ተገኝ ብሩ
ባሻዬ ላማረ ምላሽ የተስተካከለ ጥሪ መሰረት መሆኑን ፈፅሞ እንዳትዘነጋ።“ማን አንተ” ብለህ ጠርተህ “ወዬ”ን ከጠበክ አንተ የማይጠበቅ የምትጠብቅ፤ ያልገባህ ነህ፤ እመን።አንድ ከበደ የተባለ ጓደኛህን ከቤ ብለህ ስትጠራውና ክብደቱን ረስተህ አንተ ብለህ በምትጠራው ጊዜ ምላሽ የሚሰጥህ በጠራህበት አግባብ ነው።ከብዬ ስትለው “ወዬ” አንተ ብለህ ስትጠራ ደግም “ኧ…ምንድነው?” እንደሚልህ ቅንጣት ታህል አትጠራጠር።የአፍህን ፍሬ ነው የምትበላው።ከአፍህ የሚወጣው መልካም ንግግር ለጆሮህ የሚጥም ምልካም ምላሽ ያሰጥሀል፡፡
ውዶቼ አንዳንድ ስሞች በጣም እንደሚያስገርሙኝ ከዚህ በፊት በጻፍኩት አንድ መጣጥፌ ላይ መግለፅና የሚያስገርሙኝ ስሞችና ትርጓሜያቸውን ማንሳቴን አስታውሳለሁ፤ ግድ የለም የእናንተን ማስታወስ አልጠብቅም ፤ስንቱን አስባችሁት ስንቱን አስታውሳችሁት ትችላላችሁ ጎበዝ ።ዛሬም ከስም ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነገሮችን እያነሳን እንድንጫወት ፈልጌያለሁ።
አንዲት ጓደኛ ነበረችኝ ፤የሺ ትባላለች።በእርግጥ ሰሞኑን አግኝቻት ወይዘሮ የሺ ማለት ሁሉ ቃቶኝ ነበር።እነሱ ሰፈር ኑሮ አልተወደደም መሰለኝ ሰፍታለች፤ወዝታለችም።ብቻ የምቾት መገለጫ ውፍረት ፣የድሎት መገለጫ መፋፋት ይመስለን የለ ፤አዎ ብንሳሳትም ነው ብለናል።እናም ተመችቷታል መሰለኝ ትልቅ ሰው መስላለች።
ለነገሩ የእሷ እድሜ ወዲህ ነው እንጂ እንደ አጠቃላይ ያንን አንዲያ ማለት ያስችግራል፡፡ሰው ከአርባ አመት በላይ ሲሆን መወፈር ይጀምራል የሚሉ አሉ።አልወፍር አልኩ ብለህ አትጨነቅ ከአርባ በኋላ ታየዋለህ የሚሉ ያጋጥማሉ።ምክንያቱ ምናልባት ከጤና ጋር ሊያያዝ ይችል ይሆናል፡፡
ከዚህች የቀድሞ ጓደኛዬ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ያለሰፈርዋ ያገኘኋት ለምን እንደሆነ ጠየኳት ፤ስሟን ልታስቀይር ከፍርድ ቤት እየተመለሰች መሆኑን ነገረችኝ።ወላጆችዋ ያኔ ውድ ሆኖ በናፍቆት የሚጠበቀው ሺ ለልጃቸው ውድ ብለው አውጥተውት ዛሬ የስሙ መጠሪያ የሆነችው ላይ ደርሶ ረከሰና የሺ መባልዋን ጠላችው፡፡
ለምን ስምሽን መቀየር ፈለግሽ አልኳት? አስፈላጊነቱ ስላልገባኝ ለማወቅ።አይ “እንዲሁ ደብሮኝ ነው” ነበር ምላሽዋ።በመጨረሻም ካሁን በኋላ ስሜ ሜላት ሆኗልና ሜላት ብለህ ጥራኝ ስትል አስጠንቅቃኝ ተሰነባበትን፡፡ከዚህች ወዳጄ ከተለያየሁ በኋላ ብዙ አሰብኩ፤ ስምና አሰያየማቸው።በእርግጥ ስሞች ከመጠሪያነት ባለፈ ያላቸው ፋይዳ እምብዛም አይደለም።ግን ደግሞ ለጠሪው የቀለለ ለተጠሪው ደግሞ የተሻለ ትርጓሜ ያለው ስም ደስ ያሰኛል።
አባቶች ለልጆቻቸው የሚያወጡት ስም እጅግ በጣም ተጠንቅቀው ነው፤ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ እንዲሁም ለእነሱ የተለየ ትርጉም እንዲሰጥ ገጠመኛቸውን ኑሯቸውን ተመርኩዘው ስም ያወጣሉ።ወላጆች በራሳቸው ለልጆቻቸው የሚያወጡት ስም በልጆቻቸው አንዳንዴ ላይወደድ ይችላል።ለምሳሌ ከላይ የጠቀስኳት ወዳጄ በወላጆችዋ የተቀመጠላትን ስም ጠልታ በራስዋ ለውጣዋለች።ስምዋን ጠልታ መለወጧ ተገቢ ነው አይደለም የሚለው አይደልም መነሻዬ፤ ግን ደግሞ ሰዎች ስማቸው የተለየ ተፅዕኖ እንደሚፈጥርባቸው መገመት አይከብድም።
ድሮ ድሮ ኑሮ ሳይወደድ፤ ዘመን ሳይለወጥ ብር በተወደደበት ጊዜ ሺዎች እሩቅ በሆኑበት፣ ሚሊዮኖች አልፎ አልፎ እንጂ እንደዛሬ ቀለው በማይጠሩበት ዘመን የወጡ ስሞች እነ ብሩ፣ የሺ፣ ሺብሬ፣ ሺበሺና ሚሊዮንና የተሰኙ ስያሜዎች ዛሬ ላይ እንዴት ታዩዋቸዋላችሁ።ብር ቃሉ ሺ ረክሶ ሚሊዮን ተራ በሆነበት ዘመን ላይ የተወደደ ነገር ተብሎ ስም የተሳጣቸው ሰዎች ስማቸውን እያስቀየሩ ይሆን እንዴ፡፡
ትናንት ሚሊዮን ያልነው ልጃችን ዛሬ ላይ ሚሊዮን ረክሶ ስናይ ቅር ብሎን ለልጃችን ስም ቀይረን ቢሊዮን አንለው ነገር ችግር ነው።እሱም እየተደረሰበት ነው፤ትሪሊዮንም ከትምህርት ቤት ወጥቶ መጠራት ጀምሯል።ስያሜውም ወደዚሁ አይሄድም አይባልም።
በእርግጥ ሰው መጠሪያ ስሙን የመቀየር ሙሉ መብት አለው። የሚቀይረው ስም ለመቀየር የሚያበቃ ምክንያት ደረጃ እንጂ ከባድና ቀላል የሚሆነው ለመቀየር የሚያስችል መንገዱ ከባድ አይደለም፡፡አሁን አሁን ወላጆች ለልጆቻቸው ተገቢ ብለው የሚያስቡት አልያም ደግሞ ሲሰሙት ለጆሮ ደስ የሚላቸውን ስያሜ ያወጣሉ።ነገ ልጆቹ አድገው ስሙን ይወደዱት አልያም ይጥሉት ዛሬ ላይ ግድ አይሰጣቸውም፡፡
አይቻልም እንጂ አንዳንዴ ምን አስባለሁ መሰላችሁ፤ ሰው ተግባርና ባህሪው ከተለየ በኋላ ስም ቢወጣለት እላለሁ።ውዶቼ እስኪ አንድ ነገር ላንሳ።እራሱን እንኳን ያልቻለን ሰው “የሺጥላ” ተብሎ ሲጠራ ብትሰሙ አይደንቃችሁም? ቀጣፊ፣ ሌባና ውሸታም የሆነ ሰው “ታማኝ”ተብሎ ቢጠራስ አትደመሙም? ልክ በዚህ መልኩ ስያሜና ተግባር መጠሪያና ስብዕና ተራርቆም ሊገኝ ይችላል፡፡
የሰው መጠሪያ ስያሜ ላይ አተኮርን እንጂ የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት ስምና መጠሪያቸው ደጋግመው ሲቀይሩ ይታያል።የተቋማት ስም መቀየር ለተቋሙ የሰውን ያህል አይቀልም።ቀድሞ በመልካም ስሙ ይታወቅ የነበረ ተቋም ስሙ ቢቀይር የድሮ ስሙን እንጂ የለወጠው በብዙዎች ዕውቅና ስለማይኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ይደርስበታል።በአንፃሩ ደግሞ ድሮ በሚጠራበት ስሙ የተወገዘ አንድ ተቋም ስያሜውን ብቻ ቀይሮ በአዲስ መልክ ለደንበኞቹ የተሻለ አገልግሎት ሰጥቶ በመታደስ የአዎንታዊ አጋጣሚው ተጠቃሚ ይሆናል።በህግ ረገድ የተቋም ስም መቀየር የሰው ስያሜን የመቀየር ያህል አይቀልም።
ትናንት በተለያየ ምክንያት ተገፍቶ ያወጣው የድርጅቱ ስም ዛሬ ላይ ሲጠራ ጥሩ አይደለም ብሎ የሚያስብ የድርጅቱ ባለቤት ስሜን ልቀይር ብሎ ቢያስብ የሚያጣው ብዙ ነው።ያ ስያሜው ያተረፈለት ብዙ ነገር ነበር።ዛሬ ደግሞ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር አልሄድ ብሎት ሊቀይር ቢያስብ ትናንት የተከለው ስሙ ሁሉ ይፈርሳል።ስም የተቋምን ያህል የግለሰብ ማንነት የመግለፅ አቅም የለውም።አንድ ሰው ስሙን ስንጠራ ከስሙ ጋር የተራራቀ የማይገልፀው አይነት ሰው ሆኖ ልናገኘው እንችላለን።የተቋማት ስም ግን በስያሜያቸው ብቻ ተነስተን ተግባርና ስራቸውን መለካት ሀላፊነታቸውን መለየትም እንችላለን፡፡
ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች መነሻነት ለአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ስያሜው ምን ያህል ከራሱ ጋር እንደሚገናኝና እንደሚለያይ ተመልክተናል።በስያሜ አሰጣጥ ላይ ጥልቅ የሆነ ጥናት ማድረግ ቢፈልግም እኛ ለልጃችን አልያም ለምናቋቁመው አዲስ ድርጅት ስያሜ ስንሰጥ ትርጉም ሰጪ ለመጥራት የሚቀልና ሲጠሩትም ደስ የሚል ቢሆን ጥሩ ነው።ስለምናወጣው ስም ማሰብ የሚኖርብንም ለዚሁ ይመስለኛል።አበቃሁ ፤ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013