ሶሎሞን በየነ
በቤተሰቦቿ ልዩ ድጋፍና ክብካቤ ከእኩዮቿ ሳታንስ በትምህርቷ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበች ዘጠነኛ ክፍል ደርሳለች። ነገር ግን ዘጠነኛ ክፍል ስትደርስ በድንገት አባቷ ለእስር ይዳረጋሉ። በዚህ ጊዜ እናቷ የቤት እመቤት በመሆናቸው ወጥተው ወርደው በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቡን ያስተዳድሩ የነበሩት አባቷ ውህኒ ቤት ሲወርዱ መላ ቤተሰቡ ለችግር ይዳረጋል። በቀን ጨለማ ይዋጣል።
በዚህም ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ እናት ልጆቼን ምን ላብላ ? ምን ላጠጣ ?ብላ ጭንቅ ጥብብ ስትል ትዳር ይዛ ከቤት ወጥታ እራሷን ችላ የቤተሰቡን ሸክም ከማቃለል ባለፈ እናትና እህት ወንድሞቿን እረዳለሁ በሚል እሳቤ ገና የ15 ዓመት እሩጣ ያልጠገበች እምቦቃቅላ እያለች ባል ማግባቷን የዛሬው የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ መሰረት አዛገች ይናገራሉ።
ነገር ግን እሮጣ ሳትጠግብ ገና በ16 ዓመቷ በልጅ ኃላፊነትና በቤተሰብ አስተዳዳሪነት ከመታሰሯ አልፎ የኑሮ ሁኔታዋ ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ እናትና ወንድሞቿን እንዳሰበቸው ልትረዳ ባለመቻሏ ልቧ ያዝን ነበር፡፡ ይልቁንም እናቷ በትምህርቷ ከእኩዮቿ ወደ ኋላ እንዳትቀር ልጇን በመያዝና በመንከባከብ ያግዟት እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ምንም እንኳን እናቷ ትምህርቷን እንዳታቋርጥ ልጇን በመንከባከብና በመያዝ ቢያግዟትም ከእርሷ አልፎ ለእናቷ ሌላ ተጨማሪ ጫና በመፍጠሯ አእምሯዋ ክፉኛ ይታወክ ነበር፡፡ በዚህም የወለደችውን ልጇን ከአምላክ የተሰጣት በረከት መሆኑ ቀርቶ የህይወቷ መጥፎ እጣ ፈንታ አድርጋ ትቆጥር እንደነበር ያወሳሉ፡፡
እንግዲህ በልጅነቷ የልጅ ኃላፊነትን በመሸከሟና የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኗ ትምህርቷን እኩል ከጓደኞቿ ጋር ተምራ ያለመችው ውጤት ላይ አለመድረሷን የሚናገሩት ወይዘሮ መስረት፤ 12ኛ ክፍል ማትሪክ ተፈተና ጥሩ ውጤት ባይመጣላትም ተስፋ ሳትቋርጥ እራሷን ለማብቃት ባደረገችው ጥረት ኮሌጅ ገብታ ተመርቃ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሂሳብ ሠራተኝነት( አካውንታትነት) ተቀጥረው ለ15 አመታት አገልግለዋል፡፡
ሁሌም በአዕምሯቸው የእሳቸውን መስል እጣ ፈንታ የገጠማቸውን ሴቶችን ለመረዳት ያለሙ የነበሩት ወይዘሮ መሠረት፤ በቀይ መስቀል ማህበረ በነበራቸው የሥራ ቆይታ የበጎ አድራጎት ሥራ የተሰማሩ በጎ ሰዎች ማግኘታቸው ይበልጥ ህልማቸውን እውን ለማድረግ እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ፡፡
አሁን ወይዘሮ መሰረት አዛገች በተሸከሙት ኃላፊነትም ሆነ በዕድሜያቸው ከፍ ብለዋልና አንቱ እያልን ለመጥራት እንገደዳለን፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ያለዕድሜያቸው ልጅ ወልደው ጎዳና ላይ ወጥተው ልጅ የሚያሳድጉ ሴቶችን ሞራላቸውን ጠግኖ ወደ ትክክለኛው መስመር ማስያዝ እንደሚቻል ከእርሳቸው የህይወት ተሞክሮ በመነሳት ለዚህ ችግር የተጋለጡ ሴቶችን ማስተማርና መመለስ እችላለሁ በሚል የዓላማ ጽናት እጃቸው ላይ በራሳቸው የሚያዙት ገንዘብ ሳይኖራቸው የይቻላልን መንፈስ ሰንቀው ሁማኒተሪያን ኦርጋናይዜሽን የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ማቋቋማቸውን ይናገራሉ።
የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ሐምሌ 2003 ዓ.ም እንዳቋቋሙ ጠቁመው፤ ድርጅቱን ባለቤታቸው ለመኪና መግዣ ብሎ የሰጣቸውን 100 ሺህ ብር ለቅንጦት ከሚያውሉት በልጅነታቸው እርሳቸውን መሰል ጠባሳ ለደረሰባቸው ሴቶች መርጃ የሚውል ፋውንዴሽን ላቋቁም ብለው በማሰብ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት 25 በለጋ እድሜያቸው ያለ አባት ልጅ የሚያሳድጉ ሴቶችንና 50 ወላጅ አልባና ለችግር የተጋለጡ ህጻናትን ይዘው ድርጅቱን በፋውንዴሽን ደረጃ <<ሀ>> ብለው እንደጀመሩት ይናገራሉ።
ድርጅቱ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ስራውን ጌጅ ኮሌጅ ላይ <<2 በ 3>> የሆነ ክፍል ቤት ተከራይቶ እንደጀመረ የሚናገሩት ስራ አስኪያጇ፤ አሁን ላይ ድርጅቱ በቂርቆስ፣ ቦሌ፣ አራዳ፣ ጉለሌና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ላይ የተደራሽነት አድማሱን አስፍቶ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ወይዘሮ መሰረት ድርጅቱ ከተቋቋመ ጀምሮ እስካሁን ድረስ 1 ሺህ 79 ህጻናትንና 711 ሴቶችን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ላይ ብቻ ለሴቶች የህይወት ክህሎት ስልጠናና የስነልቦና ድጋፍ በመስጠት እንዲሁም ህጻናቱ ሲታመሙ ሙሉውን የምርመራና መድኃኒት ወጪ ሸፍኖ የማሳከምና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሄልዝ ኔትወርክ ከሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በቀን 10 ህጻናትና 10 እናቶች በጥቅሉ 20 ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ የህክምናና አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ።
ድርጅቱ በቂርቆስ ቅርንጫፉ ብቻ በዓመት ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገመት የህክምና ድጋፍ ለሚሹ ሴቶችና ህጻናት ድጋፍ እንደሚያደርግ ወይዘሮ መሰረት ጠቁመው፤ ከዚህ በተጨማሪ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ማዕከል ላሉ ድጋፍ ለሚሹ ልጆች ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማፈላለግ በየወሩ በቋሚነት በስፖንሰር የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ልጆች መኖራቸውን ተናግረዋል።
የድርጅቱ መስራች አክለውም፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ላይ ድርጅቱ ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሰርቶ ለህብረተሰቡ ማስረከቡን ጠቅሰው፤ ድርጅቱ በቦሌና አራዳ ክፍለ ከተሞች ላይ ማህበራዊ ተጠያቂነት (Social Accountability) የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረፅ አገልግሎት ሰጪና አገልግሎት ተቀባዩ ህብረተሰብ ተገናኝቶ በችግሮቹ ዙሪያ ተወያይቶ ችግሮቹን የሚፈታበት መንገድ የማመቻቸት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንዲሁም ድርጅቱ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ባለው ሁለት ማዕከል ላይ ከነልጆቻቸው ጎዳና ላይ የወደቁ እናቶችን ከጎዳና በማንሳት የህይወት ክህሎት ስልጠናና የስነልቦና ድጋፍ በመስጠት ከደረሰባቸው የሞራል ስብራት እንዲያገግሙ ከማድረግ ባሻገር የራሳቸውን ህይወት እንዲመሩ ማቋቋሚያ በመስጠት እንዲሁም የቤት ተከራይ ወጭ በመሸፈን እራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በኮንሶ ሶስት ወረዳዎች ላይ በአካባቢ እንክብካቤ ስራ ላይ ለሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት 750 ሴቶችን የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲዳብር ከማድረግ ባሻገር በአምቦ ጨሊያ በሚባል ወረዳ ላይ የተፈጥሮ ጥብቅ ደንን ተፈጥሯዊ ይዘቱን ተጠብቆ እንዲዘልቅ የመጀመሪያ ምዕራፍ የትምህርትና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለአካባቢው ህብረተሰብ መሰጠቱን አመላክተዋል።
ኮሮና ቫይረስን ተደጋግፎና ተረዳድቶ ለማለፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) ባቀረቡት <<የማዕድ ማጋራት>> ጥሪ ለ800 ቤተሰቦች ሙሉ የወር አስቤዛ እንዲሁም የግል ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድርጅቱ ድጋፍ ማድረጉን የሚናገሩት ወይዘሮ መሰረት፤ <<የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት>> በሚል መርህ ድርጅቱ ከብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች ላፒስ፣ እርሳስ፣ መቅረጫ ወ.ዘ.ተ የመማሪያ ቁሳቁሶችን በመስብሰብ እንዲሁም በየሳምንቱ ቅዳሜ ቅዳሜ ቡና ጠጡ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ህብረተሰቡ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንዲያደርግ በማስተባበር በአራት ክልሎች ማለትም በደቡብ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በድምሩ በ47 ጣቢያዎች በየዓመቱ ለ15ሺ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ከእርሳቸው የህይወት ተሞክሮ በመነሳት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዲሁም ጉዳዩ የኔም ነው ይመለከተኛል ያገባኛል የሚሉ ግለሰቦችን በማስተባበር ወላጅ አልባና ለችግር የተጋለጡ ህጻናት
ጤናቸው ተጥበቆ ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ፤ እንዲሁም ተገደው ወይም በኑሮ አስገዳጅነት ተታለው በለጋ እድሜያቸው የልጅ እናት በመሆን ልጆቻቸውን ያለአባት አሳዳጊ ሆነው ከዓላማቸው የተሰናከሉ ሴቶችን የህይወት ክህሎት ስልጠና በመስጠት ከሞራል ስብራታቸው በማላቀቅና የሙያ ስልጠና በመስጠት ራሳቸውንና ልጆቻቸውን መደገፍ እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ድርጅቱ ያለ አባት የተወለዱ ህጻናት አባታቸውን የማያውቁ፣ በአባታቸው ስም መጠራት እንኳን የማይችሉና የእናቶቻቸው የክፉ ዕጣ ፋንታ ማስታወሻ የሆኑ፣ በየቀኑ በአንፈለግምና በአንረባም ስሜት የሚያድጉ ልጆችን ህይወት መታደግ አላማው አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ተቋም እንደሆነ የድርጅቱ መስራች ገልጸዋል።
ወደ ስራው ሲገቡ በእርሳቸው ደርሶ የነበረው የሞራል ስብራት በሌሎች ወጣት ሴቶችና እናቶች ላይ እንዳይደርስ በሚል ስሜት ተገፋፍተው እንጂ በሙያ ተደግፈው ድርጅቱን እንዳልጀመሩትና ወደ ስራው እንዳልገቡ ወይዘሮ መሰረት ገልጸው፤ ወደ ስራው በጥልቀት ገብተው ከነባራዊ ሁኔታው መገንዘብ እንደቻሉት ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዳይዳብር ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ በልጆች መታሰር ነው።
ልጆቻቸውን ያለአባት ስለሚያሳድጉ ኑሯቸውን ስራ ሰርተው ለመደጎም ወደ ስራ ሲሄዱ ልጆቻቸውን ጠብቁልኝ ብለው ወይም አስቀምጠውበት የሚሄዱበት ሰው ወይም ቦታ ስለማይኖራቸው ስራ መስራት አይችሉም። በዚህም ልጆቻቸውን የጥሩ ነገር ማስታወሻቸው አድርገው አይቆጥሯቸውም።
ስለዚህ ልጁ ከፍ ሲል የአልፈለግም ስሜት ያድርበትና ጎዳና ላይ ይወጣል። በዚህም በችግር የተተበተበ የወደፊት ራዕይ መሰነቅ የማይችል በልቶ ለማደር ብቻ የሚዋትት ተመሳሳይ ትውልድ በአገሪቱ እየተበራከተ መምጣቱን ይናገራሉ።
ስለዚህ ድርጅቱ ቀን ቀን ላይ ድጋፍ የሚሹ ልጆችን ማዕከሉ ላይ ቀኑን ሙሉ የሚበላና የሚጠጣ በማቅረብ ከመንከባከብ ባለፈ አዕምሯቸውን የሚያድሱ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን በመስጠት የሚያውል ሲሆን፤ እናቶች ደግሞ ወጥተው ወርደው ስራ ሰርተው ማታ ተመልሰው ከልጆቻቸው ጋር ሲገናኙ እናትና ልጅ ነጻ አዕምሮ ኖሯቸው እንዲገናኙ፤ እንዲፋቀሩ የማድረግ ስራ ይሰራል።
በመሆኑም የድርጅቱ ዓላማ ልጅን ከእናቱ እናትን ከልጇ ሳይነጣጠሉ ድጋፍ መስጠት ነው። ስለዚህ ይሄንን አገልግሎት የሚፈልጉ ወላጅ አልባ ህጻናትና እናቶች ፍላጎት ከዕለት ዕለት እያሻቀበ በመምጣቱ አገልግሎቱን በኪራይ ቤት ለመስጠት አዳጋች ከመሆኑም በላይ የሚሰጠው አገልግሎት ምቹና ዘመናዊ መሆን ስላለበት መንግስት ሁለገብ የህጻናትና የእናቶች ማቆያ ማዕከል መገንቢያ ቦታ እንዲያመቻችላቸው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ስራ አስኪያጇ ይናገራሉ።
ድርጅቱም አገልግሎቱን በስፋት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና ለማዘመን የሚያስችለው ድጋፍ እንዲደረግለት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ቅደም ተከተሉን ጠብቆ ጥያቄውን ማቅረቡን ስራ አስኪያጇ ገልጸው፤ በአንድ ጊዜ 500 ህፃናትን ዕድሜያቸው ከ0 እስከ3 ዓመት የሆኑትን የማቆያና መንከባከቢያ፤ እንዲሁም እድሜያቸው ከ3 እስከ6 የሚሆኑትን ደግሞ ማቆያ፣ መንከባከቢያና የቅድመ መደበኛ ትምህርት በመስጠት ለ1ኛ ክፍል ማዘጋጃ የሚውል።
በተጓዳኝ ደግሞ ያለአባት ልጅ የምታሳድግ እናትን ልጇ የመደበኛ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ከሞራል ስብራት በማላቀቅ የሙያ ስልጠናዎችን በመስጠት ራሷንና ልጇቿን ሞራላቸውን በመጠግንና በኢኮኖሚው ዘለቄታ ባለው መንገድ የምትደገፍበትን በማመቻቸት መንግስት ለያዘው የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ የድርሻውን ለመወጣት ይችል ዘንድ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲፈቀድለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤትን የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ.ም መጠየቁን ተናግረዋል።
ከንቲባ ጽህፈት ቤቱም ድርጅቱ የሚሰራውን ስራ ወርዶ አይቶ፤ ያቀረበውን ፕሮፖዛል ፈትሾ ድርጅቱ እየሰራ ያለው ስራ መንግስት የሴቶችና ህጻናትን ሁለንተናዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በተግባር ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት የሚደግፍ ድርጅት መሆኑን በማረጋገጡ፤ ጽህፈት ቤቱ ለድርጅቱ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ቦታ እንዲሰጠው ሲል ለአዲስ አበባ ከተማ አተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የድጋፍ ደብዳቤ እንደጻፈ ይናገራሉ።
ድርጅቱም ከከንቲባ ጽህፈት ቤቱ የተጻፈለትን የድጋፍ ደብዳቤ በመያዝ በ17/10/2011 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር መያድ/0309/19 ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለወላጅ አልባና ለችግር ለተጋለጡ ልጆች እንዲሁም በለጋ እድሜያቸው ተደፍረው ወይም በችግር ምክንያት ተታለው የልጅ እናት ሆነው ልጆቸውን ያለአባት የሚያሳድጉ ሴቶችን ወደ ተሻለ ህይወት ለመምራት የሚያስችል ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያስችል 4 ሺህ ካሬሜትር ቦታ መጠየቁን ተናግረዋል።
ቢሮውም ከንቲባ ጽህፈት ቤቱ ለደርጅቱ ድጋፍ እንዲደረግለት በጻፈው ደብዳቤ መሰረት በቅንነት እንዳስተናገዳቸው ወይዘሮ መሰረት ጠቁመው፤ ቢሮውም ድርጅቱ ለጠየቀው ፕሮጀክት የሚውል ቦታ ለመስጠት ማሟላት የሚገባውን መስፈርት ድርጅቱ አሟልቶ እንዲቀርብ ባዘዘው ትዕዛዝ መሰረት፤ ድርጅቱም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ እንዲሁም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶች ኤጀንሲ የድጋፍ ደብዳቤ በማጻፍ በተጠየቀው መሰረት የድጋፍ ደብዳቤ አጽፎው ማቅረቡን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ በቁጥር ፋ/መ/397/11 በቀን 20/10/11 ዓ.ም እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ በደብዳቤ ቁጥር ሴ/ህ/ጉ/ቢ/1114/11 በቀን 26/11/11 ዓ.ም በጻፉት የድጋፍ ደብዳቤ ድርጅቱ ከቢሮዎቹ ጋር (ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ) ፕሮጀክት ተፈራርሞ ለህጻናትና ለእናቶች አገልግሎት በመስጠት የሚገኝ በመሆኑ ባለው አሰራርና መመሪያ መሰረት ሊገነባ ያለመውን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ቦታ ቢሰጠው ድጋፍ የምናደርግ መሆኑን እንገልጻለን ሲሉ ባሳወቁት መሰረት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ድርጅቱ ለሚያከናውነው ለህፃናትና ለእናቶች ማዕከል ግንባታ የሚውል 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮ ስም ለመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ተዘጋጅቶ እንዲሰጥ በቁጥር መባማ/2-19/3262/11 በቀን 06/12/11 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ማሳሰቡን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲም ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ በቦሌና ን/ስ/ላ/ክ/ ከተሞች ቦታ እንዲያማርጥ እድል የሰጣቸው መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ መሰረት፤ ድርጅቱ ከቆመለት አላማ አኳያ በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ እንዲመርጥ የቀረበለት ቦታ በአካባቢው ችግረኛ ህፃናትንና ሴቶች የሚገኙበት በመሆኑ በቅርበት እነዚህን የህብረተሰብ ክፍል ለመደገፍ ይችል ዘንድ በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ የቀረበለትን ቦታ ምርጫው ማድረጉን ይናገራሉ።
በበጎ አድራጎት ድርጅቱ የቦታ ምርጫ መሰረት ኤጀንሲውም የን/ስ/ላ/ክ/ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽ/ቤትን የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ሊገነባ ላለመው ፕሮጀክት የሚውል 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ አዘጋጅቶ እንዲልክ በተጠየቀው መሰረት ጽህፈት ቤቱ በደብዳቤ ቁጥር ን/ስ/ላ/ክ/ከ/መ/ል/ከ/ማ/ኤ/ 6051/12 በቀን 17/02/2012 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ በክፍለ ከተማው ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ከይገባኛል ነጻ የሆነና በመሬት ባንክ የገባ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ማዘጋጀቱን ለኤጀንሲው ማሳወቁን ተናግረዋል።
ኤጀንሲውም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ሊገነባ ላለመው ፕሮጀክት የሚውል ቦታ በየን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 11 ክልል ውስጥ በመዋቅራዊ ፕላን የመሬት አጠቃቀም መሠረት ለዝቅተኛ ቅይጥ መኖሪያ /R-1/ የተፈቀደ ቦታ ውስጥ ስፋቱ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ የተዘጋጀ በመሆኑ፤ በቢሮው በኩል ውሳኔ አግኝቶ ለድርጅቱ እንዲተላለፍ እና ቤዝ ማፕ እንዲወራረሱ ማሳሰቡን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ፕሮሰስ ካውንስል በቃለ ጉባኤ ቁጥር 8/2012 በቀን 14/4/2012 ዓ.ም በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 11 ክልል ውስጥ የተዘጋጀው 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ስም ለመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት እንዲሰጥ መወሰኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱም በተወሰነለት ውሳኔ መሰረት ቦታውን ተረክቦ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አሰርቶ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤትን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰራለት ሲጠይቅ፤ ጽህፈት ቤቱ ለድርጅቱ የተሰጠው ቦታ ለስምንት ሰዎች የይዞታ ማረጋገጫ በላዩ ላይ ተሰርቶ መሰጠቱን እንደተገለጸላቸው ወ/ሮ መሰረት ይናገራሉ።
ወይዘሮ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ካቢኔ ውሳኔ ካስተላለፈ ጊዜ ጀምሮ ድርጅቱ የይዞታ ማረጋገጫ ተሰርቶለት ወደ ልማቱ ለመግባት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ለድርጅቱ መልስ የሚሰጥ አካል አልተገኘም። ነገር ግን ከይገባኛል ነጻ የሆነና በማንም ያልተያዘ እንዲሁም በመሬት ባንክ የገባን ቦታ ለድርጅቱ ተፈቅዶለት እያለ በአንዴ ቦታውን ለስምንት ግለሰቦች የይዞታ ማረጋገጫ አውጥታቹህ እንዴት ልተሰጡ ቻላቹህ በሚል ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ቅሬታ ቢያቀርቡም፤ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊም <<ለቦታው አዲስ እንደሆኑና ቦታው በምን አግባብ ለግለሰቦች የይዞታ ማረጋገጫ ተሰርቶ እንደተሰጠ እንደማያውቁ ገልጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮን ጠይቁ>> ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ቀርበው አቤት ማለታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ መሰረት፤ ነገር ግን ለድርጅቱ ቦታው እንዲሰጥ በካቢኔ ሲወሰን የነበሩት ኃላፊ ተቀይረው በቦታው ሌላ ሰው መተካቱን ይናገራሉ።
በቦታው ለተተኩት አዲሱ ኃላፊም ጉዳዩን አብራርተው ማስረዳታቸውን ገልጸው፤ ኃላፊውም በምላሹ እንዴት ካቢኔ የወሰነውን ለሌላ ይሰጣል? ጉዳዩን አጣርተን በቅርቡ ምላሽ እንሰጣለን። በቅርቡ ይስተካከላል ቢሉም ቅሉ ኃላፊው የሰጡትን ተስፋ መሰረት አድርገው ምላሻቸውን ሽተው በተደጋጋሚ ቢሮ ቢመላለሱም ከኃላፊው ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተስፋ ሳይቆርጡ መልስ ለማግኘት ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት የኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ መግባቱን ተከትሎ እንደተደናቀፈባቸው ወይዘሮ መሰረት ጠቅሰው፤ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት መቀዛቀዝ በኋላ ቢሮዎች ለአገልግሎት ክፍት ሲሆኑ ለክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ በአካል ቀርበው ለህብረተሰብ አገልግሎት ለሚሰጥ ድርጅት የተፈቀደለትን ከመሬት ባንክና ከይገባኛል ነጻ የሆነን ቦታን የይዞታ ማረጋገጫ አልሰጥም ብላቹህ እንዴት ለግለሰብ በአንዴ የይዞታ ማረጋገጫ ልትሰጡ ቻላቹህ በሚል ቅሬታቸውን በድጋሚ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን ኃላፊው አዲስ እንደሆኑና በምን አግባብ ለግለሰቦቹ የይዞታ ማረጋገጫ ተሰርቶ እንደተሰጠ የሚያወቁት ነገር እንደሌለ ከመግለጽ ውጭ በጽሁፍ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ወይዘሮ መሰረት ገልጸው፤ እርሳቸውም ለምን ህጋዊ ሆነን ለጠየቅነው ጥያቄ ምላሽ አይሰጠንም በሚል አንድ ሁለት ከኃላፊው ጋር ተነጋግረው ከቢሮው ይወጣሉ። ከቢሮው ወጥተው ወደ መኪናቸው ሲያመሩ አራት ጎረምሶች/ ግለሰቦች ተከትለዎቸው <<ይሄ የኛ የአባቶቻችን ቦታ ነው። መሬት ደግሞ ደም ያፋስሳል። ድርጅቱን አውቀነዋል! ፎቶዎትንም አንስተናል! ደም እንፋሰሳለን!>> ሲሉ መዛታቸውን ይናገራሉ።
ግለሰቦቹ ይህን መሰል ዛቻና ማስፈራሪያ በድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ላይ ሲዝቱ፤ በአንጻሩ የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው ግለሰቦቹን ኑ እስኪ ብለው <<እናንተም ደም አታፍሱ። የኛም ደም አይፍስ። የእኛ ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ህጋዊ ድርጅት ነው፡፡ መንግስትን ለህብረተሰቡ አገልግሎት የምንሰጥበት ቦታ ይፈቀድልን ብለን በህጋዊ መንገድ ጠየቅን። መንግስትም ከይገባኛል ነጻ ነው ብሎ ይህን ቦታ ፈቀደልን። ስለዚህ የናንተም ይሁን የሌላ ግለሰብ ቦታ አፈናቅለን ወይም ቀምተን አልወሰድንም>> በሚል ግለሰቦቹን አረጋግተውና አግባብተው መለያየታቸውን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ድርጅቱ ለህብረተሰቡ ድጋፍ ለማድረግ ህጋዊ በሆነ መንገድ በጠየቀው አግባብ መንግስት ለአርሶ አደሮች ካሳ ከፍሎ መሬት ባንክ ያስገባውንና ከይገባኛል ነጻ የሆነ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የተፈቀደለትን ቦታ የን/ስ/ላ/ክ/ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት ለስምንት ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ የይዞታ ማረጋገጫ ሰርቶ በመስጠቱ ግለሰቦቹ ቦታውን በህገወጥ መንገድ አጥረው እንደያዙት ወይዘሮ መሰረት አመላክተዋል።
ስለዚህ ወላጅና እረዳት የሌላቸው ልጆች እንዲሁም ልጆቻቸውን ያለ አባት የሚያሳድጎ አያሌ ሴቶች እረዳት አጥተው ጎዳና ላይ ወድቀው ባሉበት አገር ለነዚህ ችግረኛ ወገኖች እንዲውል የተወሰነን ቦታ ለግለሰቦች ተቸርችሮ ወይም ተሸንሽኖ ስለተሰጠብን መንግስትና ህዝብ ይፍረደን ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት
የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ መንግስቱ በላይ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው እንዳብራሩት፤ ከዚህ ቀደም የመዲናዋ ከንቲባ የነበሩት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአንድ ወቅት ማንኛውም ክፍት የመንግስትም ሆነ የግለሰብ ቦታ ጾም ማደር ስለሌለበት ይታረስ በሚል በመገናኛ ብዙኃን መልዕክት አስተላልፈዋል። አንድ ትልቅ ከተማ የሚመራ ከንቲባ አንድም መሬት ጾም ማደር የለበትም በሚል መልዕክት ሲያስተላልፉ በክፍለ ከተማው ያሉ ሁሉም ክፍት ቦታዎች ታረሱ፤ ተወረሩ። ከንቲባው በከፈቱት ቀዳዳ ማጠር የሚችል አጥሮ ያዘ። ማረስ የሚችልም አረሰ፤ ዘራ። በዚህም በክፍለ ከተማው ክፍት ቦታዎች በሙሉ ታረሱ፤ ተወረሩ።
ከዚህ አንጻር ለመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት የተፈቀደውን ቦታ ለስምንት ግለሰቦች ተሸንሽኖ ተሰጥቶ የይዞታ ማረጋገጫ ተሰርቶ ተሰጥቷቸዋል በሚል የቀረበውን ቅሬታ ስንመለከት፤ ይህ ቦታ የኦሎምፒክ ዞን ተብሎ መንግስት ለአርሶ አደሮች ካሳ ከፍሎ ያስቀመጠው ቦታ ነው።
የቦታው ባለቤት አርሶ አደሮቹም ይነስም ይደግም በወቅቱ ካሳ በልተውበታል። ስለዚህ ይህ ቦታ ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ሃና ቀለበት ከሚወስደው አስፓልት ጫፍ ጀምሮ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ከተገነባው አዲሱ አትክልት ተራ ጫፍ ድረስ 12 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ሲሆን፤ ይህ ቦታ መንግስት ለኦሎምፒክ ሜዳ በሚል ካሳ ከፍሎ ነው ያስቀመጠው። ነገር ግን ከንቲባው ክፍት ቦታዎች ጾም አይደር በሚል ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት ይህ ቦታ በግለሰቦች ታጥሯል።
ይህ ብቻ ሳይሆን መንግስት ካሳ የከፈለባቸው በርካታ ቦታዎች በክፍለ ከተማው ታጥረዋል የሚሉት ኃላፊው፤ ከነዚህ መካከል ከተማ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት የሚውሉ ቦታዎችን ጨረታ አውጥቶ በመገናኛ ብዙኃንና በጋዜጣ አሳውጆ ለአልሚዎች አጫርቶ የሚሸጡ 20 የጨረታ ቦታዎች በወሮበሎች መታጠሩን ተናግረዋል።
ለጨረታ ከተዘጋጁ 20 ቦታዎች ውስጥ መንግስት ከአልሚዎች ጋር ውል ተዋውሎ 20 በመቶ ገንዘብ የተቀበለበት ሲሆን፤ ከነዚህ ቦታዎች ውስጥ ስድስቱ ቦታዎች አልሚዎች ከመንግስት ጋር ውል ተዋውለው ካርታ ወስደዋል። ነገር ግን ቦታው በወሮበላዎች ተወስዶ የንግድ ቤትና የመኖሪያ ቤት ተገንብቶበታል። በዚህም እነዚህ አልሚዎች ጽ/ቤቱ ድረስ በአካል በመቅረብ በወንበዴዎች ተነጥቀናል በሚል ቅሬታ እያቀረቡ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በጥቅሉ ይህ ሁሉ የመሬት ወረራ በክፍለ ከተማው የተፈጸመው ክፍት ቦታ ጾም አይደር ተብሎ በመታወጁ የመጣ ችግር ነው የሚሉት ኃላፊው፤ በከንቲባ ደረጃ ክፍት ቦታ ሁሉ ይታረስ ተብሎ በመታወጁ የመንግስት አካልም እርምጃ ወስዶ የመሬት ወረራውን ማስቆም እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ሌላው ትልቁና ዋነኛው ችግር በከንቲባ ደረጃ ክፍት ቦታ ሁሉ ይታረስ ተብሎ በታወጀ ማግስት በተጠናና በተቀናጀ እንዲሁም በባለሙያ በተደገፈ መንገድ የክፍለ ከተማው የካሳና ካሳ መረጃ እንዲጠፋ መደረጉን የሚናገሩት አቶ መንግስቱ፤ በክፍለ ከተማው አብዛኛው አርሶ አደር ይነስም ይብዛም ካሳ መብላቱን ጠቁመው፤ በተለይም የኦሎምፒክ ሜዳ ተብሎ የሚታወቀው 12 ነጥብ 5 ሄክታር (ቅሬታ የተነሳበት ቦታ በዚህ ክልል ውስጥ ነው የሚገኘው) መሬት ካሳ ተበልቶበታል። ቤዝ ማፑ ላይም ካሳ እንደተበላበት ነው የሚያሳየው።
ነገር ግን በተጠናና በተቀናጀ እንዲሁም በባለሙያ በተደገፈ አግባብ የክፍለ ከተማው የካሳና ካሳ መረጃ ማንዋል እንዲጠፋ በመደረጉ በክፍለ ከተማው እዚህ ቦታ ላይ ማነው ካሳ የበላው። ማነው ካሳ ያልበላው ቢባል እንደማይታወቅ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ክፍት ቦታ በሙሉ ጾም አይደር ተብሎ ሲታወጅ ይዞታቸው የነበረ ግለሰቦች አንዳንዶቹም ይዞታቸው ይሁን አይሁን የማይታወቁ ግለሰቦች በሙሉ መጥተው ካሳ ያልበላንበት መሬት ነው በሚል በዘመቻ ማጠራቸውን፤ እንዲሁም ማጠር ያልቻሉት ደግሞ ቦታውን እያረሱ ይዘው እንደሚዋጋ እንደእሾህ በማስፈራራት ማንንም ወደ ቦታው እንደማያስቀርቡ ተናግረዋል።
ስለዚህ እነዚህን ግለሰቦች ካሳ በልታችኋል ብሎ መመለስ አይቻልም። ምክንያቱም የክፍለ ከተማው የካሳና የካሳ ክፍያ መረጃ በተጠናና በተናበበ አግባብ ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ ከተማ ማደስ ጽ/ቤት ድረስ መረጃዎች እንዲጠፉ በመደረጉ መሰረት በጎ አድራጎት ድርጅትም ሆነ ሌላ ማንኛውም ድርጅት ወይም ግለሰብ ለሚያቀርበው ቅሬታ እንደ ተቋም መልስ ለመመለስ እንደተቸገሩ አቶ መንግስቱ ተናግረዋል።
ስለዚህ ቅሬታ የተነሳበትን ቦታ አጥረው የያዙ ሰዎችን ለማስለቀቅ ወይም ለመጠየቅ የሚያስችል መረጃ ባለመኖሩ ለመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት የተፈቀደውን ቦታ ለምን ከለከልክ የሚል አካል ቢመጣ ለአርሶ አደሮች ተሰጥቷል ከሚል ምላሽ በዘለለ ምንም አይነት ምላሽ ሊሰጡ እንደማይችሉ ኃላፊው ተናግረዋል።
በመሆኑም ቅሬታ የተነሳበትን ቦታ ያጠሩት ግለሰቦች አብዛኞቹ ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ይህ ቦታ የራሳቸው ይዞታ የነበረ ቢሆንም ይነስም ይደግም በወቅቱ ካሳ ተሰጥቷቸው ተሸኝተዋል። ነገር ግን መንግስት እረሱ በሚል ሲያውጅ እነዚህ ግለሰቦች መጥተው አረሱ፤ አጠሩ። ከዚያም በአርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጆች መመሪያ መሰረት ቦታ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት ለአርሶ አደር 500 እና ለአርሶ አደር ልጅ 150 ካሬ ሜትር ቦታ ይሰጥ ስለሚል ተሰጥቷቸዋል።
ስለዚህ መንግስት ለመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ቦታ ይሰጥ ብሎ ወስኖ ነበር ፡፡መንግስት አርሶ አደሩን እረሱ ባለው መሰረት ደግሞ ቀማቸው ማለት ነው። የመንግስትን ውሳኔ መንግስት ነው የሻረው። ስለዚህ መንግስት ሰጠ መንግስት ነሳ ነው ነገሩ ሲሉ አቶ መንግስቱ ተናግረዋል።
ኃላፊው ይሄን ምላሽ ሲሰጡ የዝግጅት ክፍላችን ክፍለ ከተማው ከይገባኛል ነጻ የሆነና ካሳ የተከፈለበት እንዲሁም መሬት ባንክ የገባ ቦታ ለመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ተዘጋጅቷል በሚል ቀደም ሲል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በላከው መረጃ መሰረት የቢሮው ፕሮሰስ ካውንስል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ስም ለመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት እንዲውል የተፈቀደን ቦታ እንዴት አርሶ አደሮቹ ካሳ እንደበሉበት እየታወቀ ለአርሶ አደሮቹ የይዞታ ካርታ ተሰርቶ ተሰጠ በሚል ጥያቄ አንስቷል።
አቶ መንግስቱ አርሶ አደሮቹ ቀደም ሲል የራሳቸው ይዞታ የነበረ ቢሆንም ይነስም ይደግም ከዚህ በፊት ካሳ በልተውበት ከሆነ ካሳ በተበላበት ቦታ ላይ ድጋሚ መብት እንደማይፈቀድ ገልጸዋል።
ወደ ኃላፊነት ቦታ ከመጡ ገና አራት ወራቸው መሆኑን አቶ መንግስቱ ጠቁመው፤ ክፍለ ከተማው ቦታው ከይገባኛል ነጻ መሆኑን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ልኮ በካቢኔ ደረጃ ቦታው ለመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት የተወሰነ ስለመሆኑ መረጃው እንደሌላቸው፤ እርሳቸው ወደ ኃላፊነት ቦታ ከመጡ ጀምሮ ድርጅቱም እርሳቸው ዘንድ ቀርቦ ቅሬታ እንዳላቀረበ ተናግረዋል።
አቶ መንግስቱ ድርጅቱም በውሳኔ ደረጃ እንጂ ቦታውን ተረክቦ እያስተዳደረው ስላልሆነ መረጃው እንደሌላቸው ገልጸው፤ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ቅሬታውን በአካል ቀርበው ያቅርቡ። ጽ/ቤቱም በቀረበው ቅሬታ መሰረት ወደ ኋላ ተመልሶ ማን ለነማን መብት ፈጠረ ወይም የይዞታ ማረጋገጫ ሰርቶ ሰጠ? እንዲሁም ቦታውን የያዙ አካላት ህጋዊ ናቸው አይደሉም? የሚለውን ያጣራል። ስለዚህ በጎ አድራጎት ድርጅቱ የተፈቀደልኝን ቦታ ለግለሰቦች ተሸንሽኖ ተሰጥቶብኛል በሚል ያቀረበው ቅሬታ እንደ ተቋም አልተጣራም ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በተባለው ቦታ ላይ የይዞታ ካርታ ተሰርቶ ወጥቷል አልወጣም የሚለው ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ኃላፊው ገልጸው፤ ቅሬታ በተነሳበት ቦታ ላይ ካርታ ከወጣበት ስንት ካርታ ወጥቷል? እነማናቸው ካርታ ያወጡበት? ካርታውስ የወጣባት አግባብስ ጤናማ ነበር ወይ? ምን ያህል ህጋዊ ነው? የሚለውን እንደ ተቋም አጣርተን መልስ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ
በሌላ በኩል የዝግጅት ክፍላችን በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምላሽ እንዲሰጠን በደብዳቤ ጭምር የጠየቀ ሲሆን፤ የቢሮው ኃላፊም ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥበት ደብዳቤውን ለቢሮው ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ለሆኑት ለአቶ ንጉስ ተሾመ መርተዋል።
አቶ ንጉስ በሰጡን ምላሽ ደብዳቤ ከተመራላቸው ቀን ጀምሮ ስለቀረበው ቅሬታ የተለያዩ የሚመለከታቸውን አካላት ማናገራቸውን ጠቁመው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ የሚውል ቦታ አዘጋጅቶ ባቀረበው መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ፕሮሰስ ካውንስል ቦታው ለድርጅቱ እንዲሰጥ ውሳኔ ማስተላለፉን ተናግረዋል።
ነገር ግን ከተለያዩ አካላት ባጣሩት መሰረት ውሳኔው ከተወሰነ በኋላ ድርጅቱ ተከታትሎ ካለማስፈጸሙ የተነሳ ቦታው የይዞታ ካርታ ስላልወጣበት ምናልባት ለሌሎች ጠያቂዎች ተሰጥቶ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ መኖሩን ጠቁመው፤ የመሬት ጉዳይ በጣም ሴንሴቲቨ እና ብዙ ጣልቃ ገብነት ያለበት በመሆኑ ቦታው ለታለመለት አላማ እንዳይውል የሚያድርጉ በርካታ መስናክሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ቦታው ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል ያልተደረገበት ምክንያቱ በዝርዝር እንዲላክ ክፍለ ከተማውን አሳስበናል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲም ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ የተፈቀደው ቦታ ለምን ለታለመለት ዓላማ እንዳልዋለ ተነጋግረው መፍትሄ ለመስጠት እየተረባረቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ ባደረጉት ማጣራት የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ተወካይ ለቢሮውም ሆነ ለክፍለ ከተማው ቀርበው ቅሬታቸውን አለማቅረባቸውን ጠቁመው፤ ድርጅቱ በወቅቱ የይዞታ ማረጋገጫ ይሰጠኝ ብሎ ሲጠይቅ አልሰጥም ሲባል ወዲያውኑ ለሚመለከተው አካል ቀርበው ቅሬታቸውን አቅርበው ቢሆን አፋጣኝ ምላሽ ይሰጠው ነበር። አሁንም ቢሆን በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ለምን ቦታው ለታለመለት ዓላማ እንዳልዋለ ባለሙያ እስከታች ድረስ ወርዶ የማጣራት ስራ ይሰራል ብለዋል።
ድርጅቱ ቦታው ሲወሰንለት እስከመጨረሻው ተከታትሎ ተፈጻሚ ባለማድረጉ አፈጻጸሙ ለችግር የተጋለጠበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸው፤ ነገር ግን ድርጅቱ በህጋዊ መንገድ ያገኘው ቦታ ስለሆነ ችግሩ በቀላሉ የሚፈታና መፍትሄ የሚሰጠው እንደሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑም የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ስለሆነ፤ በቅድሚያ በህጋዊ መንገድ የተፈቀደለትን ቦታ እንዲያገኝ ይሰራል። ነገር ግን ድርጅቱ በህጋዊ መንገድ የተፈቀደለትን ቦታ ለሌሎች ተሰጥቶ ከሆነ እንኳን ሌላ ተመሳሳይ ቦታ ተዘጋጅቶ የማይሰጥበት ምንም ምክንያት የለም። እንዲሁም ለድርጅቱ የተፈቀደውን ቦታ ለሌሎች ተሰጥቶ ከሆነ ለምንና ለማን እንደተሰጠ? የተሰጠው አካልስ ምን ያህል ህጋዊ ነው? የሚለውን በተጨባጭ ታች ድረስ ተወርዶ የማጣራት ስራ ተሰርቶ በቀጣይ ምላሽ የምንሰጥ ይሆናል ብለዋል።
በአጠቃላይ የዝግጅት ክፍላችን በቀጣይ ክፍል ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ የተወሰነለት ቦታ ለማንና ለምን እንደተሰጠ? የተሰጠው አካልስ ምን ያህል ህጋዊ ነው? እንዲሁም ለምንስ ለድርጅቱ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ቦታውን ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ ማስተላለፍ አልተቻለም? የሚለውን ምላሽ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ እንዲሁም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት የሚሰጠውን ምላሽ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013