ይበል ካሳ
መረጃ ምንነቱና አስፈላጊነቱ
መረጃ በአንድ በምንፈልገው ጉዳይ ላይ ትክክለኛና ተገቢ ውሳኔ ላይ ለመድረስ፣ አዳዲስ ሃሳቦችን ለመፍጠርና ሥራን በአግባቡ ለመሥራት፣ ከራሳችንና ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል እያንዳንዱ ሰው በግል ሊጠቀምበት የሚችል ወሳኝ ግብዓት ወይንም ኃይል ነው።
ሆኖም ብዙውን ጊዜ መነሻው በግል ወይም በግለሰብ ደረጃ ቢሆንም ከግል ይልቅ ብዙዎችን የማገልገል፣ ብዙሃናዊ የመሆን በባህሪ አለው። በተለይም የመረጃ ዘመን እየተባለ የሚጠራው አሁን የምንገኝበት ዘመን ለዓለማችን ካበረከታቸው መልካም ዕድሎች ዋነኛው መረጃን እንደልብ ማግኘትና መለዋወጥ መቻሉ ነው።
እሳትም ውሃም መሆን የሚችለው መረጃ
ይሁን እንጅ የቱንም ያህል ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆን እንኳን ማንኛውም ነገር የራሱ የሆነ አሉታዊ ጎን አለው። መረጃም ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም ይኖረዋል፤ ለልማት ሊውል እንደሚችል ሁሉ ለጥፋትም ሊውል ይችላል።
የቱንም ያህል ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆንም እንኳን እንደ ማንኛውም ነገር መረጃም የራሱ የሆነ አሉታዊ ጎን አለውና። እናም አጠቃቀሙን አውቀን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት መረጃ ኃይል በመፍጠር ፋንታ ኃይል ሊቀንስ፣ የችግር መፍቻ ሆኖ በማገዝና የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ ተጨማሪ ችግር ፈጣሪና አባባሽ፣ ከዕምነት ይልቅ የጥርጣሬና የፍርሃት፣ ከደህንነት ይልቅ የሞት መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።
በተለይም ደግሞ በችግር ጊዜያት እጅግ በጥንቃቄና በጥበብ ካልተጠቀሙበት በቀር መረጃ ከመጥቀም ይልቅ ችግርን የሚያባብስ ብሎም ተጨማሪ ችግር የሚፈጥር በእንቅርት ላይ የሚወጣ ጆሮ ደግፍ መሆኑ አይቀርም። ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በዓለማችን ላይ የደረሰውን ሁነት እንደአጠቃላይ ማሳያ በማንሳት በአሁኑ ሰዓት እኛን ስለገጠመን ተጨማሪ ችግር በስፋት ለማሳየት እሞክራለሁ።
እስከአሁን ድረስ መድሃኒት ያልተገኘለት ኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን ክፉኛ እያስጨነቃት በነበረበት ወቅት(አሁን ቢያንስ ክትባት ማግኘት ተጀምሯል) በየደቂቃው በገፍ ይሰራጩ የነበሩ ችግርን ብቻ አጉልተው የሚደጋግሙ አሉታ-ተኮር መረጃዎች(ሐሰተኞችን ጨምሮ) ከወረርሽኙ ባልተናነሰ ምን ያህል ዓለምን እዳስጨነቋት ከዓመት በፊት ገደማ በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የትዝብት አምድ ላይ ለማሳየት ሞክሬ ነበር።
ኮሮናን በተመለከተ በመደበኛውም ሆነ በድረ ገጾች፣ እንደ ፌስቡክ፣ ተዊተርና ዩቲዩብ በመሳሰሉ ማህበራዊ የመገናኛ ዓይነቶች በአጠቃላይ በሁሉም ዓይነት የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች አማካኝነት የሚወጡና ከሚሰራጩ መረጃዎች ከዘጠና ዘጠኝ በመቶ በላይ የሚሆኑት በተለያየ መንገድ ወረርሽኙ እየያደረሰ ያለውን ምንዳ በቁጥር ቀምረው የሚገልጹ ነበሩ(ናቸው)።
እዚህ ጋር ልብ መባል ያለበት ጉዳይ የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር አይዘገብ፣ በየጊዜው በቫይረሱ የሚያዙና በበሽታው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር አይገለጽ እያልኩ አለመሆኔን ነው።
እያልኩ ያለሁት የዓለም መገናኛ ብዙሃን ዓይንና ጆሮ ለምን ችግሮቹ ብቻ ላይ ሆነ? ለምን ችግሮቹን ብቻ አብዝቶ መዘገብ አስፈለገ? ከችግሮቹ እኩል በወረርሽኙ ምክንያት ዓለማችን የገጠማትን ችግር ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ ዕርምጃዎችንና እየተሠሩ ያሉ ተስፋ ሰጭ ሥራዎችንና የሚያሳዩ መረጃዎችን ለመዘገብ ለምን አልተቻለም? በየሰዓቱ ልብን የሚሰብሩና ተስፋ የሚያስቆርጡ፣ ዘወተር ሞት ሞት የሚሸቱ የችግርና የመከራ ዜናዎችን ከማሰራጨት ጎን ለጎን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ ለበሽታው ክትባትና መድሃኒት ለመሥራት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችንና እየተገኙ ያሉ ተስፋ ሰጭ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን የሚያሳዩ ተስፋ ሰጭ መልካም ዜናዎችንስ በበቂ ሁኔታ ለማሰራጨት ለምን አልተቻለም? “ይህንን እውነታ ነው ማሳየት የፈለኩት እንጅ ከነጭራሹ ስለ ሞትና ችግር መስማት አልፈልግም የምል ሆደ ባሻና አጉል ተስፈኛም አይደለሁም” በማለት የመገናኛ ብዙሃኑ አሉታዊ መረጃዎች ላይ ያተኮረ አካሄድና በተለይም በችግር ሰዓት የሚዘገቡና የሚሰራጩ መረጃዎች በአግባቡ ካልተስተናገዱ በቀር ችግሩን ከማቃለል ይልቅ ሊያባብሱ እንደሚችሉ ነባራዊና ሳይንሳዊ መከራከሪያዎችን በማቅረብ የአካሄዱን ስህተትነት ሞግቼ ነበር።
ወደ ችግር ፈጣሪነት ያደጉት ኢትዮጵያ ነክ “መረጃዎች”
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ከሃገር በቀል ሃገር አፍራሽ ጠላቶች ጋር ያካሄደችውን ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ተከትሎ በአሉታዊ መረጃዎች ምክንያት የገጠማት ችግር ከፍተኛ ነው። በአንዳችም ዓይነት ተጨባጭ መረጃ ያልተደገፉ፣ ከዓለም አቀፉ የጋዜጠኝነት መርህና ሙያ ፍጹም የሚቃረኑ ለአንድ ወገን ብቻ የሚያደሉ መረጃዎች በበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በስፋት በኢትዮጵያ ላይ እየተሰራጩ ይገኛሉ። ከኮሮና ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ ይሰራጩ ከነበሩት ችግር አባባሽ መረጃዎች የአሁኑ የሚለየው በአሉታዊ ሁነት ብቻ ላይ ያተኮረና ችግርን የሚያባብስ(ችግር ካለ) መሆኑ ብቻ ሳይሆን ችግር መፍጠርንም ያለመ መሆኑ ነው።
በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞ አሁን በኢትዮጵያ ላይ እየሆነ ያለው ከቀደምቱ የሚለየው ችግር ላይ ብቻ ያተኮረ መረጃ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ለአንድ ወገን ያጋደለና የራሱ የሆነ ድብቅ ዓላማ ያነገበ፤ ከመረጃነት ይልቅ ለፕሮፓጋንዳነት የቀረበ የለየለት የጥፋት ዘመቻ መሆኑ ነው።
የዚህ የጥፋት ዘመቻ ዋነኛ መንስዔም የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት በማይፈልጉ ፀረ ኢትዮጵያ ባዕዳን ተፈብርኮ በሃገር ውስጥ አስፈጻሚዎች ባለፉት አርባ ምናምን ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ሲተገበር የቆየው የጥፋት ተልዕኮ ሃገሪቱን ለማፈራረስ በተቃረበበት የመጨረሻ ሰዓት ፍጹም ባልተጠበቀ መንገድ መክሸፉ ነው።
ግቡም ያሳበው ይሳካ ዘንድ በሙሉ ፈቃደኝነት ወገቡን ታጥቆ ሌት ተቀን ሲሠራ የነበረውን ሃገር በቀል የጥፋት ኃይል መልሶ እንዲያንሰራራ ማገዝና ኢትዮጵያን የመከፋፈልና የማፈራረስ ፀረ ኢትዮጵያ እኩይ ዓላማውን እንዲፈፀምለት ማድረግ ነው። በዚህ መንገድ በመረጃ መልክ በሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለው የጥፋት ዘመቻ ዋነኛ ምንጩም ከውጭ ነው።
የተደራቢ አጥቂዎቹ ነገርስ
አሁን ላይ ለሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰልና የበግ ለምድ ለብሰው በተኩላ ተሟጋችነት በተለያዩ ሽፋኖች ተከልለው በኢትዮጵያ ላይ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ከላይ እንደጠቆምነው መቀመጫቸው ከውጭ ነው። በበግ ለምድ ተጀቡነው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በገፍ የሚሰራጩት “መረጃዎች” ምንጫቸው ከውጭ ነው።
እናም ሁሌም ቢሆን የኢትዮጵያ ሰላም ሰላም የማይሰጣቸው ፀረ ኢትዮጵያ ዓላማ ያላቸው ባዕዳን የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት መረጃ ቢያሰራጩ የሚገርም አይደለም። “ሊገድልህ የመጣ ጠላትህን አባዬ ብትለው አይተውህም” እንዲል ሀገርኛው ፍልስፍናችን ጠላትማ አንድ ጊዜ ጠላት ነው።
እኔን የገረመኝ የእነርሱን አጀንዳ እንደ ወረደ ተቀብለው የሚያስተጋቡ፤ የመረጃ ምንጫቸውን ከውጭ ያደረጉ የመረጃ ተቋማት ነን ባዮች መረጃ አስመጭና አከፋፋይ “የሃገር ውስጥ” ሚዲያዎች ናቸው። እኔን የገረመኝ ትክክለኛ መረጃን በማቅረብ ስለራሱና ስለሃገሩ ጥቅም እንዲታገል ሕዝብን ማንቃት የሚገባቸው የራሳችን ሚዲያዎች(በተለይም ማህበራዊ ሚዲያዎች) እና አንቂዎች(Activists) የጠላት መረጃዎችን በዋቢነት እያጣቀሱ ማውራታቸው በሃገራቸው ላይ ከጠላት ጋር በተደራቢ አጥቂነት መሰለፋቸው ነው!
ይህን ያልኩበት በቂ ምክንያት አለኝ። በሃገራችን በትግራይ ክልል ከተካሄደው ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞ ከላይ እንደገለጽነው ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ የሚፈልጉና ችግር ውስጥ እንድትኖር የማድረግ ድብቅ ዓላማ ያላቸው የውጭ ሚዲያዎች፤ “ትግራይ ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ተራበ” ብለው ሲዘግቡ የእኛወቹም(በአብዛኛው በዩቱብ የሚተላለፉ ሚዲያወች) ተቀብለው፤ እንዴያውም “አስደንጋጭ”፣ “ጥብቅ”፣ “አሳሳቢ”፣ “ሰበር” የሚሉ ቅጥያዎችን በመጨመር የባሰ አጋንነው ይደግሙልናል።
መረጃውን ከየት እንዳገኙት በኩራት ምንጩን ሲጠቅሱልንም ፀረ ኢትዮጵያ ዓላማ ያላቸውን የውጭ ሃገር ሚዲያዎች አንድ በአንድ ይዘረዝሩልናል። መጠየቅ የለም፣ እውነት ይሁን ሐሰት ማረጋገጥ የለም፤ እንደ ሳልቫጅ ሸቀጥ ከውጭ ያስገቡትን “መረጃ” ለዚህ ምስኪን ሕዝብ እንደጉድ ያከፋፍሉታል። ስለሃገራቸው ጉዳይ፣ ለዚያውም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን የብሔራዊ ጥቅም ያለበትን ዓብይ ጉዳይ ከውጭ ምንጭ በተገኘ መረጃ ይተነትኑልናል።
ሚዲያንና መረጃን ተጠቅሞ ጠላት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ሲያካሂድ “ለምን?” ብሎ እንደመጠየቅና የ“መረጃዎችን” ሐሰተኝነት እንደማገለጥና ከሃገር ጎን ቆሞ እንደመሞገት የጠላትን የሴራ ፕሮፓጋንዳ ሳያበጥሩ ተቀብለው በማሰራጨት በተደራቢ አጥቂነት ተሰልፈው ሃገራቸውንና ሕዝባቸውን ያጠቃሉ።
በተለይም ፀረ ኢትዮጵያውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያካሂዱትን የሚዲያ ዘመቻ ዕለት ዕለት እየተከታተሉ፣ በራሱ ቋንቋ ተርጉመው የጥፋት መረጃቸውን “ለሕዝባቸው” በስፋት እያዳረሱ ያሉት በአዲሱ የመገናኛ ዘዴ በማህበራዊ ሚዲያ ዘርፉ እንደ አሸን እየተርመሰመሱ የሚገኙት “ዩቱበሮች” ናቸው።
ዋነኛው ሥራቸው ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ካላቸው የውጭ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ፕሮፓጋንዳወችን እንደ ወረደ ቃል በቃል ተርጉመው እየቀዱ ለሕዝብ እንዲዳረሱ በማድረግ ጠላት ለሚያሰራጨው የጥፋት መረጃ ቱቦ ሆኖ በማገልገል ላይ ናቸው። “ዩቱበሮች” ከሚለው የተሻለ ግብራቸውን የሚገልጸው “ዩቱቦዎች” ቢባሉ የተሻለ ይመስለኛል።
ከዜጎች ሞትና መፈናቀል በግብጽና ሱዳን መሪነት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ እስከሚደርስ ዓለም አቀፍ ጫና አገሬ ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ በርካታ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች በምትገኝበት በከፍተኛ ደረጃ መተባበርና የውስጥ አንድነትን አስጠብቆ በጋራ ለሃገር መቆም በሚያስፈልግበት በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት ከጠላት ጋር በተደራቢ አጥቂነት ከተሰለፉ አከላት መካከል በሁለተኝነት የሚጠቀሱት አንቂዎች ናቸው።
የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት አንቂነት ወይም በእንግሊዝኛው አክቲቪስትነት የሚለውን ቃል “ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጠንካራ የፖሊሲ ወይም የተግባር ዘመቻ” በማለት ይተረጉመዋል።
የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንትና ተመራማሪዎች ደግሞ አንቂነት ወይም አክቲቪስትነት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ታስቦ የሚከናወን ህዝብን የማሳወቅ፣ የማስተማር፣ የመቀስቀስና ማንቃት ሥራ መሆኑን ይገልጻሉ።
ሃሳቡን በተመለከተ በምሁራኑ የተሰጠው ብያኔም ከመዝገባዊ ቃላዊ ትርጉሙ ጋር የሚስማማ እንጅ የሚጣረስ አይደለም። በዚህ መሰረት “አክቲቪስት” ወይም “አንቂ” ማነው የሚለውን ስንጠይቅ የአክቲቪስትነትን ወይንም የአንቂነትን ሥራ የሚሠራ ማለትም በአንድ በተወሰነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ህዝብን የሚጠቅም ለውጥ ለማምጣት ብዙሃኑን የሚቀሰቅስና የሚያነቃ ሰው ነው አክቲቪስት የሚባለው።
ይሁን እንጅ አሁን በእኛ አገር ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው “የአክቲቪስትና የአክቲቪስትነት ጉዳይ” ግን ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን እንታዘባለን። በአጭሩ ትክክለኛውን አካሄድ ያልተከተለና ከዓላማው የተጣላ ነው። ምክንያቱም እውነተኛ አንቂነት መጠየቅ ነው።
እውነተኛ አንቂም መረጃን በመጠቀም ሃገርና ህዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት፣ ብሎም አዎንታዊ ለውጥ እንደመጣ ከፊት ሆኖ መምራት ነው። ነገር ግን አሁን በተጨባጭ በሃገራችን ላይ እያየነው ያለነው አንቂነት ሃገርና ሕዝብን የሚጠቅም ሳይሆን የሚጎዳ ነው።
አንቂ ነን የሚሉ ግለሰቦች እንኳንስ በአዘቦት ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ባላቸው አካላት ሃገር በሚዲያ ዘመቻ እየተካሄደባት በምትገኝበት በዚህ አስቸጋሪ የፈተና ወቅትም ለሃገራቸው ጥቅም ዘብ ሲቆሙ አላየንም።
እንዴያውም በተቃራኒው ልክ እንደ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሁሉ አንቂ ነን የሚሉ የሃገር ልጆችም ሃገር ችግር ውስጥ ባለችበት ሰዓት በሃገርና በሕዝብ አንድነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ነው የተመለከትነው። አንቂነት ዋነኛ ዓላማው ለህዝብና ሃገር ጥቅም ዘብ መቆም ሆኖ ሳለ የእኛወቹ አንቂወች ግን መረጃንና የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም አገርን ለማፍረስ፣ ህዝብን ለማባላት ሲቀሰቅሱ ነው የምናስተውለው። ለሃገር ጥቅም ዘብ ከመሆን በተቃራኒው ለራሳቸው ጥቅምና ለግል ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸው የሚሠሩ አካላት በአንቂነት ስም ከጠላት ጋር በተደራቢ አጥቂነት ተሰማርተው አስተውለናል።
ለህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ያሰቡ በማስመሰል ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩና በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ሐሰተኛ መረጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዛት እየተያሰራጩ ባሉበት በዚህ ሰዓት አንድም የጠላትን የጥቃት መረጃ እንደወረደ ተቀብሎ በማስተጋባት ሁለትም የራሳቸውን የሐሰት መረጃ በመፈብረክና በማሰራጨት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጠላት መሳሪያ ሆነው ሲያገለግሉ ታዝበናል።
ይህም ለኅዝብ ጥቅም ከቆመው ትክክለኛው የአንቂነት ዓላማ በተቃራኒው የተሰለፈ በመሆኑ ለአንቂውና ለሞያው ትልቅ ፈተና ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪም የሐሰት አካውንቶችን በመጠቀምና ማንነታቸውን በመደበቅ አክቲቪስት መስለው የፕሮፓጋንዳ ሥራ የሚሠሩ አካላትም መኖራቸውም ሌላው ዘርፉን እፈተነ የሚገኝ መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎችም ያመኑት ሐቅ ሆኗል።
መረጃን ለአወንታዊ ለውጥ
በአጠቃላይ ሲታይ የአንቂነትም ሆነ የሚዲያ ወይንም የመረጃ ሥራ ትልቅ ኃላፊነት የሚያስፈልገው ሥራ ነው፤ ከራስ አልፎ ለሌሎች መጠየቅ፣ ተገቢና ትክክለኛ መረጃን በተገቢው ወቅትና ሰዓት ለሕዝብ ማዳረስና እንዲጠቀምባት የማስቻል የአንቂነትና የሚዲያ ሥራ ከሁሉም የላቀ ተግባር በመሆኑ አንቂም ሆነ የሚዲያ ባለሙያ ከማንም በላይ ትልቅ ኃላፊነት አለበት።
ይህንን ኃላፊነቱን የማይወጣና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሠራ ማንኛውም አካል አንቂ ሳይሆን “አጥቂ” በመሆኑ በሥራው ሊያፍር ይገባል። መረጃን ለጥፋት የሚጠቀም የሚዲያና የመረጃ ባለሙያም የመረጃ ባለሙያ ሳይሆን “የመፋጃ በለሙያ” ነውና በድርጊቱ ሊያፍር ይገባል።
ዘመናችን የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እጃችን ላይ ያለውን የመረጃ ኃይል በከንቱ አናባክነው፣ ለመልካም ነገር እንጠቀምበት፣ ራሳችንን፣ ሃገራችንን እና ዓለማችንን በአዎንታ ለመለወጥ እንጠቀምበት እላለሁ። ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን አልፋ፣ ጠላቶቿን አሸንፋ ሽዎች ዓመታትን በክብር ኖራለች አሁንም ለዘላለም ትኑር!
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013