ዓይነተ ብዙ ቀለም የሚስተዋልባትና የተለያዩ ባህሎች ባለቤት የሆነችው አዲስ አበባ የኢትዮጵያን ባህል፣ወግ፣ልማድና ትውፊት ትወክላለች፡፡ ለዚያም ነው ‹‹አዲስ አበባ ትንሿ ኢትዮጵያ ናት›› ሲባል የምንሰማው፡፡ አዲስ አበባ የራሷ ባህል፣ ወግ እሴትና ታሪካዊ ቅርሶች የያዘች የተዋቡ ባህሎች መድረክ፣ የትውፊትና ወግ ማሳያ፣የኢትጵያዊ ቀለም ህብር ፈጥሮና ደምቆ የሚታይባት ከተማ ነች፡፡ ዓለም አሁን ላይ በዚህች ድንቅ የባህል ከተማ ላይ ዓይኑ ያረፈ ይመስላል፡፡ በቅርቡ የአውሮፓ የባህልና ቱሪዝም ካውንስል አዲስ አበባን ‹‹የዓለም የባልና የቱሪዝም ከተማ›› ብሎ መምረጡም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ምርጫው ማግስት ግጥምጥሞሽ ሆኖ አዲስ አበባ የባህል ሳምንቷን ከጥር 24 እስከ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ የአዲስ አበባ ባህል፣ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት አካሂዳ ነበር፡፡ የዚህን የባህል ሳምንት አጠቃላይ ድባብ በተመለከተ በዛሬው ባህል አምዳችን ልናወጋችሁ ወደድን፡፡
የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በጠዋት ከወትሮ በተለየ መልኩ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና ለዝግጅት በታለሙ መድረኮች በመዋብ ሞቅ ደመቅ ብሏል፡፡ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን አልባሳት የለበሱ ከአስሩም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ የባህል አምባሳደሮች በባህላዊ ዜማና ውዝዋዜ በመታጀብ ወደ ቅጥር ግቢው በአጀብ ሲዘልቁ ለተመለከተ የውበት ጥግ ላይ በደረሰ ህብራዊ ቀለማቸውና የአብሮነት ትስስራቸው መደመሙ አይቀሬ ነው፡፡ ለካስ ኢትዮጵያዊነት የህብረ ቀለማት ውህደት በጋራ የፈጠሩት ድንቅ ውበት ነው ያስብላል፡፡
ባህል በወጉ ከተያዘና ፋይዳው ታውቆ ለጥቅም ማዋል ከተቻለ ለሀገር የሚያስገኘው ጥቅም አያሌ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የበርካታ ባህል ባለቤት የሆኑ ሀገራት የባህል ሀብቶቻቸው ጥቅም ላይ ሲውል ለሀገራቸው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ይነገራል፡፡ የማህበረሰቡን ባህል፣ቅርስና ታሪካዊ ቦታዎች ማልማትና ለሌላው ማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ማድረግ ችለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ‹‹ባህል ለህዝቦች ሰላምና አንድነት›› በሚል መሪ መልዕክት የተከበረው የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ሳምንት የከተማዋ ህዝብ ባህል፣ወግ፣ትውፊት፣ቅርስና ልዩ ልዩ መስህቦች የማስተዋወቅና የእርስ በእርስ ትስስር የማጠናከር ዓላማ ይዞ እንደተነሳ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አዲስ አበባ የባህልና የኪነ ጥበብ መድረክ ናት›› ያሉት የቢሮ ኃላፊው መድረኩ ባህላዊና ታሪካዊ የቱሪዝም ሀብቷን ለከተማው ነዋሪና በዝግጅቱ እንዲታደሙ ለተጋበዙ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ተወካዮች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ ይናገራሉ፡፡
ማህበረሰቡ ያሉትን ባህሎች ተረድቶ በበጎዎቹ እንዲጠቀም፤ የማንነቱ መገለጫዎችም ናቸውናም እንዲጠብቅ ማድረጉ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የባህል ሳምንቱ የአዲስ አበባ ባህል ለማስተዋወቅ የነዋሪዎቿ የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከሪያና ታሪካዊ ቅርሶችና ቦታዎች ለወጣቱ ትውልድ ማስተዋወቂያና ዋንኛ መንገድ ይሆናል፡፡
ማህበረሰቡ የራሱን ባህል እንዲያውቀው ለማድረግ በዓመት አንዴ ብቻ የባህል ሳምንት መከበሩ በቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህ ደግሞ የቢሮ ኃለፊው ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ መስሪያ ቤታቸው መላ መዘየዱን ይናገራሉ፡፡ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ በየወሩ በሚካሄዱ የኪነ ጥበብ ምሽቶችና የዕደ ጥበብ ዓውደ ርዕዮች ላይ የባህል ማስተዋወቅ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡
የባህል ሳምንቱ ልዩ ልዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ዓውደ ርዕይ፣የኪነ ጥበብ ሥራዎች ውድድር እና ሲምፖዚየም ያስተናገደ ነበር፡፡ ከ213 በላይ ዓውደ ርዕይ አቅራቢዎች ልዩ ልዩ ባህላዊ የእጅ ሥራ ውጤቶችን፤ ማህበረሰቡ የሚገለገልባቸው ባህላዊና ታሪካዊ ቅርስና ቁሳቁስ ለእይታና አቅርበው ነበር፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ብሄረሰቦች ባህል ገላጭ ቁሳቁስ የቀረቡበት ዓውደ ርዕይ አንዱን የሌላወን ባህል እንዲረዳና ኢትዮጵያ የብዙ ባህል ባለቤትነቷ ማሳያ መድረክ ነበር፡፡
ወጣት አደም በሊሶ የኦሮሚያን ባህላዊ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁስ ሲያስተዋውቅ አገኘነው፤ በሚያምር ባህላዊ ልብሱ ተውቦ ለእንግዶቹ ባህሉን የሚያስተዋውቀው አደም የባህል ሳምንቱ የራሱን ባህል ለሌሎች የማስተዋወቅ ዕድል እንደፈጠረለትና ብዙ የማያውቃቸውን ወገኖቹን ባህል እንዲያውቅ እንዳደረገው ይገልጻል፡፡ በጎ ባህልና ልማዶችን እርስ በእርስ ለመለዋወጥ ትልቅ ሚና እንዳለውም ይናገራል፡፡
ወይዘሮ ሳቤላ አባይነሸ አባይ ‹‹ብርሃን ኢትዮጵያ›› በሚባል ድርጅታቸው ለ32 ዓመታት የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋቅ የሠሩና በባህል ሳምንቱም ላይ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች፣ ባህላዊ ምግብና መጠጦች፣አልባሳትና ጥንታዊ ቅርሶች በወይዘሮ ሳቤላ ቀርበው የተሳታፊውን ትኩረት ስበው ነበር፡፡
ባህላዊ የምግብ ዝግጅት ሂደቶችን በተግባር በባህላዊ የምግብ ዝግጅት ባለሞያዎች በመታገዝ የማዘጋጀት ልምምድ ሁሉ የሚከወንበት ልዩ መሰናዶ ነበርና የብዙ ታዳሚ ተግባራዊ ተሳትፎ መብዛት ለባህል እውቂያ ያለውን ጉጉት ያሳብቅ ነበር፡፡ ባህልን ማስተማሪያ ጭምር ተደርጎ የሚወሰደው የብርሃን ኢትዮጵያ ጥረት ይበል የሚያሰኝ አዲስ ዓይነት አቀራረብም ነበር፡፡
አቶ መኩሪያ ጣሰው የባህል ሳምንቱ ታዳሚ ናቸው፤ የእርሳቸውም ሃሳብ የተለየ አይደለም፡፡ እዚህ መገኘቴ ብዙ ባህልና ታሪክ እንዳወቅና ከሌላ አካባቢ የመጡ እንግዶችን እንድተዋወቅ አድርጎኛል ይላሉ፡፡ ሳምንቱ መከበሩ በራሱ ለባህል ዕድገት ትልቅ ሚና እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡ መሰል የባህል ዝግጅቶች በየጊዜው ቢኖሩ ማህበረሰቡ ባህሉን እንዲያውቅ የማድረጉ ዕድል ሰፊ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በባህል ሳምንቱ ላይ ከ400 በላይ የሚሆኑ የኪነ ጥበብ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን፤ ወጣትና አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተካፍለውበታል፡፡ ባህላዊና ኪነ ጥበባዊ ትርዒቶቹ የባህል ሳምንቱ በዋናነት በተከበረበት አዲስ አበባ እግዚቢሽን ማዕከልና በአራቱ የአዲስ አበባ የመንግሥት ቴአትር ቤቶች ቀርበዋል፡፡ ቴአትር ቤቶቹ ያለ ክፍያ ባህል ተኮር የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው ለታዳሚው በተከታታይ ቀናት አቅርበዋል፡፡
ሌላኛው የባህል ሳምንቱ ትኩረት ወጣቱን ትውልድ ለአጉል ልማዶችና ለመጤ ጎጂ ባህል ያጋለጠው መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ፤ መፍትሔ የተቀመጠበት ሲምፖዚየም ነው፡፡ በዚህ መድረክ የከተማውን ወጣቶች በተመለከተ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ወጣቱም አባቶቹ ያቆዩለትን በጎ ባህል ጠብቆ በማቆየትና በመጠቀም ለሀገሩ ዕድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ሃሳብ ቀርቦበታል፡፡ በወጣቶች ዘንድ አልባሌ ቦታ መዋልና በደባል ሱሶች መጠመድ የሚታይ ችግር መሆኑንና ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ወጣቶች ጊዜያቸውን ለበጎ ዓላማ ማዋል እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011
በተገኝ ብሩ