አስናቀ ፀጋዬ
አብዛኛዎቹ ወጣቶች ገንዘብን በአቋራጭ ለማግኘትና በራሳቸው ሥራን ፈጥረው ከመንቀሳቀስ ይልቅ ተቀጥሮ በመስራት አባዜ በተለከፉበት በዚህ ዘመን ገና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ እያለ ሥራን በግሉ የመስራት ሃሳብ ነበር በውስጡ የጠነሰሰው ። ይህን ሃሳቡን እውን ለማድረግም ከጓደኛው ጋር በመሆን አነስተኛ የህትመትና ማስታወቂያ ስራ በመጀመር እንዴት በራስ ላብ ሰርቶ ማደር እንደሚቻል ተረድቷል::
ከልጅነቱ ጀምሮ በውስጡ ያደረው የዲጄነት ፍቅር አሸንፎትም ከጓደኛው ጋር የጀመረውን የህትመትና የማስታወቂያ ስራ እንዲያቋርጥ አስገድዶታል:: እንቅልፉን አጥቶ በተለያዩ የአዲስ አበባ የምሽት ክለቦች ውስጥ በመስራትም የዲጄነት ፍቅሩን አጣጥሟል:: በዲጄነት ለሁለት ዓመታት ያህል ከሰራ በኋላም አስቀድሞ ከጓደኛው ጋር ወደጀመረውና አባቱ በልጅነቱ ሲያወራ ወደሰማው የህትመትና ማስታወቂያ ስራ ተመልሷል::
የህትመትና የማስታወቂያ ሥራውን ከጀመረ ገና ጥቂት ዓመታት ቢሆነውም ደንበኛ በመያዝ ችሎታውና በሥራው ጥራት የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችሏል:: ገና ከጅምሩ አዳዲስና ጥራት ያላቸው የህትመትና ማስታወቂያ ሥራዎችን ይዞ ብቅ በማለት በቀጣይ በዘርፉ ውጤት ማምጣት እንደሚችልም አረጋግጧል- የበረከት ህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ወጣት በረከት ማሞ::
ወጣት በረከት ማሞ እድገትና ውልደቱ በአዲስ አበባ ከተማ ኮተቤ ልዩ ስሙ ዜሮ ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው:: የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ኤልቢቴል በሚባል የግል ትምህርት ቤት ተምሯል:: የአስራ አንደኛና አስራ ሁለተኛ ክፍል ኮሌጅ መሰናዶ ትምህርቱን ደግሞ የነገው ሰው በተባለ የግል ትምህርት ቤት ገብቶ ተከታትሏል:: የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተናውን በማለፉም በ2004 ዓ.ም በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተመድቦ ትምህርቱን ለአምስት ዓመታት ከተከታተለ በኋላ በኮምፒዩተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2008 ዓ.ም አግኝቷል::
ከልጅነቱ ጀምሮ ዲጄ የመሆን ህልም የነበረው ወጣት በረከት መጀመሪያ ከጓደኛው ጋር በመሆን ከቤተሰብ ባገኙት አነስተኛ የገንዘብ ድጋፍ በገዙት አንድ ፕሪንተር፣ ጠረጴዛና ወንበር አነስተኛ የህትመትና የማስታወቂያ ስራ በጓደኛው ቤት ውስጥ ጀመሩ:: በታክሲዎች ላይ የሚለጠፉ መንፈሳዊ መልዕክት ያላቸው የጥቅስ ስቲከሮችን ከጓደኛው ጋር ሰርቶ ለገበያ ማቅረብ ቻሉ:: በግዜው የእርሱም ሆነ የጓደኛው ዋነኛ ፍላጎት የህትመትና ማስታወቂያ ስራውን መስራት እንጂ ገንዘብ ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም:: በዚህም ሰዎች ሥራ ለማሰራት ወደ መሥሪያ ቤታቸው ሲመጡም ሁለቱም እጅግ ይደሰቱ ነበር:: በሂደትም ሌሎች ስቲከሮችንና ባነሮችን መስራት ቀጠሉ::
ጥቂት አብረው እንደሰሩ ወጣት በረከት ቀድሞውኑ ዲጄ የመሆን ፍላጎት በውስጥ በመኖሩ የዲጄነት ፍቅሩ አሸንፎት የጀመረውን ስራ አቋርጦ በምሽት ክበቦች ውስጥ ሥራ ጀመረ:: ለሁለት ዓመታት ያህል አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የምሽት ክበቦች ውስጥ በመስራትም የዲጄነት ፍቅሩን አጣጣመ:: ግማሽ ልቡ ወደ ህትመትና ማስታወቂያ ስራው የነበረ በመሆኑም ከዲጄነቱ ጎን ለጎን ቀደም ሲል ያውቃቸው በነበሩ ደንበኞቹ አማካኝነት ሲሰራ ቆየ::
የኮሮና ወረርሽኝ ሀገሪቷ ላይ ሲከሰት ወጣት በረከት የዲጄነት ሥራውን አቁሞ ፊቱን ሙሉ በሙሉ ቀድሞ ወደጀመረው የህትመትና ማስታወቂያ ሥራ አዞረ:: ወደዚህ የህትመትና የማስታወቂያ ሥራ ዳግም ለመመለስ የተገፋፋውም ቀደም ሲል አባቱ ከዚሁ ሥራ ጋር በተገናኘ የሚያወሩትን በመስማት እንደነበር ይናገራል። በዚህ ወቅት ጓደኛው በሌላ የሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ የነበረ በመሆኑ በጥቂት ካፒታል የንግድ ፍቃድ በማውጣት ‹‹በረከት የህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት›› በሚል ስያሜ ሥራውን በራሱ ዳግም ጀመረ::
ወደህትመትና ማስታወቂያ ሥራው ከተመለሰ በኋላም ከዚህ ቀደም ኮሚሽን በመቀበል አየር ባየር ሲያንቀሳቅሰው የነበረውን ሥራ በመተው የራሱን ቢሮ ኮተቤ አካባቢ ከፍቶ መስራቱን ቀጠለ:: አንዳንድ የህትመት ማሽኖችን በማስገባትም አብዛኛዎቹን የህትመትና የማስታወቂያ ስራዎች በራሱ መስራት ቻለ:: ከደንበኞች ተቀብሎ የሚያስተናግደው የህትመትና የማስታወቂያ ሥራዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጡ::
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ድርጅቱ አብዛኛዎቹን የማስታወቂያና የህትመት ሥራዎችን ሀያ አራት ሰዓት ሙሉ የሚያከናውን ሲሆን ከህትመት ሥራዎች ውስጥ በዋናነት የመጽሔት፣ ጋዜጣ፣ ደረሰኝ፣ መጥሪያ ካርድ፣ የቢዝነስና የእድር ካርድ፣ ሰርተፍኬት፣ ፎልደርና ስቲከሮችን ይሰራል:: ሜሽ፣ አስተላላፊ ማስታወቂያዎችን፣ የማይካ ሥራዎችን፣ የቲሸርት ህትመት፣ የካምፓኒ ፕሮፋይሎች ሥራዎችንም ያከናውናል::
ከነዚህ በተጨማሪም ፖስተር፣ ሎጎ ዲዛይን፣ የኮፍያና የሳህን ህትመት፣ በእስክርቢቶና ፍላሾች ላይ የማተም ስራ እንዲሁም ሌሎች የህትመት ስራዎችን ይሰራል:: ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ የማህተም ሥራን ጨምሮ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ፊቱን በማዞር የዌብ ሳይት፣ ሶፍትዌር፣ የሞባይል መተግበሪያዎችን እንዲሁም የዲጄ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል:: የመኪና ላይ ማስታወቂያ ሥራዎችንና የኮምፒዩተር ጥገናዎችንም ጎን ለጎን ያከናውናል::
ድርጅቱ የህትመት ስራዎቹን ለማከናወን የወረቀት ዲጂታል እና ሌሎች ማሽኖችን ይጠቀማል:: በአብዛኛው በደንበኞች ዘንድ ድርጅቱ እንዲሰራቸው የሚጠየቁ ስራዎችም የቢዝነስ ካርዶች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ ባነሮች፣ ስቲከሮች፣ ቲሸርቶችና የማህተም ስራዎች ናቸው:: እንደ ጥሬ እቃው አይነት፣ የሥራው ጥራትና እንደሚያሳትፈው የሰው ኃይል የህትመትና የማስታወቂያ ሥራ ዋጋ ይወሰናል::
በጥቂት የቤተሰብ ድጋፍ በእርሱና በጓደኛው ሥራውን የጀመረው ወጣት በረከት የህትመትና ማስታወቂያ ሥራ ድርጅት በአሁኑ ወቅት መነሻ ካፒታሉ ያሉትን የህትመት ማሽኖች ጨምሮ 500 ሺ ብር ደርሷል:: ድርጅቱ በሚሰራቸው ልዩ ልዩ የህትመትና የማስታወቂያ ሥራዎችም ከሃያ እስከ ሰላሳ የሚጠጉ ሰራተኞችን በማሳተፍ ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል::
በህትመትና የማስታወቂያ ስራ ዘርፍ ከተሰማራ ገና አራት አመት እንደሆነው የሚናገረው ወጣት በረከት፤ በዘርፉ ውጤታማ ሥራዎችን ለመስራትና ከጫፍ ለመድረስ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ይናገራል:: የህትመትና ማስታወቂያ ሥራውን ይበልጥ አስፍቶ የመስራት እቅድ እንዳለውና ይህንኑ እቅድም በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚለውጠው ያስረዳል:: ሁለት ቅርንጫፎችን በመክፈት የማስታወቂያና ህትመት ቢዝነሱን አስፍቶ መስራት እንደሚፈልግም ይገልፃል::
ወጣት በረከት በዚህ ቢዝነስ ገና ባልተሰራባቸው ስራዎች ውስጥ ገብቶ ለመስራት ተጨማሪ የህትመት ማሽኖችን በመጨመር አሁን እየሰራ ካለው በበለጠ አቅሙን አሳድጎ የህትመትና ማስታወቂያ ሥራውን የመስራት ውጥን እንዳለውም ያስረዳል፡፡ የህትመት ዘርፍ ገና ያልተሰራበት ከመሆኑ አኳያ አብዛኛውም በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ ላይ የተሰማራ በመሆኑ ከዚህ በተለየ መልኩ በህትመት ጥሬ እቃ አቅርቦት ስራ ላይ ገብቶ የመስራት አቅድ እንዳለውም ይጠቁማል፡፡ በዘርፉ ክፍተት የሚታይባቸው ቦታዎች ላይ በመግባት የመስራት ውጥን እንዳለውም ይጠቅሳል:: ቀደም ሲል ጀምሮት የነበረውን የድምፅና የምስል ማስታወቂያ ሥራም አጠናክሮ የማስቀጠል ፍላጎት እንዳለውም ይገልፃል::
የህትመትና የማስታወቂያ ስራ በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ እንደ አሸን በፈላበትና ከፍተኛ ፉክክርም በሚታይበት በዚህ ጊዜ ወጣት በረከት በሙያው ነጥሮ ለመውጣት በህትመትና ማስታወቂያ ስራ ዘርፍ የገቡና በመግባት ላይ ያሉትን እንደ አንድ የቢዝነስ እድል እንደሚቆጥራቸው ያብራራል:: እሱ ጋር የሌለውን እነርሱ ጋር በመሄድ እንደሚያሰራም እነሱ ጋር የሌሉ ስራዎች ካሉ ወደ እርሱ መጥተው እንዲሰሩ እንደሚጋብዝም ይጠቁማል::
ለዚህም ራሱን ለማስተዋወቅ የቢዝነስ ካርዶችን እንደሚበትንና በዚሁ ሥራ ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ የቢዝነስ ሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራል:: ይህም ለእርሱም ሆነ በዚሁ መሰል ቢዝነስ ውስጥ ለተሰማሩ ሰዎች እኩል የማደግ እድል እንደሚፈጥር ይጠቁማል::
በሌላ በኩል ደግሞ ጥራት ላይ ምንም አይነት ድርድር እንደማያውቅና ለሚያከናውናቸው እያንዳንዱ የህትመትና የማስታወቂያ ሥራዎች ለጥራት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይጠቅሳል::
ሥራዎቹን የሚያከናውነው በደንበኞች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ እንደሆነም ገልፆ፤ የህትመትና የማስታወቂያ ሥራዎቹን ለማስተዋወቅ ልዩ ልዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን እንደሚጠቀም ያስረዳል:: ዋነኛው ጉዳይ ደንበኞችን ወደ ስራ ቦታ ማምጣት ከመሆኑ አኳያም ለዚህ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ይጠቁማል::
‹‹በመንግስት ደረጃ ለህትመትና ማስታወቂያ ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው›› የሚለው ወጣት በረከት በተለይ ማስታወቂያ ሰሪዎችም ሆኑ አሰሪ አካላት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ማስታወቂያቸውን ሲለጥፉ በካሬ ለመንግስት የሚከፍሉት ግብር ከፍ ማለቱንና ይህም መስተካከል የሚገባው መሆኑን ይጠቁማል::
በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ ትላልቅ ነጋዴዎች ለህትመት ስራ የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችን የመያዝና ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ የሚያሳዩ በመሆናቸውና በዚሁ ምክንያት የህትመትና ማስታወቂያ ስራ ድርጅቶችም ዋጋ እየጨመሩ በመሆኑ ደንበኞች እየቀነሱ መሆናቸውንም ያመለክታል:: በዚህም ምክንያት ቢዝነሱ እየተጎዳ መምጣቱን ይጠቅሳል::
ከዚህ አኳያ የህትመትና ማስታወቂያ ስራ እንዲበረታታ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ይጠቁማል::በርካቶች በዚህ ዘርፍ ገብተው የመስራት ፍላጎት ያላቸው ከመሆኑ አኳያም ከመንግሥት በኩል የብድር አቅርቦት ሊመቻች እንደሚገባም ያመለክታል:: በዚህ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ያሉት በአብዛኛው ወጣቶች በመሆናቸው በተለይ ሰርተው ለመለወጥ እየተንደረደሩ ያሉትን ቢያንስ የሚሰሩባቸውን ማሽነሪዎች በመያዝ የብድር አቅርቦት ሊመቻችላቸው እንደሚገባም ይገልፃል:: የመንግሥት ተቋማትም በአካባቢያቸው ከሚገኙ የህትመትና ማስታወቂያ ድርጅቶች ጋር በመስራት እኩል ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸውም ይጠቅሳል::
‹‹በህትመትና የማስታወቂያ ሥራ ውጤት ለማምጣት ገና ብዙ ይቀረኛል›› የሚለው ወጣት በረከት፤ በቀጣይ በዘርፉ ቀሪ ሥራዎች ውስጥ ገብቶ በመስራት ውጤታማ ለመሆን ከወዲሁ እንደሚተጋ ይናገራል:: ውጤት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት መሰናክሎች ሊኖሩ እንደሚችሉና ከነዚሁ ውስጥ አንዱ ለሥራው በግብአትነት የሚጠቀምባቸውን ጥሬ እቃዎች ከውጪ ለማስመጣት የውጪ ምንዛሪ እጥረት ሊሆን እንደሚችልም ይጠቅሳል::
ይሁን እንጂ ውጤት ለማምጣት በሚያደርገው ትግል የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች እንደመልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀምባቸውና ከስህተቱ ተምሮ በህትመትና የማስታወቂያ ስራ ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ጠንክሮ እንደሚሰራ ይናገራል:: በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም በዚህ የህትመትና ማስታወቂያ ዘርፍ ገብተው መስራትና ውጤታማ መሆን ከፈለጉ በቅድሚያ ፍላጎቱና እውቀቱ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይጠቁማል:: ዘርፉ ሰፊ የገበያ እድል ያለው ከመሆኑ አኳያም ገብተው ቢሰሩበት ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበት እድል እንዳለም ይጠቅሳል::
በተለይ ሥራውን ለማወቅ ብዙም የማይቸግር ከመሆኑ አኳያ በቀላሉ ገብተው ሊሰሩበት እንደሚችሉና ነገር ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቢዝነሱ ጋር ግንኙነት ካላቸው ሰዎች ጋር ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈልጋቸው ይመክራል:: ገበያውን ማወቅና ከማን ጋር ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ማወቅ እንዳለባቸውም ይጠቅሳል:: ስላወቁ ብቻ ስራው በድፍረት ተገብቶ የሚሰራበት እንዳልሆነም ልብ ሊሉ ይገባል። ሥራቸውን በአግባቡ ከሰሩና ደንበኞቻቸውን በአግባቡ ከያዙ ገንዘቡን ኋላ ላይ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይጠቅሳል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013