ታምራት ተስፋዬ
ቀረብ ብሎ ለተመለከታት ገፅታዋ ህይወት እንዳልተመቻት ፣ ኑሮ እንዳደቀቃት እና እንዳንገሸገሻት ይመሰክራል፡፡ የውብ ዳር አሸናፊ ትባላለች፡፡አዲስ አበባ ከተማ የካ አባዶ ጂ ሰቭን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የነዋሪዎችን ልብስ በማጠብ ትተዳደራለች፡፡ በዚህ ስራዋም የሶስት ልጆቿን ጉሮሮ ለመድፈን ሁሌም ትታትራለች። ከአድካሚ ስራዋ የምታገኘው ገቢ በአንፃሩ የኑሮ ቀዳዳዋን ሸፍኖላት አያውቅም፡፡ ‹‹ምኑን ከምኑ አብቃቃዋለሁ›› የሚለውም የሁልጊዜ ጭንቀቷ ነው፡፡
ወይዘሮ የውብ ዳር አልወርድም ብሎ የተሰቀለው እና ከልካይ ያጣው የዋጋ ንረትን የሃሣብና፣ የሰቀቀንዋ ዋነኛ ምክንያት ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ገበያው በሰዓታት ውስጥ የዋጋ ልዩነት እያሳየ መጥቷል፤የኑሮ ውድነቱ ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ በዚሁ ከቀጠለ የእርሷም ሆነ የቤተሰቧ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ጥርጥር የላትም። እናም መፍትሄ የሚሰጠው አካል ዝም አይበል ስትል ትማጸናለች ።
በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አየር ጤና አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ታደሰም፣ ‹‹በአሁን ወቅት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ በመካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚባሉ ዜጎች ጭምር ኑሮን መቋቋም አቅቷቸዋል›› ሲሉ ይናገራሉ። እያንዳንዱ እህልና ሸቀጥ ከሀገር ቤት እየታፈሰ የኑሮ ውድነቱ ማሻቀቡ ከምን የመነጨ ነው ሲሉ ይጠይቃሉ ። ሀይ ባይ ጠፍቷል ሲሉ ያማርራሉ።
እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ፣አሁን ባለው የተመሰቃቀለ የግብይት ሥርዓት ምክንያት ዜጎች ተገቢ ያልሆነ መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው። ምንም ዓይነት አሳማኝ የሆኑ ምክንያቶች ሳይኖሩ መሠረታዊ የሆኑ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋቸው አልቀመስ ብሏል።
ምርትን በመደበቅና በገበያ ላይ ያሉ ምርቶችን በመሰብሰብ የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር የኑሮ ውድነቱን በማጋጋል፣ሕዝቡ በኑሮ ውድነት ምክንያት ለብሶት እንዲነሳ የመግፋት ፍላጎት ያለ የሚመስል ነገር መታዘባቸውን ይገልፃሉ። በሕገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኙ ምርቶችም ለዚህ እሳቤያቸውን በቂ ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ።
በኮንትሮባንድና ሕገወጥ ግብይት ላይ መልካም የሚባሉ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረጉ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሩ ገና መፍትሄ ያላገኘ በመሆኑ መንግስት በሕገ ወጦች ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት ይመክራሉ ። ‹‹ጉዳዩ ፈጣን እልባት ካልተሰጠው የዜጎች የመኖር ህልውና ይበልጥ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነዋሪ ሆኑት ወይዘሮ አለም ይሑንም፣የኢትዮጵያ ገበያ እና ግብይት ምህዳር ህገ ወጥነት የነገሰበት፣የተመሰቃቀለና ኋላቀር ከሆነ ዓመታትን እንዳስቆጠረና በተለይ በአሁን ወቅት ችግሩ አግጦና አፍጥቶ መታየት መጀመሩን ይገልፃሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ አለም ገለፃ፣በአሁን ወቅት ነጋዴው ሰው እየመረጠ የሚሸጥ አድሎኛ ሆኗል። ሲፈልግ ይሸጣል፣ ካልተመቸውም ‹‹የለም›› ይላል። በአጠቃላይ በገበያና የግብይት ስርዓቱ መተማመን የጠፋበት ሁኔታ ተበራክቷል።
‹‹በግብይት ወቅት ስለዕቃው ጥራት መጠየቅ ፈፅሞ የተከለከለ ይመስላል። ዋጋ መከራከር አይታሰብም። አማርጦ መግዛት የሚሆን አይደለም። የሸቀጦቹን ዋጋ በግልጽ በሚታይ ስፍራ አይለጥፍም። በየአካባቢው ተቆጣጣሪዎችን መመልከት ብርቅ ባይሆንም የገበያ ብልሽትን ለማስተካከል ብሎም የሸማቾችን መብት መሆን ባለበት እና በሚፈለገው ልክ የሚያስከብር ወገን አንድም አይገኝም። ›› ሲሉ ይናገራሉ ።
የገበያውን ብልሽት ያረጋጋሉ የተባሉት የሸማች ማኅበራት ሱቆች እንኳን ደሃውን ሊታደጉ ራሳቸውንም በስርዓት እንዳልተዋቀሩ የሚገልፁት ወይዘሮ አለም፣ አንዳንድ ማህበራትም ከዓላማ እና ተእልኮ ውጭ በስውርና በጅምላ ለጥቅም ተጋሪያቸው ነጋዴዎች ምርቶችን አሳልፈው እንደሚሸጡም ይጠቁማሉ፡፡
‹‹በዚህ መንገድ የማህበራቱ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በሙስና መዳከም ብሎም በቸርቻሪና አገልግሎት ሰጭ ነጋዴ የሚፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ለሕዝቡ ምሬትና መንገፍገፍ ትልቁን በር ከፍታል› ›የሚሉት ወይዘሮ አለም፣መንግስት የዋጋ ንረቱ ከዚህም የበለጠ እንዳይባባስ ህገወጥ ነጋዴዎችን አደብ ከማስያዝ ባሻገር የሸማች ማኅበራት ሱቆች ላይ የተሰገሰጉ አንዳንድ ለሕዝብ ሳይሆን ለግል ጥቅም የሚስገበገቡ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል›› ሲሉ ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ መፍትሄ የሚሉትን ሲጠቁሙም፣መንግስት ሸማቹን ሕዝብ ለመታደግና ከዕለት ገቢው ጋር ከማይጣጣም ጫና ለማዳን እንዲቻል የንግድ ስርዓቱንና ግብይቱን ፈር ከማስያዝ ጀምሮ በመረጃ ላይ ተመስርቶ ሕጎችን ማስፈጸምና መቆጣጠር፣ሕዝቡም ሕገወጥ የንግድ ተግባራትን ሲያስተውል ለፖሊስና ለሚመለከታቸው አካላት በመጠቆም ትብብሩን በተግባር ማሳየት እና ራሱን ማዳን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ከሁሉም በላይ ገበያው ተገቢውን ቁጥጥር የሚደረግበት፣ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ የሚወሰድበት፣ እሽሩሩ የማይባልበት ሆኖ በተቀናጀና በተሳለጠ አግባብ እንዲመራ ከሁሉ በላይ አገሪቱ የወጡ የንግድና የገበያ ሕግጋትን አጥብቆ መተግበርና ማስተግበር የግድ ይላል። በተለይ ሆን ብለው ምርት የሚያከማቹት ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል የሚል ጠንካራ ምክረ ሀሳባቸውንም ለግሰዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የዋጋ መናር ችግሩ ከምንጩ ከመለየት ጀምሮ የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አሳውቋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ንረት በመፍጠር ሕዝቡን ሲያማርሩ በነበሩ 30ሺ የንግድ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ከቀናት በፊት ተናግረዋል፡፡
ከቀናት በፊትም በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በተለይ በሐረማያ ወረዳ አዴሌ ከተማ በሚገኝ 3 መጋዘኖች ውስጥ ግምቱ 30 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ከ34ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ 1ሺህ 850 ኩንታል ሩዝ፣1ሺህ 450 ኩንታል ማካሮኒን፣ 300 ኩንታል ዱቄትና ሌሎችም የምግብ ሸቀጦች ተከማችቶ ተገኝቷል። የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ዘይትና የተለያዩ የምግብ ፍጆታቸውን አከማችተው የተገኙ 197 የነጋዴ መጋዘኖች እንዲታሸጉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ጀሞ አካባቢ በአንድ መጋዘን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ጀሪካን ዘይት መገኘቱ ይታወሳል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ከቀናት በፊት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት፣ መግለጫ፣ መንግስት አሁን ያለውን የዋጋ ንረትና ገበያውን ለማረጋጋት የሚያስችል የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለመንግስት ድርጅቶች በማቅረብ እንዲከፋፈል ማድረግ ከመፍትሄዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር እዮብ፣ምርቶቹን አለ በጅምላ እና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት መጋዘኖች በማስገባት የማከፋፈል ስራ እንደሚከናወንና ከዚህ በፊቱ በተለየ መልኩ መንግስት ጣልቃ በመግባት በክፍፍሉ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ነው የገለጹት ።
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2013