ይበል ካሳ
ትውልድና ዕድገት
በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ሽሮ ሜዳ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአሁኑ እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት፣ ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያለውን የሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በቀድሞው ተፈሪ መኮንን ተምሯል፡፡ ለኪነ ጥበብ ፍቅር ስለነበረው ከልጅነቱ ጀምሮ በተማረባቸው ትምህርት ቤቶች በሙዚቃና ቴአትር ክበቦች በንቃት ይሳተፍ ነበር፡፡በትምህርት ቤቶች መዝጊያ እና ዓመታዊ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሙዚቃና ድራማዎችን ያቀርብ እንደነበር ያስታውሳል:: በርካታ የህይወት ውጣ ወረዶችን በጽናት ከማለፍ ባሻገር እያንዳንዷን ፈተና ለቀጣይ ስኬት እንደመሰላል ተጠቅሞ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ደርሷል። የዛሬው የሲራራ አምድ እንግዳችን የእንድሪያስ ፊልምና ሲኒማ ባለቤት አቶ እንድሪያስ መኮንን፡፡
ችግሮችን መጋፈጥ
ወጣቱ እንድሪያስ አስራ ሁለተኛ ክፍል ካጠናቀቀ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን በመሞከር ችግሮችን በመጋፈጥ ኑሮን “ሀ” ብሎ ጀመረ፡፡ “እውነቱን ለመናገር ያልሞከርኩት ሥራ የለም” የሚለው እንድሪያስ ወደ አሁኑ ህይወቱ ከመምጣቱ በፊት “ሰው ምን ይለኛል” በሚለው የሃገራችን መጥፎ ልማድ ሳይሸበብ ሥራዎችን ዝቅ ብሎ ሰርቷል፡፡ ቡና ቤቶች ውስጥ አስተናጋጅ ሆኗል፣ የልጅነት ዝንባሌውን ተከትሎ በፊልም ፕሮዳክሽኖች ውስጥ በተላላኪነት ሰርቷል፤ “የማልረሳው ነገር በጣም ስለቸገረኝ በግለሰብ ድርጅት ውስጥ በጥበቃነት ሳይቀር ተቀጥሬ ለተወሰነ ጊዜ ሰርቻለሁ” ይላል፡፡ ንግድም ሞክሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጎን ለጎን ደግሞ በምሽት ቤቶችና በሰርግ ቤቶች እየተዟዟረ ሙዚቃዎችን በመጫወት ከልጅነቱ ጀምሮ የሚወደውንና መክሊቴ ነው ብሎ የሚያምነውን የኪነ ጥበቡን ዘርፍ ዝንባሌው ብቻ ሳይሆን መተዳደሪያ ሥራው እንዲሆንለት ሞክሯል፡፡ እጅግ ከብዙ አስቸጋሪ ውጣ ውረዶች በኋላ በመጨረሻም ተሳክቶለት እንዳሰበው የልጅነት ህልሙን ተከትሎ በጥበቡ ዘርፍ በተለይም በፊልም ፕሮዳክሽን፣ በፊልምና ትወና ጥበባት ትምህርትና በሲኒማ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ውጤታማ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ትንሽ ከሌለ ትልቅ የለም
መስረቅ እንጂ መሥራት አያሳፍርም ሰው ምን ይለኛል ሳይሉ እንዲህ ዝቅ ተብሎ በትንሹ የተጀመረው ሥራ በተለይም ዝንባሌዎቹ በሆኑት በሙዚቃና ፊልምና ቴአትር ሥራዎች ቀጥሎ በ1998 ዓ.ም አካባቢ የመጭውን ጊዜ ብርሃማነት የሚያሳዩ የተስፋ ጭላንጭሎች መታየት ጀመሩ፡፡ “በፊልም ሥራ ውስጥ ተላላኪ፣ በሙዚቃ ደግሞ ምሽት ክበቦችና ሰርጎች ላይ እየሰራሁ በነበርኩበት ወቅት በተለይም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ቀስ በቀስ ከነገሮች ጋር እየተግባባሁ መጣሁ፣ ብዙ ሰዎችን ማወቅ ቻልኩ፣ በዘርፉ ከተሰማሩ ትልልቅ ባለሙያዎች ጋርም መገናኘት ጀመርኩ፣ በዚህም ነገን የተሻለ ማድረግ እንደምችል እየተገነዘብኩ ተስፋን እየሰነቁ መጣሁ፣ ከሰዎች ስር ስር እየተከተልኩ 1999 ላይ ትንሽም ብትሆን የራሴን ምሽት ክበብ ለመክፈት በቃሁ” በማለት ያስታውሳል ፡፡
ከሌሎች ሰዎች ጋር በመዋጮ ሀያ ሁለት አካበቢ የከፈተው ምሽት ቤት ስሙም “ኢቫንጋዲ” ይባል ነበር። እዚያ መንገድ እየተሰራ በነበረበት ወቅት ከጥቂት ጊዜ በኋላ በምሽት ቤቱ ሊዝናና ከሰበታ በመጣ የእንድሪያስ ጓደኛ አማካኝነት ስለነ እንድሪያስ ጥረት የሰሙ በሰበታ ከተማ ውስጥ “አሴና” የሚባል የታወቀ ምሽት ቤት ያላቸው ጥላሁን የሚባሉ አንድ ባለሃብት ወደ ኢቫንጋዲ መጡና “ለምን እዚህ መጥታችሁ አትሰሩም? የሚል ግብዣ አቀረቡላቸው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ያኔ በጊዜው ሰበታ ከተማ ውስጥ ብዙ ምሽት ቤቶች ስለሌሉ እነእንድሪያስ እዚያ ሄደው ቢሰሩ ከአዲስ አበባው የበለጠ መሥራትና ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ የሚል ነበር፡፡
ትልቅ የመሆን ጽኑ ፍላጎት
“አንተ መሆን የምትፈልገውን ነገር ከልብህ ወደኸው ጽኑ ፍላጎት ኖሮህ በተግባር መጣር በምትጀምርበት ጊዜ ፍላጎትህ እንዲሳካ መላው ዓለም ከአንተ ጋር አንድ ላይ ያሴራል” ይላል ታላቁ የምንጊዜም ምርጥ ሽያጭ መጽሐፍ የ“ዘ አልኬሚስት” ደራሲ ፓውሎ ኩዊንልሆ:: ምክንያቱም የሰበታው “የአሴና ምሽት ቤት” ባለቤት አቶ ጥላሁን በነገሯቸው መሰረት የእርሳቸውን ግብዣ ተቀብለው ሰበታ ሄደው የራሳቸውን ምሽት ቤት ከፍተው መሥራት የጀመሩት እነ እንድሪያስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ ያስገኘላቸውን ውጤታማ ሥራ መስራት ቻሉ፡፡ ለቀጣይ ዕቅዳቸው መተግበሪያና ለረጅም ጊዜ ራዕያቸው ማስፈጸሚያ መነሻ የሚሆን በቂ ገንዘብ አገኙ፡፡ ቤትም የመስሪያ ዕቃዎችንም ተከራይቶ ይሰራ የነበረው እንድሪያስ አሁን የሚሰራው በኪራይ ቤት ቢሆንም የመስሪያ ዕቃዎችን ግን ገዝቶ መሥራት ጀመረ፡፡ “እዚያ ጋር ነው የእኔ ህይወት መለወጥ የጀመረው፤ ዝቅ ብዬ መስራቴ ሳያሳፍረኝ፣ ያ ሁሉ ችግር ሳይበግረኝ ራዕዬን ተከትዬ እስከመጨረሻው በዓላማዬ ጸንቼ መቀጠሌ እና የሰበታው ሰውዬ ያመጡልኝ መልካም ዕድልና ያደረጉልኝ ቀና ትብብር ነው ህይወቴ የተለወጠበትን አጋጣሚ የፈጠረው” በማለት ነው እንድሪያስ ያችን ቀን የሚያስታውሳት፡፡
አዲስ ምዕራፍ፤ የበለጠ ፈተና
አሁን የእንድሪያስ ጉዞ ከበፊቱ ይበልጥ በአዳዲስ ፈተናዎች ታጅቦ ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል:: የሰበታው የምሽት ቤት ሥራ ለስምንት ለዘጠኝ ወራት ጥሩ ከተጓዘ በኋላ በመጠጥ ግፊት ከሚፈጠሩ የወጣት ደንበኞች አምባጓሮ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ተደጋጋሚ ችግሮች ምክንያት በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ማስከተል በመጀመሩ በፀጥታ አካላት ትዕዛዝ ሊዘጋ ግድ ሆነ፡፡ሆኖም በሰበታ የነበራቸው ቆይታ አጭር ጊዜም ቢሆን እንድሪያስና ጓደኞቹ በደንብ ሰርተው ጠቀም ያለ ገንዘብም ማግኘት ችለው ስለነበር ሥራቸው በመቋረጡ አልተጎዱም፡፡ እንዲያውም እንድሪያስ በዚህ ሥራ ያገኘውን የተሻለ ገንዘብ እንደ መነሻ ተጠቅሞ ድሮም ይፈልገው የነበረውን የፊልምና የሙዚቃ ሥራ በተደራጀ መንገድ እንደ አዲስ መጀመር ችሏል፡፡ ባገኛት ገንዘብ በመንቀሳቀስ ቀጥታ ወደ ፊልሙ ሥራ ገባ፡፡ በፊት ይሞካክራቸው የነበሩ የፊልም ጽሁፎችን ቀደም ሲል ለተዋወቃቸው በዘርፉ ለሚሰሩ ጓደኞቹና አንዳንድ ባለሙያዎች ሲያሳያቸው ይበልጥ አበረታቱት፡፡ ከ1999 ዓ.ም ክረምት መጨረሻ ጀምሮ ጥቂት የማይባሉ ወሮችን እልህ አስጨራሽ ተግዳሮቶችን ሲጋፈጥ ከቆየ በኋላ በመጨረሻም ተሳክቶለት የካቲት 12 ቀን 2000 ዓ.ም የመጀመሪያ ፊልሙን “ጉራማይሌ”ን ማስመረቅ ቻለ፡፡
“ሥራው እንደታሰበው ቀላል አልነበረም:: ከበፊቱ የበለጠ በህይወቴ እጅግ ከባዱን ፈተና የተጋፈጥኩበት ነው፡፡ ፊልሙን ስጀምር ሰማንያ ሁለት ኪሎ ግራም የነበርኩት ስልሳ አራት ኪሎ ሆኜ ነው የጨረስኩበት፡፡ ከባድ መስዋዕትነት ከፍየበታለሁ፤ ሆኖም አይቆጨኝም በዚያው ልክ ብዙ ነገሮችን ተምሬበታለሁ፤ ትዕግስትን፣ ጽናትን፣ ጠንክሮ መስራትን አውቄበታለሁ፡፡ እንዲያውም አሁን ያለው ማንነቴ በደንብ የተቀረጸው ያኔ ነው ብዬ አስባለሁ፣ በመሆኑም በህይወቴ ሌላ አዲስ በር የተከፈተበት ወሳኝ ምዕራፍ ነበር ማለት እችላለሁ”::
ለቀጣዩ ስኬት መስፈንጠሪያ
ፈተናው ቢበረታም “ጉራማይሌ” የተባለው የመጀመሪያ ፊልሙ መመረቁ ወደፊት የሚወስዱ መልካም ዕድሎችንም ይዞ መጣ፡፡ ታላቁ አሜሪካዊ የሥነ ልቦና የስብዕና ዕድገት ሊቅ አንቶኒ ሮቢንስ እንዳለው ሰዎች ውድ ሃብቶቻችን ናቸውና የመጀመሪያ ፊልሙ ለምርቃት ከበቃችለት በኋላ ከብዙ አዳዲስ ሰዎች ጋር የሚተዋወቅበት ዕድል ተፈጠረ፡፡ በእንድሪያስ የህይወት ጉዞ ሁለተኛው ወሳኝ ምዕራፍ ሆኖ የተከፈተው በር ሌሎች ተከታታይ በሮችን መክፈት ጀመረ፡፡ ከዓመት ቆይታ በኋላ “አልተዋትም” የተባለ ሁለተኛ ፊልሙን አሳተመ፡፡ ከዚያም ከ2002 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት “እንዳልስምሽ”፣ “በሰርጌ ዋዜማ”፣ “ስወድሽ”፣ “ዓይኔ”፣ “የዜግነት ክብር”ን የመሳሰሉ ከዘጠኝ በላይ ፊልሞችን በተከታታይ ማሳተም ቻለ፡፡ ፈተናን ወደ መልካም አጋጣሚ እየቀየረ፣ ስኬት ስኬትን እየወለደለት በዚህ መልኩ ወደፊት መገስገስ የቻለው እንድሪያስ በዘርፉ በቂ ልምድ እያገኘ ሲመጣ አሁን ራሱን መጠየቅ ጀመረ::
እንድርያስ ከበፊትም ጫማ ፋብሪካ ጫማ፣ ልብስ ፋብሪካ ልብስ እንደሚያመርተው ሁሉ በመደበኛነት ፊልሞችን የሚያመርት የፊልም ኩባንያ ለምን አይኖረኝም የሚል ራዕይ ነበረው፡፡ በዚህ ላይ ፊልሞቹን የሚሰራው በየቦታው እየተዘዋወረ የፕሮዳክሽን ቤቶችን እየተከራየ በመሆኑ በዚህ የተነሳ 2009 ዓ.ም ላይ “አልተዋትም” የተባለውን ፊልሙን በሰራበት ወቅት ሁለቴ ጠፍቶበት እጅጉን አዝኖ ስለነበረ አጋጣሚው “ፕሮዳክሽን ቤት መክፈት” የሚለውን ሃሳብ የበለጠ እንዲገፋበት ስላደረገው ከእህቱና ከቅርብ ጓደኞቹ ጋር ተመካክሮ የመጀመሪያዋን የፊልም ስቱዲዮ ወይንም ፕሮዳክሽን ቤት ስድስት ኪሎ አካባቢ ተከራይቶ ከፈተ:: ያች የመጀመሪያዋ የእንድሪያስ ፊልም ፕሮዳክሽን ስቱዲዮ በአንዲት ኮሞፒውተርና በ50 ሺህ ብር በብድር በተገዛች ሌንስ የሌላት ካሜራ የምትሰራ ነበረች፡፡ በዚያ መንገድ የተጀመረው የፊልም ፕሮዳክሽን ሥራ አሁን ላይ ግን እያንዳንዳቸው ከመቶ ሺህ ብር በላይ ዋጋ ባላቸው ከስልሳ በላይ ዘመናዊ ካሜራዎችን ያቀፈ በእንድሪያስ አባባል ሚሊዮኖችን የሚያንቀሳቅስ በከተማው ውስጥ አለ የሚባል ግዙፍ ስቱዲዮ ሆኗል፡፡
ይሁን እንጂ ከስቱዲዮው ወይም ከፊልም ፕሮዳክሽን ጋር ተያይዞ ይገጥመው የነበረውን ችግር የራሱን በመገንባትና በራሱ ባለሙያዎች ተጠቅሞ ፊልሞችን መስራት ሲጀምር በዘርፉ ካለው አስተሳሰብና ከተዋናዮቹ ሌላ ፈተና ገጠመው:: ከዚህ ቀደም በገበያው ላይ የነበሩ ታዋቂ ሰዎች ካልተሳተፉበት በቀር በአዳዲስ ባለሙያዎች የሚሰሩ ፊልሞችን የሚያስተናግድ አስቻይ ሁኔታ ጠፋ፡፡ በችግሮች ተስፋ ቆርጦ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ፋንታ በየጊዜው የሚገጥሙትን ፈተናዎችን ወደ መልካም በመቀየርና ለቀጣይ ስኬት እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም እዚህ ደረጃ የደረሰው ባለ ራዕዩ እንድሪያስ ግን ከዚህ ተግዳሮት ላይ ተነስቶ አሁንም ሌላ ስኬት ለማስመዝገብ አሰበ፡፡ እናም “ተመልካቹ በአዳዲስ ሰዎች የተሰሩ ፊልሞችን ማየት የማይፈልገው ችሎታና ልምድ ያጥራቸዋል በሚል ነው” የሚለውን አስተሳሰባዊ ተግዳሮት ለመሻገር እርሱ በሚሰራቸው ፊልሞች ላይ የሚሳተፉ አዳዲስ ተዋንያንን በዕውቀትና በክህሎት አብቅቶ የሚያፈራ “የፊልም አካዳሚ” መገንባትን በመፍትሔነት አቀረበ፤ ተሳክቶለትም በ2010 ዓ.ም “እንድሪያስ የፊልም አካዳሚ” ሰባ ደረጃ አካባቢ ከፈተ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከሁለት መቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ የፊልም ሙያዎች በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
አሁንም ሌላ ተግዳሮት መጣ፡፡ “ብታስተ ምራቸውም፣ ክህሎትና ብቃት ቢኖራቸውም በአዲስ ባለሙያዎች የተሰራ ፊልምህን ማን ያይልሃል” ተባልኩ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ከመደናገጥና ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አሁንም ችግሩን ወደ ሌላ ስኬት ሊፈነጠርበት አሰበ፣ “ለምን የራሴን ሲኒማ ቤት አልከፍትም” ብሎ አቀደ፤ አደረገውም፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ጀሞ ሚካኤል ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ “እንድሪያስ ሲኒማ” በሚል የራሱን ሲኒማ ቤቶች ከፍቶ በራሱ ትምህርት ቤት የተማሩ፣ በራሱ ባለሙያዎች፣ በራሱ ፕሮዳክሽን የተሰሩ የራሱ ፊልሞችን በራሱ ሲኒማ ቤቶች ማሳየት ጀመረ፡፡
እንድሪያስ በአሁኑ ሰዓት ሰባት የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖች፣ አንድ ግዙፍ ዘመናዊ ፊልም ፕሮዳክሽን ስቱዲዮ፣ ሁለት ባለ መቶ ሃምሳ ወንበር ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶች፣ ሁለት መቶ ተማሪዎችን እያስተማረ የሚገኝ አንድ የፊልም ትምህርት ቤት በአጠቃላይ በገንዘብ ሲተመኑ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዋጋ ያላቸው ኢንቨስትመንቶች ባለቤት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ግን ከመጨረሻው ህልሙ ለመድረስ ነው፤ እርሱም አሁን ባለው ላይ ልክ እንደነ ሆሊውድ የፊልም መንደርን ጭምር ያለው ሁሉንም በአንድ አቅፎ የያዘ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ አንድ ግዙፍ የፊልም ካምፓኒ መመስረት ነው፡፡ እኛም ለእንድሪያስ ህልም መሳካት እንመኛለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013