አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ ህብረት መስራች ለሆኑት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ የተሠራው ሐውልት ተመረቀ። ሐውልቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ወጪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ-ፈለገ ሰላም የስነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተዘጋጀ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህመትና የጋናው ፕሬዚዳንት ናና አዶ አኩፎ ሐውልቱን ትናንት መርቀዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችና ታዳሚዎችም በምርቃቱ ላይ ተገኝተዋል።
አጼ ኃይለሥላሴ የመታሰቢያ ሐውልት የቆመላቸው ለአሁኑ የአፍረካ ህብረት ለቀድ ሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላበረ ከቱት ጉልህ አስተዋጽዖ መሆኑን ህብረቱ አስታ ውቋል። አጼ ኃይለሥላሴ ከ55 ዓመታት በፊት ካዛብላንካንና ሞኖሮቪያ በሚል ቡድን ለሁለት ተከፍላ የነበረችውን አህጉረ-አፍሪካ አንድ በማድረግ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት አድርገዋል።
እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም በኢትዮጵያ አዲስ አበባ መቀመጫውን እንዲያደርግ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ይታወቃሉ። በወቅቱም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ጋር በመሆንም ከ32 የአፍሪካ አንድነት መስራቾች መካከል የ28ቱን ድምፅ በማግኘት ሴኔጋል ዳካርን በማሸነፍ አዲስ አበባ መመረጧ ይታወሳል።
የአፍሪካ ህብረት መሪዎች እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2017 ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአሁኑ የአፍሪካ ህብረት መመስረት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወቃል።
ከትናንት በስቲያም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ መሪ ለነበሩት ቀደማዊ ኃይለሥላሴ ሐውልት እንዲቆምና እንዲታወሱ በማድረጉ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011ጌትነት ተስፋማርያም