስካሁንም በዚሁ አግባብ እየሰራ እንደሚገኝ ተናገረ።ሀላፊው የሰራተኛው ምላሽ አላሳመነውም።ድርጊቱ ህገወጥ እንደሆነና አሁንም ተያዥ ማቅረብ ግድ እንደሆነ አሳወቀው።
በላይነህ በሰውዬው አዲስ ሀሳብ ተናደደ።እስከዛሬ ያለምንም ጥያቄ በሰራበት ግቢ ይህን መባሉ አበሳጨው።ምርጫ አልነበረውም።ይህን ማድረግ ግድ እንደሆነ ገባው።ወዳጅ ዘመድ ፈለገ። ታማኝ ዋስ የሚሆነውን አሰሰ፣ ተማጸነ።ጥቂት ቢጉላላም ዋሱን አገኘ።እንደተባለው ከቢሮ አቅርቦ በአዲሱ ቅጽ አድምቆ ፈረመ።ከዛን ጊዜ ወዲህ ሀላፊውና የጥበቃው ሰራተኛው በላይነህ ዓይንና ናጫ ሆኑ።በላይነህ ሰውዬውን ሲያየው ይናደዳል።በየስራ አጋጣሚው ሲገናኙም ከሰላምታ ግልምጫ ይቀናቸዋል፡፡
በላይነህን ጨምሮ ሌሎች ጥበቃዎች በሀላፊው ቂም ይዘዋል።ሁሌም እንደሚሉት እሱ ለእነሱ በጎ እይታ የለውም።ብሄር እየለየ፣ ስም እየጠቀሰ ሊበትናቸው ይሞክራል። ያመናጭቀናል ፤ ይሰድበናል የሚሉቱም ቢሆኑ ሰውዬውን አምርረው ጠልተውታል።ጥቅማጥቅም ከልክሎናል ያሉ በርካቶችም ሀላፊውን በጥላቻ እያዩ ጥርስ ይነክሱበታል።
ከሂሳብ ክፍሉ ሀላፊ ጋር የቆየ ቂም ያለው በላይነህ ሰሞኑን ጥላቻው አይሏል።ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ ጭማሪ እንዳላገኝ አስፈርሞኛል በሚል መፎከርና መዛት ጀምሯል።ይህን እውነት የሚያውቁ ሌሎች በዛቻው ተው ይቅርብህ አላሉትም።ብሶቱ ብሶታቸው ሆኖ ነገር እያነሱ፣ የተረሳን እየመዘዙ ቁስሉን አባባሱት፡፡
ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም …
በዚህ ዕለት በላይነህ የሌሊት ጥበቃ ተረኛ ነበር።እንዲህ በሆነ ጊዜ ስራውን የሚረከበው ተተኪ ጥበቃ እስኪመጣ በስፍራው ይቆያል።በዚህ ሰዓት ማልዶ የሚገባው የሂሳብ ክፍል ሀላፊው በስራው ላይ ካደሩት ዘቦች ጋር ቀድሞ ይገናኛል። በላይነህ አዳሪ በሆነ ቀን ማልዶ ለሚመጣው ሀላፊ የመኪና በር ከፍቶ በእጁ የሚይዘውን ቦርሳ ይቀበላል።ሀላፊው የግቢውን ዙሪያ ገባ ቃኝቶ ወደ ቢሮው ይገባል።የዛን ቀን ማለዳም ከሌሎች ቀናት የተለየ ድርጊት አልታየም።በላይነህ ለሰውዬው የመኪና በር ከፍቶ የእጅ ቦርሳውን ተቀብሏል፡፡
ሀላፊው ወደ ውስጥ እንደዘለቀ በላይነህ ተከትሎት ደረሰ።ይህን ያስተዋለው አለቃ መለስ ብሎ የዘጋውን የውጭ በር እንዲከፍተው አዘዘ።ጉዳዩ ያልገባው በላይነህ በዚህ የበሽታ ዘመን በር ተከፍቶ መቆየት እንደሌለበት ተናገረ።ሰውዬው አልሰማውም።በሩን ድንጋይ አሰደግፎ እንዲከፍተው ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
ሀላፊውና ጥበቃው አልተስማሙም።ጭቅጨቅና ውዝግብ ጀመሩ።በዚህ መሀል ሀላፊው በላይነህን ወደ ቢሮው እንዲመጣ ነገረው።በላይነህ የሚለውን መስማት አልፈለገም።እንዲያውም የቆየ በደሉን አንስቶ ብሶቱን ማውራትና መዘርዘር ያዘ።ሰውዬው ለጥበቃው ንግግር ቦታ አልሰጠም።ከዚህ ቀደም የሆነውን እያስታወሰ አስጠነቀቀው።አሁንም ደብዳቤ እንደሚጽፍበትና እንደሚያባርረው ደጋግሞ ነገረው።ሁለቱ ቂመኞች ዳግም ተፋጠጡ፡፡
ንግግሩን የሰማው በላይነህ ንዴቱ ከአቅም በላይ ሆኖ ተበሳጨ።ዓይኑን እያፈጠጠ፣ እጁን እንደጨበጠ ቀረበው።ለሀላፊው እሱን ማባረር እንደማይችል ሲነግረው ፊቱ በንዴት ግሎ ውስጡ በብሽቀት ተቃጥሎ ነበር።ሁኔታውን ያየው ሀላፊ በውሳኔው ቆረጠ።መልሶም ያለውን እንደሚፈጽም አረጋገጠለት፡፡
በላይነህ ተንደርድሮ አጠገቡ ሲደርስ ለራሱ መጠበቂያ የሚይዘው ባለእጀታ ጩቤ በእጁ ነበር።በሰውዬው ትከሻ ላይ ሰክቶ በፍጥነት ነቀለው።መልሶም ጩቤውን አወጣ።ወደነበረበት አልመለሰውም።በጀርባው በተንጋለለው ሰው አካል አስራ ሁለት ቦታ ላይ ወጋግቶ ከበሩ ጥግ ጥሎት ተሰወረ።
የፖሊስ ምርመራ…
የወንጀሉ መፈጸም መረጃ የደረሰው ፖሊስ ከግቢው ቅጥር ሲገባ የግለሰቡ ህይወት አልፎ ነበር።ከዕለቱ ተተኪ ጥበቃ ተገቢውን መረጃ ጠየቀ።ጥበቃው ግቢው ሲደርስ ያየውን እውነት አንድ በአንድ አስረዳ።ፖሊስ የተጠርጣሪውን ማንነት እንዳወቀ ወደ መኖሪያ ቤቱ አመራ።በላይነህን አላጣውም።ቤቱ ቁጭ እንዳለ አገኘው።ተጠርጣሪው ስለወንጀሉ ተጠየቀ።ያደረገውን አልካደም።ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ ቃሉን ሰጠ።የጉዳዩ መርማሪ ዋና ሳጂን ገብረ ብርሀን ምሩጽ በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 1478/12 ቃሉን አንድ በአንድ አሰፈረ።ክስ ይመሰረትበት ዘንድም የመረጃ ዶሴውን ለዓቃቤ ህግ አሳለፈ፡፡
ውሳኔ
ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሹን የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮ ተገኝቷል።ፍርድ ቤቱ ከፖሊስ ምርመራና ከዓቃቤ ህግ መዝገብ የደረሰውን መረጃ መርምሮ ተከሳሹ አቶ በላይነህ ደረሰ በፈጸመው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል።ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ባሳለፈው ውሳኔም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስር ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013