መልካምስራ አፈወርቅ
የልጅነት ህይወቱ በውጣ ውረድ የተሞላ ነው። ህጻንነቱን እንደሌሎች እኩዮቹ በምቾት አላለፈም። በጨቅላነቱ ከእናቱ ደረት ተለጥፎ ጡት አልጠባም፣ እናቱን በፍቅር ሽቅብ እያስተዋለ አልሳቀም፣ አላወራም፣ በእናቱ ተሞካሽቶ አልተሳመም፤ አልተቆላመጠም። ገና በጠዋቱ እናትና ልጅን የለየው ክፉ ሞት ይህን በረከት እንዲካፈል ዕድል አልሰጠውም።
ህጻኑ ደረሰ ወላጅ እናቱን በሞት ያጣው ገና ከአንቀልባ እዝል ሳይወርድ ነበር። የእናቱን ሞት ተከትሎ የቤተሰቡን ኃላፊነት የተረከቡት አባት እሱን ጨምሮ ሌሎች ልጆችን ለማሳደግ ሲታትሩ ቆዩ ፤ ህይወት እንደቀድሞው አልቀጠለም። ሀዘን የገባውን ቤተሰብ በቀላሉ ሊታደጉት አልቻሉም።
ደረሰ ከሌሎች በተለየ ፍቅርና እንክብካቤ ያሻዋል። በወጉ ያልጠገበውን የእናት ፍቅር በሌሎች ሰዎች ለመተካት ቀላል አልሆነም። ጠዋት ማታ በለቅሶው የሚለየው ጨቅላ ደስታ ራቀው። ነጭናጫና ብስጩ ሆነ።
አባት ውሎ አድሮ ጤናቸው ሲቃወስ የልጃቸው ጉዳይ ያሳስባቸው ያዘ። ደረሰ የሙት ልጅ ነው። ክፉ ደጉን አያውቅም። የጨቅላው ልጅ ነገር ሰላም አልሰጣቸውም። ይህን እያሰቡ ህመማቸው በረታ። ከአልጋ መዋል ጀመሩ።
አንድ ቀን ማለዳ በመንደሩ የደረሰ አባት ሞት ተሰማ። ይህን ክፉ ዜና የሰሙ ሁሉ ስለትንሹ ልጅ ጭምር አነቡ። እናት የማያውቀው ህጻን አባቱን ዳግም ማጣቱ አሳዘናቸው ። ሞት የዘጋው ጎጆ ጭር ሲል ልጁን ማን እንደሚያሳድግ እያሰቡ ተጨነቁ።
የለቅሶ ጊዜው አብቅቶ ወዳጅ ዘመድ በየቤቱ ሲቀር አሳሳቢው ጊዜ እውን ሆነ። ደረሰ በብቸኝነት ቆዘመ፤ በእናት አባት ፍቅር ተሳቀቀ፤ ሰው ተራበ፤ ጠባቂ አልባው ህጻን ብቻውን መዋል ሲጀምር ፈተናዎች አላጡትም።
አንድ ቀን ህጻኑ ከድመት ጋር ሲጫወት ዋለ። ድመቱ ሲበዛ ሀይለኛ ነው። በየምክንያቱ መቆጣትና መጮህ ያበዛል። ይህ ያልገባው ደረሰ። ከእሱ ውሎ መጫወትን ፈለገ። ድመቱ ለጊዜው ፊት አልነሳውም። እንዳሻው ሊሆንለት ሞከረ። ይህን ያየው ብቸኛ ህጻን ፍቅር ያገኘ ቢመስለው ጅራቱን ይዞ ጎተተው ። ቁጠኛው ድመት በእጅጉ ተበሳጨ። የተያዘ ጅራቱን ሊያስለቅቅም የሾሉ ጥፍሮቹን ወደ ህጻኑ ፊት አዞረ።
የድመቱ ሀይል የበዛበት ደረሰ አምርሮ አለቀሰ። እየጮኸ እየተንከባለለም ሰዎችን ፈለገ። ጩኸቱን ሰምተው ካለበት የደረሱ በሆነው ሁሉ ደነገጡ። የህጻኑ ፊት በድመቱ ሹል ጥፍሮች እንዳይሆን ሆኗል ። ድመቱን አባረው ልጁን ያነሱት ሰዎች ፈጥነው ደም የለበሰ ፊቱን ዳበሱ። በግንባሩ ስር ካሉት ዓይኖቹ አንደኛው ክፉኛ ተጎድቷል።
አምርሮ የሚያለቅሰውን ህጻን አጣጥበው ዳግመኛ ፊቱን ፈተሹ። ይህን ከማድረጋቸው ውስጣቸው በድንጋጤ ተሞላ። እያዩት ያለውን ማመን፣ መቀበል ተሳናቸው። የህጻኑ አንደኛው ዓይን በድመቱ ሹል ጥፍሮች ከመጎዳት አልፎ ጠፍቷል። ደረሰ በማይበቀለው የቅርብ ጠላት አይተኬ ዓይኑን አጥቷል። የትንሹ ልጅ ጫንቃ ሌላውን የመከራ ምዕራፍ ጀመረ።
ጥቂት ቀናት እንዲህ አልፈው ዳግም ሌላ ቀን ነጋ። ይህ ቀን ለደረሰ ሌላ አማራጭ ይዞለት ነበር። አያቱ እሱን ተረክበው ሊያሳድጉ ከቤታቸው ወሰዱት። ይህኔ ሰው የናፈቀው፤ ፍቅር የተራበው ህጻን ቀልቡ ተመለሰ ። ከአያቱ ጉያ ውሎ መሳቅ መደሰት ጀመረ።
ነፍስ ማወቅ ሲጀምር ተማሪዎች ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት ሲሄዱ አየ ። ደረሰ እነሱን ባስተዋለ ጊዜ አብሯቸው ሊማር ፣ ፊደል ሊቆጥር ፈለገ። አያቱ የልጅ ልጃቸው እንደሌሎች ቢማርላቸው አይጠሉም። ይህን የማድረግ አቅሙ ግን የላቸውም። እናም ከልብ አዘኑ ።
መማር ያልቻለው ትንሽ ልጅ ሀሳባቸው በገባው ጊዜ እንደሳቸው አዘነ ። የመንደሩ ልጆች ሜዳውን አቋርጠው ሲሄዱ እያየም ለቀናት ሆድ ባሰው። ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ግን ሁሉን ረስቶ ቤት መዋሉን ለመደ። የእኩዮቹን መማር ከቁብ ሳይቆጥርም ከአያቱ መስሎ መኖር ቀጠለ።
አሁን ደረሰ በዕድሜው ከፍ ማለት ጀምሯል። የዕድሜው ከፍታ በአእምሮው ጥያቄ እያመላለሰበት ነው። የእሱ አንድ ዓይን እንደሌሎች አይደለም። በአይነቱ ለየት እንደሚል ከገባው ቆይቷል። ይህን ማሰብ ከጀመረ ወዲህ ለአያቱ ጥያቄ አቅርቦ ተመልሶለታል። ከዓይኖቹ አንደኛው በድመት ቡጥጫ መጥፋቱን ባወቀ ጊዜ ለራሱ ደጋግሞ አዝኗል።
ደረሰ ከዕድሜው መጨመር ጋር ሌላ ሀሳብ መጣለት። እሱንና አያቱን እያገዘ ገንዘብ ማግኘት እንዳለበት ወሰነ። በወቅቱ ከእረኝነት የዘለለ ስራ አልተገኘለትም። ይህ መሆኑ አልከፋውም። መማር ባይችል በመጠነኛ ገቢው ተደስቷል።
ባለአንድ ዓይናማው ልጅ የመንደሩን ከብቶች ሲጠብቅ ውሎ አመሻሹን ይመለሳል። ቤት ያፈራውን ቀማምሶም ስለነገው ያስባል። አሁን ከትናንት በተሻለ እየኖረ ነው። ትንሽ ብትሆንም የገንዘብን ጥቅም አውቋል። ይህን ማወቁ አርቆ እንዲያስብ ምክንያት ሆኗል።
ደረሰ ገጠር ኖሮ በእረኝነት ከሚቀር ከተማ ገብቶ የተሻለ ህይወት ቢቀጥል ፍላጎቱ ነው። በዚህ ሀሳብ ደጋግሞ ሲብሰለሰልበት ቆይቷል። ከተማ መኖር አሁን ካለበት ህይወት የበለጠ እንደሆነም ከገባው ቆይቷል።
የገጠሩ ወጣት ሀሳቡን በውጥን አላስቀረም። ሲያወጣ ሲያወርድ የቆየውን ዕቅድ ዕውን ሊያደርግ ጓዙን ሸከፈ። የጉዞ አቅጣጫው አዲስ አበባ ነበር። የትውልድ አገሩን ሰሜን ሸዋን፣ ያደገበት ቀዬውን ‹‹ጅዳ››ን ተሰናብቶ ሲወጣ አልከፋውም። ህልም አለውና ሩቅ ያስባል።
ደረሰ እንዳሰበው ሆኖ አዲስ አበባ ገባ። ስፍራው ሲደርስ የከተማ ህይወት ከበደው። ለእሱ የሚመጥን ስራ፣ ለኑሮው የሚበጅ ገቢ የት እንደሚገኝ አላወቀም። በግራ መጋባት ቀናትን ያሰለፈው እንግዳ መዳረሻው ካለፈበት የህይወት መልክ አልዘለለም። በቅርብ ያገኛቸው ሰዎች በእረኝነት እንዲቀጠር ጠየቁት። ምርጫ አልነበረውም።
ደረሰና እረኝነት ዳግመኛ ተገናኙ። አሁን አዲስ አበባ ገብቷል። ያለበት ስፍራ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ከሚገኝ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው። ቦታውን አልጠላውም። ገጠሩን ስለሚያስታውሰው ወዶታል። እንደ አምና ካቻምናው የመንደሩን ከብቶች እየነዳ ከሜዳ ይውላል። ለዓይን ሲይዝ ከብቶቹን መልሶ ከሚያርፍበት ይደርሳል። በማግስቱ ህይወቱ እንደትናንቱ ይቀጥላል።
ደረሰ ከገጠር ወጥቶ አዲስአበባ ከገባ ወዲህ የግራ ዓይኑ ጉዳይ ያሳስበው ይዟል። አንዳንዴ አንዳንዶች ትኩር ብለው ካዩት ይበሽቃል። እሱ ከሁሉም የተለየና ያነሰ መስሎ ይሰማዋል። ይህ ስሜት ልጅነቱን አጋምሶ ወጣትነቱን ከያዘ ጀምሮ የሚፈታተነው ሆኗል።
ደረሰ በልጅነቱ በድመት የደረሰበት ጥቃት የግራ ዓይኑን እንዳሳጣው ከአያቱ ሰምቷል። አገሩ እያለ ለአንድም ቀን የበታችነት ተሰምቶት አያውቅም። የዛኔ የሚያውቃቸው ሰዎችም ቢሆኑ በዓይኑ መጎዳት ሲገረሙ አላየም። አሁን ግን ብዙ ሰዎች ትኩር ብለው ሲያዩት ያያቸዋል። መለስ ሲሉ ብዙ እንደሚሉት ያስባል። ይህን ሲያስብ ውስጡ በቁጭት በነገር ይጎሻል።
ደረሰ የአዲስ አበባን ህይወት በእጅጉ ለመደው። ከብዙዎች ተዋወቀ። ከበርካቶች ተግባባ። እንዲህ መሆኑ በእረኝነት የቆየበትን ውሎ እንዲቀይር ዕድል ሰጠው። ከልጅነት እስከ ዕውቀት የከብቶችን ጭራ ሲከተል የኖረበትን ስራ ቀየረ። የተሻለ ገቢ ማግኘት ሲጀምር ቤት ተከራይቶ መኖር ያዘ ። አለባበስ፣ አረማመዱ ተለወጠ ።
አሁን ደረሰ የቀን ሰራተኛ ሆኗል። ጠዋት በስራ ሲደክም ውሎ ማታ ቤቱ ይመለሳል። በተከራየበት አካባቢ ከጎረቤቶቹ ይግባባል። ከአንዳንዶቹ ጋር የዓይን ሰላምታ አለው። ሁሌም በሚያመሽበት ጠጅ ቤት ከብዙዎቹ ጋር ይገናኛል። ጠጅ ቤቱን እንደሱ ያሉ ባተሌዎች ያዘወትሩታል።
ደረሰ ጠጅ ቤት ባመሸና ሞቅ ባለው ጊዜ ሰው ሁሉ እሱን የሚያየው ይመስለዋል። አንዳንዶች በግላቸው ሲያወሩም በጨዋታቸው እንደሚያነሱት ይጠረጥራል። ያም ሆኖ ከጠጅ ቤቱ ቀርቶ አያውቅም። ለብ እሰኪለው ጠጥቶ አመሻሽቶ ይገባል።
ጠጅ ቤቱ የአካባቢው ነዋሪዎችና ቋሚ ደንበኞቹን ጨምሮ ሌሎች መንገደኞች ይታደሙበታል። በሁካታ ሲተራመስ የሚውለው ስፍራ ምሽቱ ሲገፋ ጭር ማለት ይጀምራል። ጥቂቶች የልማዳቸውን አድርሰው በጊዜ ይለዩታል። የጠጅ ቤቱ ባለቤት ደንበኞቻቸውን ሸኝተው በሰዓቱ በራቸውን ይዘጋሉ።
ሰኔ 23 ቀን 2011 ዓ.ም
ሰኔ ግም ካለ ከራርሟል። ምሽቱ ‹‹መጣሁ›› በሚለው ዝናብ ተይዟል። ደጋግሞ የሚያስተጋባው ነጎድጓድ እግረኛውን እያሯሯጠው ነው። ድንገት ሽው የሚለው ሀይለኛ ንፋስ ሊዘንብ ካቆበቆበው ዝናብ ጋር ትግል ገጥሟል። ከዚህ ሁሉ ርቀው በአንድ ጥግ የታደሙት ነፍሶች ግን የደመቀ ጨዋታ ይዘዋል።
ዛሬም በጠጅቤቱ ሳቅና ሁካታው ቀጥሏል። ገና በጊዜ ከአግዳሚው የተሰየሙት ደንበኞች የያዙትን እንደጨረሱ ሌላ ያስቀዳሉ። ከወዲያ ወዲህ የሚለው አሳላፊ ትዕዛዝ እየተቀበለ የተጨለጡ ብርሌዎችን ይሞላል።
ከታዳሚዎቹ አብዛኞቹ የሰፈሩ ሰዎች ናቸው። ከነዚህ መሀል አንደኛው የደረሰ ጎረቤት ነው። ሁሌም በዓይን ይተያያሉ። ሁለቱ በተገናኙ ጊዜ በአንገት ሰላምታ ይተላለፋሉ። ከዚህ በዘለለ አጋጣሚ ተገናኝተው አውግተው አያውቁም። ሰውዬው ያን ምሽት ከጠጅ ቤቱ የደረሰው በጊዜ ነበርና ሲጠጣ አምሽቷል። የእጁን እንደጨለጠም ወደ ቤቱ ያዘግማል ።
ደረሰ ስራ ውሎ ከመምጣቱ ወደ ጠጅ ቤቱ አመራ። በዚህ ሰዓት ጎራ ማለት ልምዱ ነው። ወደ ውስጥ እንደዘለቀ አሳላፊው ብርሌና ጠጅ ይዞ አስተናገደው። ከጠጁ ጎንጨት ብሎ ቀና ከማለቱ በአንገት ሰላምታ ከሚያውቀው ጎረቤቱ ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጩ። ሁለቱም እንደልማዳቸው ሰላም ተባባሉ ።
ደረሰ ከጠጁ ደጋገመ። ጎረቤቱ በእጁ ያለውን አልጨረሰም። ጥቂት ቆይቶ ጨዋታ ተጀመረ። ሰውዬው አሳላፊውን ጠርቶ እንዲቀዳለት አዘዘው። ጎረቤታሞቹ ያለወትሯቸው ተቀራርበው ብዙ አወጉ ።
ምሽቱ መግፋት ጀመረ። ሁለቱም አልተጨነቁም። መንገዳቸው አንድ በመሆኑ አብረው ሊሄዱ ወስነዋል። ሰዓቱ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ማለት ሲጀምር ሁለቱም እኩል ተነሱ ። ያለባቸውን ሂሳብ ከፍለው መንገዳቸውን ቀጠሉ።
በመንገዱ ላይ…
በሞቅታ ስሜት መንገዳቸውን የያዙት ጎረቤታሞች የጀመሩትን ጨዋታ ቀጥለዋል። ደረሰ ከሰውዬው ቀደም እያለ ይራመዳል ። ሰውዬው እሱን ተከትሎ ይጓዛል። ጨለማው ‹‹ዓይን ቢወጉ አይታይም›› ይሉት አይነት ሆኗል።
መንገዱን ማጋመስ እንደያዙ ደረሰ ከሰውዬው ፊት የተጋደመ ትልቅ ድንጋይ መኖሩን አስተዋለ። ፈጠን ብሎም ‹‹እንዳያደናቅፍህ በዚህ በኩል እለፍ ›› ሲል አቅጣጫ ጠቆመው። ይህን የሰማው ጎረቤት ‹‹ አታስብ እኔ ከአንተ የተሻለ አያለሁ ›› ሲል ምላሽ ሰጠ።
ይህን ቃል የሰማው ደረሰ ፊቱ ተለዋወጠ። ውስጡ ተቆጣ፤ ንዴትና ብሽቀት ይንጡት ያዙ። ሰውዬው ‹‹ከአንተ የተሻለ አያለሁ›› ማለቱ የእሱን ዓይን ከራሱ ማስበለጡ እንደሆነ ገባው። ይህን ሲያብሰለስል በዓይኑ ምክንያት ከሰው በታች መሆኑን ተረዳ። ሰውዬው በአሽሙር የተናገረው አንተ አታይም ‹‹ ዕውር›› ነህ ለማለት መሆኑን አረጋገጠ።
አሁን የደረሰ ስሜት ክፉኛ ተቀይሯል። ሰውዬው ሁኔታው አልገባውም። በጀመረው ጨዋታ መጓዙን ቀጥሏል። ደረሰ የሚለውን እየሰማው አይደለም። በንግግሩ በሽቋል ‹‹ዕውር›› ነህ በመባሉ ውስጡ ተክኗል። መንገዱ እንደጅምሩ አልቀጠለም። ደረሰ ጎንበስ ብሎ ትልቅ ድንጋይ አነሳ። ወደ ሰውዬውም ቀረበ። መንገደኛው አልጠረጠም።
ድንገት ጭንቅላቱ ላይ ባረፈበት ድንጋይ ሰማይ ምድሩ የዞረበት ሰው የኋሊት ተዘረረ። መውደቁን ያያው ደረሰ ፈጽሞ አልተወውም። እየደጋገመ ድንጋዩን አሳረፈበት። የተመታው ሰው ጉዳቱ በረታ። ከወደቀበት መነሳት አልቻለም ደሙን እያዘራ ተዘረረ ።
ደረሰ የሰውዬውን ሁኔታ እንዳየ በጨለማው እያቆራረጠ ወደ ባልንጀራው ቤት ገሰገሰ። ደንግጧል፤ ልቡ ይመታል። ለባልንጀራው የሆነውን አንድም ሳያስቀር ዘረዘረለት። ታሪኩን የሰማው ጓደኛው ደነገጠ። እንግዳው ምሽቱን እዛው አሳለፈ። ወደቤት መሄድ አልፈለገም አደረ። ሊነጋጋ ሲል ደረሰ ከተኛበት ተነሳ። ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ግራቀኙን አስተዋለ። ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ሲመጡ ተመለከተ ።
የፖሊስ ምርመራ…
ፖሊስ በስፍራው ከመድረሱ አስቀድሞ ስለምሽቱ ሁኔታ ሪፖርት ደረሰው። አንድ ግለሰብ ጭንቅላቱን በድንጋይ ተመቶ ህይወቱ አልፏል። በቦታው ተገኝቶ የጠጅ ቤቱን ባለቤት ጠየቀ። ሟች ትናንት ማታ ከደረሰ ጋር አምሽቶ መውጣቱን ነገሩት።
መርማሪ ፖሊስ ዋና ሳጂን አማረ ቢራራ ወደ ተጠቆመው ስፍራ አመራ። አማረን አላጣውም፤ ስለሁኔታው ጠየቀው። ግለሰቡን በወጉ እንደማያውቀውና በአንዲት ቃላት ትርጉም ብቻ ተናዶ በድንጋይ ቀጥቅጦ እንደገደለው አመነ።
ውሳኔ
ውሳኔ
የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ተከሶ የቀረበውን ግለሰብ ጉዳይ መርምሮ ለመጨረሻ ውሳኔ በችሎቱ ተገኝቷል። ተከሻሹ ስሙን እንኳን በወጉ የማያውቀውን ግለሰብ በግፍ በመግደሉ ጥፋተኝነቱ ተረጋግጧል። ፍርድቤቱ በዕለቱ በሰጠው ብይንም ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የአስራ አራት ዓመት ጽኑ አስራት ይቀጣ ሲል ወስኗል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም