በ1888 ዓ.ም በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የዓድዋ ድል የተገለፀው ጥበብ፣ ፍቅርና ወኔ የሰው ልጆች ሁሉ እኩል የሰውነት ክብር ያላቸው እንጂ ነጭ ስለሆነ ከሰው ሁሉ የበለጠ፤ ጥቁር መሆኑ ደግሞ ዝቅ ያለ እና ለነጭ የሚገዛ አፈጣጠር ያለው አለመሆኑን በተግባር ማሳየት አስችሏል:: በእብሪት ተወጥሮ አህጉር አቋርጦ በጥቁሮች ላይ የበላይነትን ለመጨበጥ እየገሰገሰ ከዓድዋ ተራሮች የደረሰው ፋሺስት አንገቱን ደፍቶ እንዲመለስ አድርጓል::
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም የጥበብና የአንደፈር ባይነት ገድላቸውን እያስነበቡ፤ የመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት አርአያነታቸውን እንደያዙ እነሆ 125 ዓመታት ተቆጥሯል:: ይህ ድል ብስለት የተሞላበት የውጊያ ጥበብ የተገለጸበት፤ የሰው ልጅን ሙሉና ጎዶሎ አድርጎ የሚከፋፍል የቅኝ ገዥዎች ከፍ ብሎ የነበረ አስተሳሰብ የተሰበረበት ታሪካዊ የተጋድሎ ክስተት ነው።
የዓድዋ ድል መላው ጥቁር ሕዝቦች ቅኝ ግዛትን እና ባርነትን አሽቀንጥረው ከመጣል የሚያግዳቸው አንዳችም ዓይነት ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ዐይናቸውን ገልጠው እንዲያዩ፣ ስለ ነፃነታቸውና ሰብአዊ ክብራቸው እንዲያስቡና ለዚህ የሚሆን አቅም እንዲፈጥሩ ያስቻለ የድል ብስራት ዜማ ነው።
ተስፋ የሚሰጥ ነገር በጠፋበት፣ የሰውን ልጅ ሙሉ እና ጎዶሎ አድርጎ የከፋፈለው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በተንሰራፋበት፤ ማንም ሊነቀንቀው እንደማይችል ብዙዎች አምነው አንገታቸውን በደፉበት በዚያ ዘመን የተከሰተ የዓለምን የታሪክ ጉዞ የለወጠ አትንኩኝ ባይነት የተጋድሎ ዜማ ፍሬ ነው::
በዚህም ኢትዮጵያ የቀደምት የሰው ልጆች መገኛ ብቻ ሳትሆን ዘላለማዊ ታሪክ ፈጽመው የሚያልፉ ኩሩ ሕዝቦች ያሏት መሆኗም ለመላው ዓለም የተበሰረበት፤ በዚህም ብዙዎች ጥቁርነት የትንሽነት እና የተገዥነት መለያ እንዳልሆነ ከቆዳ ቀለም ውስጥ ያለው ሰውነት ከፍ ያለ ክብር እንዳለው በተጨባጭ ያዩበት ነው። ለዚህም እውነት በግድ እራሳቸውን ያስገዙበት ታሪካዊ ክስተት ጭምር ነው።
የድሉ መንፈስ ለማናቸውም የሰው ዘር የሕይወት መመሪያ ሆኖ ሊዘልቅ የሚችል ነው። በተለይም የድሉ ባለቤቶች እኛ ኢትዮጵያውያን ለድሉ መሠረት የሆኑትን ጥበብ፣ ፍቅር፣ አንድነትና መደማመጥን ዛሬ ላይ ለሚገጥሙን ፈተናዎች ሁሉ መሻገሪያ ድልድይ አድርገን ልንጠቀምባቸው ይገባል::
እስኪ ያኔ የዛሬ 125 ዓመት እነዛ የትጋት፣ የመተባበር፣ የፍቅር፣ የጥበብና ወኔ፣ የአልሸነፍ ባይነት አርነት የሆኑት የዓድዋ ኩራቶች እናስባቸው:: ያኔ እነሱ መተባበር ተስኗቸው፤ መዘናጋት ገብቷቸው፤ ፍቅርና መተሳሰብ ርቋቸው፤ በቂምና በቀል ተሸብበው አንድነታቸውን አጥተው፤ የአሸናፊነት ወኔያቸው ተሰልቦ ቢሆን ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለማሰብ ለዚህ ትውልድ ከባድ አይሆንም።
ዛሬ እኛ ማን ነበርን? አፍሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝቦችስ ቀና ብለው የሚናገሩት ምን አኩሪ ታሪክ ይኖራቸው ነበር? ነጮችስ አፍሪካን ለቅቀው የሚወጡበት የነፃነት ትግል ምዕራፍ መነሻው ምን ይሆን ነበር? ክብር ለዓድዋ ጀግኖች እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ላይነሱ በታላቅ የተጋድሎ መስዋእትነት በዕለተ ዓድዋ ገድለው ቀብረዋቸዋል::
እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ የዓድዋ ድል መንፈስ በእጅጉ የሚያስፈልገን መሆኑን መረዳት መቻል አለብን:: እኛ ዛሬ በአንድም በሌላ ምክንያት በበዙ ፈተናዎች የታጠርን፤ በአያሌ መሰናክሎች የተከበብን ትውልዶች ነን:: እነዚህን ችግሮችና መሰናክሎች ደግሞ መሻገር የምንችለው የዓድዋን ድል መንፈስ በመላበስ ነው::
የዓድዋ ድል መንፈስ ስንል ሃይማኖት ማለት አይደለም፤ የዓድዋ ድል መንፈስ ብሔርና ዘር አይደለም፤ የዓድዋ ድል መንፈስ በክልል ታጥሮ አትድረስብኝ አልድረስብህ ማለት አይደለም፤ የዓድዋ ድል መንፈስ ለራስ ጥቅም ሲባል ጓደኛን፣ ወገንን፣ ወይም አገርን አሳልፎ መስጠት አይደለም፤ የዓድዋ ድል መንፈስ ባለፈ ቂምና ቁርሾ እርስ በእርስ መገፋፋትና መጠፋፋት አይደለም::
ይልቁንም የዓድዋ ድል መንፈስ በህብር የደመቀ አንድነታችንን ከሚሸረሽሩ እና ለጠላት አሳልፈው ከሚሰጡን እኩይ ነገሮች መራቅ ነው:: የዓድዋ ድል መንፈስ ፍቅርን ማንገስ፤ አንድነትን ማጠንከር፤ ሰላምና መተሳሰብን ማጎልበት፤ ስለ ወገንና አገር ሲባል ራስን አሳልፎ መስጠትን መለማመድ ነው::
የዓድዋ ድል ምስጢር የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ መተሳሰብ፣ ጽናትና አይበገሬነት፤ ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ ሀገራቸው የነበራቸው ፍቅርና ታማኝነት ነው:: ይሄን መሰሉን የዓድዋ ድል መንፈስ ዘላቂ ማድረግ የዚህ ትውልድ ትልቁ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል::
ኢትዮጵያ ከሁሉም ነገር በላይ ናት:: ኢትዮጵያ ከግለሰብ በላይ ናት፤ ከፖለቲካ ፓርቲም የላቀች ናት:: እናም ግለሰባዊ ማንነትም ሆነ የፖለቲካ ጉዳይ ከኢትዮጵያ በታች ተይዞ ሊሰራ እንጂ ከኢትዮጵያ በላይ ከፍ ብሎ ሊታይ እንደማይችል ማወቅ ያስፈልጋል:: የዓድዋ ጀግኖችም ማንኛውም ፍላጎቶቻቸው ከአገር በታች መሆናቸውን በመገንዘባቸው ነው ለዚህ አኩሪ ድል የበቁት::
እኛ በትናንትናዎቹ ባለታሪኮች ታሪክ አንገታችንን ቀና አድርገን እየሄድን ነው፤ የነገዎቹ ትውልዶች ደግሞ በኩራት የሚናገሩለትና አርአያነቱን የሚከተሉት እኛ የምናቆይላቸው አዲስ ታሪክና ገድል ይፈልጋሉ:: እኛ የታሪክ ገጽ ከታቢ ባለተራዎች የሆንን የዚህ ዘመን ትውልዶች ይሄን ተገንዝበን ካለንበት ችግር መውጣት፣ ታሪክ በበጎ የሚያወሳልንን ድልና ገድል መፈጸም ይኖርብናል:: ይሄን እውን ለማድረግ የዓድዋን የፍቅር፣ የጥበብ፣ የመተሳሰብ፣ የአልበገር ባይነትና አርቆ ተመልካችነት አስተምህሮ ለዛሬው የክፉ ቀን መሻገሪያ ድልድያችን ማድረግ ይጠበቅብናል::
አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም