እስማኤል አረቦ
በውጭ ሀገራት የሚኖር ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከሶስት ሺህ እንደሚዘል ይነገራል:: ይህ የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፤ በፖለቲካ ተጽእኖ፤ ለትምህርት ወዘተ ሀገሩን ለቆ የወጣና ኑሮውንም በአውሮፓና አሜሪካ የመሰረተ ነው::
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ እስካሁን በነበረው ሁኔታ በሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ ድምጹን ሲያሰማ ቆይቷል::
በተለይም የኢህአዴግ መንግስት የሚፈጽማቸውን የመብት ጥሰቶችንና አፈናዎችን በመቃወም የነበረው መንግስት በህዝብ አመጽ እንዲገረሰስ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል::
በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ መንግስት ስልጣኑን ከያዘ በኋላ የዲያስፖራው ተሳትፎ ከመቃወም በዘለለ በተለያዩ ልማቶች ላይ አሻራውን ወደ ማሳረፍ ተሸጋግሯል:: ለህዳሴ ግድብ፤ለገበታ ለሀገር፤ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍና በየጊዜው ለሚደርሱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ያለውን ገንዘብ በማዋጣትና በሀሳብና በዕውቀት በመደገፍ ሀገራዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል::
በተለይም በቅርቡ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ በመደገፍ ያሳየው ሀገራዊ ተቆርቋሪነትና አለሁ ባይነት በእጅጉ የሚያስመሰግነው ነው:: የህወሓት ቡድን እራሱ ቆስቁሶ በጋየበት የሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም በአንጸባራቂ ድል ቢጠናቀቅም በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቡድኑ ርዝራዦች የከፈቱት ሀሰተኛ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ዘመቻ ግን መጠነ ሰፊ ነበር ::
ይህ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ሀሰተኛ ዘመቻ የተጀመረው ገና ቡድኑ ሳይደመሰስ በፊት ነበር:: ትግራይ ቴሌቪዥንን ፣ ድምጺ ወያኔን ፣ ወይንን ፣ ትግራይ ሚዲያ ሀውስን (TMH )፣ ትግራይ ፈርስት፣ አይጋ ፎረምን፣ ትግራይ ፕሬስን፣ ቮይስ ኦፍ ትግራይ፣ ትግራይ ኦን ላይንና አውራምባ ታይምስ የሚያካትት ነው::
ዲጂታል ወያኔ የተሰኘውም ሀሰተኛ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ዘመቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የዲጂታል ጭፍራ ያለው እና በአንድ ለአምስትና በአንድ ለሀያ ተደራጅቶ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ በፌስ ቡክ ፣ በቲዊተር፣ በዩቲውብ፣ በቴሌግራም፣ ወዘተረፈ የተዛባ መረጃን፣ ውሸትን፣ ጥላቻን፣ ልዩነትን፣ መጠራጠርን፣ ሴራን፣ ወዘተረፈ የሚነዛ ተከፋይና ምንደኛ ስብስብ ነው:: ሌላው የሀሰተኛው ዘመቻ ስልት አለማቀፍ ሚዲያውን የተዛባ መረጃ የሚመግብ ምድብተኛ ነው ።
ዓለም አቀፍ ታዋቂ ሰዎችን በገንዘብ በግዛትም የኢትዮጵያን ስም ለማጥፋት የሚደረገው ስልትም የዚሁ ዘመቻ አንዱ አካል ነው:: በዚህ ምድብ ነጮች ስፒን ዶክተርስና ሎቢስትስ (spin doctors & lobbyist) የሚሏቸው ሲሆኑ አላማቸው እንደቅደም ተከተላቸው አንድን ርዕሰ ጉዳይ እነሱ ከሚፈልጉት አቅጣጫ አንጻር እንዲተረጎምና እንዲበየን ጥረት ማድረግ ነው::
ሎቢስቶች ደግሞ ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈላቸው የመንግስት ባለስልጣናትን፣ የምክር ቤትና የሰኔት አባላትን በማግባባትና በማባበል ከቀጠራቸው ወይም ከከፈላቸው መንግስት ወይም ቡድን ጎን ለማሰለፍ ግፊት የሚያደርጉና የሚያግባቡ ናቸው። እነዚህ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አለማቀፍ ሚዲያውንና እንደ መንግስታቱ ድርጅት ያሉ አለማቀፍ ተቋማትን የሚመግቡና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ናቸው።
የቡድኑ ርዝራዦች በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያ ሌት ተቀን እየዘሩት የሚገኘውን የጥላቻና የልዩነት ሀሰተኛ መረጃ በመመከት ረገድ አሁን አሁን በኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ቅንጅት እየተመከተ ይገኛል::
በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ የዲያስፖራው አባላት ያለማንም ቀስቃሽነት የራሳቸውን ዕውቀት፤ ገንዘብ እና ሃሳብ በማዋጣት ሀገር የማፍረስ ዘመቻውን እየመከቱ ይገኛሉ::<<UNITY FOR ETHIOPIA>> በሚል መጠሪያ አምስት የሚደርሱ የትዊተር ዘመቻዎችን በማካሄድ እውነተኛውን የኢትዮጵያ ገጽታ ለማሳየት እየሞከሩ ነው::
የዘመቻው የሚዲያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ስዩም አሰፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩትም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በህወሓት ርዝራዦች አማካኝነት ለዓለም ህብረተሰብ እየደረሰ ያለውን ሀሰተኛ መረጃ በማጋለጥ ኢትዮጵያ ያለችበትን ትክክለኛ መንገድ ለማሳየት አምስት የትዊተር ዘመቻዎች ተካሂደዋል::
በየአንዳንዱ ዘመቻም የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳየት የተደረገው ጥረትም ፍሬ እያፈራ ነው:: ለአብነትም በአራተኛው የቲዊተር ዘመቻ 130 ሺ ሰዎች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በአምስተኛው ዘመቻ ይህ ቁጥር ወደ 200ሺ አድጓል::
በቅርቡም ስድስተኛውን ዘመቻ ለማካሄድ እንቅስቃሴዎች መጀመራችውንም ጠቁመዋል:: በተደረጉት ዘመቻዎችም ቀደም ሲል ተደናግረው የነበሩ የውጭ ዜጎችና ባለስልጣናት የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለመረዳት እንደቻሉ የሚዲያ አስተባባሪው ተናግረዋል::
መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ የበላይነት ዘመቻ በወሰደበት ወቅት ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ የሚከቱ፤ አለማቀፍ ማህበረሰቡን ዛሬ ድረስ የሚያደናግሩ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች በዲጂታል ወያኔ አማካኝነት ሲሰራጩ በቆዩበት ወቅት ሁሉ እነዚህ የዲያስፖራ አባላት ሀገራቸውን ለመታደግ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል::
ሆኖም ግን በህወሓት ርዝራዦችና በሚከፈላቸው ሎቢስቶችና የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የሚነዙ ሀሰተኛ መረጃዎች ስፋት ያላቸው በመሆኑ እነዚህን ሀሰተኛ መረጃዎች ለመመከት የሚያስችል በቂ መረጃዎችን በማግኘት ረገድ ችግር እንደገጠማቸው አቶ ስዩም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግረዋል::
መንግስት በነዚህ የጥፋት ኃይሎች የሚነዙትን ሀሰተኛ ወሬዎች እየተከተለ ለእያንዳንዱ መልስ መስጠት ባይችል እንኳን አንኳር የሆኑትን በመለየት በፍጥነት መልስ የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋት ነበረበት ይላሉ አቶ ስዩም::
መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻውን በውጤታማነት ከተወጣ በኋላ ለሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ስራው ትኩረት አለመስጠቱ ሀሰትና ወሬ ለማናፈስ ለሚፈልጉ አካላት ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው በመሆኑ የዲያስፖራውም አካላት እነዚህን ሀሰተኛ ወሬዎች እየተከታተሉ ለማምከን ለጊዜውም ቢሆን ችግር ማጋጠሙን አቶ ስዩም አልሸሸጉም:: ሆኖም ግን መንግስት ሁኔታውን ተመልክቶ መረጃዎች በተደራጀ መልኩ በፍጥነትና በጥራት የሚለቀቁበትን አሰራር ይዘረጋል የሚል እምነት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል::
በአጠቃላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ለመታደግ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታና በሰው ሀገር ከኑሮ ጋር ግብግብ እየገጠሙም ቢሆን ለሀገራቸው ቅድሚያ እንደሚሰጡ ያሳየ አኩሪ ገድል ነው::
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ኃይላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ያሉትን የህወሓት ቡድን ርዝራዦችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድና የተረጋጋች፤ የበለጸገችና የታፈረች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በዲያስፖራ አባላት የተጀመረው ሀገርን የመታደግ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት እንላለን::
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013