አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ህገወጥ ንግድ ስርዓት እንዲይዝ በማድረግ በከተማዋ ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽእኖ ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ቢሮ በጋራ በመሆን ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የህግ ወጥ ንግዱ በመዲናዋ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ለመቅረፍና በቀጣይ ሥርዓት ለማስያዝ ሥራ እንደሚሠሩ ገለጹ፡፡
አቶ መስፍን አሰፋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የንግድ ዘርፍ አስተባባሪ እንደተናገሩት፤በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን ህገወጥ የንግድ ሥርዓት በተለይም የጎዳና ላይ ንግድን መስመር ለማስያዝ ደንብ ቁጥር 88/2009 እና መመሪያ ቁጥር 5/ 2010ን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አስራ አራት ሺ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በከተማዋ መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፣ በተለይም መመሪያና ደንቡ ከሚለው ውጭ ህገ ወጥ ግንባታዎችን መገንባታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ከአስሩም ክፍለ ከተማ ባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ምክክር እንደተደረገና በቀጣይም መመሪያና ደንቦችን የማስከበር ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ የጎዳና ላይ ንግዱና ህገወጥ ግንባታው በከተማዋ ገጽታ ፣ በትራፊክ መጨናነቅና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጅማሉ ጀንበር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አስፈላጊና ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ህግን ተከትሎ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
እንደእርሳቸው አባባል የሥራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ለዜጎች የሥራ ዕድል ሲፈጥር ለምን ያህል ዜጎች? በምን ያህል ዘርፍ? ምን ያህል የመሥሪያ ቦታ ያስፈልጋል? እንዴትስ ይሟላላቸዋል? የሚለው ተጠንቶ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት የመሥሪያ ቦታ የሚያስፈልጋቸው የሥራ አይነቶች ሲፈጠሩ ቦታ አዘጋጅቶ መስጠት ከቢሮው እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ፣ ማስፋፊያ የተደረገባቸውንና የአምስት ዓመት ገደባቸውን የጨረሱትን በማስለቀቅ ለሥራ አጥ ዜጎች የማስተላለፍ ሥራ እንደተሠራ ገልጸዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ህገ ወጥ አካሔድ በከተማዋ ላይ የሚፈጥረውን መጥፎ ገጽታ ለማስቀረት በቅንጅት በመሥራት ሥርዓት የማስያዝ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ጠቅሰዋል፡፡
ከተማዋ የአፍሪካ መዲናና የዲፕሎማት መናኸሪያ እንደመሆኗ ይህንን ሊመጥን የሚችል ገጽታ እንድትላበስና እየተስተዋለ ያለው የጎዳና ላይ ንግድና ህገወጥ ግንባታ በአስቸኳይ ሥርዓት እንዲይዝ ከተማ አስተዳደሩ በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አስታውሰው፤ በአብዛኛው ለሥራ ዕድል ፈጠራውም ይሁን ለኢ-መደበኛ ንግዱ ቦታ የተሰጣቸው አካላት ምንም አይነት ግንባታ ማከናወን እንደማይፈቀድላቸውም አበክረው ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከሶስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ሼዶችን ለማስገንባት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ በመግለጽ፣ የቦታ ርክክብ የዲዛይን ስራና ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ በቅርብ ቀን ወደ ተግባር እንደሚገቡም ተናግረዋል፡፡ እስከአሁንም ቁጥራቸው ሶስት መቶ የሚደርሱ ሼዶች በግንባታ ላይ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ኢያሱ መሰለ