አስናቀ ፀጋዬ
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የግል ጤና ተቋማት ማህበርን በሊቀመንበርነት፣ የኢትዮጵያ የግል ጤና ተቋማት ማህበርን ደግሞ በምክትል ሊቀመንበርነት እያገለገሉ ይገኛሉ ።ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ እምብዛም የማይሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን ወደ ደቡብ ክልል በማምጣትና የህብረተሰቡን የጤና ችግር በመቅረፍ ረገድ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል ።
እንደግል የጤና ተቋም የቀዶ ህክምናና የድንገተኛ አደጋ ህክምና ስፔሻላይዝድ ማዕከል በደቡብ የኢትዮጵያና በኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ በማስጀመር ፋና ወጊ ናቸው ።በሀገሪቱ ብዙም ያለተለመደውን የዲጂታል ቴሌ ሄልዝ ህክምና አገልግሎትን በማስጀመርም እንዲሁ ፈር ቀዳጅ ናቸው ።ሁሉንም የጤና አገልግሎቶች በዲጂታል ቴሌ ህክምና የመስጠት ውጥን ይዘውም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ።የዚህ ሁሉ በጎ ሥራ ባለቤት የስነ ደዌ ሰፔሻሊስት ሃኪምና የ‹‹ሊያና›› ዲጂታል ሄልዝ ኬር ሶሊዩሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ግርማ አባቢ ይባላሉ ።
ዶክተር ግርማ ውልደትና እድገታቸው በቀድሞው አጠራር ሰላሌ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ ወረ ጃርሶ ወረዳ ቱሉ ሚልኪ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው ።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቱሉ ሚልኪ አንደኛ ደረጃ፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በገብረ ጉራቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገብተው በሜዲካል ዶክተር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ1990 ዓ.ም ተቀብለዋል።ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም የመጀመሪያ ሥራቸውን የጀመሩት በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሲዳማ ዞን ዳራ ወረዳ ቀባዶ ጤና ጣቢያ ውስጥ ነው ።በጤና ጣቢያው ጠቅላላ ሃኪምና የጤና ጣቢያ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል ።በጤና ጣቢያው ከሁለት ዓመት በላይ አልቆዩም ።ወደ ዲላ አቀኑ ።በዚያም በዲላ የትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት ነበር የተቀጠሩት ።እዚያም ከሁለት ዓመት በላይ በመምህርነቱ አልቆዩም ።በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የስነ ደዌ ስፔሻሊቲ ሥልጠና ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጡ ።ሥልጠናቸውንም እንዳጠናቀቁ ወደ ዲላ ነበር የተመለሱት ።ወቅቱ 1998 ዓ.ም ነበር ።
ወደ ዲላ ከተመለሱ በኋላ ደግሞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነት ተቀጠሩ ።በዩኒቨርሲቲው ለአራት ዓመት ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው ካገለገሉ በኋላ ደግሞ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ ደዌ ትምህርት ክፍል መምህርና የዲፓርትመንት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል ።ዶክተር ግርማ ከመምህርነቱ ጎን ለጎንም ከህክምናው ጋር ተያያዥ የሆነ የግል ሥራ ይሠሩ ስለነበር የግላቸውን የውስጥ ደዌ ስፔሻላይዝድ ማዕከል ለመክፈት አልተቸገሩም ።
ዶክተር ግርማ እንዳጫወቱኝ፤ በህክምና ንግድ ውስጥ እገባለሁ ብለው አስበው አያውቁም ።ፍላጎትም አልነበራቸውም።የግላቸውን እንዲከፍቱ ካደረጋቸው ምክንያት አንዱ በህክምናው ተቀጥረው ሲሠሩም ሆነ በውጭም ሆነው ሲታዘቡ የህክምና አገልግሎቱ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሸፈን እንዳልሆነ ይገነዘባሉ ።ሙያው እያላቸው ህክምና ፍለጋ የሚንከራተተውን ማህበረሰብ መርዳት አለመቻላቸው ቁጭት ውስጥ ይከታቸዋል ።መርዳትም እንዳለባቸው ይሰማቸዋል ።እንዲህ ከራሳቸው ጋር ከታገሉ በኋላ ነው የግል የህክምና ተቋም ከፍተው ወደ አገልግሎቱ የገቡት ።በግላቸው የህክምና አገልግሎቱን ሲጀምሩም ባልታዩ የጤና አገልግሎት ዘርፎች ላይ ነበር ትኩረት ያደረጉት ።እርሳቸው ወደ ሥራው ሲገቡ በሃዋሳ ከተማ ሰፋ ያለ የላብራቶሪ አገልግሎት ያልነበረ በመሆኑ ይህን ችግር የሚያቃልል እንዲሁም የኤም አር አይ እና የዲያሊሲስ አገልግሎቶችንም የማዳረስ ሥራዎችን ያካተተ ነበር ።
በተመሳሳይ የካንሰር ምርመራ አገልግሎትን በዚያው በከተማው የማቅረብ፣ የማሞገራፊና የጡት ካንሰር ምርመራዎችንም የማድረግ ሥራዎችንም ተጨማሪ አገልግሎቶች ነበሩ ።ከጥቁር አንበሳ ውጪ በአዲስ አበባ በተወሰኑ የግል ጤና ተቋማት ውስጥ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የካንሰር ህክምና በስፔሻሊስት ሃኪሞች በመስጠት አገልግሎቱን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል ።
ዶክተር ግርማ በዘርፉ ያለውን ክፍተት እያዩ ችግሮችን ለመፍታት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ያስተዋሉትን የድንገተኛ አደጋዎች መብዛትንም ለመፍታት በሐዋሳ ከተማ የቀዶ ህክምና ድንገተኛ አደጋዎች ማዕከል ከፍተው አገልግሎት በመስጠት ተጎጂዎችን ታድገዋል ።የኦክስጂን ፋብሪካ በማቋቋምም ክፍተቱን ለማቃለል ሞክረዋል ።
‹‹ያኔት›› በሚል ስያሜ በ2005 ዓ.ም በዘጠኝ የጤና አገልግሎት ዘርፎች ሥራውን በሐዋሳ የጀመረው የህክምና ተቋማቸው በጊዜው የነበሩት የጤና ባለሞያዎች አስራ ስምንት ሲሆኑ፤ መነሻ ካፒታሉም ከ 3 ሚሊዮን ብር የማይበልጥ ነበር ።ተቋሙ በመጀመሪያ የስፔሻላይዝድ ህክምና ማዕከልና የህክምና መገልገያዎችና የመድሃኒት ማከፋፈያ የነበሩት ሲሆን፤ በሂደት ሥራዎች እየሰፉ በመምጣታቸው የቀድሞ ሥራዎቹን አካቶ ከሦስት ዓመት በፊት ‹‹ሊያና›› በሚል አዲስ ስያሜ በልዩ ልዩ የጤና ዘርፎች ላይ እየሠራ ይገኛል ።ላለፉት ስምንት ዓመታትም በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል በጤና እንክብካቤ አገልግሎት ቢዝነስ ውስጥ ለስምንት ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል ።
በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ባጠቃላይ 400 ለሚሆኑ የጤና ባለሞያዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ አጠቃላይ የተመዘገበ ካፒታሉም ወደ 23 ሚሊዮን ብር ተጠግቷል ።የተቋሙ ዋነኛ ዓላማ ለጤና ችግሮች የተቀናጀ መፍትሔ ይዞ መምጣት ከመሆኑ አኳያም በሐዋሳ ከተማ ሦስት ተቋማትን አቋቁሞ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል ።
የመጀመሪያው ያኔት የውስጥ ደዌ ስፔሻላይዝድ ህክምና ማዕከል ሲሆን፤ ኤም አር አይ፣ ሲቲ ስካን፣ ዲያሊሲስ፣ ኢንዶስኮፒ፣ ኮሎኖስኮፒ፣ ማሞግራፊ ፣ የጡት ራጅና የካንሰር ህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣል ። ከ150 በላይ የሚሆኑ የህክምና ባለሞያዎችንም አቅፏል።
ሁለተኛውና ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመው በሀገሪቱ የመጀመሪያው የግል ያኔት የቀዶ ህክምናና የድንገተኛ አደጋ ህክምና ስፔሻላይዝድ ማዕከል ደግሞ በተለይ በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍልና የኦሮሚያ አካባቢ ከድንገተኛ አደጋዎች ጋር በተያያዘ በስፋት ይሠራል ።በዘጠኝ ሜካኒካል ቬንቲሌተሮችና በጠንካራ የፅኑ ህሙማን ክፍሎችም ተደራጅቷል ።የላፓራሰኮፒክ ቀዶ ህክምናን ጨምሮ በሀገሪቱ ሊሠሩ የሚችሉ ማናቸውንም የቀዶ ህክምና አገልግሎቶችንም ይሰጣል ።ሦስተኛው የዲቫይን ተች የማገገሚያና ተሃድሶ ማዕከልም በሪሃብሊቴሽንና ፓሊየቲቭ ኬር ህክምነ ዙሪያ ይሠራል ።
በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙ ከውጭ ሀገር የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በማስመጣት በሀገር ውስጥ ያከፋፍላል።በፋርማሲዎቹ አማካኝነትም መድሃኒቶችን ለተጠቃሚዎች ያቀርባል ።የማማከር አገልግሎትና በትምህርት ዘርፍም የህክምና ተቋሙ ያኔት ሊያና የጤና ሳይንስ ኮሌጅን በመመስረት በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል እጥርት ለመቅረፍ በፋርማሲ፣ በአንስቴዢያ፣ በራዲየሽን ቴክኖሎጂና በላብራቶሪ ቴክኖሎጂ በባችለር ዲግሪ እንዲሁም በስነተዋልዶ ጤናና በሄልዝ ኬር ማኔጅመንት በማስተርስ ዲግሪ በዚህ ዓመት ትምህርት ለማስጀመር ራሱን አደራጅቷል ።
ሊያና የምርምርና የማማከር ክፍሎችንም አዋቅሮ በሁሉም የጤና ዘርፎች ላይ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ በራሱ ማዳረስ ያልቻላቸውን የጤና አገልግሎቶችን ከሌሎች አካላት ጋር በመሆንም ይሠራል ።ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ የጀመረውና በቀን እስከ 600 ሲሊንደር ኦክሲጂን የማምረት አቅም ያለው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካም ለዚህ አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ በተለይ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ትልቅ ሥራ ተሠርቶበት ማህበረሰቡን መታደግ ችሏል ።
ተቋሙ በእህት ኩባንያው ‹‹ኦንኮ›› ፓቶሎጂ ዳያጎነስቲክ ማዕከል አማካኝነት በአዲስ አበባ ፓስተር አካባቢ አቋቁሞ የካንሰር ችግሮችን መርምሮ የመለየት ሥራ በማከናወን በሀገሪቱም የመጀመሪያው የግል ተቋም ለመሆን ችሏል ።በቅርቡ ደግሞ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻልና የአገልግሎት ክፍያን ለመቀመነስ በማሰብ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የግል ዲጂታል ቴሌ ህክምና አገልግሎት ማዕከል አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል ።
በዚህ ማዕከል አማካኝነትም ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም መሄድ ሳያስፈልጋቸው በቤታቸው አልያም በሚሠሩበት ቦታ ላይ ሆነው የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻችቷል ።በዚሁ አገልግሎት 300 ለሚጠጉ ጀማሪ የጤና ባለሞያዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም አቅዷል ።
‹‹ሊያና በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀንድ ቁጥር አንድ የቴሌ ህክምና አገልግሎት ሰጪ መሆን ይፈልጋል›› የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ ተቋሙ ለዚህ አገልግሎት ፈር ቀዳጅ በመሆኑ በቴሌ ህክምና ዙሪያ በርካታ ምርምሮችንና መደላድሎችን ሲሠራ መቆየቱን ይናገራሉ ።ሆኖም ይህን ህልሙን በሚገባ ለማሳካት የአሠራር ስርዓቶች በሚገባ መዘርጋት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ ።አገልግሎቱን ለመስጥ የህግ ማእቀፉ በቦታው ላይ ካለ ይህን እቅድ ለማሳካት ተቋሙ ብዙም እንደማይቸገርም ያስረዳሉ ።
የህግ ማእቀፉ ከተቀመጠና የምክርና ህክምና አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ከተፈቀዱ በቀጣዮቹ ስድስት ወራቶች የዲጂታል ቴሌ ህክምና አጎልግሎቱን በስደተኛ ካምፖችና በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች በየደረጃው የማስፋት ሃሳብ እንዳለው ዶክተር ግርማ ያመለክታሉ ።
በየገጠሩ ያሉ የመንግሥትና የግል መስሪያ ቤቶች፣ ፋብሪካዎች፣ መአድን አውጪ ኩባንያዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ የህክምና አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ እየተዳረሰ ባለመሆኑም በእነዚህ ቦታዎች ላይ ተቋሙ የምክርና የህክምና አገልግሎት ቢሮዎችን በማቋቋም ሰዎች አገልግሎቱን የሚያገኙበትን ዘዴ የመቀየስ ውጥን እንዳለውም ይጠቁማሉ ።
በቦታው ላይ ከሚሰጠው አገልግሎት አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ የሪፈራል ሊንኬጅን በማጣናከር ታካሚዎች መጉላላት ሳይደርስባቸው አገልግሎቱን የሚያገኙበት ስርዓት የመዘርጋትና በተለያዩ ምክንያቶች በሰዎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን በቶሎ ደርሶ የመለየት ሥራ በቴሌ ትራውማ ኬር አማካኝነት የመሥራት እቅድ እንዳለውም ይጠቅሳሉ። ማንኛውንም የህክምና አገልግሎት በዲጂታል የቴሌ ህክምና በኩል የመስጠት ሃሳብ እንዳለውም ይናገራሉ ።
በሂደትም ተቋሙ በርካታ ችግሮችን ይቀርፋል ተብሎ የሚታሰበውን ‹‹የሪሞት ሞኒተሪንግ›› አሠራርን ሥራ ላይ ለማዋል ማቀዱንም ዶክተር ግርማ ገልፀው፤ ይህም ከስማርት ሰዓቶች ጀምሮ በሰውነት ላይ ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን በመግጠም የሰዎችን ሙሉ የጤንነት ሁኔታ ዕለት በዕለት ለመከታተል የሚያስችል መሆኑን ያስረዳሉ ።ይህንኑ አሠራር በተቋሙ ውስጥ በማካተት የመሥራት ሃሳብ እንዳለውም ይጠቅሳሉ። እነዚህኑ መሣራያዎች ወደሀገር ውስጥ ለማስገባትትና አገልግሎቱን መጠቀም ለሚችለው የህብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስም ከአንዳንድ ኩባንያዎች ጋር ከወዲሁ ንግግር እየተደረገ መሆኑንም ይጠቁማሉ ።
የግሉ ጤና አገልግሎት ዘርፍ መበረታታት ከጀመረ ገና አጭር ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ግርማ፤ በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ከ34 ከመቶ ያላነሰ የጤና አገልግሎት አበርክቶ እንዳለው ይጠቁማሉ ።ሽፋኑ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት በኩል እየተደረጉ ያሉ ሰፊ ጥረቶችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማምጣቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ አገልግሎቱን ያለመቆራረጥ በመስጠትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመሞከር ረገድ የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ያብራራሉ ።
ይሁንና በግሉ የጤናው ዘርፍ ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በተለይ ደግሞ ለህክምና ኢንቨስትመንት ከመንግሥት በኩል በቂ የመሬት አቅርቦት ችግር መኖሩን ያስረዳሉ ።ከዚህ አኳያ መንግሥት በተወሰነ ደረጃ አብዛኛውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችልና የኢንቨስትመንት ቦታን ለማግኘት የሚያበቃ ማእቀፍ ማዘጋጀት እንደሚገባው ይጠቁማሉ ።
በሌላ በኩል ደግሞ ከባንክ የገንዘብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች እንዳሉ አስረድተው፤ ልክ እንደሌሎቹ ዘርፎች ለግሉ የጤና ዘርፍ እኩል ትኩረት እንደማይሰጠው ይገልፃሉ ።አብዛኛዎቹ ባንኮችም ገንዘብን የሚያቀርቡት በማኒፋክቸሪንግና በእርሻ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩት መሆኑን ይጠቅሳሉ ።በመሆኑም መንግሥት በዚህ በኩል ለጤናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ባንኮች የገንዘብ አቅርቦት እንዲያደርጉ ግፊት ማድረግ እንዳለበት ያመለክታሉ ።
በተመሳሳይ ከህክምናው ጋር የተያያዙ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት መኖርም የዘርፉ ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ዘርፉ በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ ችግር መፍጠሩን ያስረዳሉ ።ከዚህ አኳያ በመንግሥት በኩል ዘርፉን ለማሳደግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው አሁንም ሰፊና ትርጉም ያላቸውን ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባ ይጠቁማሉ ።
እንደ ሊያና ‹‹አስከአሁን ባለው ሂደት በግሉ የጤና አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ በመግባትና ዘጠኝ በሚሆኑ የተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት ህብረተሰቡ በቅርበት የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ተሳክቶልናል›› የሚሉት ዶክተር ግርማ ተቋማቸው በአሁኑ ወቅት የጀመረው በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል ቴሌ ህክምና አገልግሎት በሌሎች ዘርፎችም ጭምር ገብቶ ለመሥራት የሚያበረታታ መሆኑን ይጠቁማሉ ።ይሁንና ተቋሙ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ዘርፍ ለማቅረብና ተመራጭ የህክምና ተቋም ለመሆን ካስቀመጠው ራእይ አኳያ ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ይጠቅሳሉ ።
የማህረሰቡን የጤና ችግር በመቅረፍ ሂደት ውስጥ የራሱ ጉልህ ሚና እንዲኖረው ጥረት ማድረጉና በሀገር ደረጃም ሆነ ከዚያም ባለፈ ለዘርፉ መሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት ፍላጎት ያለው መሆኑ ለእስካሁኑ የተቋሙ ውጤት ጥሩ ማሳያ መሆኑንም ዶክተር ግርማ ይናገራሉ ።ይህንኑ ራእይም መላው የሊያና ቤተሰብ ተጋርቶ ራዕዩን ለማሳካት ሌት ተቀን እንደሚለፋም ያስረዳሉ ። አጋሮችንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ረገድም ጠንካራ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም ይጠቁማሉ ።
ሊያና ትልቅ ራእይ ያለውና ብቻውን መሮጥ የማይፈልግ የህክምና ተቋም መሆኑንም ዶክተር ግርማ ጠቅሰው ፤ ለሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ እንዲኖረው ሌት ተቀን የሚተጋ ተቋም መሆኑን ይመሰክራሉ ።የሀገሪቱን የጤና አገልግሎት እጥረት በመንግሥት ብቻ ሊቀረፍ የማይችል በመሆኑ ልክ እንደሊያና ሁሉ ሌሎችም ችግሮችን ተጋፍጠውና ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይረው በዚሁ የግል ጤና አገልግሎት ዘርፍ ገብተው በመሥራት ለዘርፉ መሻሻል የራሳቸውን አሻራ ማስቀመጥ እንዳለባቸውም ይመክራሉ ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013