መልካምስራ አፈወርቅ
ሁለቱ ሴቶች ውዝግብ ከፈጠሩ ቆይተዋል። በመሀላቸውም ቅራኔ ውሎ ሰንብቷል። ሁለቱም በየግላቸው የሚያነሱት ሃሳብ እያግባባቸው አይደለም። ቅሬታቸውን በንግግርና በመደማመጥ ያለመፍታታቸው እውነት በየቀኑ ያወዛግባቸው ይዟል።
አንዳቸው የሌላቸውን አስተያየት አያዳምጡም። ወይዘሮ ሀና አድማሱና ወይዘሮ የሺሀረግ ከበደ በየግላቸው የሚያነሱት መከራከሪያ ሁሌም በየራሳቸው ውስጠት ትክክል እንደሆነ ጊዜያትን ቆጥሯል። ወራት አልፎ ዓመታትን ያስከተለው አለመግባባትም መፍትሄ ሳያገኝ በቅያሜ ዘልቋል።
ሁለቱን ሴቶች በጋራ የሚያከራክራቸው ምክንያት የአንድ መኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው። መኖሪያ ቤቱ ቀድሞ በማዕድ ቤትነቱ ይታወቃል። እንዲህ በነበረ ጊዜ ወይዘሮ ሀና አድማሱ እንጀራ ሲጋግሩበት፣ ወጥ ሲሰሩበት፣ ዳቦና ቂጣ ሲጋግሩበት ነበር። ኩሽናው በጭስ ቤት ስያሜ እየተጠራም የዓመታት እድሜን ተሻግሯል።
ውሎ አድሮ ግን ይህ ሙያ ብዙ ቤት ለሁለቱ ሴቶች መቀያየም ምክንያት ሆነ። ይዞታው ከቀድሞ ገጽታው መሻሻሉ፣ ተስፋፍቶ መሰራቱና መኖሪያ መሆኑም ኩሽና መባሉን አስቀርቶ ትርጉሙን አስለወጠ። ቤቱ ቤት ሆኖም ቤተሰቦችን ማሳደር፣ ማኖር ጀመረ።
እንዲህ መሆኑ ግን ወይዘሮ ሀና ከወይዘሮ የሺሀረግ ጋር እንዲወዛገቡ ምክንያት ፈጠረ። ውዝግቡ ተጠናክሮም ጠብና ቅያሜን አጫረ። መግባባት ያልፈታው ችግር ውሎ አድሮ በህግ አግባብ ሊዳኝ ፍርድቤት አስቁሞ አከራከረ።
ወይዘሮ ሀና የቀድሞውን ኩሽና ለወይዘሮ የሽሀረግ አሳልፈው ከሰጡ ቆይተዋል። ቀደም ሲል ወይዘሮዋ ይዞታውን በውርስ ያገኙት ስለመሆኑ ይናገራሉ። ወይዘሮ የሽሀረግም በበኩላቸው ሀና መኖሪያውን በውርስ ቢያገኙም እሳቸውም ቤቱን በስጦታ ውል ተረክበው እየኖሩበት መሆኑን ይገልጻሉ።
ወይዘሮ የሺሀረግ የቀድሞውን ኩሽና ለመኖሪያ ሲያስቡት ነባር ይዞታውን አፍርሰው በአዲስ ዛኒጋባ ቤቶች ተክተውታል። ማዕድቤት ይሉት ስሙን ቀይረውም ‹‹መኖሪያ ቤት ›› ተብሎ እንዲጠራ አድርገዋል።
ይህ አውነት ግን በወይዘሮ ሀና ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። በወጡና በገቡ ቁጥር ቤቱን ሲያዩ ይናደዳሉ፣ ይበሳጫሉ፤ የቤት ባለቤትነቸውን ጉዳይ በግልጽ እያነሱም ክፉ ደግ ለመናገር ይሞክራሉ። አንዳንዴ ወይዘሮዋ ይህን ስሜት በቅያሜ ብቻ ማሳለፉ ጥቃት መስሎ ይታያቸዋል።
እሳቸው ይህን ቤት በዚህ ገጽታው አያውቁትም። ይሁን እንጂ ቀድሞ በቦታው የነበረው የማዕድቤት የራሳቸው እንደሆነ ማንም ያውቃል። ይህን እውነት ብቻ ይዘው መቀመጥን ያልመረጡት ሴት አንድ ቀን ቤቱን አስመልሰው በእጃቸው ማድረግን ይሻሉ።
ወይዘሮ ሀና ሁሌም የሚቆጩበትን የቤት ጉዳይ አንስተው ለወዳጅ ዘመድ አማከሩ። ጉዳዩን የሰሙ ሰዎች ግራቀኙን አንስተው ሁኔታውን በህግ አግባብ መፍታት እንዳለባቸው መከሩ። ሴትዬዋ ምክሩን ሰሙ። ቀን ከሌት በጉዳዩ አስበውም ከውሳኔ ደረሱ።
አንድ ቀን ወይዘሮ ሀና ማልደው ተነሱ። በአግባቡ ተጽፎ የተዘጋጀ ማመልከቻ ይዘው ከፍርድ ቤት ደረሱ። የመዝገብ ሹሙ ጉዳያቸውን ጠይቆና በአግባቡ አጣርቶ ወደሚመለከተው አሳለፋቸው።
ወይዘሮዋ የቀድሞ የቤታቸው ይዞታ ይመለስልኝ ሲሉ በፍርድ ቤት ክርከር ጀመሩ። የፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር ያዘ። ክርክር ለቀረበበት ቤት ተጠሪ የሆኑትን ወይዘሮ የሺሀረግ ከበደን በአካል አቅርቦም ጠየቀ።
እንደተባለው ሆኖ ተጠሪ ክርክር የተነሳበትን ቤት በኩሽና ይዘት ተረክበው ወደ መኖሪያ ቤት ቀይረውታል። አመልካች እንዳሉትም የቤት ቁጥር 423 አካል የሆነውን ማዕድ ቤት ለዓመታት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። የቤቱ የቀደመ ይዞታ የራሳቸው በመሆኑም የሺሀረግ እንዲለቁላቸውና የኪራይ ገንዘብ እንዲከፍሏቸው ይፈልጋሉ። ለዚህም ፍላጎታቸው ዳኝነትን ይሻሉ።
ተጠሪ በበኩላቸው ከፍርድ ቤቱ ችሎት ቀርበው ጉዳዩን ማስረዳት ያዙ። ቤቱን በስጦታ ውል ያገኙት በመሆኑ አሁንም እየተጠቀሙበት ነው። ቀድሞ የጭስ ቤት ነበርና ለመኖሪያ አላመቻቸውም። ይህን ሲያውቁ ደግሞ አሮጌውን ቤት በአዲስ ሊተኩ አሰቡ። ነባር ይዞታውን አፍርሰውም ግንባታ ጀመሩ። ከግንባታው በኋላ ሁለት ዛኒጋባ የተሰራበት ቦታ መልኩን ቀይሮ መኖሪያ ቤት ሆነ። እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ቤተሰቦችን ይዞም ማኖር ፣ ማሳደር ጀመረ።
ወይዘሮዋ ይህን ካስረዱ በኋላ አሁን እየኖሩበት ያለው ቤት የግላችው መሆኑን ተናገሩ። ገንዘብ አውጥተው፣ ለፍተውና ደክመው የሰሩት በመሆኑም ‹‹ልቀቂ ልባል አይገባም›› ሲሉ ሞገቱ።
ተከራካሪዎች በችሎት…
ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ሴቶች በአካል አስቀርቦ ማከራከሩን ቀጠለ። ሁለቱም ‹‹አለን›› የሚሉትን ማስረጃ እንዲያቀርቡም ፈቀደ። የፍርድ ቤቱን ይሁንታ በተሰጣቸው ዕድል መጠቀም የፈለጉት ሴቶች ለክርክር ይበጃል ያሏቸውን ማሳያዎች ሁሉ አቀረቡ። በምስክርና በሰነድ አስደግፈውም የአሸናፊነቱን ቦታ ሊወስዱ ታገሉ።
ክርክሩ ቀጠለ። ማስረጃዎች ከየአቅጣጫው ቀረቡ። ተከራካሪዎች በይገባኛል የሚከራከሩበት ቤት ለማን ይሁን? የሚለው ነጥብ ሃሳብ እየጫረ ፣ መረጃን ከማስረጃ አየመዘዘ ቆየ። በቀጠሮ ምልልስ ጊዜያትን የቆጠረው ጉዳይ እልባትና ውሳኔ ያገኝ ዘንድም ከመጨረሻው ምዕራፍ ደረሰ።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ …
ፍርድ ቤቱ አሁን ለጊዜያት ግራ ቀኝ ሲያከራከራቸው የቆዩትን ሴቶች ጉዳይ እልባት ሊሰጥ ከመጨረሻው ችሎት ደርሷል። የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቁጥር 22011 በተከፈተው መዝገብ የካቲት 30 ቀን 2002 ዓ.ም ውሳኔ ለመስጠት ከችሎቱ ተሰይሟል።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ክርክር የተነሳበትን ቤት በሚመለከት የቀረቡለትን ማስረጃዎች በማሳያ ተጠቅሞ በአራቱም አቅጣጫዎች ያሉትን የቤቱን አዋሳኞች በጽሁፍ ማብራሪያ አመላክቷል። በዚህም መሰረት በስተምስራቅ መንገድ፣ በስተምዕራብ የመንግስት ቤት፣ በደቡብ ወንዝ፣ በስተሰሜን ደግሞ በቤት ቁጥር 423 የተመዘገበውና ክርክር የተነሳበት ቤት ከመንገድ ጋር እንደሚዋሰኑ አሳይቷል።
በዕለቱ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ተጠሪ ወይዘሮ የሺሀረግ ከበደ አመልካች ወይዘሮ ሀና አድማሱ ይገባኛል ሲሉ ጥያቄ ያነሱበትን ቤት እንዲመልሱላቸውና ይዞታውን ለቀው እንዲወጡ ወሰነ። ለውሳኔው ፍርድ ቤቱ ባሰፈረው ምክንያትም ተጠሪዋ ቤቱን በስጦታ በማግኘታቸው አዲስ ቤት ሰርቻለሁ ቢሉም ይህ የስጦታ ውል በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በመቁ 00691 በፍርድ የተሰረዘ በመሆኑ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም ሲል አስቀምጧል።
ለውሳኔው ተፈጻሚነትም ተጠሪ ቤቱን አስፋፍተው የሰሩበትን ሙሉ ወጪ የዳኝነት ከፍለው የመጠየቅ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አሳወቀ። የሁለቱ ሴቶች የቤት ይገባኛል ክርክር እልባት ካገኘ በኋላም መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመለሰ፡፤
ክስ
አሁን የቤት ይገባኛል ክርክሩ የፍርድ ውሳኔ ለወይዘሮ ሀና አድማሱ ብይን ሰጥቷል። የፍርድ አፈጻጸም ውሳኔውም ተጠሪ ሆነው ለቀረቡት ወይዘሮ የሺሀረግ ደርሷል። ይህ አፈጻጸም በወይዘሮዋ እጅ እንደገባ ‹‹አሜን›› ብለው ለመቀበል አልፈለጉም። በተራቸው ጉዳዩን አንቀሳቅሰው ቅሬታቸውን ሊያቀርቡ ከፍርድ ቤት ተገኙ።
ወይዘሮ የሺሀረግ በማመልከቻቸው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔን እንደማይቀበሉ ገለጹ። እሳቸው አዲስ የሰሩትን ቤት፣ ባህርዛፎችና ሌሎች ንብረቶች ለአመልካች እንዲያስረክቡ መደረጉ አግባብ አለመሆኑንም ጠቀሱ። እንዲህ በማድረጋቸው ተጠሪ ማዕድ ቤቱን ብቻ ለአመልካች እንዲያስረክቡ ተወሰነ።
ይህን ውሳኔ ተከትሎ አመልካች ወይዘሮ ሀና በንብረቱ ላይ የፍርድ ባለመብት መሆኔ እየታወቀ በፍርድ አፈጻጸም ወቅት ተፈጻሚ አልሆነልኝም ሲሉ ‹‹አቤት›› አሉ። በህገመንግስቱ አንቀጽ 25 እና 37 መሰረትም የእኩልነትና ፍትህ የማግኘት መብቴ ተጥሷል በሚል አቤቱታቸውን አቀረቡ።
ወይዘሮ የሺሀረግ ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት ውሳኔ በኋላ ጉዳዩን አንቀሳቅሰው እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚችሎት ተጓዙ። የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔም በአብላጫ ድምጽ ጸድቆ በእሳቸው ላይ ተመሳሳይ ውሳኔን አሳለፈ።
የቀድሞዋ ተጠሪ አሁን አመልካች ሆነው አቤቱታ ማሰማት ይዘዋል። በፍርድ ቤቶቹ የተሰጣቸው ውሳኔ በህገመንግስቱ አንቀጽ 9 ፣37፣ 27 እና 78 የተቀመጠውን ድንጋጌ የሚቃረን በመሆኑ በህጉ መሰረት የህገመንግስት ትርጉም ይሰጥልኝ ሲሉ አቤት ብለዋል።
የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄ የቀረበለት የህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ሲመክር ቆየ። በመጨረሻም ለፌዴሬሽን ምክርቤት የውሳኔ ሃሳቡን ለማሳለፍ የፍርድ ውሳኔውን መመርመር ያዘ።
ጉባኤው በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን የፍርድ ውሳኔ መመርመር እንደያዘ በዋናው ውሳኔ ተጠሪ ማዕድ ቤቱን አፍርሰው የገነቡትን አዲስ ቤት ለአመልካችዋ እንዲለቁና በቤቱ ላይ ያወጡትን ወጪ ዳኝነት ከፍለው መውሰድ ይችላሉ በሚል የተላለፈውን ውሳኔ ተመለከተ።
ተጠሪ ማዕድ ቤቱን ያስረክቡ በሚል የተሰጠው የአፈጻጸም ውሳኔ የቀድሞ ቤቱ ፈርሶ አዲስ በመሰራቱና በተጨባጭ መሬት ያለው ሌላ በመሆኑ ውሳኔውን ለመፈጸም እንደማያስችል ጉባኤው ከስምምነት ደርሷል።
ጉባኤው የፍርድ ውሳኔውን በተጨባጭ ለመመርመር ያግዘው ዘንድ ጉዳዩ ከሚመለከተው የጉለሌ ክፍለ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ጥያቄዎችን አቅርቧል። ጽህፈት ቤቱ መጋቢት 28/ 2008 ዓ.ም ለጉባኤው ጥያቄዎች የጽሁፍ ምላሽ አድርሷል።
የጽሁፉ ፍሬ ሃሳብ አመልካችና ተጠሪ በሚከራከሩበት ማዕድ ቤትና ሰርቪስ ቤት ተጠሪዋ 6 ክፍሎችን የሰሩ ሲሆን ቤቶቹ የሚገኙት ግን በአመልካችዋ 530 ካ.ሜ የመሬት ይዞታ ውስጥ መሆኑን ያስቀምጣል። ተጠሪዋ ማዕድ ቤቱን አፍርሰው አዲስ ቤት ሰርቻለሁ በሚል ሲከራከሩ ቆይተዋል። ማዕድ ቤቱንም በስጦታ ውል እንዳገኙት ደጋግመው አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ውሉ በሌላ መዝገብ ህገወጥ ነው በሚል ተሰርዟል፤ በዚህም ምክንያት ክርክሩ ውድቅ ሊሆን ግድ ብሏል።
ጉባኤው አሁንም ጉዳዮችን መመርመር ቀጥሏል። በፍርድ ሂደቱ ወቅት ለውሳኔ የደረሱ ነጥቦችን እያጣራ መለየት ይዟል። በዚህም አግባብ የዋናው ቤት አካል በሆነው ይዞታ ተጠሪ መብት የላቸውም በሚል ለቤቱ ያወጡትን ለዳኝነት ከፍለው እንዲቀበሉ በሚል የተወሰነውን ብይን እየመረመረ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አመልካች የፍርድ ባለመብት ሆነው በአፈጻጸም የተረከቡትን ቤት እንዲመልሱ መወሰኑ በዋናው ፍርድ የተሰጠውን ውሳኔ ዋጋ አልባ እንደሚያደርገው ሰፍሯል።
አመልካች በፍርድ ባለመብት የሆኑበትን ንብረት በአፈጻጻም ውሳኔ ማጣታቸው በህገመንግስቱ አንቀጽ 40 /1/ መሰረት ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ ይከበርለታል›› የሚለውን ድንጋጌ የሚቃረን ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የቀረበው አቤቱታ የህገመንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በሚል ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተስማምቶ ለፌዴሬሽን ምክርቤት እንዲቀርብ ወስኗል።
የፌዴሬሽን ምክርቤት ውሳኔ..
ምክር ቤቱ የአጣሪ ጉባኤውን ውሳኔ መሰረት አድርጎ ነጥቦቹን አንድ በአንድ ማየት ጀመረ። በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱ የህገመንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብም መረመረ። ምክር ቤቱ በማጣራት ሂደቱ የተረዳውን እውነት ሲያስቀምጥ ክርክሩ የተነሳበት ቤትና ቤቱ የተሰራበት ቦታ አመልካች ከእናታቸው በውርስ ተላልፎላቸው ያገኙት መሆኑን በማስረጃዎች ማረጋገጡን አመላክቷል።
ከዚሁ ማረጋገጫ ጋር ተያይዞ ምክር ቤቱ ባስቀመጠው ማሳያ ተጠሪዋ በቤቱና ቦታው ላይ ምንም አይነት መብት እንደሌላቸው በፌዴራል ፍርድ ቤቶቹ በማስረጃ ተረጋግጦ መስፈሩን ጠቁሟል።
ምክር ቤቱ መጨረሻ በደረሰበት መደምደሚያም አመልካች በዋናው ክርክር በፍርድ አፈጻጸም መመሪያ አመልክተው እንደፍርዱ ከተፈጸመላቸው በኋላ በተጠሪ ቅሬታ አቅራቢነት በየደረጃው የሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከህጉ ውጭ የሰጡት የአፈጻጸም ትዕዛዝና ውሳኔ አግባብ አለመሆኑን ተረድቷል።
በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመልካች በዋናው ፍርድ ባለመብት የሆኑበትን ንብረት በፍርድ አፈጻጸም መዝገብ ላይ ንብረቱን እንዲያጡ የተደረገበት ውሳኔ በህገመንግስቱ አንቀጽ 40/1/ የተደነገገውንና ዋስትና ያገኘውን የዜጎች የንብረት መያዝ መብት የሚጥስ በመሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9/1/ መሰረት ውሳኔው ተፈጻሚ ሊሆን አይገባውም በማለት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ውሳኔውን አሳልፏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013