ዳግም ከበደ
ዲዛይነር ሃናን መሀመድ ትባላለች። የባህላዊ አልባሳትን ዲዛይን በማድረግ ትታወቃለች። በርካታ የፋሽን ዲዛይነሮች ባህላዊ አልባሳት ዲዛይን ተሳትፎ ያላቸው ቢሆንም፣ የእርሷ ስራዎች ግን ያልተለመዱና ከዚህ ቀደም ያልተሞከሩ ናቸው።
ዲዛይነር ሃናን በበረራ አስተናጋጅነት በታላላቅና ተወዳጅ አየር መንገዶች ውስጥ ሰርታለች፡፡ የልጅነት ፋላጎትና ምኞቷ የሆነው “modest fashion wear” የዲዛይንና ፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ መሳተፍ ከጀመረች ቅርብ ጊዜ ሆኗታል። በዚህ ሙያ ውስጥ መሳተፍ ከመጀመሯ አስቀድሞ “በኢትዮጵያ አየር መንገድና የኤምሬትስ ኤርላይንስ” ውስጥ ስትሰራ ቆይታለች።
ሃናንና የበረራ መስተንግዶ
ዲዛይነር ሃናን ከልጅነቷ ጀምሮ የበረራ አስተናጋጅ የመሆን ራእይ ነበራት። ይህን ራእይዋን ለማሳካት ደግሞ ብዙ ጥረቶችን አድርጋለች። ለዚህም እንደ እናት በመሆን ያሳደገቻት አክስቷን ፈለግ በመከተል ለምትፈልገው ሙያ እንደ አርአያ አይታታለች። ከብዙ ልፋትና ጥረት በኋላም የበረራ አስተናጋጅ የመሆን ምኞቷን አሳክታ ለአመታት መስራት ችላለች።
ፋሽን ዲዛይነር ሃናን በኢትዮጵያ አየር መንገድ መስራት የጀመረችው በጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2005 ላይ ነበር። ባገኘችው አጋጣሚም የልጅነት ራእይዋ በነበረው ከፍላጎትና በውስጥ ከመነጨ ፍቅር ማገልገል ጀመረች። በተለይ ሃናን ስለቆይታዋ ስትናገር “በዚህ ሙያ ላይ መስራት በመቻሌ ትልቅ ልምድ እንዲኖረኝ አድርጓል” ትላለች። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በነበራት ቆይታ አገሯን ወክላ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ትጓዝ ስለነበር አጋጣሚው መልካም ሁኔታ እንደፈጠረላት ትገልጻለች።
“የበረራው ወቅቶች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚመጡ ደንበኞች ጋር የመተዋወቅ ልምድና ተሞክሮዎችን የማግኘት እድሉን አግኝቻለሁ፤የኢትዮጵያ አየር መንገድ እይታዬ እንዲሰፋ በርካታ ልምዶችን እንዳካብት አግዞኛል ትላለች።
ሃናን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኤምሬትስ አየር መንገድም ሰርታለች። በዚያ ከ100 በላይ ከሆኑ ከተለያዩ አገራት ዜጎች ጋር ሰርታለች። ይሄም ተጨማሪ ልምድና የሰፋ አድማስ እንዲኖራት አድርጓል፡፡“አጋጣሚው በተለያዩ የአለም ክፍሎች ምን እንዳለ ያስተዋልኩበት፣ ባህሉን አመለካከቱን የተጋራሁበትና የአገሬን ባህልና ማንነት የማስተዋወቅ አጋጣሚ ያገኘሁበት ነው” ትላለች።
አየር መንገድና ባህል
ፋሽን ዲዛይነር ሃናን በርከት ያሉ አገራትን በስራ ምክንያት ለማየት ችላለች። ይህ አጋጣሚ ደግሞ በእረፍት ጊዜዋ የምትዋብባቸውን አልባሳት የማስተዋወቅ አጋጣሚውን አስገኝቶላታል። የተለያዩ አገራት ዜጎችም በእርሷ አማካኝነት ኢትዮጵያን ለማወቅ ፍላጎት ያድርባቸዋል። ይሄ ደግሞ ለሃናን ክብር ከመሆኑ ባሻገር አገሯን በመልካም ነገር መወከል በመቻሏ ድርብ ደስታ ድርብ ኩራት እንድታገኝ አስችሏታል። በተቃራኒው ደግሞ የሌሎች አገራት ባህል፣ ልምድና ወግ እንድትረዳ ጠቅሟታል።
ወደ ፋሽኑ ዓለም
ዲዛይነር ሃናን ከስድስት ዓመት ከመንፈቅ የበረራ አስተናጋጅነት ቆይታ በኋላ ፊቷን ያዞረችው ወደ ፋሽን አልባሳት ዲዛይኖች ላይ ነው። የበረራ አስተናጋጅ የመሆን ፍላጎቷ የተጠነሰሰው በልጅነቷ እንደሆነው ሁሉ አልባሳትን ዲዛይን ማድረግን ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ በውብ ልብሶች አምሮ የመታየት ፍላጎቷም የጀመረው ከልጅነቷ አንስቶ ነው።
በተለይ ከሙስሊም አባት እና ከክርስትና እምነት ተከታይ እናት ተወልዳ በሃረር እንደማደጓ በርካታ መልካም ነገሮችን እያየች አድጋለች። በልጅነቷ እናቷ ኢትዮጵያዊ ባህልን በሚያንፀባርቁ በባህላዊ አልባሳት ይዋቡ ስለነበር ያንን እያየች አደገች። ይህም ቆየት ብሎ ፈንቅሎ ለወጣው የዲዛይን ሙያ ፍላጎቷ ደግሞ እርሾ ሆኖላታል።
ዲዛይነር ሃናን እስላማዊ አልባሳት ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ሳይለቁ በባህላዊ አልባሳት ጥለት በማስጌጥ
ኢትዮጵያዊ ቃናና ይዘት እንዲኖራቸው በማድረግ እየሰራች ትገኛለች። ይህም የመጀመሪያው ሙከራዋ ተወዳጅነትና ከፍተኛ ተቀባይነት አስገኝቶላታል። ከአረብ አገራት የሚመጡ አልባሳትን ብቻ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሚለብስ ኢትጵያዊ ባህል የተላበሱ ጥለቶችን በመጨመር የበለጠ የተዋበና ያማረ ለማድረግ ያደረገችው ጥረት ተቀባይነት ማግኘቱን ትናገራለች።
“እስላማዊ አልባሳቶች ባህላዊ ይዘት እንዲኖራቸው የምጠቀመው ጥለት ነው። ሁላችንም ጥለትን ስናስብ አገራችንን እናስታውሳለን። ይህን ምክንያት በማድረግ ጥለትን ተጠቅሜ አልባሳቱን ዲዛይን አደርጋቸዋለሁ” የምትለው ሃናን፣ በዚህ መንገድ ተወዳጅ ይዘት ያለው ኢትዮጵያዊ የሙስሊም አልባሳትን ለማህበረሰቡ ይፋ ማድረግ እንደቻለች ትናገራለች።
ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎች ዲዛይነር ሃናን አዲስ ባስተዋወቀችው ኢትዮጵያዊ ባህልንና ሃይማኖታዊ ይዘታቸውን ያልለቀቁ እስላማዊ አልባሳት ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝታባቸዋለች። የፈጠራ ውጤቶቿ በሆኑት የሃባያ አልባሳት በከተማ ውስጥ የሚያጌጡ ቆነጃጅት መመልከት አሁን አዲስ ነገር አይደለም። የእስልምና እምነት ተከታይ ፋሽን አይከተልም በሚል የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ አስተያየቶች እንደሚደርሷት የተናገረችው ዲዛይነሯ፣ ይሄ ግን ከተሳሳተ ግንዛቤ የሚመነጭና የአብዛኛውን ማህበረሰብ ፍላጎት ያላማከለ መሆኑን ትናገራለች።
ዲዛይነር ሃናን ይህን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመቀየር ጥረት ማድረጓን እንደምትቀጥል ትገልፃለች። እንደ ጅምር በጊዮን ሆቴል በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሂጃብ ቀን ላይ በመሳተፍ ስራዎቿንና በጎ ገፅታዎቹን ለማሳየት ሞክራለች። በተለያዩ የፋሽን ሳምንቶች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት በመግለፅም የረጅም ጊዜ ልምድና ኔትወርኩ ያላቸው ዲዛይነሮች መሰል መድረኮችን ቢያመቻቹና አብረዋት ቢሰሩ ፍላጎቷ መሆኑን ገልጻለች።በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀ የፋሽን መድረክ ላይ ስራዎቿን ይዛ በመቅረብም ሰፊ ተቀባይነት ከመፍጠሯ ባሻገር ግንዛቤውን ለመፍጠር ችላለች።
እንደ መውጫ
ሃናን ዘርፉን በቅርብ ጊዜ ተቀላቅላ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እያተረፈች የምትገኝ የፋሽን ዲዛይነር ነች።ታላቅ ስኬት ላይ የመድረስ ግብ ይዛ እየሰራች ነው። በዓለም አቀፍ የፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የመግባትና የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ራእይም አላት። ለዚህ ደግሞ የጀመረችው መንገድ ወደ ራእይዋ እየመራት መሆኑን ታምናለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም