በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ የሆነው ኦሬንጅ ኩባንያ በአፍሪካ ከሴኔጋል እና ቱኒዚያ ቀጥሎ ሦስተኛውን የአይሲቲ የልህቀት ማዕከል ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ከፍቷል ፡፡ በጎሮ በአይሲቲ ፖርክ 500 ስኩዬር ሜትር መሬት ላይ የተገነባውን የዲጅታል ማዕከል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ፣የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፤የኦሬንጅ ዲጂታል ማዕከል ኃላፊዎች እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡
የዲጂታል ማዕከሉም መተግበሪያዎችን /አፕሊኬሽን/ለሚሰሩና የፈጠራ ውጤት ያላቸው ደግሞ ወደ ምርት የሚለወጡባቸው ስልጠና የሚሰጥበት ነው።የፈጠራ ክህሎትን ከማሳደግ ባሻገር ወጣቶች በቴክኖሎጂ መስክ ልምድ እንዲያካብቱ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተመልክቷል፡፡
የዲጂታል ማዕከሉ በአንድ ጣሪያ ውስጥ የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ፕሮግራሞችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡የወጣቶች ዲጂታል እውቀት ማሳደጊያ ማዕከሉ የኮንዲንግ ማሰልጠኛ ክፍል፣ የንድፍ ስራ ማበልፀጊያና ወደ ገበያ ማቅረቢያ ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡
ማዕከል ለወጣት ኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ዕውቀትን በማጋራት የተሻለ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የራሱን ሁነኛ አስተዋፅኦና ድጋፍ ያበረክታል።አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ፣ሥራ ፈጣሪዎችን በመደገፍ እና የንግድ ሐሳባቸውን እንዲያጎለብቱ በማድረግ ብቁ የሆኑ ሐሳቦች ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የሚደግፍ ይሆናል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክ ኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደ ዲጂታል ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት እና ለዚህም ይረዳ ዘንድ መንግሥት ከፖሊሲ ጀምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
‹‹የግሉ ዘርፍ እድገት ቴክኖሎጂ ላይ መሰረት ያደረገ እንዲሆን እንፈልጋለን››ያሉት ሚኒስትሩ ፣ ለዚህም የበይነ መረብ እና ኢኖቬሽን ስነምህዳሩን መገንባት እንደሚያስፈልግ እና ይህም የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡
የማዕከሉ መከፈት እና የሚሰጠው ስልጠናም ለልምድና እድገት ወሳኝ የሆኑ ተሞክሮዎች የሚቀሰምበት እንደመሆኑ በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት ጠቀሜታው የላቀ እንደሆነ ጠቁመው፣ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሰማራቷንም አድንቀዋል፡፡ በተለይም ቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ የሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት መሰጠቱን ነው ያብራሩት ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው፣ኢትዮጵያ ባለብሩህ አዕምሮ ወጣቶች እና ቴክኖሎጂዎችን የሚደግፉ ፖሊሲዎች እንዳላትም አስረድተዋል፡፡ማእከሉም የወጣቶች የዲጂታል እውቀት እንዲዳብር፣የዲጂታል እውቀትና ልምድ ልውውጥ እንዲጎለብት እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡አገሪቱ ቴክኖሎጂን የሚያስፋፋ አሠራር ከመዘርጋት ጋር ተዳምሮም የማዕከሉ ሥራ ውጤታማ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በበኩላቸው፣ከማዕከሉ የሚፈልቁ እውቀቶች የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ግቦችን ለመደገፍ ብሎም ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚፈጥሩ አስገንዝበዋል፡፡
የኦሬንጅ መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ዋና ስራ አስፈፃሚ አሊዮኔ ናዲያ፣በዚህ ፕሮግራሙ በተለይም ወጣቱን ለመድረስ ማዕከላትን በተለያዩ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለማስፋት እቅድ እንዳለው ነው ያስታወቁት ፡፡
ማዕከሉን ወደ ሥራ ለማስገባት የኢትዮጵያ መንግሥት ከጀርመን የልማት ድርጅት /ጂ.አይ.ዜድ/ ጋር ሰርተዋል፡፡በምርቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አወር፣ ማእከሉ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ይበልጥ በማሸጋገር እና ማጎልበት በተለይ ለወጣቱ ዘርፈ ብዙ ትሩፋትን እንደሚቸር አስረድተዋል፡፡
የዲጂታል ማዕከሉ ከክፍያ ነጻ 90 በመቶ ተግባር ተኮር ሥልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል።በአሁን ወቅትም በኦሬንጅ ዲጂታል ሴንተር የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኮዲንግ ትምህርት ክፍል ውስጥ አንጉላር ስልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙ ሲሆን በተመሳሳይ በፋብላብ ሶሊዳሬ ክፍል ውስጥ የኢምቤድድ ሲስተም ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ኩባንያው በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ 18 አገራት የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ ከ128 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችም ባለቤት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2013