ለምለም መንግሥቱ
ይህ የያዝነው የካቲት ወር ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የሚታወሱበት፣እንደሀገርም ገድል የተሰራበት፣ሁሌም ሲታወስ የሚኖር የታሪክ ወቅት እንደሆነ ይታወቃል:: በተለይም ከኢትዮጵያውያንም አልፎ የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ የሆነው ይህው ድል ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነታቸው ከመጡ አይበገሬ መሆናቸውን ያሳየ ድንቅ የተጋድሎ ውጤት ነው:: ጀግንነት የዓለምንም ህዝብ ያስደመመው የዓድዋ ድል ቀዳሚነቱን ይይዛል::
የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ያከበርነው የሰማዕታት ቀንም በድል የታጀበ ባይሆንም ጣሊያን በጀግኖቹ ኢትጵያውያን ዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል በጠራራ ፀሐይ ሀገር አማን ብሎ በአዲስ አበባ ከተማ ጐዳና ላይ ሲጓዝ የነበረውን ሰላማዊ ሰው በመጥረቢያና በተለያየ የስለት መሳሪያ በግፍ ያደረሰው ጭፍጨፋ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ የሚጠፋ አይደለም:: ጣሊያኖች በዚህ ጭካኔ በተሞላበት የግፍ አገዳደል ጾታና ዕድሜ ሳይለዩ ነበር ከ30ሺ በላይ የሚሆኑትን ኢትዮጵያውያን የጨፈጨፉት::
በመታሰቢያ ቀኑ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት ሥር የአበባ ጉንጉን የማኖር ሥነሥርአት ሲደረግ ተማሪዎችና ወጣቶች ታዳሚ ነበሩ:: እንዲህ ያሉ የማይረሱ ታሪካዊ ኩነቶች ላይ ወጣቱ የለበትም የሚሉ ወቀሳዎች ይቀርባሉ:: እርግጥ ነው ተማሪዎችም ሆኑ ወጣቶች ዕለቱን በመገናኛ ብዙሃን ሲጠየቁ ተገቢ ያልሆነ ምላሽ የመስጠታቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል:: ከእነርሱ አልፎም መምህራኖቻቸውንና የታሪክ ሰዎችን አስወቅሷል::
ከዛሬ 125 ዓመት በፊት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ዓድዋ ላይ ድል ሲቀዳጁ በዓለም ላይ ሰበር ዜና ሆኖ የቀረበን ታሪክ አለማስታወስ እንደ ድል ባለቤት ልናፍር ይገባል:: በሥርአተ ትምህርት ተቀርጾ እንደ አንድ ትምህርት አለመሰጠቱ፣የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎችም በመጽሐፍ ሰንደው ትውልዱ ስለታሪኩ እንዲያውቅ አለማድረጋቸው በአንድ በኩል እንደክፍተት ይነሳል:: ትውልድን የሚወቅስ ብዙ የመሆኑን ያህል እኔስ ምን ሰራሁ የሚለው ግን አይነሳም የሚሉ ወገኖችም አይጠፉም::
የታሪክ ምሁራንም ታሪክን ሰንዶ ለትውልድ በማስተላለፍ ላይ ይስማማሉ:: እነርሱ እንደሚሉት ሁሉም ሰው ታሪክ ሊጽፍ ይችላል:: ግን ደግሞ ሰፊ ታሪክ ያለውን የዓድዋ ድልን እየቆራረጡ በመጽሐፍ ሰንዶ ማቅረቡ የሚፈለገውን ውጤት ያመጣል ብለው አያምኑም::
እንደሀገር የታሪክ ምሁራን ማህበር እንዲመሰረት ሀሳብ የተነሳው እንኳን በዚህ ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው:: ይህ የምሁራኑ ሀሳብ እንኳንስ የተሟላ ታሪክ ተሰንዶ ያልቀረበለትን ትውልድ ለመውቀስ ቀርቶ እንደሀገርም ለታሪክ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ መሆኑን ነው::
ታሪክ የአንድና የሁለት ግለሰብ ሳይሆን የሀገር ሀብት ነው:: በመሆኑም ብሄራዊ ትርክት ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት አላቸው የታሪክ ምሁራኑ:: ወጣቱ አላግባብ መወቀስ የለበትም ብለው የሚከራከሩ የታሪክ ምሁራን፤በዚህ ወቅት በብዙ ፈተና ውስጥ የሚገኝ ትውልድ በመሆኑ በተረጋጋ አዕምሮ ታሪኩን ለማወቅ አልታደለም::
ስለዓድዋ ድል በፊልም፣በመድረክ ላይ ቲያትርና በተለያየ መልክ ቀርቦለት እንዲማር አልተደረገም:: ትውልዱን በደፈናው ከመውቀስ በጥናት የተደገፈ ሥራ መሥራቱን አንዳንዶች ይስማማሉ::
ዛሬ እዚህም እዛም የሚነሱ ግጭቶችና ሁከቶች በጥቂት የግል ጥቅምና ሥልጣን ፈላጊዎች መጠቀሚያ በሆኑ ወጣቶች የተነሳ የብዙዎቹ ስም አብሮ መነሳት የለበትም:: ትኩስ ኃይልነቱን በመጠቀም መልካም አጀንዳዎችን በመስጠት የሚያነሳሱ መኖራቸው መዘንጋት የለበትም::
ችግሮቻቸው ብቻ ሳይሆን ብዙ አስገራሚ ነገሮች የሰሩ ወጣቶችንም ማንሳትና ማወደስ ያስፈልጋል:: ባህላችን ከማወደስ ይልቅ መውቀስ ላይ ጠንከር ያለ በመሆኑ እንጂ የዓድዋ የድል በዓልን ሥፍራው ድረስ ሄዶ ለማስታወስ ከአንድ ወር በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ተነስተው የእግር ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው:: በጥቂቶች የተጀመረው የእግር ጉዞ በአሁኑ ጊዜ ብዙ አባላትን ያፈራ እንደሆነም ይነገራል::
እነዚህ ተጓዦች መንግሥት ወይንም አንድ ታዋቂ ድርጅት አስገድዷቸው አይደለም:: ተጓዦቹ በየደረሰቡት አካባቢ በነዋሪዎች ከሚደረግላቸው ድጋፍ ያለፈም ጥቅም የተለየ ነገር አያገኙም:: ከኪሳቸው ገንዘብ አውጥተውና ለአንድ ወር በእግራቸው ተጉዘው ነው በሥፍራው ተገኝተው ዕለቱን የሚያከብሩት::
ግን ደግሞ ዓመት ጠብቆ የዓድዋ ድል በተገኘበት ሥፍራ በእግሬ ተጉዤ ሄድኩ ለማለት ብቻ መሆን እንደሌለበት ወጣቱ ሊገነዘብ ይገባል::በተለይም የዓድዋ የድል ሚስጥርን ጠንቅቆ ማወቅና ለሌላውም ማሳወቅ ይጠበቅበታል::የዓድዋ የደል በዓል የሁሉም ኢትዮጵያዊ አኩሪ ገድል ነው:: ዛሬ ስማቸው የሚነሳው የወለጋው የዓድዋ ዘማች ራስ ሐብተማርያም መቃብራቸው የሚገኘው ወረኢሉ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው::
መቃብራቸው ላይም የመስቀልና ጨረቃ መቃብር መኖሩን በታሪክ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ነው:: ወረኢሉ በጦርነቱ የስንቅ ማደራጃና የጦር መሣሪያ ማከማቻ እንደሆነም ይነገራል::ዛሬ ላይ አንተ ከወዴትነህ ብሎ ዘርና ሐረግ ቆጥሮ ደም ለማፋሰስ ለሚነሳው እንዲህ ያለውን አኩሪ ታሪክ በማንሳት አሳፍሮ መመለስ ከወጣቱ ይጠበቃል::
ወጣቱ የቱንም ያህል ለታሪኩ ግድ ባይሰጠው በዓድዋ ድል ይደራደራል ማለት አይቻልም::በዓሉን ለማክበር ከአልባሳት ጀምሮ በየአመቱ የሚያደርገው ዝግጅት አንዱ ማሳያ ነው::አምና አዲስ አበባ ከተማ ላይ የነበረው ድምቀት አይዘነጋም::በአሁኑ ደግሞ የበለጠ እንደሚሆን ይጠበቃል::እንደ ሀገርም የካቲት ወር ለዓድዋ በመሰጠቱ በተለያየ ዝግጅት መታሰብ የጀመረው ከየካቲት ወር መግቢያ ጀምሮ ነው::
ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች የሚያመለክቱት የዓድዋ የድል በዓልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ታሪኮች ከፍ ከፍ ማለት የጀመሩበት ወቅት ነው::ወጣቱን ማዕከል አድርገው ብዙ ነገሮች እንደሚሰሩና እንደሀገርም አኩሪ ታሪኮች ወደ አህጉርም ተሻግረው ለገጽታ ግንባታ እንደሚውሉ ታቅዷል::ተነሳሽነቱ ከታላላቆችና ብሎም ከሀገር ሲጀመር ትውልዱም ይከተላል::
በውጭዎች ባህልና አጀንዳ የተቃኘው ትውልድም ወደራሱ ማንነት ይመለሳል::ድንጋይ የሚወረውርና ያለምክንያት የሚቃወም ወጣት ሳይሆን በሀሳብ የሚሟገትና ለሀገር ዕድገት የሚተጋ ወጣት መፍጠር ይቻላል::እንጨት እንዳይጣመም ሥራው መሰራት ያለበት በችግኝ ተከላ ወቅት በመሆኑ ወጣቱም ከመስመር ሳይወጣ መመለስ የሚቻልበት ዕድል ይኖራል::
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013