አዲስአበባ፡- በሜቴክ እንዲገነቡ ውል ተይዞላቸው የነበሩ ሶስት ፋብሪካዎች ወቅቱን ጠብቀው ባለመጠናቀቃቸው ከ9 ነጥብ4 ቢሊየን ብር በላይ ለሆነ ኪሳራ እንደዳረገው የስኳር ኮርፖሬሽን ገለፀ።
በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ሜቴክ ይዟቸው የነበሩት ጣና በለስ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት እንዲሁም ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ በኮንትራት ውሉ መሰረት በ18 ወር ውስጥ በ2006 አጋማሽ መጠናቀቅ የነበረባቸው ቢሆንም እስካሁን አልተጠናቀቁም።
ፋብሪካዎቹ በውላቸው መሰረት ተጠናቀው ስራ ባለመጀመራቸውም ከ2006 እስከ 2010 ባለው ጊዜ ኮርፖሬሽኑ ሊያገኘው ይችል የነበረውንና ፕሮጀክቶቹ ከመዘግየታቸው ጋር ተያይዞ ለተጨማሪ ወጪ በመዳረጉ በአጠቃላይ ከ9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ለኪሳራ ተዳርጓል።
ፋብሪካዎቹን ለመገንባት ከሜቴክ ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰው በኢትዮጵያ ብር የሚከፈል ሆኖ ለእያንዳንዱ ፋብሪካ 235 ሚሊየን 772 ሺ 160 የአሜሪካ ዶላር ነበር። ከዚህም ውስጥ ለጣና በለስ ቁጥር አንድ 257 ሚሊየን 34 ሺ 424 ዶላር፤ ለጣና በለስ ቁጥር ሁለት 192 ሚሊየን 779 ሺ 336 ዶላር እንዲሁም ለኦሞ ኩራዝ አንድ ፕሮጀክት 236 ሚሊየን 97 ሺ908 ዶላር ለሜቴክ ተከፍሏል። ይሁንና ፋብሪካዎቹ ሳይጠናቀቁ በጀቱ በማለቁ ተይዞ የነበረው ውል ተቋርጧል።
በሀገሪቱ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ወደ 50 በመቶ እንዲያድጉ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት ገለጻ አስታውቀዋል።በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ ግንባታዎቹን ለማስቀጠል የሚያስችለውን ጥናት ያጠናቀቀ በመሆኑ ከባንኮች ብድር ለማግኘት እንዲችል ጥያቄውን ለመንግስት የሚያቀርብ ይሆናል። ብድሩ ተሳክቶ ገንዘቡ ከተለቀቀም ከስድስት እስከ ስምንት ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ፋብሪካዎቹ ተጠናቀው ወደ ስራ የሚገቡ ይሆናል ሲሉም አቶ ጋሻው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ