መልካምስራ አፈወርቅ
ቅድመ -ታሪክ
ባልና ሚስት ለዓመታት በትዳር ዘልቀዋል:: በአብሮነታቸውም ልጆች ወልደው ሀብት ንብረት አፍርተዋል:: አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 የሚገኘው ቤት ለቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ሆኖ ቆይቷል::
የጥንዶቹ ሁለት መኪኖች የቤተሰቡ ተጨማሪ ሀብቶች ናቸው:: ለዓመታት ያሻቸውን ሲያሳፍሩባቸው ፣ የፈለጉትን ሲጭኑባቸው ቆይተዋል:: ባልና ሚስት በእነዚህ መኪኖች ልጆች ትምህርት ቤት አድርሰዋል:: ወዳጅ ዘመድ ሸኝተዋል፣ ከፈለጉበት በፍጥነት ደርሰው ተመልሰዋል::
ንብረቶቹ በአባወራው ስም የተመዘገቡ ናቸው:: ይሁን እንጂ ሚስትም በባለቤትነት በእኩል ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል:: ደስታና መከራን ተጋርተው ዓመታትን በዘለቁበት ትዳር ንብረቶቹ ለቤተሰቡ ህልውና አቅም ሆነው ዓመታትን አሻግረዋል::
አቶ ባህታ ትርፌና ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ተስፋጽዮን ዓመታትን በዘለቁበት ትዳር በንብረቶቻቸው እኩል ሲያዙና ሲጠቀሙ ቆይተዋል:: በቤቱ እየኖሩ በመኪኖች ለመገልገልም አንዳቸው የሌላቸውን ይሁንታ አይሹም:: ንብረቱ የጋራ ነው:: ከልካይና ለምን ባይ የለውም:: ይህ እንዲሆንም የትዳራቸው አብሮነት ግድ አድርጎታል::
የውጭ ጉዞ …
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጤንነት እየተሰማቸው አይደለም:: ለዚህ ችግራቸው እልባት ለመስጠትም የሀኪም ቤት ደጃፎችን ሲመላለሱባቸው ከርመዋል:: ያገኙት ውጤት እምብዛም ቢሆን ትካዜ ገብቷቸዋል:: ውሎ አድሮ ግን ከአንድ ውሳኔ ደርሰዋል:: ሀገር ውስጥ የጀመሩትን ህክምና ትተው በውጭ አገር ሊታከሙ::
ወይዘሮዋ ከጊዜያት በኋላ ውሳኔያቸው ዕውን ሆነ:: የውጭ አገር ህክምናው ተሳክቶ የጉዞ ሂደቱን ጀመሩ:: ደርሰው አስኪመጡ ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ ቆም ብለው አሰቡ:: አስኪመለሱ ንብረቶችን መልክ ማስያዝ አለባቸው:: ቤቱን መኪኖቹን ፣ ሌሎች ሀብቶችን ውክልና መስጠት ግድ ይላቸዋል::
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ከጉዟቸው ጎን ለጎን ንብረቶቹን ‹‹ይበጁኛል፣ ይታመኑኛል›› ላሏቸው ሴት በውክልና ሰጡ:: ውክልናው ህጋዊ መስመሩን ይዞ በአግባቡ ተከወነ:: ተወካይ የንብረት አደራውን በጽሁፍ ማስረጃ አስመዝግበው ከእጃቸው አስገቡ:: ንብረቶቹን ተረክበውም ታካሚዋን ሸኙ::
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ህክምናቸውን ለመጀመር የንብረቶቹን ጉዳዩ ለበለአደራው አስረክበው ወዳሰቡት አገር ተጓዙ:: አደራ ሰጪና ተቀባይ የወደፊቱን በስልክ ሊወያዩ ተነጋግረው በአድራሻ ልውውጥ ተለያዩ::
ጊዚያት ተቆጠሩ:: ታካሚዋ ከውጭ አገር፣ አደራ ተቀባይዋ ከአገር ቤት፣ በስልክ መስመር መገናኘት ያዙ:: የአገር ቤቷ ስለህክምናው፣ ስለውጤቱ ጠየቁ:: ከውጭ ያሉት ስለአገር ቤት፣ ስለንብረቶች ጠየቁ:: ሁለቱም ከያሉበት፣ እየጠየቁ፣ እየመለሱ ጊዜያት ቆጠሩ::
ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ለወይዘሮ ኤልሳቤጥ የደረሳቸው መረጃ አስደንጋጭ ሆነ:: አገርቤት ያለው ሀብት ንብረታቸው በመንግስት አካላት መወሰዱንና ድርጊቱ ከተወካይዋ አቅም በላይ መሆኑ ተነገራቸው:: ወይዘሮዋ ይህን ሲሰሙ ደነገጡ፣ አዘኑ:: ጓዛቸውን እየሸከፉ አርቀው አሰቡ:: ህክምናው እንዳበቃ ፈጥነው ሊመለሱ ወሰኑ::
መልስ -ወደ አገር ቤት…
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ከሄዱበት ወደ አገር ቤት እንደተመለሱ ስለንብረቶቻቸው ጠየቁ:: የተባለው ሁሉ እውነት ሆኗል:: ከጊዜያት በፊት በውክልና አደራ የሰጡት መኖሪያ ቤትና ሁለት መኪኖች ባስቀመጧቸው አግባብ የሉም:: ቤቱም ሆነ መኪኖቹ ከተወካይ ይሁንታና አውቅና ውጭ በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስገዳጅነት ተወስደዋል::
ወይዘሮዋ ይህን እውነት እንዳወቁ በባለቤታቸውና በእሳቸው ስም የአቤቱታ ማመልከቻ አዘጋጅተው ፍርድቤት አመሩ:: ፍርድ ቤቱ የጥንዶቹን ማመልከቻ ተቀብሎ መመርመር ጀመረ::
ማመልከቻው ወይዘሮዋ ለህክምና ወደ ውጭ አገር ሲጓዙ ንብረቶቹን ለተወካይ በህግ አግባብ መስጠታቸውን ያመለክታል:: ከዚሁ ተያይዞም ንብረቶቹ በተወካይ አውቅና ስር መቆየታቸውንና ከጊዜያት በኋላ ግን ከተወካይዋና ከአመልካቾቹ ፈቃድ ውጭ እንደተወሰዱባቸው፣ ይህም አግባብ ባለመሆኑ እንዲመለስላቸውና ህግ እንዲዳኛቸው ጠይቀዋል::
አመልካቾቹ ከአቤቱታው ጋር ባቀረቡት ተጨማሪ ጥያቄም ንብረቶቹ ተሽጠው ከሆነ ይህን ያደረጉ አካላት የመሸጥ ስልጣኑ ስለሌላቸው የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ፣ለመሸጥ ህጋዊ ምክንያት ካላቸው ደግሞ የወይዘሮዋ የመሸጥ መብት እንዲከበር፣ ሲሉ ጠይቀዋል::
ክርክሩን በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪውን የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደርና ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያላቸውን አካላት አስቀርቦ ጠየቀ::
በአንደኛና ሁለተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተጠሪዎች በፍርድ ቤቱ ለተጠየቁት ምላሽ ሰጡ:: ንብረቶቹ ኤርትራዊ ዜግነት ባላቸው ሁለተኛ አመልካች አቶ ባህታ ትርፌ ስም የተመዘገቡ መሆኑንና ግለሰቡ እንደውጭ አገር ዜግነታቸው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት የመሆን መብት እንደሌላቸው አስረዱ::
ተጠሪዎቹ ምላሻቸውን በማስረጃ አስደግፈው ሲያስረዱም በፍ/ብ/ህ/ቁ 90 መሰረት በ1991 ዓ.ም ኤርትራውያን ያላቸውን የማይንቀሳቀስ ንብረት ለኢትዮጵያውን እንዲሸጡ ሲታወጅ አመልካቾች ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ለሶስተኛው ተጠሪ በጨረታ መሸጡን ለፍርድ ቤቱ አስረዱ::
የሽያጭ ገንዘቡንም በሁለተኛው አመልካች ስም በዝግ የባንክ ሂሳብ የገባ በመሆኑና ስመ ንብረቱ ስለዞረ የሽያጭ ውል ሊፈርሰ አይገባም:: እኛም በህግ መጠየቅ አይኖርብንም በማለት ምላሽ ሰጡ::
በፍርድ ቤቱ ሶስተኛው ተጠሪ በጣልቃ ገብነት ተከራካሪ ሆነው ቀርበዋል:: ተጠሪው የሌሎች ተጠሪዎችን ክርክር ከማጠናከር በዘለለ አመልካቾች ንብረቱን በጋራ ስለማፍራታቸው ማስረጃ ባለመቅረቡ ክሱ ውድቅ ሊደረግልኝ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል::
የፍርድቤቱ ውሳኔ…
ፍርድ ቤቱ ክርክሩን በጥሞና ካየ በኋላ ሊሆን ይገባል ያለውን ውሳኔ አሳለፈ:: ወይዘሮዋ በዜግነት ኢትዮጵያዊት ናቸው:: ባለቤታቸው ሁለተኛ አመልካች ኤርትራዊ ቢሆኑም ዜግነታቸውን መሰረት አድርጎ ብቻ የተፈጸመው የቤት ሽያጭ ውል ህጋዊነት የሌለው በመሆኑ ውሉ ሊፈርስ ይገባል ሲል ወሰነ::
ከዚሁ ጋር አያይዞም ንብረቶቹ በጋብቻ ውስጥ የተፈሩና የጋራ በመሆናቸው እንዲሁም ጋብቻው እስካሁን የጸና በመሆኑ፤ የንብረት ድርሻ ክፍፍል ሊነሳ አይገባም:: ስመ ንብረቱም ቀደም ሲል በነበረበት በሁለተኛ አመልካች ስም እንዳለ ሆኖ ንብረቱን አንደኛ አመልካች ሊረከቡት ይገባል ሲል ብይን ሰጠ::
ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ አንደኛና ሁለተኛ ተጠሪዎች በአንድነት፣ ሶስተኛው ተጠሪ በተናጠል ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የይግባኝ ሲሉ ቅሬታቸውን አመለከቱ:: ቅሬታውን በጥምረት የተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ጉዳዩን መመልከት ጀመረ::
አንደኛና ሁለተኛ ተጠሪዎች ሽያጩን የፈጸሙት ሁለተኛው አመልካች አቶ ባህታ ትርፌ የውጭ አገር /ኤርትራዊ/ ዜግነት ያላቸው በመሆኑና የማይንቀሳስ ንብረት ባለቤት መሆን ስለማይችሉ እንዲሁም በወቅቱ በነበረው በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት አገር ውስጥ ባለመሆናቸው ምክንያት ተጠሪዎቹ ህጉን ለማስፈጸም ሲሉ ያደረጉት የሽያጭ ሂደት መሆኑን አመለካተ::
ፍርድ ቤቱ በሶስተኛው ተጠሪ ስም የተመዘገበው ንብረት ተሰርዞ መኖሪያ ቤቱ በሁለተኛው አመልካች ስም እንዲመዘገብ መደረጉም የፍትሀብሄር ቁ/390 እና 391 ላይ የተቀመጠውን ህግ በቀጥታ የሚቃረን በመሆኑ ውሳኔው ሊሻር ይገባል ሲል ብይን ሰጠ፡፡
ከዚህ ውሳኔ በኋላ አቤቱታቸውን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አንደኛ አመልካች በፍርድ ቤቱ የተሰጣቸው ውሳኔ ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ:: ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአመልካችዋን አቤቱታ ዳግም መመርመር ያዘ:: የቀረቡ ማስረጃዎችን ከተጠሪዎች ሃሳብ አዛምዶም በተላለፈው ውሳኔ ላይ የህግ ስህተት አልተፈጸመም ሲል በአብላጫ ድምጽ ወሰነ::
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የውሳኔ ሂደት የቀረበው አናሳ ድምጽ ደግሞ የአንደኛ አመልካችን ኢትዮጵያዊ ዜግነትን መሰረታዊ ጭብጥ በማለፍ የባለቤታቸውን ኤርትራዊ መሆንን መሰረት አድርጎ በኢትዮጵያ ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዝ እንደማይችሉ፣ ከያዙም በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሰው የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለባቸው የሚደነግገውን ህግ ይጠቅሳል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዳኝነት የጠየቁት አንደኛ አመልካች ንብረቱ በጋብቻ ውስጥ የተገኘ እንደመሆኑ ውሳኔው የዜግነታቸውን ሁኔታና መብት በማለፍ የተላለፈ ነው:: የባለቤታቸውን ኤርትራዊ መሆን ብቻ ምክንያት አድርጎም ንብረታቸውን እንዲሸጥ መደረጉ ተገቢ አይደለም:: የተሰጠው ብይንም መሰረታዊ የህግ ጥሰት ያለበት ነው:: ሲል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን አብላጫ ውሳኔ ለመሞገት ሞክሯል:: ይሁን እንጂ በፍርድ ቤቱ አብላጫ ድምጽ ውሳኔው በነበረው ብይን እንዲጸና ሆኗል፡፤
አቤቱታ ለህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ…
አመልካች በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተወስኖ በሰበር ሰሚው አብለጫ ድምጽ የጸደቀውን ውሳኔ ተቀብለው በይሁንታ መቀመጥ አልፈለጉም:: ንብረታቸው ያለአግባብ መወሰዱንና የተሰጣቸው የፍርድ ውሳኔም ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ የህገ መንግስት ትርጉም ይሰጥልኝ በማለት ጥያቄ አቀረቡ::
ጥያቄው የቀረበለት የኢፌዴሪ የህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የአመልካችዋን ጥያቄ ተቀብሎ መመርመር ጀመረ:: አመልካች ሐምሌ 17 ቀን 1990 ዓ.ም ወይዘሮ ሮዛ ካርሎ ለተባሉ ግለሰብ ንብረታቸውን ውክልና በመስጠት ለህክምና ወደ ውጭ አገር ተጉዘዋል::
በሌላ በኩል አንደኛ ተጠሪ በቀን 01/06/93 ዓ.ም አቶ ግዛው የተባሉ ግለሰብን ንብረቶቹን የመሸጥ ውክልና የለዎትም በሚል በዞኑ ለተቋቋመው ኮሚቴ ቤቱንና መኪኖቹን እንዲያስረክቡ ያደረጉበት ሰነድ መኖሩ ተመላክቷል:: በሶስተኛው ተጠሪ አማካኝነትም የሽያጭ ገንዘቡን ለአዲስ አበባ መስተዳድር ፋይናንስ ቢሮ ገቢ ያደረጉበት ደረሰኝ ከፋይል ጋር ተያይዟል::
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ኤርትራውያን ለአገር ደህንነት ሲባል ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሲወሰን፣ ንብረታቸውን በተመለከተ ህጎች ወጥተው እንደነበር ጉባኤው ከግምት በማስገባት ጉዳዩን መመርመር ጀመረ::
በወቅቱ ንብረታቸውን በተመለከተ በነበረው ሂደትም በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በደህንነት የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን በኩል እንዲፈጸም መደረጉ ጭምር በጉባኤው ተወሳ:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጦርነቱ ምክንያት ከአገር እንዲወጡ የተደረጉ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ያላቸውን ንብረት ማግኘትና ማልማት እንዲችሉ በሚኒስትሮች ምክርቤት የወጣው መመሪያ በማሳያነት ቀረበ::
በመመሪያው በ1990 ዓ.ም ለሀገር ደህንነት ሲባል ከሀገር እንዲወጡ የተደረጉ ኤርትራውያንን ንብረት አስከ ማስተዳደርና ሽያጭን አስከመወሰን የሚደርስ ህግ አልተቀመጠም:: እንደውም በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰላማዊ ኤርትራውያን ንብረታቸውን ማግኘት የሚችሉበትን አግባብ የሚወስን ህግ ነው::
ጥንዶቹ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በትዳር እንደመጣመራቸው ንብረታቸውም በጋራ የተገኘ እኩል ሀብት ነው:: አንደኛዋ አመልካች በዜግነት ኢትዮጵያዊት መሆናቸው ደግሞ ንብረቱን በባለቤትነት ተረክበው ሙሉ ለሙሉ የማስተዳደር መብት እንዲኖራቸው ያደርጋል::
ተጠሪዎች የሁለተኛውን አመልካች ኤርትራዊ መሆን መነሻ በማድረግ ብቻ የባልና ሚስትን የጋራ ንብረት ገዥና ሻጭ በመሆን የፈጸሙት ውል ተገቢነት የለውም:: አንደኛ አመልካች ዳኝነት የጠየቁበት የግል ንብረት ጉዳይም የዜግነትና የንብረት መብትን ከማረጋገጥ አኳያ በዝምታ ሊታለፍ የሚገባው አይደለም::
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ በሰጠው ውሳኔ ሶስተኛው ተጠሪ በፍትሀብሔር ቁጥር 1185 መሰረት ቤቱን በስማቸው አስመዝግበው እንደሚገኙ ተጠቅሷል:: ድንጋጌው እንደሚያሳየው ግን ንብረቶቹን በውል ማስተላለፍ የሚቻለው በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ መሆን ይኖርበታል::
እስካሁን የተሰጠው ውሳኔም አመልካችዋ ኤርትራዊ ዜግነት ካላቸው ሰው ጋር ትዳር በመፈጸማቸው ብቻ በዜግነታቸው የማይንቀሳቀስ ንብረት የማፍራትና ባለቤት የመሆን ፣ በሽያጭ የማስተላለፍና ተገቢውን ጥበቃ የማግኘት መብታቸውን የጣሰ መሆኑ ተረጋግጧል::
የመጨረሻው ውሳኔ …
ውሳኔው ህገመንግስታዊ ጥበቃ ያለውን የንብረት ባለቤትነትና የዜግነት መብትን የከለከለ መሆኑን ያሳያል:: በመሆኑም የአመልካችዋ ንብረቶች የሆኑት ሁለት መኪኖች ከራሳቸው ፈቃድ ውጭ በማናቸውም የመንግስት አካላት ትዕዛዝ መስጠትም ሆነ ማስተላለፍ አይቻልም:: እስካሁን የተካሄደው ውል ህገመንግስታዊ ባለመሆኑም የመኖሪያ ቤቱና የመኪኖቹ ሽያጭ እንዲሁም የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ ህጉን የሚቃረን ሆኖ ተገኝቷል::
ውሳኔው ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ከማድረግ ጀምሮ ለንብረቱ ባለቤት ንብረታቸውን በመመለስ ስመ- ንብረቱን በስማቸው መመለስ ይገባል ያለው ጉባኤ የተጣሰውን ህገመንግስታዊ መብት ማረም ግድ እንደሚልም አስምሮበታል::
የኤፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የፓርላማ ዘመን፣ የ3ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔም እስካሁን በፍርድ ቤቶቹ የተሰጠው ብይን የአመልካችን ህገመንግስታዊ መብቶች የጣሰ በመሆኑ በህገመንግስቱ አንቀጽ 9/11/ መሰረት ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም በማለት በሙሉ ድምጽ ወስኗል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013