መልካምስራ አፈወርቅ
መቸገር ይሉትን እውነት የስሙ ያህል ጠንቅቆ ያውቀዋል። በቤተሰቦቹ ስር የሰደደ ድህነት የልጅነት ዕድሜውን በመከራ ገፍቷል። እሱን ጨምሮ እህት ወንድሞቹ በችግር ሲፈተኑ ቆይተዋል። ከእጅ ወደአፍ የሆነው የወላጆቹ ገቢ መላ ቤተሰቡን በወጉ አሳድሮ አያውቅም።
ደበበ ደብተር ይዞ ትምህርት ቤት መሄድ የጀመረው እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ገና በጠዋቱ ነበር። ለቀለም የነበረው አቀባበል መልካም እንደሆነ ጥቂት ጊዜያትን ዘለቀ። እሱም እንደሌሎች ተምሮና ተለውጦ ራስን ማሻሻል፣ ቤተሰብን ማገዝ እንደሚቻል ያውቃል።
በልጅነት አዕምሮው ፊደል መቁጠር የጀመረው ታዳጊ ትምህርቱን ወደደው። አንደኛ ክፍልን አልፎ ሁለተኛ ሲገባ በውሎው ይበልጥ ተማረከ። ሁለተኛ ክፍልን ተሻግሮ ቀጣይ አመታትን ሲቀበልም መንገዱ የተሻለ ሆነለት። ትምህርትና ታዳጊው እንደተወዳጁ ቀጠሉ። አሁንም ደበበ ውሰጡ ያለው ብሩህ ተስፋ አልጨለመም። በልጅነት አዕምሮው ነገን እያሰበ ይደሰታል።በትምሀርት መለወጡ እየታየው ፈገግ ይላል።
ጥቂት ዓመታት በዚህ መልክ አለፉ። አሁንም በነደበበ ቤት ያለው ችግር ቀጥሏል።ቤተሰቡ በወጉ በልቶ የሚያድር አልሆነም። ከባዱ የኑሮ ውድነት ከልጆች ፍላጎት ተዳምሮ ችግሩን አብሶታል። እጅ ያጠራቸው ወላጆች አሁንም ትካዜ ውስጥ ናቸው። እንደወትሮው ለልጆቻቸው ማሰብ መጨነቅ ይዘዋል።ከዕለት ቀለብ የማያልፈው ገቢ ሌሎች ጉዳዮችን እየሸፈነ አይደለም።
ተስፋ መቁረጥ…
አሁን የደበበ ውጥን መፈተን ጀምሯል። ከሆድ መሙላት ያልዘለለው የቤተሰቡ አቅም ለሌላው ፍላጎት የሚተርፍ አልሆነም።በወላጆች ትከሻ ብቻ የወደቀውን ጫና ልጆች ሊካፈሉት ግድ እያለ ነው። እንዲህ መሆኑ ትምህርትና ተማሪውን በአንድ አላዘለቀም።የቤተሰቡ አቅም ማጣት ደበበን ወደኋላ ያስቀረው፣ ቤት ያውለው ይዟል።
ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ደበበ ትምህርቱን አቋርጦ እጁን ለስራ ሰጠ።ይህ ይሆን ዘንድም የኑሮው ውድነትና የወላጆች አቅም ማጣት አስገደደው። ከሶስተኛ ክፍል ያልዘለለው ተማሪ ራሱን ለማሳደር የመጀመሪያ ምርጫው የጉልበት ስራ ሆነ። ደበበ ከማለዳ እስከምሽት አቅሙ የቻለውን ይሸከማል። በሰራው ልክ የሚከፈለውን ይዞም ከቤቱ ይገባል።
ወላጆቹ ቤት ያፈራውን አይነፍጉትም፤ የተሰጠውን ጎርሶ ለነገው የጉልበት ስራ ራሱን ያዘጋጃል። ማግስቱን ከቀናው ጉልበቱን ከፍሎ ላቡን አንጠፍጥፎ የውሎውን ይቀበላል።አንዳንዴ ክፍያው ከዕለት ጉርሱ አያልፍም።በልቶና ጠጥቶ የሚተርፈው እምብዛም ይሆናል።ደበበ በጉልበቱ ለፍቶ አዳሪ ከሆነ ወዲህ ቤተሰቦቹን አስቸግሮ አያውቅም።
ለእነሱ የሚተርፍ ብር ይዞ ባይገባም ለራሱ የሚሆን አያጣም። አንዳንዴ ውሎው ሳይቀናው ይቀራል። ገቢው ያሰበውን ያህል ባልሆነ ጊዜ በትካዜ ይቆዝማል። የተራበ ሆዱን እያከከ፣ደጋግሞ እያዛጋ ጠሪዎቹን ይናፍቃል።እንዲያም ሆኖ አንዳች ላይሰራ ይችላል።
ይህኔ በኪሱ ያለውን ጥቂት ገንዘብ እያሰበ ከተወዘፈበት ይነሳል። እግሮቹ አቅጣጫቸውን አይስቱም። ዓይኖቹ መድረሻቸውን አያጡም። በመንደሩ ከሚገኙ አረቄ ቤቶች በአንዱ ይታደምና መለኪያውን ያስሞላል። ከመለኪያው ጥቂት ሲደጋግም የውስጡ ርሀብ ጥሎት ይሄዳል።
ባዶ ሆዱ እየፋመ፣መላ አካሉ እየጋመ ማንነቱ ይቀየራል። ረሀቡን በአልኮል ሸንግሎ ሁሉን ሲረሳ ውስጠቱ በድንገቴ ብሶት ይወረራል። ይህኔ ያለፈውን ከአሁኑ እያሰበ፣ከራሱ ውዝግብ ይጀምራል። ከውስጥ ስሜቱ እየተጣላም ዙሪያ ገባውን ይቃኛል።አጋጣሚው ከሌሎች ካገናኘው ሰላም የለውም። ምክንያት እየፈለገ፣ ሰበብ እየፈጠረ ከብዙዎች ይጋጫል።አፉ ያመጣለትን እየተሳደበም ለድብድብ ይጋበዘል።
ባህሪውን የሚያውቁ በትዕግሰት ያልፉታል። ሁኔታው ያበሸቃቸው ለጠብ ይሹታል። እንዲህ በሆነ ጊዜ እስከድብድብ የሚያደርስ ከባድ ግጭት ይፈጠራል። ብዙ ጊዜ ገላጋዮች ጠቡን አብርደው ሰላም ያወርዳሉ።ከቻሉ አስማምተው፣ከበረቱ አስታርቀው ያለያያሉ።አንዳንዴ ግን ጉዳዩ ከዚህ አልፎ ጠቡ ይጋጋላል።የደበደበ አሸንፎ የተደበደበ ተሸንፎ ልዩነት ይፈጠራል።
ደበበ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ሲፈጠር ቂሙን አይረሳም።ቀን ጠብቆ ጊዜ ለይቶ ለሌላ ጠብ ይዘጋጃል። ጠቡን ሲያስነሳ የውሎ ድካሙን ይረሳል።አረቄውን ተጎንጭቶ ፣ራሱን አበርትቶ ጠበኛውን ይፈልጋል።
አንድ ቀን…
አንድ ቀን ደበበ ከአንድ ሰው ጋር ተገናኘ።ሰውዬውን ሲፈልገው ቆይቷል። ቀድሞ ጠብ ነበራቸውና ቂሙን አልረሳም። ሳያስበው ወደእሱ ቀርቦ አነቀው። ሰውዬው ጠበኛውን መቋቋም አልቻለም። ባገኘው ቡጢና ጡጫ ክፉኛ ተጎዳ። ድብድቡን ያስተዋሉ አንዳንዶች መሀል ገብተው ገላገሉ።ተጎጂው ሆስፒታል ሲደርስ ደበበ በፖሊስ እጅ ወደቀ።
ከቀናት በኋላ ተደብዳቢው ምስክር ቆጥሮ፣ ማስረጃ ሰብስቦ ክስ መሰረተ። ጉዳዩን በበቂ መረጃዎች የመረመረው ፍርድቤት የተከሳሹን ጥፋተኝነት አረጋግጦ በአንድ አመት ከአስር ወር እስራት እንዲቀጣ ወሰነበት።
ደበበ የእስር ቅጣት ውሳኔውን ተቀብሎ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ወረደ።ይህ ቆይታ ለወጣቱ ታራሚ መልካም ዕድል ያመጣ መስሎ ቆየ።ከለመደ ድርጊቱ ታቅቦ ራሱን እንዲፈትሽ ምክንያት ሆኖም ወራትን ቆጠረ ።ጊዜውን ጨርሶ ከእስር ሲፈታ ደበበ ወደቀድሞ ስራው ተመልሶ የሸክም ተግባሩን ቀጠለ። በአዲስ ጉልበትና በተረጋጋ አዕምሮ ከብዙዎች ተግባብቶም የተሻለ ገቢን መቁጠር ያዘ።
ውሎውን በስራ እያሳለፈ ማምሻውን አረቄ እየተጎነጨ ጊዜያትን ቆጠረ። ከእስር ከተፈታ በኋላ ገቢው አልበቃውም።ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ፍላጎቱ ጨመረ። ከሸክም ስራው ባለፈ ዓይኖቹ መቃበዝ ለመዱ።ከላቡ ወዝ ፣ከጉልበቱ ድካም የዘለለ ጥቅም ማግኘት አማረው።
የደበበ የበረታ ፍላጎት በአቋራጭ ከሌብነት አገናኘው።ከሸክሙ ስርቆቱ ቢጥመው ሌብነቱን ደጋገመው። ኪሱ ሲወፍር ተግባሩን ማቆም አልቻለም። እንደስራ ቆጥሮ ተመላለሰበት። በዚህ ልማዱ እምብዛም አልተጓዘም። በፖሊስ ተጠርጥሮ ድርጊቱ በምስክሮች ዓይን ተረጋገጠ። ውሎ አድሮ ክስ ተመሰረተበት።
ፍርድቤቱ አሁንም ስለድርጊቱ ውሳኔ ሰጠ። ሶስት አመት ከስድስት ወር በእስር እንዲቆይ ብይን አሳለፈ።ደበበ ተመልሶ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ዘለቀ። እንደገና ከእስር ህይወት ተገናኝቶ አመታቱን ቆጠረ ። ወራት አለፉ፣ ጊዜያት ነጎዱና ከመፈቻው አደረሱት።ዳግመኛ ወደሸክም ስራው ተመለሰ።
ህይወት እንደገና…
አስራ ሁለት አመታትን በጉልበት ስራና በእስር የገፋው ሰው በህይወት ለመኖር መስራት መድከም ግድ አለው።አሁንም ሌላ አማራጭ አላገኘም። ጉልበቱን አጠንክሮ ትከሻውን አስፍቶ ራሱን ለሸክም አዘጋጀ። ደበበ በዚህ ስራ አመታትን ሲቆጥር ጉልበቱን ገብሮ ላቡን አፍስሶ ነው።ስራው ቀላል የሚባል አይደለም። ሮጠው የሚያድሩበት ነውና ከሌሎች መጋፋትን ይጠይቃል። አንዳንዴ መጋጨት መጣላት ይኖራል። ለእኔ ብቻ የሚል ስሜትም ብዙዎችን አያግባባም። ያሸነፈ ወስዶ፣ ያልቻለ የሚያጣበት፣ ከእጁ የሚነጠቅበት አጋጣሚ የበዛ ነው።
ደበበ ከእስር መልስ ወደስራው ሲገባ ከብዙዎች ጋር ያለው ውሎ ሰላም ያጣ ሆነ።አረቄ በተጎነጨ ቁጥር ከአንደበቱ ክፉ ቃላት ማውጣትን ልምድ አደረገ። ባህሪው ሲደጋገም ጠበኝነቱ ጨመረ።ጠበኝነቱ ሰላም አሳጣው፣ፍቅር ነሳው።በሚገባባቸው አረቄ ቤቶች ሁሉ ማንነቱ ተለየ ፣ ድርጊቱ ታወቀ።
ግንቦት 11 ቀን 2010 ዓ.ም…
የግንቦት ጸሀይ ‹‹አናት ትበሳለች›› ይሏት አይነት ሆናለች። ገና በጠዋቱ አቅል ማሳጣት የጀመረው ሙቀት መንገደኛውን ያስጨንቀው ይዟል። ደበበ በዚህ ቀን እንደወትሮው ከሸክም ስራው ውሏል። በማለዳ ከሸቀለው ጥቂት ሳንቲም ሆዱን እንደ ነገሩ ሸንግሎ አመሻሹን ከአረቄ ቤት ጎራ ብሏል።
ደጋግሞ የተጎነጨው አረቄ ከሰውነቱ ደርሶ ውስጡን ያሞቀው ይዟል። የደበበ ሞቅታ እያየለ ነው። እሱ ግን ወደቤቱ መግባት አልፈለገም። የወቅቱ ሙቀትና የአረቄው ፍጅት ሰውነታቸውን ያዛለው ጠጪዎች የእጃቸውን መለኪያ አላስቀመጡም። እየተጎነጩ፣ሌላ ያስቀዳሉ፣ እያወሩ፣ እየተሟዘዙ ይንጫጫሉ። ይጮሀሉ።
ደበበ ከነዚህ ሰዎች መሀል ተቀምጦ እየጠጣ ነው።ጥቂት ቆይቶ ግን ሀሳቡን ቀየረ። ሂሳቡን ከፍሎም ለመሄድ ተነሳ። ሞቅታ ይዞታል የሚሄድበትን አላጣውም። እየተንገዳገደ፣ እየቆመ ፣እየሄደ ወደ ሌላ አረቄ ቤት አመራ እየመሸ ነው አረቄ ቤቱ ጭር ማለት ጀምሯል።
ወደውስጥ ሲዘልቅ ጥቂት ሰዎችን አስተዋለ። ኮማሪቷ አረቄ ጠጥተው ለመውጣት ለተዘጋጁ ሰዎች ብር ቆጥረው መልስ እየሰጡ ነው። ከቤቱ ሌላ ጥግ የተቀመጠ አንድ ሰው አረቄውን አስቀድቶ እየተጎነጨ ነው። ደበበ ቀረብ ብሎ አስተዋለው። ሰውዬውን በደንብ ያውቀዋል።ሰላም ማለት፣ ማነጋገር አልፈለገም። ባሻገር እያስተዋለው ፊቱን አዙሮ ተቀመጠ።
መቀመጡን የተመለከቱት ሴት ጠርሙሳቸውን ይዘው አረቄ ሊቀዱለት ቀረቡ፤ የተቀዳለትን አንድ መለኪያ ጨልጦ ባዶውን መለኪያ አሳያቸው። አሁንም ሴትየዋ ከጠርሙሱ ወደመለኪያው በጥንቃቄ ሰፈሩ፤ ከአናቱ ጥቂት ፉት ብሎ ከአግዳሚው ላይ አስቀመጠው።
ጥግ ላይ የተቀመጠው ደንበኛ የደበበ ጉዳይ ያስገረመው ይመስላል።ሰላም ሳይለው በዝምታ መቀመጡን እያስተዋለ ምላሹን ጠበቀ። አሁንም ደበበ ዝም እንዳለ ነው።ሰውየው መገረም መደነቁን አልተወም። ሰላምታው ከእሱ አስኪመጣ እየጠበቀ ቆየ በደበበ ገጽታ አዲስ ነገር አልታየም እንደማያውቀው ሆኖ መጠጣቱን ቀጠለ።
ጥቂት ቆይቶ ሰውየው መናገር ጀመረ ንግግሩ ወቀሳና ትዝብት የታከለበት ነበር። ተናጋሪው ወደ ደበበ እያስተዋለ ስለምን ሰላምታ እንደነፈገው ጠየቀ ደበበ በሰውየው ጥያቄ ደንታ የሰጠው አይመስልም የሚናገረውን ንቆ ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ››ሲል ፊቱን አዞረበት።
አሁንም ሰውየው ውትወታውን ቀጠለ ‹‹ወንድሜ ነህ፣ ብዙ አሳልፈናል፣ ስለምን ሰላምታህን ነፈግኸኝ ምን አጠፋሁ? ›› አለው ይህኔ ደበበ ጥያቄውን ወደጎን ትቶ ከተቀመጠበት ተነሳ ፊቱ ላይ ንዴት እየተነበበ ወደ ሰውየው ቀረበ ቀርቦ የመሀል ጣቱን ወደፊት ቀስሮ ጩኸቱን ቀጠለ።
እየደገመ፣እየደጋገመ እናቱን በጸያፍ ቃላት ተሳደበ ሰውዬው ሊያረጋጋው ሞከረ ደበበ አልሰማውም ደጋግሞ እናቱን ጠራ ደጋግሞ ጠያፍ ቃሉን አሰማ ሰውዬው ስለንግግሩ ተመሳሳይ ምላሽ ሊሰጠው ሞከረ በአረቄ ቤቱ የእናት ስም ተብጠለጠለ፣ በጸያፍ ስድብ ባልተገባ ቃላት ወረደ ተዋረደ።
የደበበ ጩኸት ከአረቄው ተዳምሮ ስካሩን አባሰው ቃሉን አውጥቶ ድምጹን ከፍ አድርጎ ስድቡን ቀጠለ ቤቱ በብጥብጥና በከባድ ጨኸት ታመሰ ይህ ብቻ አልበቃውም እየተንደረደረ ወደሰውየው ሮጠ አጠገቡ ሲደርስ እጁ ባዱ አልነበረም መያዣው የእንጨት የሆነ ቢላዋ ከጎኑ አውጥቶ በግራ ጭንቅላቱ ላይ አሳረፈው።
ሰውየው ከወደቀበት እየተነሳ ደበበን ለመያዝ ሞከረ አልቻለም። ደም አስክሮት ከመሬት ተዘረረ ይህን ያየው ደበበ ቢላዋውን በእጁ እንደያዘ ወደውጭ ተፈተለከ መለስ ብሎም ወደነበረበት አረቄ ቤት ገባ የወጋው ሰው በደም እንደተነከረ ተዘርሯል ደም የነካውን ቢላዋ አጥብቆ ያዘው፤ ስካሩ ከላዩ ጠፋ ሀይልና ጉልበት አገኘ ሰዎች ሳያገኙት፣ ፖሊሶች ሳይደርሱበት ጨለማውን አቋርጦ ከስፍራው ሸሸ አመለጠ።
የፖሊስ ምርመራ …
ምሽት አራት ሰአት አካባቢ ጩኸት ሰምቶ ከአረቄ ቤቱ የደረሰው ፖሊስ ስለሁኔታው ጠየቀ ባለአረቄ ቤቷ የምሽቱን ትዕይንት አንድም ሳያስቀሩ አስረዱ ።መርማሪ ፖሊስ ምክትል ኢንስፔክተር ስንታየሁ ፈጠነ የግለሰቡን መሞት ተረድቶ ምርመራዎችን ቀጠለ ተጠርጣሪው ከድርጊቱ መፈጸም በኋላ ከአካባቢው ተሰውሯል።
መርማሪው ክትትሉንና ሌሎች መረጃዎችን በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 1337/10 ላይ መዝግቦ አዲስ ውጤት ጠበቀ ከቀናት በኋላ ተጠርጣሪው ደበበ መርሻ እጁን ለህግ ለመስጠት ከፖሊስ ጣቢያ ተገኘ ወንጀሉን የፈጸመው እሱ መሆኑን አምኖም በድርጊቱ መጸጸጹቱን ተናገረ።
ውሳኔ
ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት የተከሳሹን የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ለማየት በቀጠሮው ተገኝቷል ፍርድቤቱ በፖሊስ ምርመራና በዓቃቤህግ ማስረጃዎች ተጣርቶ የደረሰውን ሰነድ በማየት ግለሰቡ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም ግለሰቡን ያስተምራል ፣ሌሎችንም ያስጠነቅቃል ያለውን የአስራዘጠኝ አመት ጽኑ እስራት በይኖ መዝገቡን ዘግቷል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013