አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን ከመመሪያና ከጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚያነሱት የመልካም አስተዳደር ችግር እየተፈታ አለመሆኑን ተና ገሩ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ችግሩን የሚፈታ ጥናት አድርጎ በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባ አመልክቷል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና መምህራን ማህበር በጋራ ትናንት በአዘጋጁት የውይይት መድረክ መምህራን እንደገለጹት፤ ከመመሪያና ከጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚያነ ሷቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻቸው እየተመለሱላቸው አይደለም፡፡ የከተማ አስተዳ ደሩ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የመምህራኑን ጥያ ቄዎች ለመመለስ በጥናት ተደግፎ ወደሥራ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
መምህራኑ በውይይቱ ወቅት፣ ከርዕሳነ መምህራን ምደባ ጋር በተያያዘ፣ የአካል ጉዳተኞችን የሚደግፉ ቅጥር በተመለከተ እንዲሁም ከክልል መጥተው አዲስ አበባ ሲቀጠሩ የሥራ ልምዳቸው እንዳይያዝ የሚያደርገው መመሪያ በመምህራኑ ላይ እክል የፈጠሩና የመልካም አስተዳደር ችግር ከሆኑባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም፣ ለመምህራን መኖሪያ ቤት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መሰጠት እንዳለበት አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ታቦር ገብረመድህን በበኩላቸው እንዳሉት፤ በውይይቱ ወቅት የተነሱት ጥያቄዎች አግባብነት አላቸው። የርዕሳነ መምህራን ምደባን በተመለከተ፣ ለአካል ጉዳተኞች ረዳት መቅጠር እንዲሁም ከክልል መጥተው ሲቀጠሩ በዜሮ ልምድ የሚለው አሠራር ጥናት ተደርጎበት በቅርቡ ይፈታል፡፡
ዶክተር ታቦር፣ ለመምህራን ቤት ለመስጠት የተጀመሩት ሥራዎች እንደሚቀጥሉና በቀጣይም አስተዳደሩ ሲወስን ቤቶች እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል፡፡ ቤት ኖሯቸው ቤት የወሰዱ አስተማሪዎች ካሉም ጥቆማ ቢሰጥ የማጣራት ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል። በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ፖለቲካዊ መልክ ያላቸው ስብሰባዎች መከልከሉን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩም የመምህራኑን ጥያቄ ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ አመልክተዋል። ሆኖም መምህራን ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተግተው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት4
መርድ ክፍሉ