መልካምስራ አፈወርቅ
ዘመዳሞቹ ተደውሎ በተነገራቸው ክፉ ዜና ሲጨነቁ ውለዋል። ሁሉም ጥልቅ ኀዘን ገብቷቸዋል። አገር ቤት ያለችውን የአጎታቸውን ልጅ ሞት የሰሙት በከባድ ድንጋጤ ነው። እነሱ ከቤተሰብ ርቀው አዲስ አበባ ይኖራሉ። እንጀራ ፍለጋ ያመጣቸው እግር ሁሉንም ሲያሮጥ፣ ሲያባክናቸው ይውላል።
የስልክ መርዶውን የሰሙ ላልሰሙት እያዳረሱ ነው። ዘመድ አዝማዱ ፣ ማልዶ ለቀብር ሊደርስ መሰባሰብ ይዟል። ኮንትራት መኪና የሚይዙ ፣ በትራንስፖርት የሚጓዙ ቀድመው ተዘጋጅተዋል።
አንዳንዶች ስልክ እየደወሉ ኀዘንተኞችን ያጽናናሉ፣ ሌሎች ይበጃል ባሉት ይመክራሉ፣ ያወራሉ። ቀኑ ረፍዶ ያስረፈዳቸው ሰድስቱ ወጣቶች ነገውን በጠዋት ለመውጣት ቦታና ሰዓት መርጠዋል። ሁሉም በአጎታቸው ልጅ ሞት ሲያዝኑ ሲያለቅሱ አርፍደዋል።
በአንድ ቤት አድረው ሰብሰብ ብለው ለመውጣት የአንድ ዘመዳቸው ቤት ምርጫቸው ሆኗል። ቤቱ ከሌሎቹ በተሻለ ለመንገድ ቅርብ ነውና ሁሉም መርጠውታል። አገራቸው ሲደርሱ ለኀዘንተኞች የሚያድርጉትን ለመምከር ጭምር መሰባሰባቸውን ወደውታል።
ከስድስቱ ዘመዳሞች ሁለቱ ሴቶች ናቸው። ሁለቱ ደግሞ እህትና ወንድም። የተቀሩትም በኀዘንና ደስታ ተለያይተው አያውቁም። ችግር ሲያጋጥም ይረዳዳሉ። አውደ ዓመት በደረሰ ጊዜ ተሰባስበው አገር ቤት ይሄዳሉ። አገራቸው ጉራጌ ዞን ‹‹እዣ›› ወረዳ ነው። ኑሯቸው አዲስ አበባ ቢሆንም ልባቸው ከትውልድ ቀያቸው ርቆ አያውቅም።
ዛሬም በአንድ ቤት ያሳደራቸው የአጎታቸው ልጅ ድንገቴ ሞት ነው። ሟችቷ ወጣትና እኩያቸው ነበረች። በመሞቷ ፣ ድንገት ከእነሱ በመነጠሏ ከልብ አዝነዋል። ዘመዳሞቹ ዘመዳቸው በተከራየው ቤት አድረው የከተማውን ከአገር ቤቱ ሲያነሱ ፣ሲያወጉ አምሽተዋል።
ሦስቱ – ባለጥቁር ጃኬቶች
ጎረምሶች ናቸው። እነሱን ማንም ኃይል የሚጥል፣ የሚበግር አይመስላቸውም። ከቀን ይልቅ የጨለማ መንገድ ይቀናቸዋል። ዓይናቸው ከአንድ አያርፍም። ከወዲያ ወዲያ ይቅበዘበዛል። እግራቸው ፈጣን ተራማጅ ነው። እጆቻቸው ከያዙ አይለቁም። ሁሌም ከሽንጣቸው የሚስጡት፣ የሚወሽቁት አያጡም። በጥቁር ጃኬትና ጥቁር መነጽራቸው ይለያሉ።
ጨለማውን፣ ስርጡን፣ ጫካና ጉድባውን እየመረጡ ዘረፋ ይፈጽማሉ። ዝናቡ፣ ሌትና አውሬው አያስፈራቸውም። የሰዎች ኮቴን እየፈለጉ አሳቻ ቦታን እየመረጡ ያደፍጣሉ። በእነሱ ወጥመድ ድንገት የሚገባ ቢኖር ያሻቸውን ሊያደርጉ ከልካይ የላቸውም።
ሦስቱ ሰዎች የቀን ውሏቸው በገንዘብ ክፍፍል ያልፋል። የለሊቱን ግዳይ እያስታወሱ፣ በቀጣይ ምሽት ስለሚደግሙት ዝርፊያ ያስባሉ። ጫት እየቃሙ፣ ሲጋራ እያቦነኑ አዲስ ዕቅድ ይነድፋሉ። የሚሄዱበትን፣ የሚያደፍጡበትን ይለያሉ። የጎናቸውን ስለት፣ የሽንጣቸውን ሽጉጥ እየነኩ ለድርጊቱ የሚመጥን፣ ለዝርፊያው የሚያመች ጊዜና ቦታ ይመርጣሉ።
ባለጃኬቶቹ ለደፈጣቸው የእጅ ባትሪ አያጡም። ባትሪው አንዳንዴ ለጨለማው ብርሃን ይሆናል። ዋንኛው ሥራ ግን በሚያዙ ሰዎች ዓይን ኃይለኛ ጨረር መርጨት ነው። እንዲህ በሆነ ጊዜ መንገደኞች እነሱን ፈጥነው አይለዩም። ተደናግጠው፣ ተብረክርከው ያላቸውን ይሰጣሉ።
አንዳንዴ የጨለማው ባለጃኬቶች ዘርፈው፣ ነጥቀው ብቻ አይተውም። የእጃቸውን ለመስጠት ባልፈቀዱ መንገደኞች ላይ ኃይል ይጠቀማሉ። መልክ ቁመናቸው እንደታወቀ ከጠረጥሩ ጭካኔያቸው ከዚህ ያልፋል። በጩቤና በቢላዋ አካል ይወጋሉ ፤ ይሸረክታሉ። በትላልቅ ድንጋይ ጭንቅላት ይመታሉ፣ ይፈረክሳሉ።
ዘመዳሞቹ…
ምሽቱን ለአዳር የተገናኙት ዘመዳሞች ራት በልተው ቡና ጠጥተው ጎናቸውን አሳርፈዋል። ለጉዞ የተዘጋጁ ሻንጣዎች በልብስና ዕቃዎች ታጭቀዋል። መንገደኞቹ ማልደው ከአውቶቡስ ተራ ለመድረስ ለሊቱ ሳይነጋ መውጣት አለባቸው። ከኀዘኑ ለመታደም የዝምድናው ቅርበት ግድ ብሏቸው እየተጨነቁ ነው። ሁሉም የሞባይል ሰዓታቸውን እያዩ የሰዓቱን መድረስ ይጠብቃሉ።
ለሊቱ ተጋምሷል። በአብዛኞቹ ዓይን የረባ ዕንቅልፍ ይሉት የለም። በግማሽ ልብ ያሸለቡት መንገደኞች አሁንም ጉዟቸውን እያሰቡ ነው። ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ሲሆን ሁሉም ከተጋደሙበት ተነስተው መለባበስ ያዙ። ገሚሶቹ እየታጠቡ ገሚሶቹ ሻንጣዎቹን አዘጋጁ። ሁሉም በዚህ ሰዓት ከቤት መውጣት እንዳለባቸው ተስማምተዋል።
ሩብ ጉዳይ ለአስር ማለት ሲጀምር ስድስቱ ዘመዳሞች የቤቱን በር ዘግተው የግቢውን አጥር አልፈው ወጡ። ሁለቱን ሴቶች ከፊት አስቀድመው መንገዱን ሲጀምሩ ደጅ ያለው ቅዝቃዜ ፈጥኖ ተቀበላቸው። የህዳር ወር ብርድ ከለሊቱ አብሮ ብርታት አግኝቷል። ጨለማው አሁንም ገና ድቅድቅ ነው። በወጉ አልገፈፈም።
ጭር ባለው ለሊት ከውሾች ጩኸት በቀር ጎልቶ የሚሰማ የለም። በመንገዱ መንገደኞች የሉም። የሰፈሩ ትላልቅ ቤቶች በብረት መዝጊያዎቻቸው ጠብቀው ተከርችመዋል። ስድስቱ ተጓዦች ሻንጣዎቻቸውን አዝለው መንገድ ጀምረዋል። ጥቂት ተጉዘው አስፓልት እስኪደርሱ የመንደሩን መታጠፊያዎችና የጸበሉን መውረጃ ማለፍ አለባቸው። የለሊቱ ግርማ ያስፈራል። አካባቢውን በጨለማ ማቋረጥ ይከብዳል።
ስድስቱ መንገደኞች ይህ ሁሉ ያሰጋቸው አይመስልም። ከቤታቸው እምብዛም ባይርቁም ፍርሐት አልያዛቸውም። እያወጉ፣ እየተያዩ መንገዳቸውን ቀጥለዋል። ጸበል መውረጃው ዘንድ ሲደርሱ አንዳች ኮሽታ የሰሙ መሰላቸው። ሁሉም ለአፍታ ቆም ብለው አደመጡ። አልተሳሳቱም። ድምፅ በሰሙበት አቅጣጫ ሦስት ሰዎች ወደእነሱ እየቀረቡ ነው።
መንገደኞቹ ከሰዎቹ ተፋጠጡ። ሦስቱም ጥቁር አንድ ዓይነት ጃኬት ለብሰዋል። ከመሀላቸው አንደኛው በቁመቱ ረጅምና ግዙፍ ነው። ሁሉም ሰዎቹን ባዩ ጊዜ ደነገጡ። በዚህ ውድቅት በዚህ ስፍራ የመኖራቸው ጉዳይ አሳሰባቸው። ከሃሳባቸው ሳይመለሱ አጠር ያለው ባለጃኬት ጀርባውን እየነካካ ቀረባቸውና እንዲቆሙ አስገደዳቸው። አስከትሎም ሁሉም በያለቡት እንዲንበረከኩ ትዕዛዝ ሰጠ። ይህን የሰሙት ወንዶቹ በአንድ ድምፅ ‹‹አንንበረከክም›› ሲሉ መለሱ።
ውዝግቡ ቀጠለ። ባለጃኬቶቹ በኃይል ማስገደድ ጀመሩ። ሁለቱ ሴቶች ብርክ ያዛቸው። እየተንቀጠቀጡ፣ እያለቀሱ ሊለምኗቸው ሞከሩ። ባለጃኬቶቹ ሌላ ትዕዛዝ ቀጠሉ። ከየትኛው ቤት እንደወጡ ጠይቀው ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እንዲያሳዩ እያመናጨቁ አዘዙ። ይሄኔ ሴቶቹ አከራዮቹን ሊቀሰቅሱ ወደኋላ ተመለሱ።
ይህን ያስተዋለው ሦስተኛው ሰው ሴቶቹን ሊመለስ ተከተላቸው። ወዳሰቡት ሳይደርሱም መንገዱን ዘግቶ መለሳቸው። ይሄኔ ከመንገደኞቹ አንደኛው ጎንበስ ብሎ ድንጋይ አነሳ። በሰዎቹ ድርጊት በእጅጉ ተናዷል፤ የሚያድርጉት እያበሸቀው በእልህ መናጥ ጀምሯል።
አብረው ያሉት ዘመዶቹ ዘመዳቸውን በድንጋጤ አስተዋሉት። ያነሳውን ድንጋይ ከመሬት አልመለሰውም። እያከታተለ ወደሰዎቹ ወረወረ። በዚህ መሀል ሴቶቹ እየሮጡ ሄዱ። በዚህ መሀል አስቀድሞ ጀርባውን ሲነካካ የነበረው በለጃኬት እጁን ሰዶ ሽጉጥ አወጣ። ከመንገደኞቹ ሁለቱ ወንዶች ሽጉጡን ሲያዩ ደነገጡ። እየቀረቡ ሊለምኗቸው ሲሞክሩ ባለ ደማቅ ጨረር የእጅ ባትሪያቸውን ከዓይናቸው አብርተው ግራ አጋቧቸው። አሁን ድንጋጤና እልህ የያዛቸው ቡድኖች ተፋጠዋል። ጊዜው እየገፋ ነው። የለሊቱ ተጓዦች ካሰቡት እንደማይደርሱ አውቀዋል።
ሴቶቹ አከራዮቹን ሊጠሩ እንደሄዱ አልተመለሱም። ባለሽጉጥና ባለድንጋዮቹ አሁንም እንደተፋጠጡ ቆመዋል። ከመንገደኞቹ አንደኛው እንደ ዘመዶቹ ልቡ አልደነገጠም። ሰዎቹ አደገኛ ማጅራት መቺዎች መሆናቸውን አውቋል። የያዙት ሽጉጥ ግን አርተፊሻል እንደሆነ ጠርጥሯል።
ባለሽጉጡ በእጁ ያለውን እንዳጠበቀ ወደ ወንዶቹ ተጠጋ። ወጣቱ ባየው ነገር አልደነገጠም። በእጁ ያለው ሽጉጥ አርተፊሻል እንደሆነና በድርጊቱ እንደማይደነግጥ ለሰውዬው ደጋግሞ አስረዳው።
ባለጥቁር ጃኬቱ ዞር ብሎ ባልንጀሮቹን አስተዋለ። ልጁ የተናገረው ሐሰት መሆኑን በድርጊት እንዲያሳይ የጠቀሱት መሰለው። ከፊታቸው የይሁንታ ማረጋገጫ እንዳየ ተረዳ። ሽጉጡን እንዳጠበቀ ወደ ወጣቶቹ ቀረበ። አስቀድሞ የሞገተውን ልጅ ነጥሎ አስተዋለው። የውስጡ ስሜት አልተቀየረም። ባለጃኬቱ ጊዜ አላባከነም። በእጁ ያለውን የሽጉጥ ቃታ አነጣጥሮ ሳበው። ሁለት ጥይቶች በወጣቱ አካል ተመሰጉ። ወዲያው ኃይለኛ ድምፅ በአካባቢው ተናወጠ። ባለቃታው እጁን አልመለሰም። አፈሙዙን ከወጣቱ ደረት እንደደገነ ነው።
አሁን ወጣቱ በጥይት ደረቱን ተመቶ ከመሬት ወድቋል። ዘመዶቹ ያዩትን አላመኑም። የሆነው ሁሉ ህልም ቢመስላቸው ለመጮህ፣ ለመሮጥ ሞከሩ። ተኳሹ የበቃው አይመስልም። ግዳዩን አዘቅዝቆ እያየ ወደ እግሮቹ አነጣጠረ። አሁንም ሁለት ጥይቶች ከግራ እግሩ አረፉ። የለሊቱ ዝምታ ዳግም ተናወጠ። አየሩ በሚሰነፍጥ የጥይት ባሩድ ተሞላ።
አከራዮቻቸውን ለመጥራት ወደቤት የሄዱት ሁለት ሴቶች ወደስፍራው ሲመለሱ ዘመዳቸው በጀርባው ተዘርሮ በአፉ ደም እየተፋ ነበር። ከወንዶቹ መሀል አንደኛው በእጁ ድንጋይ ይዞ ሾስቱን ሰዎች ያባርራል። የተቀሩት እጃቸውን ከራሳቸው ጭነው ይጮሀሉ። ባለ ድንጋዩ ወጣት ባለሽጉጡን ከኋላ እያሳደደ የያዘውን ወረወረ። ጀርባውን አላጣውም። ሦስቱም ፊትና ኋላ ሆነው በጨለማው ተሰወሩ። ዘመዳሞቹ እየጮሁ የወደቀውን ወጣት ለማንሳት ተጣደፉ። የጨለማው ጭርታ በለቅሶና ጨኸት ደፈረሰ። በስሱ ትንፋሹ የሚሰማው መንገደኛ ዓይኑን እያንከራተተ ተማጸናቸው።
በደም የተነከረውን ወጣት ተሸክመው ሆስ ፒታል ያደረሱት ዘመዳሞች በሀኪሞች ከተዘጋው በር ጀርባ የመትረፉን ተስፋ ጠበቁ። ከኮሪደሩ እየተቁነጠነጡ፣ በዕንባ የሚራጩት ወጣቶች መልካም ዜና አልደረሳቸውም። ከደቂቃዎች በኋላ የቁስለኛ ዘመዳቸውን ህይወት ማለፍ ተረዱ።
የፖሊስ ምርመራ
ህዳር 4 ቀን 2011 ዓ.ም የወንጀሉ መፈጸም ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ ከስፍራው ተገኝቶ መረጃዎችን ሰበሰበ። በዕለቱ የነበሩትን እማኞች ጠርቶም ቃላቸውን ተቀበለ። ዘመዳሞቹ የሆነውን ለማስረዳት የሚያስታውሱትን ተናገሩ። የባለጃኬቶቹን መልክና ቁመና፣ ድምፅና ድርጊት ሳይቀር አንድ በአንድ አስረዱ።
ፖሊስ የተደጋጋሚ ወንጀለኞችን መዝገብ አውጥቶ ከተርጣሪዎች ጋር አመሳከረ። ምስክሮቹን አስቀርቦም ፎቶግራፎችን አሳየ። ምክትል ሳጂን ደጉ ዓለም አብዬ በየቀኑ የሚያገኘውን መረጃ በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 604/ 11 ላይ እየመዘገበ ምርመራውን ቀጠለ።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ የተደራጀው የፖሊስ ኃይል ይገኙባቸዋል የተባሉ ስፍራዎችን እያሰሰ መረጃዎችን ሲሰበስብ ቆየ። ተጠርጣሪዎች በተያዙ ጊዜ ምስክሮች በአካል እየተገኙ እንዲለዩ ሲደረግ ቆየ። ለጊዜው የተጨበጠ ውጤት አልተገኘም።
የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመ ሦስት ወራት በኋላ ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ከአንድ ፖሊስ ጣቢያ ተገኘ። በዕለቱ የደረሰው መረጃ እስከአሁን ሲመረምረው ለቆየው ወንጀል አመላካች ሆኖ አግኝቶታል። በጣቢያው ከታሰሩ ተጠርጣሪዎች መሀል የአንደኛው መልክና ቁመና ቢያጠራጥረው ምስክሮችን አስጠራ።
ምስክሮቹ በርከት ካሉ ተጠርጣሪዎች መሀል ድርጊቱን ፈጽሟል የሚሉትን ሰው በመልክ ለይተው እንዲያወጡ ተደረገ። ምስክሮቹ ከሚያዩዋቸው እስረኞች መሀል በአንደኛው ላይ አተኮሩ። እጃቸውን አርዝመውም የወንጀሉ ፈጻሚ ራሱ እንደሆነ አረጋገጡ።
በሁሉም ምስክሮች እይታ ማረጋገጫ ያገኘው ፖሊስ ተጠርጣሪውን አስቀርቦ ጠየቀ። በስም ደበበ ደጉ ሲል ያስመዘገበው ተጠርጣሪ ፈጽሞ ድርጊቱን እንዳልፈጸመው ተናገረ። ፖሊስ አላመነውም። እየደጋገመ ስለድርጊቱ ጠየቀው። አሁንም ተጠያቂው ‹‹ማንንም አልገደልኩም›› ሲል ደመደመ። ፖሊስ በምርመራው የእሱን ጨምሮ ያልተያዙ ግብረአበሮቹን የኋላ ታሪክ ደረሰበት።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በውንብድና ወንጀልና በጦር መሳሪያ ዘረፋ ተጠርጥሮ ምርመራ ሲጣራበት ነበር። ሌሎች በስሙ የተከፈቱ መዝገቦችም የድርጊቱን አደገኝነት የሚያስረዱ ናቸው።
ፖሊስ ወንጀሉ የተፈጸመበትን የመሳሪያ ዓይነት መረመረ። 3ኛ ደረጃ መትረየስ የሚባል ስታተር ሽጉጥ ነው። የውግ ቁጥሩ 103938 በሚል መለያ ተመዝግቧል። የምርመራ መዝገቡ እንዳበቃ ፖሊስ በበቂ መረጃና ማስረጃዎች ያጠናከረውን ሰነድ ዓቃቤህግ ክስ ይመሰረትበት ዘንድ አስተላለፈ።
ውሳኔ
የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድቤቱ ግለሰቡ የፈጸመው ወንጀል በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች በመረጋገጡ ጥፋተኛ ስለመሆኑ ጠቅሶ እንዲከላከል ዕድል ሰጥቷል።
ተከሳሹ የመከላከያ ምስክሮችን አላቀረበም። ወንጀሉን እንዳልፈጸመ የሚያስረዳ አዎንታም አላሳየም። ፍርድቤቱ በማስረጃ ተደግፈው የቀረቡ ሰነዶችን በማጣራት ውሳኔውን አሳለፈ። ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የአስራሦስት ዓመት ጽኑ አስራት ‹‹ይቀጣልኝ›› ሲል ብይን ሰጠ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013