ይቤ ከደጃች.ውቤ
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የመንግሥት ገቢ እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናሩት፤ ሀገሪቱ በ2010 በጀት ዓ/ም 176 ነጥብ9 ቢሊየን ብር ገቢ ሰብስባለች:: በ2011 በጀት አመት ደግሞ 196 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል:: በ2012 228 ነጥብ ቢሊዮን 9 ብር ገቢ ተሰብስቧል፤ በተያዘው የ2013 በጀት አመት ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 191 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የሚታይ ዕድገት ነው፤ ግን በቂ አይደለም::›› ሲሉም አስገንዝበዋል:: የኢትዮጵያ ገቢ ማስገባት ከሚገባው አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑንም ገልጸዋል::
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችና መንግስት በተደጋጋሚ እንደሚሉትም፤ በሀገሪቱ የሚሰበሰበው ገቢ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ያነሰ ነው :: በርካታ ግብር የማይከፍሉ ነጋዴዎችና ዜጎች እንዳሉ ይገለጻል:: እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ግብር በትክክል ይከፍላሉ ተብለው ሲጠቀሱ የነበሩት የመንግስት ሰራተኞች ብቻ ናቸው::
እንደተባለው መንግስት በግብር አሰባሰቡ ላይ ለውጥ ቢያመጣም ገና ብዙ ያልተሰሩ ስራዎች ይቀሩታል:: እየተሰበሰበ ያለው ገቢና ኢኮኖሚው እያመነጨ ያለው ሀብተ ሲታይ የተገኘው ገቢ “አለገና ፤ መቼ ተነካና” የሚያሰኝ ነው:: ኢኮኖሚ ግብር መክፈል ያለባቸው ዜጎችና የንግድ ድርጅቶች ወደ ግብር መረቡ እንዲገቡ በተከናወነው ተግባር ግብር ሳይከፍሉ የቆዩ በርካቶችን ግብር መረብ ውስጥ ማስገባት የተቻለበት ሁኔታ አለ:: ይህ ግን ጅምር እንጂ ብዙ ርቀት የተሄደበት ነው ብዬ አላስብም:: ምክንያቱም ዛሬም አየር በአየር የሚካሄደው ንግድ ከፍተኛ ነውና:: በዚህ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ ከመሆናቸው በተጨማሪ እሁን እየታየ ላለው የኑሮ ውድነት በዋነኛነት ተጠያቂ ናቸው::
በአየር በአየር ንግድ ላይ ጥብቅ እርምጃ በመውሰድ በግብር አሰባሰቡ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ይቻላል:: በዚህ ላይ የሚወሰድ እርምጃ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ለኑሮ ውድነት ምክንያት ከሆኑት አንዱ የሆነውን ይህን የንግድ እንቅስቃሴ ለመከላከል ይቻላል:: አሁንም በእዚህ ላይ በትኩረት ይሰራ እላለሁ::
በአዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ከፍተኛ የቤቶች ልማት ይታያል:: የቤቶች ልማቱ የሚሰራው ለመኖሪያ ብቻ አይደለም:: ለንግድ አገልግሎትም ነው :: ከዚህ አገልግሎት ገቢ ለመሰብሰብ አንዳንድ ሙከራዎች ሲደረጉ ይታያል:: ይህን ያህል ገቢ ከኪራይ ገቢ ግብር ተገኘ የሚል መረጃ ባላይምና ፣ከኪራይ ገቢ ግብር ይህን ያህል ለመሰብሰብ ታቅዷል የሚል መረጃም ባልሰማም በአካባቢዬ ካሉ እውነታዎች ተነስቼ መናገር የምችለው ግን አለኝ::
ከቤት ኪራይ ገቢ የሚሰበሰበው ብር በጣም ውስን ነው :: አንዳንዶች የቤት ኪራይ ገቢያቸውን አሳውቀው ህጉ በሚያዘው መሰረት የሚከፍሉበት ሁኔታ ቢኖርም ፣ መረጃው ግን በየጊዜው የሚታይ አይመስለኝም:: ከአስር አመት በፊት ከተከራይ ጋር በገቡት ውል መሰረት ግብር የሚከፍሉ በርካታ ናቸው:: ባለፉት አስር አመታት በርካታ ተከራዮች ተቀያይረው፣ የቤት ኪራይ ዋጋም እንዲሁ እያሸቀበ መምጣቱ እየታወቀ ባረጀ ባፈጀ ውል ላይ ተመስርቶ የሚሰበሰብ የቤት ኪራይ ገቢ ግብር ትክክል ነው ብዬ አላምንም:: እዚህ ላይ በሚገባ ተሰርቷል ብዬም አልወሰድም ::
ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እያረጉ ተጨማሪ እሴት ታክስ የማይሰበስቡም እንዳሉ ይታወቃል:: ታክሱን እየቆረጡ ለተገልጋይ ደረሰኝ በመክፈል ግብሩን ለመንግስት የሚያቀርቡ እንዳሉ ሁሉ ታክሱን ሰብስበው ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ስለመኖራቸው ደረሰኝ ካለመቁረጣቸው በመነሳት መናገር ይቻላል::
ጥሩ እየሠሩ የማይገብሩ፣ ግብር የሚያጭበረብሩ ተጨማሪ ዕሴት ታክስ እየሰበሰቡ ለሸማቾች የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ትኬት የማይሰጡ ብዙ ንግድ ቤቶችና ምግብ ቤቶች አሉ:: ብዙ ተስተናጋጅ በሞላበት የተጨማሪ ዕሴት ዕሴት ታክስ ጭምር የሚያስከፍሉ ግን ትኬት የማይሰጡ ነጋዴዎች አለመቅጣት አጭበርባሪነትን ማበረታታት ነው::
በእነዚህ አካላት ተጨባጭ መረጃ ከተገኘባቸው ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እርምጃ መውሰድ ይገባል:: የተለመደው ቅጣት ማሸግ ነው፤ ማሸግ ብቻውን ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚያመጣ አይመስለኝም:: ይህ አይነቱ እርምጃ ብቻውን ለእኔ የለብለብ እርምጃ ነው:: አስተማሪ ቅጣት መውሰድ ያስፈልጋልና:: ፈረንጆች የብልፅግና ደረጃ ላይ የደረሱት ዜጎች ሁሉ እየሠሩ ተገቢውን ግብር እንዲከፍሉ ስላስተማሩና የሀገር ፍቅር ስለሚያስገድዳቸው ጭምር ነው:: በኛ ሀገር አንዳንድ ነጋዴዎች ዘንድ ግን ግብር በአግባቡ የሚከፍል ሞኝ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው :: ይህ አመለካከት እንዲቀየር መስራት ያስፈልጋል::
በእዚህ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ መስራቱ እያደገ የመጣውን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ወደ በለጠ ደረጃ ያደርሰዋል:: ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ተጨማሪ ዕሴት ታክስ ከዓመት እስከ ዓመት በአግባቡ እየሰበሰቡ ለመንግሥት ታክስ የሚከፍሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትንና ድርጅቶችን ለማበረታተት እየተሄደ ያለበትን አሰራርም አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ::
ከዚህ አኳያ መንግስት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል:: በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመርካቶ ያለውን ሁኔታ አስመልከተው ሲገልጹ
‹‹ በመርካቶ ያለው አጠቃላይ የንግዱ ስርአት ሶስት ችግሮች አሉበት:: ሶስቱም ወንጀሎች ናቸው:: ደረሰኝ አለመቁረጥ፣ ከዋጋ አሳንሶ መቁረጥ ፣ ሁለተኛ ደረሰኝ መቁረጥ፣ በዚህ ላይ በጣም በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው›› ብለዋል::
ይህን የሚሰራ ግብረ ሀይል እንዳለም ጠቅሰው፣ እርምጃዎቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል:: በመርካቶም በባህርዳርም፣ ጎንደርም፣ ጅማም በሁሉም ቦታ ነጋዴዎች ህግ አክብረው ትክክለኛ የሆነ ሰርአት ያለው የንግድ ስርአት ተከትለው ማተረፍ ነው እንጂ ገቢ ላለማስገባት አንዳንዴም አፍነው ይዘው በማከማቸት ዋጋ ማስወደድ ላይ የሚያደርጉትን ስራ በህግ ማስተካከል ያስፈልጋል:: በዚህ ላይ እየሰራንበት እንገኛለን፤እንሰራበታለን ብለዋል::
እርምጃው መንግስት ከግብር ፣ ከገቢ መሰብሰብ፣ ከህገወጥ ንግድ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ያመለክታል:: የሀገራችንን የንግድ እንቅስቃሴ ለማስተካከል እና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ወሳኝ ነውና ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል:: በዚህ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎችና ያሰገኙት ለውጥም ለህዝብ ይፋ የሚደረግበት ስርአት ሊዘረጋም ይገባል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2013