ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የመንግሥት ስልጣንን በጥቂት የቤተሰብ አባላት ተቆጣጥሮ የሀገሪቱን ሀብት እና የህዝቡን ስነልቡና ሲዘርፍ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀብት ሲያከማች፤ ስልጣኑን መከታ አድርጎ ህዝብን ሲያማርር እና በዘር ሲከፋፍል የኖረው የህወሓት ጁንታ ቡድን ዳግም ላይመለስ ከተደመሰሰ ወራቶችን አስቆጥሯል።
ዋና ዋናዎቹ የጁንታው ቁንጮዎች ሲደመሰሱ ጥቂቶች ደግሞ በየበረሀው ተበታትነዋል። አንዳንዶችም ሀገር ጥለው ፈርጥጠዋል። ይሄ የትግራይንም ሆነ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ያስደሰተ እፎይም ያስባለ የድል ውጤት ነው።
የጁንታው ቡድን አባላት ገና ከመነሻቸውም ህዝብን እንደ መከለያ አድርገው ተንቀሳቀሱ እንጂ አንድም ጊዜ የህዝብ ወገንተኛ ሆነው አያውቁም። አንድም ጊዜ ለህዝብ አድረው ፣ ለሀገር ልማትና ዕድገት አስበው አያውቁም።
ይልቁንም የሀገርንና የህዝብን ሀብትና ንብረት ለብቻቸው ጠቅልለው ህዝቡንም እንደ ጠላት በመቁጠር ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩበትን መንገዶች ሲቀርጹ ፤ ይሄንኑ ሲሰብኩና ሲያራምዱ በሴራ ኖረዋል። ይሄ በህዝቦች መካከል የቀበሩት ህዝብን የመከፋፈል ቦንብ በየቦታው ፈንድቶ በሀገር ላይ ምን አይነት የሰላም መደፍረስ አስከትሎ እንደነበር ከለውጡ ዋዜማ የነበረውን ጊዜ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው ።
የጁንታው ቡድን በትግራይ ክልልም ቢሆን ህዝብን ሳይሆን ራሱን ሲጠቅም፤ በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም ዘርፍ ራሱን ሲያገነግን እንደነበር ይታወቃል። የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው በሚል አደናጋሪ ብሂሉ ህዝቡን በቃላት ከመደለል ውጪ ለህዝቡ ምንም የፈየደው ነገር አልነበረም።
በትግራይ የህግ ማስከበር ዘመቻ በተካሄደበት ወቅት እንኳን ከተማውን ለቆና ፈርጥጦ ሲሸሽ ያደረገው የትግራይ ህዝብ የሚጠቀምባቸውን የመሰረተ ልማት አውታሮች ማውደም ነው። በዚህ እኩይ ተግባሩም መንገዶችን ማረስ፤ ድልድዮችን ማፍረስ ፤የአየር ማረፊያዎችን መፈነቃቀል ፤ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን፣ መንግሥታዊ እና ሌሎች ህዝቡን የሚያገለግሉ ተቋማትን አፍርሷል፡፡ ዘርፏልም።
ይህ አልበቃው ብሎ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ ሌላ የግፍ ግፍ ፈጽመዋል፡፡ ለዚህ እኩይ ተግባሩም ታስረው የነበሩ ከአሥር ሺህ በላይ ወንጀለኞችን በከተሞች በመልቀቅ በሰላማዊው ነዋሪ ህዝብ ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል።
በተደጋጋሚ ሴቶችን በመድፈር፣ በዝርፊያ እና በተለያዩ ወንጀሎች በማረሚያ ቤቶች የነበሩ እስረኞችን ፈትቶ በከተማው ላይ በመበተን ድሮውንም የሚጠሉትን ህዝብ ዳግም ጥቃት እንዲደርስበት ፣ በዘራፊዎች እንዲሰቃይ አድርጓል።
እነዚህ እኩይ ተግባራቱ ከብዙ የጥፋት ድርጊቱ ጥቂቱን ለማሳየት ያክል የተጠቃቀሱ በቅርቡ በህግ ማስከበር ወቅት የታየው እውነታ መገለጫዎች ናቸው። የጁንታው ቡድን ቀደም ሲል ሲሰራው የነበረው ሴራም ይሄንኑ ሀቅ ዳግም ያረጋገጠ ነው። ይሄ በተጨባጭ የታየ ህዝቡም በአይኑ አይቶ በእጁ ዳስሶ የመሰከረው እውነታ ነው።
ዛሬም የጁንታው ርዝራዦች ከዚሁ ተግባራቸው አልተቆጠቡም። በህዝቡ ላይ የተለያዩ የሽፍትነት ትንኮሳ እያደረሱ እና የውንብድና ጥቃትም እየፈጸሙ ናቸው ። በየጉራንጉሩ እየተሹለኮለኩም በንጹሃን ላይ ተማሪዎች ጭምር መንገድ ላይ ጠብቆ መግደል ማቁሰልና መኪና ማቃጠል ሌላው የርዝራዦቹ መገለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡
ይህ የሚያሳየው ደግሞ ምንም እንኳን ዋናዎቹ የተለቃቀሙ ቢሆንም በየሸጡ ተቆራርጠው የቀሩ እና በየቦታው ተሸሽገው ያሉ ርዝራዦች አሁንም በትግራይ ክልል ማህበረሰቡን የሚጎዱ ተግባራት ከማድረግ አለመቆጠባቸውን ነው፡፡
በዚህ እኩይ ተግባራቸውም ጁንታው ቀደም ሲል ያወደመውን የኤሌክትሪክ ኃይል መልሶ በመገንባት ለህዝቡ ጥቅም እንዲሰጥ ቢደረግም፤ ወር ባልሞላው ጊዜ ውስጥ እነዚህ ርዝራዦች ዳግም ለከፍተኛ ውድመት ዳርገውታል። ይሄን ማድረጋቸው ደግሞ የሚጎዳው መንግሥትን ወይም ሌላውን ህዝብ አይደለም።
በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት ሥራ የሚቋረጥበት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያጣው፣ የህክምና እና የባንክ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዳያገኝ የሚሆነው ለዘመናት ግፍ ሲፈጽሙበት የነበረው የትግራይን ህዝብ ነው።
የትግራይ ህዝብ ዛሬ የሚፈልገው ሰላም ነው፤ ልማት ነው ። ከሌላው ብሄር ብሄረሰብ ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ መኖርን ነው። ሆኖም ግን የጁንታው ርዝራዦች አሁንም የሽፍትነታቸውን ጥቃት በመፈጸም እነዚህን ዜጎች ለስቃይና ለችግር እየዳረጉ ነው። አለሁልህ ቆሜልሀለሁ እያሉ በራሱ እንዳይቆም እያደረጉትና እየጎዱት ይገኛሉ።
ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ሰላሙ እንዲመለስ በመንግሥት የተጀመረው መልሶ የማልማት እንቅስቃሴም ፍሬ እንዲያፈራ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ የጁንታውን ርዝራዦች ጠራርጎ ማጥፋት ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ ከህዝብና ከአካባቢው ነዋሪዎች የሚደበቅ ምንም አይነት ወንጀልና ወንጀለኛ የለምና ህዝቡም ከመንግሥት ጎን በመቆም ርዝራዦችን ከያሉበት እንዲለቃቀሙ ሊተባበር ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013