ኮቪድ 19 ወደ ሀገራችን ከገባ አንድ አመት ካለፈው ቀናቶች እየተቆጠሩ ነው ። በነዚህ ጊዜያት ውስጥ 204ሺ 521 ዜጎች በቫይረሱ ተይዘዋል ። 2ሺ 841 ለህልፈት ተዳርገዋል ። 45ሺ 053 ዜጎች ደግሞ ከቫይረሱ ጋር እየኖሩ ነው ። ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ለተለያየ የጎንዮሽ የጤና ችግር የተጋለጡም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ይገመታል።
ከዚህም ጎን ለጎን በማገገም ሂደት ውስጥ ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱ ዜጎቻችንም ቁጥር ትንሽ ሊሆን እንደማይችል በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማሰብ በቂ ነው ። በነዚህ ዜጎቻችን ላይ ቫይረሱ የፈጠረው የስነ ልቦና ጫናም በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡
መንግስት፣ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊትም ሆነ ከገባ በኋላ የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመከላከል በኃላፊነት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፤ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል ። ወረርሽኙ ፈጥሮት የነበረውን ስጋት ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየርም አጠቃላይ በኢኮኖሚውም ሆነ በጤና ዘርፉ ላይ ያስከትላል ተብሎ የተሰጋውን አደጋ መቀነስ ተችሏል ፡፡ ይህ ተግባሩም ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አስችሮታል።
በአንድ በኩል የቫይረሱ ወረርሽኝ የተከሰተበት ወቅት ሀገሪቱ በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ የነበረችበት መሆኑ፤ ከዛም በላይ አገራዊ ኢኮኖሚው በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ የነበረበት መሆኑ፤ እንዲሁም በለውጡ ጥቅማቸው የተነኩ ኃይሎች ለውጡን ለማጨናገፍ በአንድነት ለጥፋት የተንቀሳቀሱበት ከመሆኑ አንጻር ወረርሽኙ ፈጥሮት የነበረው ስጋት ከፍ ያለ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የለውጥ ኃይሉ በእነዚህ ፈታኝ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሄደበት መንገድ እና ሕዝቡ እራሱን ከበሽታው ለመጠበቅ ያሳየው ቁርጠኝነት ተዳምሮ ያንን ብዙ ጨለማ ያጠላበትን ወቅት መሻገር ችለናል ። ስጋቶች የታሰበውን ያህል የአደጋ ምንጭ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ይሁን እንጂ ይሕ የመንግሥትና የመላው ሕዝብ ተናቦ የመንቀሳቀስ እውነታ ቀናት አልፈው ወራት ሲተኩ በብዙ መዘናጋቶች እየተለወጠ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር ነው ። በአንዳንድ ሁኔታዎች የቫይረሱ መኖርና ሊያስከትል የሚችለው ሀገራዊ አደጋ ተረስቶ ግዴለሽነት ነግሷል ። ቀላሎቹን የበሽታው መከላከያ የጥንቃቄ መርሆች የከበዱ የሚመስሉበት ሀገራዊ መንፈስ ተፈጥሯል ።
እጅግ የሚያሳዝነው እውነታ ደግሞ በሽታው ከትናንት ይልቅ ዛሬ ላይ ለህልፈት የሚዳርጋቸው ፣ በቫይረሱ ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎቻችን ቁጥር እለት ተእለት እየጨመረ ባለበት ሁኔታ ውስጥ መዘናጋቱ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው ።
በአንዳንድ የሀገሪቱ ከተሞች የወረርሽኑ ደረጃ እጅግ ከመግዘፉ የተነሳ ሁኔታዎች ወዴት እየሄዱ ነው እየተባለ ባለበት ሰዓት፤ መዘናጋቱ ሊያስከፍለን የሚችለውን ዋጋ መገመት እያስቸገረ ባለበት የሁኔታዎች ግምገማ ውስጥ ሆነን እየታየ ያለው ሀገራዊ መዘናጋት ለተመልካችና ለወሬ የሚመች አይደለም።
በየእለቱ ወደ መቃብር የሚወርዱ ዜጎቻችን ቁጥር እየጨመረ ባለበት በተለይም የሀገር ባለውለታዎችን በየእለቱ ወደ መቃብር እየሸነን ባለንበት፤ ወረርሽኑ በበቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች አልፎ አጠቃላይ የጤና ሥርዓቱ ላይ ከፍ ያለ ጫና እያስከተለ ባለበት ሁኔታ የጤና ሚኒስቴር ሆነ የጤና ባለሙያዎች ስጋታቸውን አስመልክተው በየእለቱ የሚሠጧቸው መግለጫዎችና ሙያዊ ምክሮች ሰሚ እያገኙ አይደለም ።
የበሽታ ወረርሽኝ ከጤና ስጋት በላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ዘርፈ ብዙና የሚስከፍለውም ዋጋ ከፍ ያለ ስለሚሆን እንደ ህዝብ ቀልባችንን ሰብስበን ከፊታችኝ ያለውን አደጋ በአግባቡ መመልከትና ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚጠበቅብን ወቅት ላይ ነን። ይህን ማድረግ ባለመቻላችን ለሚከሰተው ሀገራዊ አደጋ ማንንም ተጠያቂ ልናደርግ የምንችልበት የሞራል መሰረት የለንም።
አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታየው መዘናጋት እና መዘናጋቱ ሊያስከትለው ከሚችለው አደጋ አንጻር የመከላከያ የጥንቃቄ መርሆዎች የቱን ያህል ቀላል እንደሆኑ መገመት አይከብድም ። እየሄድንበት ያለው የግዴለሽነት መንገድ የት ሊያደርሰን እንደሚችል አሁን ላይ ቆሞ መገመት ተገቢ ነው።
ነገሮች ከብደው በትንሹ ለቀናት በቤት ውስጥ መዘጋት አስገዳጅ ቢሆን ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው። ክልከላው አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ምን ማለት እንደሆነ ፣ ሊያስከትል የሚችለው ሀገራዊ ምስቅልቅል ምን አይነት ምስል እንደሚኖረው ለአፍታ ማሰብ በራሱ በቂ ነው ።
የነገውን ረጅሙን ዘመናችንን ተስፋ እያደረግን የመጣን ከመሆናችን አንጻር ነጋችን ላይ ያለው ተስፋችን እንዳይጠፋ ዛሬን በአግባቡ በኃላፊነት መንፈስ ልንኖርበት ይገባል ። ከነገ ጋር በሚታይ የተስፋ ክር ለተሳሰረው ትውልድም ሆነ ለራሳችን ለሌላውም ተስፋ ህያውነት በአግባቡ ማሰብና መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል ። ይህ ዛሬ በራሱ ከእኛ የሚጠብቀው ትልቁ አሻጋሪ እውነታ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም