ዘካርያስ ዶቢ
ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ምግብ ነው፤ ከምግብ ዓይነቶች አንዱ የሆነው ዳቦ ደግሞ የማይገባበት ቤት የለም። አመጋገባቸው ከዳቦ ጋር በእጅጉ በተቆራኘ ሀገሮች ዳቦ ትርጉሙ ሰፊ ነው። እኛ እንጀራና የመሳሰሉት ምግቦችን በስፋት ስለምንመገብ የዳቦ ጉዳይ በሌሎች ሀገሮች የሚነሳውን ያህል ሲነሳ አይስተዋልም። በሌሎች ሀገሮች ዳቦ ሲጠፋ ሀገር በአንድ እግሯ ልትቆም ትችላለች።
ዳቦ ብዙ መገለጫዎች አሉት። የራሱ ይዘትና ቅርጽም አለው። ዳቦ ሲባል እኔ የሚታሰበኝ ፋፋና ቅንብር ብሎ የሚታይ፣ ብሉኝ ብሉኝ የሚል፣ ትኩስ በሆነ ጊዜ መአዛው ከሩቅ የሚጣራ፣ ሲበሉትም ከአንጀት ጠብ የሚል ነው።
ዳቦ ልብ (ቡጥ) አለው። የቀደመው ዳቦ እንደዚህ ዘመኑ ዳቦ ቅርፊት ብቻ አይደለም። በሀገራችን ዳቦ እና ልብ ከተፋቱ ቆዩ። ያን ልባም ዳቦ የተመለከቱ የያኔዎቹ ሰዎች ዳቦና ልቡ ሰምና ወርቅ በነበሩበት ወቅት ዳቦ ሌሎች ጉዳዮችንም እንዲገልጽላቸው ያደርጉ ነበር፤ እየተቀባበልነው እዚህ የደረሰው ‹‹በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት›› የሚለውም ለእዚህ ምሳሌ ይሆናል። ልጆቻችን ይህ አባባል ምን እንደሆነ ቢጠይቁን ዳቦው ልብ ባጣበት በዚህ ዘመን እንዴት አድርገን እናስረዳቸው ይሆን?
ዳቦ የወፍራም ነገር መለኪያ ነው። ጥሩ እርጎም ዳቦ ተብሎ ይገለጻል። እስቲ ማግ አድርጋችሁ አስቡት፤ የማትጾሙትን ማለቴ ነው። አፍ ይሞላል፤ በጉሮሮም ሲወርድ የሆነ የእርካታ ስሜት ይፈጥራል። አንጀት ሲያርስም እንደዚያው ነው። የከተማውን እርጎ ተብዬ ማለቴ አይደለም። እንጀራ በጣም ሲወፍር ዳቦ ሆነ ይባላል። ያ የዳቦ ውፍረት በሌለበት በዚህ ዘመንስ በምን እናነጽር?
እንዲህ የነገር ማንጸሪያ ሆኖ የኖረውን ዳቦ የሚመስል ዳቦ በሀገራችን በተለይ በአዲስ አበባ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። የዳቦ ግራም እና ይዘት ጉዳይ በእጅጉ ጥያቄ ውስጥ ናቸው። ይህ ግን የቅርብ ጊዜ ጉዳይ ብቻም አይደለም። የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ነውና ዳቦ ሲጠፋ፣ ሲሳሳ፣ ወዘተ ለምን ሲባል ኖሯል፤ እየተባለም ነው፤ የዚህ ዘመኑ ግን ከፋ ብሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የስንዴ አቅርቦት እጥረት ታይቷል። እርግጥ ነው ችግሩ የዳቦ ዱቄት ማግኘቱን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል። በቅርቡ የዳቦ እጥረትን እንደሚፈታ ታምኖበት ወደ ሥራ የገባው ግዙፉ የሸገር ዳቦ ፋብሪካም ከተቸገረባቸው ምክንያቶች አንዱ የስንዴ አቅርቦት አለመኖር ነው፤ በዚህ የተነሳም የሚፈለገውን ያህል ዳቦ እያቀረበ አልነበረም፤ የቅርቡን እንጃ። ፋብሪካው ዳቦ በሚፈለገው ልክ ለማቅረብ ከመቸገሩም በላይ በተጠቀሱት ችግሮች ሳቢያ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል። በእዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ታዲያ የታሰበውን ያህል ባይሆንም ዳቦ አያቀረበ ነው። እናመሰግናለን።
የግል ዳቦ ጋጋሪዎችም በዱቅት አቅርቦት እጥረት የተነሳ የሚፈለገውን ያህል ዳቦ እያቀረቡ አይደሉም። መጋገር ያቆሙም አይጠፉም። እያቀረቡ ያሉትም ቢሆኑ ዳቧቸው ከሚጠበቀው ግራም በታች የወረደ፣ ልብ ያልተፈጠረበት፣ ሲያዩት ቢያስጎመዥም፣ ገና ሲቆርሱት ቅርፊቱ የሚበታተን ሆኗል። ለቤት አጽጂዎች ሌላ ሥራ! ጫን ሲሉት ቺፕስ ሆኖ ያርፈዋል።
በቅርቡ ከሥራ ስመለስ በዚያ ሰዓት ዳቦ ከሚኖርበትና አልፎ አልፎ ከምገዛበት ቤት ስምንት ዳቦ አዝዤ 50 ብር ሰጥቼ መልስ መጠበቅ ያዝኩ። 18 ብር ተመለሰለኝ። መልሱ ትክክል ነው? አንዱ ዳቦ ስንት ነው ስል አከታትዬ ጠየቅሁ። አራት ብር ነው፤ ጨምሯል ተባልኩ። ይህን ዳቦ በቅርቡ ብቻ ሦስት ብር ገዝቼዋለሁ። ከዚያ ባነሰም የገዛሁበት ወቅት አለ። ዳቦውን ይዤ ስሄድ እውነቴን ነው የምላችሁ ዳቦ ሳይሆን ፌስታል ብቻ የያዝኩ ነው የመሰለኝ።
ሳንድዊች ነገር ተሰራና መብላት ጀመርን፤ እንደ ደጉ ቀን ዳቦ በሁለት እጄ ይዤ ጫን ስለው ቺፕስ (የድንቹን) የሆነ መሰለኝ። አሁን ይህን አንድ ዳቦ ለልጆች ሰጥቶ ቁርስ በሉ ማለት ይቻል ይሆን? አንድ ልጅ አስሩን ዳቦ ቢበላ ዓይን ይገባስ ይሆን? ስል አሰብኩ።
ነጋዴዎቹ ዱቄት ላያገኙ፤ ቤት ዘግቶ ከመቀመጥ በሚል በውድ ገዝተው ሊጋግሩ ይችላሉ። ኪሳራቸውን እና ትርፋቸውን ታዲያ ግራም በመቀነስ ላይ ከሚያሰሉ ለምን ዋጋ ላይ አያደርጉትም፤ ስል አሰብኩ። ለነገሩ እሱንም በአናት በአናቱ እያደረጉ አይደል፤ ከግራም መቀሸብ ፊትም ርስት ነበረች፤ አሁንም ቀጥላለች። እኔ ግራሙ ተጠብቆ ዋጋ ቢጨመር ይሻለኛል፤ በዱሮ እያሰብን አንድ ዳቦ ለአንድ ልጅ ብንሰጥ አይሆንም።
የግራሙን ነገር ሳስብ በቅርቡ የሃያ ብር ዳቦ ከሸገር ገዝቼ ስመለስ ያ በ32 ብር የገዛሁት ዳቦ ታወሰኝ። ክብደታቸው የሰማይና የምድር ያህል ነው። በ20 ብር የተገዛው ዳቦ በክብደት የ32ቱን ብር በሚገርም ሁኔታ ያጥፈዋል።
የሸገር ዳቦ ሲታይ ትንሽ ነው። ክብደቱ ግን ደረጃውን የጠበቀ ይመስለኛል። ሲበሉትም አንጀት ጠብ ይላል። ከሌሎች ዳቦ ቤቶች የሚገዛው ደግሞ ዳቦው ሲያዩት ያምራል፤ ያ የሚታሰበውን ዳቦ ይመስላል፤ ተነፍቶ፤ ተነፍቶ፤ ባሉን ምስጋን ይጣ! ሸገር ዳቦ ግን ግራሙ ላይ ችግር የለብኝም። ዳቦ እንዲመስል ግን ትንሽ ብድግ እንዲል ቢደረግ ጥሩ ነው። እኔ ግራሙ ብቻ ዳቦውን ዳቦ አያሰኘውም፤ ሲታይም ያ የምናውቀው ዳቦ መሆን አለበት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሸገር ስንዴ ለማቅረብ የገባው ስምምነት ቶሎ መሬት ወርዶ ኅብረተሰቡ እንደልብ ዳቦ ማግኘት ይኖርበታል። እየተገነባ ነው የሚባለው ሌላ የዳቦ ፋብሪካም ቶሎ ተጠናቆ ሥራ እንዲጀምር ማድረግ፣ ሸገር የገጠመው ዓይነት ችግር እንዳይገጥመው ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል።
ከሸገር ውጪ ያላችሁ ዳቦ አቅራቢዎች በዚህ ችግር ወቅት ዳቦ ማቃመሳችሁ መልካም ነው። ይህ ችግር በዚሁ አይቀጥልም። ነገሮች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ይመለሳሉ፤ ቢያንስ መሻሻል ይመጣል፤ ያኔ እናንተም በዳቦ ዋጋ ላይ ያደረጋችሁትን ጭማሪ ወደ ቀድሞ ቦታው መመለስ ይኖርባችኋል። የግራም ቅሸባውም መቆም አለበት። ስታንዳርዱ መጠበቅ አለበት።
ይህን ሁሉ ያነሳሁት መንግሥትና ዳቦ ጋጋሪዎች ዳቧችንን እንደ ስሙ ዳቦ እንዲያደርጉልን ነው። ጉዳዩ በእነሱ እጅ ነዋ። ዳቦን አንደ ልብ እንድናገኘው ሊደረግም ይገባል፤ እንደ ሀገር ለዜጎች ዳቦ እንደልብ ማቅረብ ማለት ከዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት አንዱን መመለስ ነው ።
ዳቦው እንደስሙ ዳቦ ይሁንልን። እያነጋገረ ያለው የዳቦ ግራም ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት አለበት። ቢያንስ በተቀመጠለት ግራም መሠረት ይቅረብልን፤ ሲሆን ሲሆን ደግሞ ዳቦው ከአንጀት ጠብ የሚል እንዲሆን ግራሙ ቢጨመር መልካም ነው አላለሁ። በግራሙ መሠረት እየተመረተ ስለመሆኑም ክትትል ይደረግበት፤ ክትትል እየተደረገ ነው የሚያሰኝ ሁኔታ የለም። ዳቦው ከባዶነት ይውጣ! አንደስሙ ዳቦ ይሁን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013