የልቤ ደርሶ
የአንዳንድ ሰው ባህሪም ሆነ ዓመል እንደ የሁኔታው ይቀያየራል። በዚህ ነው ስንለው በዚያ ብቅ እያለ አመሉን መያዝ መጨበጥ የሚያስቸግረን ሰው ቁጥር ጥቂት አይደለም። ነጭ ነው ስንለው ጥቁር፤ ቀይ ስንለው አረንጓዴ ሆኖ ግራ ያጋባናል። በተከበረ ቦታ የሚውሉት ግለሰቦችና አባቶች ሳይቀሩ (እውነት ፍትህ ጽድቅ እንኳ በሚነገርበት ስፍራ ሳይቀር) ሲገለባበጡ ማየት ተለምዷል:: ቀጥሎ የቀረበውን ታሪክ እየተመለከትን ርእሰ ጉዳያችንን በጥልቀት ለማየት እንሞክር።
በመንግስት መስሪያ ቤት የሚሰራ፣ በግሉ ደግሞ በመንፈሳዊ ህይወቱ አንቱ የተባለ አስተማሪ ነበር። ይህ ሰው ስሙ ወሰንየለህ ይባላል። ታዲያ ግለሰቡ ሁሌም ወደ ስራ ከመሄዱ በፊት ማታ ማታ ለስራው የሚያስፈልጉትን ነገሮች አስተካክሎ ነው ወደ መኝታ ቤቱ የሚሄደው:: በአንድ ምሽትም እንደተለመደው አድርጎ ወደ መኝታው አመራ። የስራ ሰዓት መቀስቀሻ አስታዋሽ አላርሙንም ሞላ።
ይሁን እንጂ ጠዋት ላይ እንዲቀሰቅሰው የሞላው ሰዓት ድምጹን ሳያሰማ ቀረ:: በዚህ ምክንያት ከዚህ ቀደም ከእንቅልፉ ከሚነቃበት አንድ ሰዓት ዘግይቶ ተነሳ። ከወትሮው የስራ መግቢያ ሰዓቱ አንድ ሰዓት አሳልፎ እንደሚገባ ስላወቀ በጣም አዘነ:: እንዲቀሰቅሰው ሰዓቱን የሞላው ራሱ ስለሆነ ምክንያት አድርጎ የሚቆጣው ሰው አልነበረውም::
የዚህ ሰው ባህሪ አስቸጋሪ ነው። ሊተኛ ሲል ሰዓቱን ሚስቱ ሞልታው ቢሆን ኖሮ ጉድ ፈልቶባት ነበር:: ወስንየለህ “ተሳስቼ ነው የሞላሁት” በማለት ፋንታ “ጊዜውን ጠብቆ የማይደውል የማይረባ ሰዓት ነው” በማለት በሰዓቱ ላይ መበሳጨት ጀመረ:: በዚህም አላበቃም:: የማይናገር የማይጋገር ሰዓቱን አንስቶ በኃይል ወርውሮ ሰባበረው።
ሰዓቱን ሲሰብረው በወጣው ድምፅ ተረብሻ ሚስቱ ተነሳች። ደንግጣ ነበር። ምን እንደተፈጠረ ስትጠይቀው ቀና መልስ ከመስጠት ይልቅ እንደብራቅ ጮሆባት፤ አፀያፊ ቃላት ጭምር ወረወረባት:: ቀጥሎ እየከነፈ ወደ ስራው ሄደ። ፤ቢሮ እንደገባ አለቃው እንደሚፈልገው ተነገረው:: አለቃው ለምን እንዳረፈደ ሲጠይቀው ባለቤቱ ታማ ሆስፒታል ይዟት እንደሄደ ይናገራል:: አለቃውም ሁኔታውን በጥሞና ከተረዳ በኋላ ምክንያቱን ተቀበለው።
ወሰንየለህ በዚህ መልኩ ቀኑን አሳለፈ። በሳምንቱ መጨረሻ የሀይማኖት ትምህርት የሚሰጠው እርሱ ነበር:: የትምህርቱ ርዕስ ደግሞ “ራስን ስለመግዛት” ነበር:: እናም በስብከቱ ላይ ሆኖ ለሃይማኖቱ ተከታዮችም “በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ በትዕግስት ራስን በመግዛት እንዲያልፉት” መንገር ጀመረ። ይሄን ማድረግ የመንፈሳዊነት ግዴታና የፈጣሪ ትዕዛዝም እንደሆነ ደጋግሞ አስገነዘበ::
ይህን ትምህርቱን ግን እርሱ በተግባር መኖር አልቻለም። የማይኖሩትን ማስተማር መደስኮር “በአንድ ራስ ፤ሁለት ምላስ” ማለት ይህ ነበር:: ይህ አጭር ታሪክ ብዙ ያስተምረናል። ብዙዎቻችን የምንናገረውን በአደባባይ ወጥተን የምንደሰኩረውን በህይወታችን ላይ አንተገብረውም። አሁንም በአገራችን የምናስተውለው መዛነፍ ይህ ነው። በምላሳችን የምንናገረው ብቻ ሳይሆን የምንከውነውም ሁሌም የተለያየ ነው። የሚጨበጥ አይደለም። “ቀድሞ ወርቅ ነው ያሉትን አድረው ጨርቅ ነው” ይላሉ፤ ቋሚ ሀሳብ እና ወዳጅ የማይታይበት ሆኗል::
የአፍን ቃል የልብን ሀሳብ ማስማማት መልካም ነው። ምክንያቱም ዓለም ራሷ መርጋት የማታውቅ ወላዋይ ናትና!! ሃያላን የተባሉት ይዋረዳሉ፤ በአንጻሩ ደካሞች ይነግሳሉ ፤ ሀብታሞች በተለያዩ ምክንያቶች ጎዳና ላይ ይወድቃሉ። ምንዱባን በሰማይ ጠቀስ ህንፃ ይንፈላሰሳሉ። ሳር ቅጠሉን የተፀየፈው ጨፍጫፊ አረመኔ ከአይጥ ጎሬ ሲያደፍጥ ታየዋለህ። የትናንቱ ተሳዳጅ ተራውን ሲያሳድድ ትመለከታለህ። ይቺው ናት ዓለም!! ብልጭ ብላ ድርግም፣ ቦግ ብላ እልም የምትል። ሁሌ ሳቅ የለም! ሁሌ ድል የለም።
ታዲያ እንዲህ ባለች ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ እየኖርን ደግሞም ሺህ ዓመት ለማንኖረው፤ አንድ አቋምና አንድ ማንነት ይዘን ብናልፍ አይሻልም ወገን:: ነገ እዳሪ የሚሆን ፍርፋሪ ስላላገኘህ የተጎዳህ ሊመስልህ ይችላል። ነገር ግን ለእውነትና ለምትናገረው ቃል ስትኖር ጥሩ እንቅልፍ ትተኛለህ።
ከያኒው “ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ይሉኝታ ከማጣ ዛሬ ገንዘብ ልጣ” እንዳለው ነው::
የቀረው ቀርቶ የአአምሮ እረፍት፣ ሰላም እና ደስታን ማግኘት እንዴት መታደል ነው:: ማንኛውም ፖለቲከኛም ሆነ የማህበረሰብ አንቂ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖረው ይችላል። መተኪያ በሌላት አንድ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ግን ከቀኝ አሊያም ከግራ ይነሱ አንድ አይነት ልብ እና አቋም ሊኖራቸው ግድ ይላል::
የሀገራችን ታሪክ የሚያስገነዝበውም ይህንኑ ነው :: ኢትዮጵያውያን በአንዳንድ ነገሮች ላይ ባላቸው ልዩነት ሲጋጩ ሲዋጉ ኖረዋል:: የውስጥ ጠብ ማለት ነው:: ሀገራቸውን ሊወር በመጣ ጠላት ላይ ግን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ወራሪውን ጠላት ለመመከት እንዲሁም ድል ለመምታት ይነሳሉ:: በዚህም አይነት መንገድ ነው በወራሪው የጣልያን ሰራዊት ላይ በአድዋ ድልን የተቀዳጁት::
በአንድ ራስ ሁለት ምላስ እንደ ምክር
በነገራችን ላይ መንግስትን አቋም ይዞ መሞገት ጨዋነት ነው፤ ነገር ግን በዚህኛው ማሊያ (መለያ ልብስ) ለዛኛው ቡድን መጫወት አግባብ አይደለም:: ከፍ ሲልም ወንጀል ነው:: በሕይወት የሚገጥምህንም ችግር “በሎጂክ” ድርድር አትተብትበው። ፍርሃትን በአይናውጣነት አንቀልባ አዝለህ አትዙር፣ ሰሚ አገኘሁ ብለህ የባጥ የቆጡን በመቀባጠርህ አትኩራራ። ሀፍረተ ቢስነትህን አስወግድ ፤የምፈራው የለም እያልክ፣ ዞር ብለህ አትለማመጥ።
ከምትቀባጥረው አንዳንዱ እውነት ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ይሉኝታ ቢስነትህ ግን መጠን የለውም። ከግብዝነትህ የተነሳ ሀቅህን አደባባይ አውጥተህ ታረክሰዋለህ። በእርግጥ ማለት የምትሻው ነገር አለ፣ እቅጩን እንዳትናገር ግን ፍርሃት ጠፍሮ ይዞሃል፣ሆድህ እንቅፋት ሆኖብሃል ፤ለመናገር የሚያበቃ ድፍረት አጥሮሃል። ስለዚህም እንዲህ ካለ ውዥብር ውጣ ፤ በአቋም የአመንክበትን ተናገር:: አትወላውል ህይወት አንድ ናት:: የልብን ሃሳብ እና የአንደበትህን ቃል አንድ አድርግ፤ያኔ የሆንከውን ትሆናለህ፤ከትወና ወደ እውነተኛው ዓለም ትቀላቀላለህ::
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10/2013