ዘመኑ የመረጃ ከመሆኑ አንጻር የመረጃ ጉዳይ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጠው ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል። በተለይም መረጃ በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በማሰራጨት ሥራ ላይ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የተወዳዳሪነታቸው መሰረት ለመረጃ ያላቸው ቅርበት፣ የሚያቀርቡት መረጃ ጥረትና የማሰራጨታቸው ፍጥነት ላይ የተመሰረተ ነው።
የታማኝነት ፣ ግልጽነት ፣ አሳታፊነት ፣ሀቀኝነት ፣ ሚዛናዊነት …ወዘተ ጉዳይ ሙያው አበክሮ የሚጠይቃቸው ሙያዊ መርሆች ናቸው። የአንድ መገናኛ ብዙሃን ውጤታማነት መመዘኛም ከዚሁ የሚመነጭ ነው።
ጋዜጠኝነት እነዚህን ሙያዊ እውነታዎች ገና በጠዋቱ ተቀብሎ እና ትልቅ ቦታ ሰጥቷቸው እስከ ዛሬ ድረስ እያስተናገዳቸው ይገኛል። ሙያው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈም በየዘመኑ በተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የዓለምን ህዝብ በመረጃ ለማስተሳሰር በሚደረገው ዓለም አቀፋዊ ጥረት ውስጥ ሙያው ሰፊ ቦታ እንዲያገኝ አስችለውታል።
በተለይም በሙያው ውስጥ ክፍለዘመናትን ያስቆጠሩና ከፍ ያለ ስፍራ ይዘው የቆዩ ዓለም አቀፍ የመገናና ብዙሃን በረጅም ዘመን ካካበቷቸው ልምዶች እና በሥራቸው ካፈሯቸው ከፍ ያለ ስምና ዝና ካተረፉ ባለሙያዎቻቸው ትጋትና ሙያዊ ታማኝነት አንጻር ሙያው አሁን ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አይካድም።
ከዕድሜያቸውም ሆነ ከፍ ካለው ስምና ዝናቸው አንጻር ለመላው ዓለም የሚያስተላልፏቸው ዘገባዎች ሊኖራቸው ከሚችለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ እና አሉታዊ አደጋዎች አንጻር ከፍ ያለ የኃላፊነት መንፈስ እንዲላበሱ ያስገድዳቸዋል። መገናኛ ብዙሃን ከሙያዊና ሰብዓዊ ኃላፊነት እያፈነገጡ በወጡ ቁጥር የቱንም ያህል ዋጋ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉም የቅርብም ይሁን የሩቁ የዓለማችን ታሪኮች በግልጽ ይናገራሉ።
በመገናኛ ብዝሃን የተሟሟቁ እና የማይጨበጡ ዘገባዎች የፈረሱ ሀገሮች አስከ ዛሬ ድረስ ዜጎቻቸው ፍርስራሽ ውስጥ ሆነው ቀናትን አሸንፈው ለመውጣት ታላቅ ጣር ላይ ስለመሆናቸው ኢራቅን ፣ ሶሪያን ፣ ሊቢያውንና ልሎችንም በሰቆቃ ውስጥ ያሉ ሀገራትን መጥቀስ ይቻላል።
በእነዚህ በተሟሟቁ መርህ አልባ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች በዘመናት መካከል የታላላቅ ስልጣን ባለቤት የነበሩ፣ ከዚያም በላይ ለዓለም በብዙ መልኩ ባለውለታ የነበሩ ሀገራትን ሊወጡበት ወዳልቻሉት አዘቅት ውስጥ ጨምረዋቸዋል። እስከዛሬ ድረስም እያስተናገዱት ባለው መከራና ስቃይ የመገናኛብዙሃኑ ዕለታዊ ዜና እንደሆኑም ናቸው።
ግጭት በተፈጠረበት ቦታ ሁሉ ከጉዳዩ ባለቤት በላይ ባለቤት ሆነው የሚገኙት አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በአንድ እጃቸው የፖለቲካ አጀንዳ በሌላኛው እጃቸው ሙያዊ አጀንዳ ይዘው የመንቀሳቀሳቸው እውነት የአደባባይ ምስጢር ነው።
ይህ እውነታ የህወሓት ጁንታ ሀገርና ህዝብን አደጋ ላይ በጣለ የእብሪትና ማናለብኝነትና ጀብደኝነት የተሞላ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ባእድ የሆነ ተግባር ከፈጸመ ማግስት ጀምሮ ሲስተዋል ቆይቷል።
የዘመቻ ያህል ቅንጅትና መናበብ የታየበት የተሳሳቱና የተዛቡ መረጃዎችን ለዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ የመልቀቅ እውነታዎችም ተከስተዋል።
ይህ ክስተት ልጓም ከሌለው የማህበራዊ ድረ-ገጽ መጥቶ በእነዚህ አንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸው መገናኛ ብዙሃን በተለይም ዓለም አቀፍ ስምና ዝና ባተረፉ ትላልቆቹ የምዕራብ ዓለም የመገናኝ ተቋማት ውስጥ ሳይቀር መስተዋሉ፣ ከትናንት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች አንጻር ሁኔታውን በአግባቡ መመልከትን የሚጠይቅ ሆኗል።
አንቱ የተባሉ ተቋማት ሳይቀር በሚያስተዳድሯቸው የመገናኝ ብዙሃን ግጭት አባበሽ ፣ ሙያዊ ስነምግባር ያልተላበሱና የአንድ ወገን ሪፖርቶችንና ከዚህ የሚመነጩ የትንታኔ ሥራዎችን ሲያስተናግዱ ተስተውለዋል። እነዚህ ማረሚያ የበዛባቸው ዘገባዎች የቱን ያህል የችግር ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉም የሚሰወርባቸው አይሆንም።
በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ የገለልተኝነት፣ የሚዛናዊነት ከዚህም በላይ የታማኝነት ጥያቄ የሚያስነሱ ዘገባዎችን አቅርበዋል። በእነዚህ ዘገባዎቻቸው ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ማግኘት የሚገባውን ትክክለኛ መረጃ እንዳይደርሰው አድርገዋል። በዚህም የተዛቡ አስተሳሰቦች እንዲፈጠሩ ሆኗል። በተዛቡ አስተሳሰቦችም የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍሏል።
እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን ሀገር ውስጥ ገብተው የመዘገብ ዕድል አለማግኘታቸውን እንደ ምክንያት ቢያነሱም ፣ ዕድሉን ባገኙባቸው አጋጣሚዎች በዘገቧቸው የተዛቡ መረጃዎች የፈጠሯቸው ምስቅልቅሎች ችግሩን ከዕድሉ ጋር የማያያዙን እውነታ ውሃ የሚያነሳ አያደርገውም።
አንድን ሉአላዊ ሀገር ከአንድ የመገናኛ ብዙሃን የፈለገውን ከማድረግ መሻት ጋር የማነጻጸሩም እውነታ የሉአላዊ ሀገርን የሉአላዊነት ጥግ ካለመረዳት አልያም ከሉአለዊ ሀገር እራስን አግዝፎ ከማየት የሚመነጭ ነው። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ስነልቦና ጋር ፈጽሞ የሚሄድ አይደለም።
ከአንድ ሀገር ሉአላዊ መንግሥት ፈቃድ ውጪ ወደ አንድ ሀገር መግባት አለብኝ ብሎ ዓለም አቀፍ ህግንና መርህን ባፈነገጠና ችግር ወላጅ በሆነ መልኩ መንቀሳቀስ በሙያው ዘመናት ካስቆጠሩ ቀርቶ ትናንት ወደ አደባባይ ከወጡ የመገናኛ ብዙሃንም የሚጠበቅ አይደለም።
መንግሥት በትግራይ አካባቢ ከነበረው የፀጥታ ችግር አንጻር ኃላፊነቱን ውስዶ እንዲገቡ ያለማድረግ ቢያንስ የሞራል ኃላፊነት አለበት። ይህ ኃላፊነት ደግሞ ከኢትዮጵያዊ ስነልቦና የሚመነጭና ከፍ ያለ ሰብዓዊ ክብርን በውስጡ የያዘ ነው።
መንግሥት ከወሬ ነጋሪ ተቋማት በላይ ለህዝቡ የማሰብ የሞራልም የህግም ኃላፊነት አለበት። ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ደግሞ የማንንም ጉትጎታ የሚፈልግ አይደለም። ኢትዮጵያውያን በወንድማማችነትና በሉአላዊነት ጉዳይ የማንንም ውትወታ አይፈልጉም። የመንግሥታቸውም ባህሪ ከዚህ የተቀዳ ነው።
አሁን ሜዳውም ፈረሱም ይሄው መንግሥት ወደ ሀገር ወስጥ ገብታችሁ እንድትዘግቡ ዕድሉን ሰጥቷችኋል። ምን ያህል በዓይናችሁ ፊት ያለውን እውነታ በገለልተኝነት ፣ በሚዛናዊነት፣ በታማኝነት እና በሙያዊ ስነምግባር ልትዘግቡ እንደምትችሉ እኛም ሆንን ዓለም የምንታዘብበት ትክክለኛው ሰዓት ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013