ብስለት
ያለ ጭንቅ ዘመን እንዳንገፋ ግዜ ባለበት ቆሟል። ሰቱም ወደ ፊት ማለትን ትቶ እንደ ቆመ ተረድተናል። የመኖር ዘዬው ጠፍቶብን ሰብኣዊነታችን ከኛ ርቆ የህይወት ኡደቱ ተዛብቶ መኖር አከተመ ልል ፈለኩና….
ሳስበው አመመኝ። ሀገሬ አንቺን ማስከፋቱ አንቺን ማሳዘኑ ውስጤን ቆጠቆጠኝ፤ ምን ባጠፋሽ አንቺን ልውቀስ ብዬ ተውኩት። ሳይዳምን ዘነበ ግራ አጋባን መኖር፤ ሳይነጋ ጨለመ ቀንና ለሌሊቱ ተደበላለቀ፤ በሜዳ ተተካ ሸለቆ ዳገቱ ፤ከቅጠል አነሰ የሰው ልጅ ህይወቱ። የሞት ዜና ማስደንገጡ ቀረ፤ ውጥር ያለ መንፈስ በሁሉም ፊት ላይ ታየ። ግራ የገባው አለም ግራ የገባን ለታ ማምለጫ መንገድ ማቋረጫ ነገር ልባችን ከጅሏል።
ግን ግን እናት አለም ምን ይሁን ምንም አንቺው ነሽ ቤታችን፤ ከቤትሽ አንወጣም ባንቺው ተወልደናል ፤ካንቺው ጋር እንሙት። የጨነቀን ሰኣት ግራው በሞላበት አባሮሹን ተይው እንደ ልጅ ጨዋታ አንድ እድል ስጭና የማሪያምን መንገድ፤ አድገን እናሳይሽ። ከወደድሽን በላይ አንቺን እንድንወድሽ። ካረግሽልን በላይ ላንቺው እናርግልሽ፤ ካደመቅሽን በላይ አንችኑ አስውበን ባንቺ እንድመቅብሽ።
ልክ እንደ ልጅነት ጫወታ እንደ አባሮሽ፤ ስንጫወትና ልንያዝ ስንል ስናመልጥ ቤታችን ገባን እንደምንለው፤ የአባሮሽ ቤት ላለመያዝ ዋስትናችን ሲሆን መደበቂያ ሁኝን ማሪፊያ ቤታችን ከችግር ከጥል ከክፋት ከሁሉም መሸሸጊያችን ሁኚ።
ወደደጅ ለመውጣት ብዙ ጠባቂዎች ደጃችን ሲኮሎኮሎ የማሪያም መንገድ ስጡንና ሮጠን እናምልጥ እየተባባልን እንደምንሮጠው፤ ለመፈናፈኑም ተስፋ ያለው ነገር ካንቺ እንሻለን። እንዲያ በልጅነት ልብ በህግና በስርዓት የተመራው ጫወታችን አሁን ላንቺ ያሻል እናት ማለት አንቺ መሆንሽንም ለይቶ እንባሽ የሚደርቅበት ፤ ሰቆቃ ካነቺ የሚርቅበት የማሪያም መንገድ ልጆችሽ ይስጡን ጠይቂ።
አሁን ባለንበት ሁኔታ ሞት ቤታችን ባይገባም ጓደኞቻችንን ዘመዶቻችንን በየቀኑ እየነጠቅን፤ በሽታው በሰቀቀን እግር ከወርች አስሮ አላራምድ ባለን በዚህ ወቅት፤ ወደ ደጅ ለመወጣት የግድ መተፋፈንን ሲጠይቅ፤ መኖርና መሞት በውል ሳይታወቅ፤ ፈገግታ ከፊታችን ጠፍቶ የሞት ወሬ የቡና ማድመቂያ ከመሆን የዘለለ የማያስደነግጠን በሆነበት በዚህ ዘመን፤ መንገድ ዙሪያው ጨለማ ገደል በሆነበት በዚህ ወቅት የተስፋ ጭላንጭል የምናይበት ከውጥረታችን እፎይ የምንልበት ቀጭን መንገድ ያሻናልና የማሪያም መንገድ ሰጡን።
ኑሮ ጣሪያ ነክቶ ሰው የያዘውን ገንዘብ ለቤት ክራይ ያደርግው ለምግብ፤ ለልብስ ይሁን ለልጆች ትምህርት ቤት፤ እያለ በጭንቀት በተወጠረበት እንዳሁኑ ባለ ጊዜ፤ እናት ዛሬ ልጆቿን አብልታ ነገ ለመድገማቸው ምንም ዋስትና ሳይኖራት በሰቀቀን አይኗ በሚንከራተትበት በዚህ ወቅት፤ የኢኮኖሚ ጫናው በላይ በላይ እየተደራረበ ግራ እያጋባን ነውና እባካችሁ‹‹ ሀገራችን ለመኖረያ ምቹ ትሆናለች፤ ነገ ይነጋል፤ ሊነጋ ነው ጨለማው የተጫነን፤›› ብለን የምናስብበት ጭላንጭል ብርሃን የምናይበት፤ የጋረደውን የችግር ግንብ ብታፈርሱትም ሸንቁሩና እባካችሁ የማሪያም መንገድ ስጡን።
ከላይ ማህበራዊ ችግሮቻችንን እናንሳ እንጂ ሰሜን፤ ደቡብ፤ ምስራቅ፤ ምዕራብ ሁሉም የሀገራችን ዳር ድንበር፤ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ አለቁ፤ ጠፉ፤ ተደመሰሱ፤ ታረዱ፤ ተሰደዱ፤ ተፈናቀሉ፤ በሚሉ የወሬ ንፋሶች ሲሞሉ፤ ጆሯችን እለት በእለት የሰቆቃ ወሬ እየሰማ አልሞላም ሲለን፤ ግራ በመጋባት ውስጥ ቆመን ፈገግታችን ከፊታችን ጠፍቶ፤ ማን ይሆን ትክክል እያልን ግራ በተጋባንበት ፤እናት ልጆቻችን በመውለዷ ተፀፅታ መልሳ አትውጣቸው ነገር ግራ ገብቷት ባለችበት በዚህ ወቅት፤ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ከማሪያም መንገድ የተሻለ ምን ማመለጫ ምን አማራጭ ይኖረናል። ንግግራችሁን ወደን እጃችንን ዘርግተን በፍቅር የተቀበልናችሁ እንደታላቅ እረኛ አምኖ የሚከተላችሁን ህዝብ እባካችሁ ሰከን ብላችሁ ወደ ብርሃን የምተሻገሩበት የማሪያም መንገድ ፈልጉ።
ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድምና የራሳችሁን ሰሜት ብቻ ከማዳመጥ ይልቅ አምኖ የሚከተላችሁን መንጋ ሳሩና ውሃው የት እንዳለ ፈለጎ ማግኘት የእናንተ ሀላፊነት ነውና፤ በጎቻችሁ በተኩላው ፤በአውሬው ተበልተው እንዳያልቁባችሁ፤ ሸሽጋችሁ ወደ ተስፋይቱ ምድር የምታሻገሩበት ትልቅ አይደለም በጣም ትንሽ፤ እጀግ በጣም ቀጭን መንገድ፤ እንደ ልጅነታችን ሹልክ ብለን በማለፍ ሰፊው ሜዳ ላይ የምንቦርቅበት የማሪያም መንገድ ስጡን።
የሀገር ውስጡ አልበቃ ብሎን ጠላቶቻችን እንደተራበ አንበሳ ሊውጡን የሀገራችንን ዳር ድንበር ሲዞሩ፤ ለውጡን ሲያሰፈስፉ መመልከት በራሱ ሰቆቃ የሆነበት፤ ሀገር ስትታመስ እነ እገሌ ጋ ሄደን እንደበቃለን የምንለበት የረባ ጎረቤት እንኳን የለን፤ መጣፊያው በጠፋበት የሰማይ ስባሪ ያህል ጭንቅ ህዝባችሁን እግር ከወርች እንዳሰረው ስታውቁ፤ ተስፋ በጣልንባችሁ ያህል ለኛ የሚሆን የማሪያም መንገድ እንዴት ታጣላችሁ? ቆም ብሎ ነገሮችን በማስተዋል ከመከራ ውስጥ ደስታን ፈልቅቆ የሚያወጣ የብርሃን ብልጭታ አእምሯችሁ ይሰጣችሁ ዘንድ ሳትሰለቹ የማሪያም መንገድ ፈልጉ እባካችሁ።
ጭንቅ፤ ጥብብ በበዛባት በዚህ ወቅት ብልህ አሻጋሪ እንደሙሴ በበትሩ ባህርን ለሁለት የሚከፍል መሪ ያሻናልና ዞር ብላችሁ ስሙን የህዝባችሁን የልብ ትርታ አዳምጡና እንደምንም ብላችሁ የማርያም መንገድ ፈልጉ ብዬ አበቃሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013