ሙሉቀን ታደገ
ከአሁን በፊት በአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ፍረዱኝ አምድ ስር በሁለት ክፍሎች በቀረበ ፅሁፍ “የባለ ብሩህ አእምሮው እና የልማት ባንክ ውዝግብ“ በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ማድረሳችን ይታወቃል:: ከዚህ ቀደም ለህዝብ ባደረስናቸው ጽሁፎች ለመግለጽ እንደሞከርነው የሚመለከታቸው አካላትን በማናገር የውዝግቡን መጨረሻ ለአንባቢን እንደምናደርስ ገልጸን ነበር::
በቃላችን መሰረት ውዝግቡ የት እንደደረሰ ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ በዚህ ጹሁፋችን ይዘን ቀርበናል:: ቀጥታ ዛሬ ላይ ከባለድርሻ አካላት ያገኘነውን መልስ ከመጥቀሳችን በፊት ለመንደርደሪያ ይረዳን ዘንድ ሁለቱን ወገኖች ያወዛግብ ስለነበረው ጉዳይ ትንሽ ማለቱ አይከፋም::
አቶ ሰለሞን ሰብስቤ ይባላሉ በህክምና ሳይንስ ተመርቀው በሙያቸው ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተው በሙያቸው ላይ እያሉ ተፈጥሮ የቸረቻቸውን የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ብዙ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር የቻሉ ባለ ብሩህ አእምሮ ሰው ናቸው:: በዚህ የፈጠራ ስራቸው በሀገራችን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በአህጉር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የፈጠራ ባለቤትነት ሽልማቶችን አግኝተዋል::
ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት ስራዎቻቸው በሃገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የባለ አእምሮ ባለንብረትነት ሰርተፍኬት ሽልማቶችን ለማግኘት ችለዋል::
ይህን የተመለከቱ የተለያዩ ድርጅቶች አቶ ሰለሞን ሰብስቤ የብድር አቅርቦት ቢመቻችላቸው ራሳቸውን ብሎም ሀገራቸውን መጥቀም እንደሚችሉ በማመን የብድር አገልግሎት እንዲመቻችላቸው ለልማት ባንክ የድጋፍ በደብዳቤ ይጽፉላቸዋል::
ይህን ተከትሎ አቶ ሰለሞን ሰብስቤ የብድር ጥያቄ ፕሮፖዛል በ2008 ዓ.ም ለልማት ባንክ ያስገባሉ:: ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ባለ ብሩህ አእምሮው ያስገብትን ፕሮፖዛል በወፍ በረር መመልከቱ ተገቢ ነው::
አቶ ሰለሞን ሰብስቤ ሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ኃ/የተ/የግ ማህበር የሚባል ድርጅት በማቋቋም ከልማት ባንክ ብድር ይጠይቃሉ:: አቶ ሰለሞን ብድር ሲጠይቁ ያገስገቡት ፕሮፖዛል ለአጠቃላይ ስራ ማስኬጃ 15ሚሊዮን 571ሺህ 680 እንደሚያስፈልግ እና ከዚህ ገንዘብ 12 ሚሊዮኑ 55ሺህ 400 (80.6%) ብር ለካፒታል ኢንቨስትመንት(fixed investment)፣ 550 ሺህ 000 (3.5%) ብር ደግሞ ደግሞ ለቅድመ ምርት ወጪ(pre-production expense) ቀሪው ሁለት ሚሊዮን 470 ሺህ 280 (15.9%) ብር ደግሞ ለስራ ማስኬጃ ( working capital) እንደሆነ በፕሮፖዛሉ ላይ አመልክተዋል ::
አጠቃላይ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ የተወሰነውን ብር በስራ ፈጣሪው የሚሸፈን ሲሆን 12 ነጥብ 55 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደሚሸፈን፣ ድርጅቱ ስራውን ለመጀመር ምን ምን ማሽን እንደሚያፈልግ ፣ የሚገዘው ማሽን ምን ምን ማምረት እንደሚያስችል እና ድርጅቱ ምርት ለማምርት የሚያስችለው በ194 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ እንደሚያስፈልገው ይህም ቦታ በአዲስ አበባ በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 02 እንደሚገኝ የብድር ዝርዝር ዕቅዱ(ፕሮፖዛሉ) ግልጽ እንደሚያመላክት አቶ ሰለሞን ይናገራሉ ::
ከዚህ ባሻገር በፕሮፖዛሉ ላይ የተቀመጠው ድርጅቱ የሚያመርተው ምርት የሚኖረውን ሃገራዊ ፋይዳ ይጠቁማል የሚሉት አቶ ሰለሞን በዚህ መሰረት ፋብሪካው ያለቀላቸውን እና በጥሬ እቃነት የተለያዩ መለዋወጫዎችን (ስፔር ፓርቶችን) ለተለያዩ አምራች ድርጅቶች ማቅረብ ያስችለዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከእንጨት እና ከብረት የሚሰሩ ለህክምና አገልግሎት የሚያገለግሉ (የሜዲካል) ፈርኒቸሮችን እና ቁሳቁሶችን በዋናነት ስለሚያመርት (Important medical furniture and equipment manufacturing የሚባሉትን forging, stamping, bending, forming, and machining, used to shape individual pieces; and other processes, such as welding and assembling, used to join separate parts together) ለሃገራችን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ለመቀነስ ድርጅታቸው የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት በፕሮፖዛሉ መካተቱን አቶ ሰለሞን ይናገራሉ::
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ ፕሮፖዛሉን የተመለከተው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሳያቅማማ እና ውሎ ሳያድር የገባውን የብድር ፕሮፖዛል አዋጭነቱን በማጥናት ከልማት ባንክ የእቃ ሊዝ የፋይናንስ ብድር እንዲመቻችላቸው አድርጓል::
በዚህም መሰረት ከላይ ያሉትን የተቋሙን አላማ፣ የመስሪያ ቦታ እና ስፋት፣ የሚያመርተውን የምርት አይነት እና ድርጅቱ የጠቀሳቸውን ምርቶች ለማምረት የሚያስፈልጉ ማሽኖች በመመልከት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሶለሰብ የቤት እና የቢሮ የእቃዎች ማማረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ብድር ይፈቅድላቸዋል::
በዚህም መሰረት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር አፅዳቂ ቡድን አጠቃላይ ዋጋ ውስጥ ብር 12 ሚሊዮን 586 ሺህ 231/ አስራ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰማኒያ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ አንድ ብር/ በፀደቀው የብድር ስምምነት መሰረት የካፒታል እቃው Ethio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት አረብ ኢሜሪትስ (UAE) አቅራቢ ድርጅት እንዲገዛ በተወሰነው መሰረት ግዥ ተፈፅሟል::
እነዚህ ማሽኖች በሊዝ ብድር ወይም በኪራይ የሚተላለፉ ናቸው:: ማለትም ባንኩ አበዳሪ ወይም አከራይ ሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማማረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደግሞ ተበዳሪ ወይም ተከራይ ናቸው ::
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአከራይ እና በተከራይ መካከል ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም የተፈፀመውን የካፒታል እቃ ዱቤ ግዢ እና ኪራይ ውል መነሻ በማድረግ ከዚህ ሰነድ ጋር በተያያዘው ዝርዝር መግለጫ ( specification or packing list ) መሰረት Ethio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት አረብ ኢሜሪትስ (UAE) አቅራቢ ድርጅት የተፈቀዱ የማሽን ግዥ ተፈፅሞ የፕሮጀክቱ ሳይት የደረሱ 31 የሚሆኑ ማሽኖች መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም ድርጅቱ በሚገኝበት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፤ የካ ክፍለ ከተማ ፣ ወረዳ 02 የቤት ቁጥር Shee/ 19 በሆነው ቦታ ላይ ጊዜያዊ እርክክብ መፈጸሙን አቶ ሰለሞን አመልክተዋል::
እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ ከዚህ በኋላ ነው በባንኩ እና ሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማማረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሃከል ስምምነት ጠፋ:: ለዚህም ዋናው ምክንያት በብድር/በሊዝ ኪራይ ውሉ ላይ ባንኩ የተስማማውን ስምምነት ስላልተፈፀመ ነው ሲሉ ሶለሰብ የቤት እና የእቃዎች ማማረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሰብስቤ ጠቁመዋል::
የተፈጠረውን የአለመግባባት መነሻ ምክንያት የአከራይ እና ተከራይ ውል በመሆኑ የአከራይ እና ተከራይ ውል ለማስታወስ የተወሰነውን በወፍ በረር መመልከት ያስፈልጋል:: ውልም እንደሚከተለው ያትታል::
“ተከራይ በዚህ ውል መሰረት “ፕሮዤው ” ተብሎ የሚጠራውን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ክልል ውስጥ የቤት እና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅት ለማቋቋም አጠቃላይ ዋጋው ብር 12 ሚሊዮን 586 ሺህ 231 የሚያወጣ በዚህ ውል የተጠቀሰውን፡- medical manufacturing ማሽነሪ/ የካፒታል ዕቃ ከ Ethio-Arab International General trading L.L.C ከተባለ የተባበሩት አረብ ኢሜሪትስ (UAE) አቅራቢ ድርጅት እና ቶዮታ ፒካአፕ Ethio-Arab ለማቅረብ ባንኩ መስማማቱን ይገልፃል:: ይህ የሚሆነው በአንቀፅ ሶስት ላይ ተከራዩ ወይም ተበዳሪው የሚጠበቅበትን ከአከናወነ ነው:: “ ከዚህ ጋር ተያይዞ የብድር ውሉ አንቀፅ ሶስት ምን ይላል የሚለውን ማየት ተገቢ ነው::
“3.1 ተከራይ በዚህ ውል አንቀፅ አንድ ስር የተጠቀሰው እቃ ከመገዛቱ በፊት እና ይህን ውል በሚመለከት አስፈላጊ መስፈርቶች (ፎርማሊቲዎች) ሁሉ ከተጠናቀቁ በኋላ ለፕሮዤው ስራ ማስሄጃ የሚውል የራሱን መዋጮ ብር 3,146,588 / ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሰማኒያ ስምንት ብር / በጥሬ ገንዘቡ በባንኩ የማይንቀሳቀስ ሂሳብ / Blocked Account/ ውስጥ ማስቀመጡ ሲረጋገጥ በዚህ ውል አንቀፅ አንድ መሰረት የእቃው መግዣ ገንዘብ ለአምራቹ ወይም ለአቅራቢው ይከፈላል::
3.2 ተከራይ በዚህ በላይ በተጠቀሰው አንቀፅ መሰረት ከራሱ መዋጮ ለባንኩ ገቢ ያደረገው ገንዘብ፤ የኪራይ እቃውን / የማምረቻ መሳሪያውን መረከቡን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ለባንኩ ማቅረቡ ሲረጋገጥ ለስራ ማስኬጃ እንዲውል ከዚህ ቀጥሎ በተመለከተው አኳኋን ከተከራይ ሂሳብ ላይ ወጪ ይደረጋል :: “
ይህን የአንቀጽ ሶስት ተፈፃሚነት በመጓደሉ አቶ ሰለሞን ከልማት ባንክ ጋር የተለያዩ ደብዳቤዎችን ቢጻጻፉም ደብዳቤዎቹ ከተራ ወረቀትነት ያለፈ ረብ ያለው መፍተሄ ከልማት ባንክ ማግኘት እንዳልቻሉ አቶ ሰለሞን አመልክተዋል::
ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በተለይ ማሽኑ ርክክብ ከተፈፀመ አንስቶ ለሶስት ዓመታት ያህል የባንኩ የቅርንጫፍ እና የዲስትሪክት አመራሮች ከእቃ ብድር ውል ውጭ የሚሰጡ ያልተገቡ ተልካሻ ምክንያቶች ናቸው የሚሉት አቶ ሰለሞን በዚህም ማሽኑ ሸረሪት ድር አድረቶበት እና በአቧራ ተውጦ ስንት ሰራተኞችን በመቅጠር የስራ አጥነትን ችግር እና የውጭ ምንዛሬ ችግርን መቅረፍ ሲችል ያለምንም ስራ ለሶስት ዓመታት ያለ ስራ ቁጭ እንዲል ተፈርዶበት እንደኖረ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ ::
በዚህ ሁሉ ነገሬን አጥቻለሁ የሚሉት ባለ ብርህ አዕምሮው ሰው መፍትሄ ለማግኘት ያረገጥኩት የመንግስት ቢሮ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም ሲሉ ይናገራሉ:: ለምሳሌ የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ፣ የየካ ክፍለ ከተማ እና በየካ ክፍለ ከተማ ስር ለሚገኘው ወረዳ 02 ፣ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር ለሚገኘው ለኬሚካል እና ለብረታ ብረት ዘርፍ ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወዘተ ይገኙበታል::
በዚህ ጊዜ ነበር የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ፍረዱኝ በሚል አምዱ በጓዳ ጎድጓዳ እየገባ ይመለከታቸዋል የሚላቸውን የመንግስት አካላት የጠየቀው:: የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ካነጋገራቸው የመንግስት አካላት መካከል የኢትዮጵያ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ሃላፊ ፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብረታብረት ዘርፍ ተጠሪ፣ የልማት ባንክ ወዘተ ይገኙበታል::
እነኚህ ከልማት ባንክ ውጭ ያሉት የመንግስት ተቋማት “በእቃ ሊዝ ኪራይ ውል መሰረት የመስሪያ ገንዘቡ ወይም ወርኪንግ ካፒታል ለምን አልተለቀቀም ሲሉ የልማት ባንክን ይጠይቃሉ::” ነገር ግን የልማት ባንክ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሳይቀር ለጉዳዩ አንድ ቁርጥ ያለ ሃሳብ ከመናገር ይልቅ በዚህ ወጥቶ በዚህ ወርዶ እያለ ሁነኛ መፍትሄ መስጠት አልቻለም::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በፍረዱኝ አምዱ ከላይ የተጠቀሱትን የመንግስት ተቋማት በተለይም የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ፣ የየካ ክፍለ ከተማ እና በየካ ስር ለሚገኘው ወረዳ 02 ፣ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብረታ ብረት ዘርፍ ፣ ስለጉዳዩ በተለያየ ጊዜያት መፍትሄ እንዲመጣ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ::
በመጨረሻም የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ በባንኩ የሚገኙ ሌሎች ሃላፊዎች እና በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኬሚካል እና የብረታ ብረት ዘርፍ ባለሙያዎች ባደረጉት ውይይት ችግሩ መፍትሄ ሊያገኝ ችሏል::
በዚህም ጊዜ ፕሮጀክቱ ለሃገር ኢኮኖሚ የሚያደርገውን አውንታዊ ተፅዕኖ በውል የተገነዘበው እና የሶለሰብ ስራ አስኪያጅ እሮሮ ያሳሳበው የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጉዳዩን በጥብቅ ሲከታተል ስለነበር በልማት ባንክ እና በብረታ ብረት ዘርፍ ባለሙያዎች ተገናኝቶ በሚወያዩባቸው ጊዜ የተገኘው የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍለ ስለጉዳዩ የሁለቱንም መስሪ ቤቶች አነጋገሮ የሁለቱንም መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ምላሸ እንደሚከተለው አሰናድቷል::
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሊዝ ፋናንሲግ ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መለሰ ማሩታ እንደሚሉት ለሶለሰብ የቤት እና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ድርጀት በሊዝ የተላለፉት ማሽኖች በጣም ትልልቅ እና ዘመናዊ ማሽነሪዎች ናቸው:: እነዚህ ማሽነሪዎችም የተለያዩ የቢሮ እና የህክምና እቃዎችን ማምረት የሚያስችሉ ናቸው::
ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህ ማሽነሪዎች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ ቆይተዋል:: ትልልቅ ማሽነሪዎችን በእንዲህ አይነት ሁኔታ መቀመጣቸው በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ዘርፈ ብዙ ችግሮች መሆኑን የተረዳው በልማት ባንክ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ማሽኖቹ ወደ ስራ ለማስገባት መፍትሄ በማምጣት እና ፕሮጀክቱ ከዚህ የበለጠ መጓተት ውስጥ የሚከት ነገር መፈጠር እንደሌለበት ታምኖበታል::
ስለሆነም ከስራ ባልደረቦቼ ጋር በመነጋገር ስራውን ማስጀመር እንዳለብን እና ከባንኩ የሚጠበቀውን መፈጸም እና ደንበኛው ደግሞ ይህ ማሽን ወደፊት የራሱ እንደሚሆን ተገንዝቦ ማሽነሪውን በአግባቡ ጠብቆ ስራውን ጀምሮ የሚጠበቅበትን ኪራይ
ክፍያ ፈፅሞ ባለንብረቱን እንዲያዛዋውር እንፈልጋለን::
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ወደፊት እንደዚህ አይነት መጓተቶች እንዳያጋጥሙ የልማት ባንክ አሰራሩን ፈትሿል፣ ፖሊሲውን ከልሷል:: የነበሩትን መጓተቶች ላለመድገም የልማት ባንክ ለአንድ ዓመት ያህል ሊዝ ፋናንሲንግ አቆሞ ነበር:: አሁን የሊዝ ፋናንሲንግ ስንጀምር ከዚህ ቀደም ብሎ በነበሩት አካሄዶች ውስጥ ማለፍ ስለሌብን ድክመታችንን የት አካባቢ እንዳለ ለይተናል::
በዚህም ከዚህ ቀደም የነበረውን መጓተት በማሻሻል እና በመቅረፍ በተሻለ ሁኔታ አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው :: ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የልማት ባንክ በሰው ሃይሉም፣ በአሰራሩም፣ በአደረጃጀቱም ለውጥ ላይ ይገኛል:: በዚህም ከዚህ በፊት የነበሩበትን ድክመቶች በመቅረፍ የተሻለ እና የተስተካከለ አገልግሎቶችን ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ::
አቶ ሰለሞን እውቀቱ ያለው ሰው ነው ፤ የሜዲካል ቁሳቁሶችን በማምረት ልምድም እንዳለው ተግንዝበናል የሚሉት ዳይሬክትሩ፤ እንኳንስ እንደ አቶ ሰለሞን ያሉ ባለሙያ ተገኝቶ ይቅር እና ሙያው የሌላቸውን ሰዎች ቢሆን እንኳን ስልጠናዎችን በመስጠት እና ሰዎችን ለስራዎች ብቁ በማድረግ ሃገሪቱን እድገት ማፋጠን የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው::
ስለዚህ እንደ አቶ ሰለሞን ያሉትን ሰዎች በመደግፍ ህብረተሰቡ የሊዝ ፋይናንስግ ተጠቃሚ ለማድረግ ማበረታታት ይኖርብናል:: በተለይ ደግሞ እንደ አቶ ሰለሞን እውቀቱ ኖሯቸው በገንዘብ ችግር ማሽነሪውን ማግኘት ላልቻሉት ለማገዝ እና ለማበረታታት በተቻለ መጠን ባንኩ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበት ተረድቶ በትጋት እየሰራ ይገኛል:: ሁሉም ሐገሪቱ ክፍሎችም ላይ ተደራሽ ለመሆን እየሰራ ይገኛል ሲሉ ዳይሬክትሩ አመላክተዋል::
እንደዳይሬክትሩ ገለጻ ህብረተሰቡ ስለባንኩ የሚናፈሱ የተጋነኑ ውሸቶችን ወደ ጎን በመተው ባንኩ በሚያቀርበው የሊዝ ብድር መጠቀም አለበት:: በባንኩ ያለው አሰራር የተጓተተ እንዳይሆን በተቻለ መጠን ባንኩ እራሱን እየፈተሸ እያስተካከለ በመስራት ላይ ይገኛል የሚሉት ዳይሬክትሩ በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለመሆን እንዲቻል ቅርንጫፎችን ከፍቷል::
አካባቢውን ማልማት የሚችለው የአካባቢው ማህበረሰብ ነው የሚሉት ዳይሬክትሩ፤ ህብረተሰቡ አካባቢውን ብሎም ሃገሩን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክን የሊዝ ፋይናንሲግ መጠቀም አለበት ሲሉ ጠቁመዋል ::
እገሌ በዚህ ተጠቅሟል የሚል ሳይሆን አዋጭ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት ከባንኩ አደራጅ ክፍሎች ጋር በመመካከር አዋጭ የሆኑ እና የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት መጠቀም የሚያስችሉ እና የደንበኞችም እውቀት ያንን ነገር ለማንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን አይነት እቅድ ይዞ ባንኩ ጋር በመቅረብ አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል የሚናገሩት ዳይሬክትሩ ፤ ባንኩ የተሻለ አገልግሎት እሰጣለሁ ብሎ እራሱን እየለወጠ እና እየፈተሸ ያለበት ጊዜ በመሆኑ ህብረተሰቡ ባንኩ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በትክከል እና በደንብ መጠቀም ይኖርበታል ሲሉ ዳይሬክትሩ አመልክተዋል::
አንዳንድ ባንኩ የሚሰጣቸውን ብድር ከተገቢው መስመር ውጭ ለመጠቀም የሚፈልጉ ተበዳሪዎች እንዳሉም አመልተዋል:: ለምሳሌ ከማሽን ጋር መኪና ይወስዱ እና ማሽኑን ቁጭ አደርገው መኪናውን ይዘው የሚዞሩ አሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ እንደዚህ አይነት ሰዎች የማሽኑን ኪራይ ክፈሉ ተብለው ሲጠየቁ ከባንኩ የወሰዱትን ብድር ሳይከፍሉ አድፍጠው ይቆዩ እና ባንኩ ብድሩን ለማስመለስ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ባንኩ ላይ መጥፎ የሆነ ስም በመለጠፍ የስም የማጥፋት ሙከራ ለማድረግ ይጥራሉ::
ስለዚህ ህብረተሰቡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች እንዳያሳስቷቸው በመጠንቀቅ ይኖርባቸዋል ሲሉ ፤ ዳይሬክትሩ ተናግረዋል:: ሃገርን ለመለወጥ እና ለማሳደግ ከተፈለገ አውንታዊ አስተሳሰቦች መኖር አለባቸው የሚሉት ዳይሬክትሩ ሁላችን ለአገር ዕድገት በቅንነት የድርሻችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ሲሉ አመላክተዋል::
ሁላችንም ለሃገር ልማት ነው የምንቀሳቀሰው ፣ ሀገር ደግሞ የአንድ ግለሰብ ወይም የአንድ ቡድን አይደለችም፤ የሁላችንም ናት የሚሉት ዳይሬክትሩ የሃገር መለወጥ ለሁላችንም ለውጥ ስለሆነ የምንሰራው ስራ በአግባቡ ህግ እና ስርዓትን ተከትሎ መሆን ይኖርበታል ይላሉ:: በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ደግሞ የሀገሪቷን ገቢም ማሳግ እንችላለን :: ከውጭ የሚገባውንም ቁሳቁስ መተካት እንችላለን::
በዚህም የሃገሪቱ ከፍተኛ ችግር የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት መቅረፍ እንችላለን:: ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ህብረተሰቡ የተሻለ አመለካከት በመያዝ በለውጡ የተፈጠሩት የተሻሻሉ የልማት ባንክ አሰራሮችን በመጠቀም ህብረተሰቡ ለስራ እንዲነሳሳ ሲሉ ጠቁመዋል::
ሌላው በፕሮጀክቱ መጀመር ጉልህ አስተዋጽኦ ካበረከቱት የመንግስት አካላት አንዱ የሆኑት በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኬሚካል እና ብረታብረት ዘርፍ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ እና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ካሳ ናቸው::
እንደ አቶ ደረጄ ገለፃ ይህ ድርጅት ወደ ስራ ቢገባ በመጀመሪያ ደረጃ ለዜጎች ስራ እድል ይፈጥራል። በእያንዳንዱ ማሽን እንኳን አንድ አንድ ሰው ቢቀጠር ለሰላሳ ወጣቶች የስራ እድል ይፈጥራል:: ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በዚህ ድርጅት የተቀጠሩ ወጣቶች ቢኖሩ ኖሮ የተቀጠሩት ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ሊፈጥሩ የሚችሉበት እድል ነበር :: ይህ የተቋቋመው ድርጅት የህክምና መጠቀሚያ ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅት ነው::
አሁን ሃገሪቱ ባላት ውስን የውጭ ምንዛሬ የህክምና መገልገያ እቃዎች ለማግኘት ከውጭ እየገዛች ነው ያለው:: ስለዚህ ባለፉት ሶስት ዓመታት ድርጅቱ ወደ ስራ ቢገባ ኖሮ ብዙ ውጭ ምንዛሬዎችን ማዳን ይችል ነበር:: ስለዚህ ይህ ድርጅት የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ሀገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ችግር በመቅረፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት የበኩሉን ሃገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ድጋፍ ማድረግ ይችል ነበር ::
እንደ አቶ ደረጄ ገለጻ ከዚህ በፊት የምንደግፋቸው አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራዞች ተመሳሳይ ችግር ከሌላ ባንክ ጋር ገጥሟቸው ነበር :: እኛም አንደ አንድ የሚመለከተው አካል የእነሱን ችግር መፍታት ችለናል::
ከዚያ አቶ ሰለሞንም ይህን ችግር እንደሚፈታ በማሰብ በብረታ ብረት ኢንስትቲዩት ድጋፋ ለማግኘት መጥቷል:: ከዚያም መጥቶ አነገጋረኝ:: ከዚያም ዶክመንታቸውን ተቀበልኳቸው ፤ ዶክመንቱን አነበብኩት:: ዶክመንቱ ላይ በልማት ባንክ በኩል ክፍተት እንዳለ ተረዳሁኝ::
ስለዚህ ይህን ሰው እንደ ተቋም ለመርዳት በመወሰን እና ዘርፉን ደጋፊም የእኛ ተቋም ስለሆነ የሶለሰብን ድርጅት ለመርዳት እንዳለብን በማሰብ ወደስራ ገባን:: እኛ አላማችን ከልማት ባንክ ጋር መከራከር ሳይሆን ድርጅቱ ቶሎ ወደ ስራ እንዲገባ እና ለዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥር ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርለት ነው ::
ከልማት ባንክ ሃላፊዎች ጋር በስልክ ከምናደርጋቸው የሀሳብ ልውውጥ ባሻገር በተደጋጋሚ በአካል ተገናኝተን ውይይት አደርገናል የሚሉት አቶ ደረጄ ፤ አሁን የመጡት ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ይልማ አበበ ችግርን ለመፍታት ያላቸው አወንታዊ አስተሳሰብ እና ተነሳሽነት በጣም የሚበረታታና የሚደነቅ በመሆኑ ችግሩ መፍትሄ ለማግኘት ስብሰባዎች ላይ ያደርግናቸው ውይይቶች ፍሬማ እንደነበሩ አመልክተዋል::
ወደፊት እንደዚህ አይነት ችግሮች በሚገጥሙ ጊዜ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመስራት ዝግጁ ነን የሚሉት አቶ ደረጄ ፤ ከአሁን በፊት በሀገራችን በተቋማት መካከል የነበረው ቅንጅታዊ አሰራር በጣም ደካማ እና ችግር ፈች አልነበረም ፤ አንድን ችግር ደግሞ አንድ አካል ብቻ ሊፈታ አይችልም ይላሉ::
የድጋፍ ስራ የተያየዘ ነው የሚሉት አቶ ደረጄ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ከመነሻው ችግሩን በመመርመር ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ ለማምጣት በጋራ የምንሰራበት እና ምንስማማበት ነገር መፍጠር ይገባናል::
የሶለሰብ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከመነሻው ችግር እንደገጠመው የኬሜካል እና የብረታ ብረት ዘርፉ ጣልቃ ቢገባ ኖሮ ችግሩ እዚህ ደረጃ ሳይደርስ የሚፈታበት እና ድርጅቱ ወዲያው ወደ ስራ መስገባት ይቻል ነበር::
ሌሎች ተቋማት ከአጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት የእኛን እንደተሞክሮ በመውሰድ በቀጣይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የችግሩን ምንጭ በማጤን በጋራ በመነጋገር ያለውን ክፍተት እንዴት እንሞላዋለን የሚለውን በመወያየት እና ችግሩን የጋራ በማድረግ መፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል::
እንደ አቶ ደረጄ ገለጻ ስለሶለሰብ ድርጅት ችግር እንዳጋጠመው የሰሙት የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንቱ በባንኩ ውስጥ የሚገኙ የሚመለከታቸውን አካላት አሰባስበው እዚያው ተነጋገሩ :: እናም ወዲያውኑ ወደ መፍትሄ ነው የሰጡት :: በእኔ እምነት ችግሩን የፈጠረው ሰው ችግሩን ይፈታዋል ብዬ አላምንም :: ምክንያቱም ችግር ፈጣሪው ሰው ትክክል ነኝ ብሎ ስለሚያስብ ::
ስለዚህ ችግር ፈጣሪ ከሆነው ሰው ውጭ የሚመለከታቸውን አካላት በተፈጠረው ጉዳይ ላይ ቢወያዩ ወደ መፍትሄ ይመጣሉ::
ሌላው ወደ መፍትሄ ለመምጣት ችግሩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት አውንታዊ የሆነ አመለካከት፤ ቀና የሆነ አስተሳሰብ መኖር አለበት:: ከዚያም ወደ መፍትሄ ለመሄድ የተሰበሰበው አካላት ወደ መፍትሄ ለመሄድ ካሰበ እና ቅንነት ካለ መፍትሄ ማምጣት አይከብድም ::
በአጠቃላይ እንደ ሃገር ሁሉም ሰው ነገሮችን ለመዝጋት ሳይሆን ጭንቅላትን ክፍት አድርጎ ለመፍታት ሰውን ለመርዳት የተቀናጀ ስራ ለሁሉም ነገር መፍትሄ ነው ብዬ አምናለሁ ሲሉ አቶ ደረጃ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013