አስመረት ብስራት
ከተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የመጡ በአስራዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎች ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ በብልጭልጭ ነገሮች ተታለው ከማይወጡት የህይወት አረንቋ ውስጥ የሚገኙትን ቤዛ ፕሮስፕሪቲ በተባለ ሀገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ ነበር ያገኘኋቸው።
የኤች አይ ቪን ስርጭት ለመግታት በሚል የተቋቋመው ይህ ግብረሰናይ ድርጅት እነዚህን ህፃናት ቀን ቀን ማረፊያና ንፅህናቸውን የሚጠብቁበት ቁሳቁስ እያቀረበ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ ከዛም በአስተሳሰብም ተቀይረው ወደ ትክክለኛው የህይወት መስመር እንዲገቡ የማገዝ ስራ ይሰራል።
እነዚህን ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ በአስራዎቹ እድሜ ከልል የሚገኙ ታዳጊዎች ባነጋገርኩበት ወቅት ግን የተመለከትኩት በፍፁም ተሰፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው የነገን ተስፋ ሳይሆን ጨለማውን ብቻ እያሰቡ የሚኖሩ መሆናቸውን ነው። ምንም ተሰፋ የሌለው ንግግር ለዚያውም በሰለቸ አንደበት ሲናገሩ መመልከት ፍፁም ልብን ይነካል።
አዲስ (ለዚህ ፅሁፍ ስሟ የተቀየረ) የተባለችው ወጣት ከተወለደችበት ወለጋ አከባቢ እናሳድጋት በሚል ሰበብ ወደ ቢሾፍቱ ስትመጣ ነፍስ የማታውቅ ህፃን እንደነበረች ትናገራለች። አዲስ በአሳዳጊዎቿ ቤት ልጅነቷ ይቅርና እንደሚከፈለው ሰራተኛ እንኳን መታሰብ ባለመቻሏ፤ ኑሮ ዳገት እየሆነባት አልገፋ ቢላት የሰባተኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ አንድ ጓደኛዋን ተከትላ ወደ አዲስ አበባ መጣች።
በአዲስ አበባ ለወራት በቤት ሠራተኝነት ለመቀጠር ደላላ ቤት ብትመላለስም ተያዥ የሌለው ሰራተኛ መቅጠር የሚፈልግ አንድም ሰው ባለማግኘቷ በወቅቱ የነበራትን ብቸኛ አማራጭ ለመጠቀም ተገደደች – ሴተኛ አዳሪነት። ያውም በለጋ ዕድሜዋ።
የሴተኛ አዳሪነት ህይወቷን አንድ ሁለት ያለችባቸውን የመጀመሪያ ቀናት ስታስታውስ ይዘገንናታል። የሴትነት ክብሯን ያሳጣት የመጀመሪያ ደንበኛዋ ለሰጠችው “አገልግሎት” የከፈላት 100 ብር እንደነበረ የምታስታውሰው አዲስ ከዛን ቀን በኋላ ውስጧ የሚመላለሰውን ፍርሀት ለማውጣት ብዙ ጊዜ እንደወሰደባት ትናገራለች። በመጀመሪያው አዳር ያሳለፈችው ስቃይ ለቀናት አላራምድ እያለ ከፈተናት የህመም ስሜት ካገገመች በኋላ ወደ ስራዋ መመለሷን ነው የምትናገረው።
ልጅነቷንና ትኩስ ገላዋን የተመኙ ሁሉ ጥቂት ብሮችን እያስጨበጡ የፍላጐታቸውን ፈፀሙባት። “በዕድሜ ከእኔ ከሚያንሱ ልጆች ጀምሮ አያቴ እስከሚሆኑ አዛውንት ድረስ ደንበኞች ነበሩኝ። አብዛኞቹን ደንበኞቼን የማገኘው ጐዳና ላይ እና ተቀጥሬ የምሰራበት ቡና ቤት ውስጥ ነው።
በዚህ ስራ ለምን ወደዚህ ህይወት ገባሽ እያለ ሲያዝንና ሲንዘባዘብ ከሚያድረው ደንበኛ እስከ በግድ አስገድዶ እስከሚደፍረው እንደየመልኩ የተለያየ አይነት ባህሪን ማየቷን የምትናገረው አዲስ ስለነገ ተስፋዋ ስጠይቃት እንኳን ነገን ዛሬን በቅጡ ስለመኖሬ አላውቅም የሚል ምላሽ ሰጥታኛለች።
̋አሁን ስራም የለም ቀን እዚህ መጥተን ታጥበን ተኝተን ብንሄድም ሆድ ነገን አያውቅምና ከሚበላ ነገር ተርፎ ነገን በተስፋ ለማየት የሚያስችለን አቅም የለም” የምትለው አዲስ ተስፋ መቁረጥ ተጫጭኗት መመልከት ልብን የሚሰብር ነው።
ሌላዋ ባለታሪካችን ከወላይታ አከባቢ ከእናቷ ጋር መምጣቷን ከዛም በኋላ ከእናቷ ጋር ድህነቱም ተጨማምሮ መግባባት ባለመቻሏ ከቤት ወጥታ ጎዳና ተዳዳሪ መሆኗን ትናገራለች። ጎዳና ላይ በወጣችበት በመጀመሪያው ቀን እንደተደፈረች የምትናገረው ይህች ልጅ ̋ጎዳና ላይ የማንም መጫወቻ ከምትሆኚ ገንዘብ እየተከፈለሽ ለምን አትሰሪም” ብላ ጓደኛዋ አንድ ቡና ቤት እንዳስቀጠረቻት ትናገራለች።
ከእናቷ ቤት ጎዳናን ያስመረጣት ድህነት ጎትቶ በዚህ ስራ ላይ ያሰማራት ይህቺ ታዳጊ የልጅነት ወዟ እስካሁን ከፊቷ አልጠፋም። ለነገ ምንም ራእይ ያልሰነቀች በወጣትነቷ ፍፁም ድካም የተሰማት ልጅ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረች አስታውሳ ነገን በምንም አይነት ሁኔታ ተስፋ እንደማታደርግ ነው የምትናገረው።
ሌላዋ ታዳጊ ወጣት ከተወለደችበት የደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር አከባቢ የመጣችው የአስረኛ ክፍል ውጤት ስላልመጣላት ነበር። ያሳደጓት እናቷ በብቸኝነት ስለነበር በግል ኮሌጅ ለመማር አቅም ሰለማይኖራቸው የእናቷን ኑሮ ቀና ባደርግ ብላ ነበር ከቤት የወጣችው፤ እንደ ሌሎቹ ልጆች የጉልበት ስራም ሆነ ሌላ ለመስራት ብትፈልግም አቅም የለሽም በሚል ምክንያትና ተያዥ በማጣት ለአንድ ሳምንት ያክል በጣም ከባድ ችግር ውስጥ ወደቀች::
አንድ ቀን ጠዋት ካለችበት ተነስታ ሰው ቤት ለመግባት ወደ ደላላ ስትሄድ በአጋጣሚ እሷ ከተወለደችባት መንደር የመጣች ልጅ አገኘች፤ ከዛም ወደ ቤቷ ወሰደቻትና ለቀናት አብራት ኖረች። ያኔ ነው እንግዲህ ይህች ልጅ ወደምትሠራው ሴተኛ አዳሪነት ህይወት እንድትቀላቀል መንገድ ያሳየቻት።
“ለጊዜው ስለጉዳዩ ለመነጋገር በራሱ አፈርኩ:: እንዴት ይህንን ነውር የሆነ ነገር እንድሠራ ትመክሪኛለሽ? ብዬም ተበሳጨሁባት:: እርሷ ግን ‘ለመኖር ያለሽ አማራጭ ይኼ ብቻ ነው፤ እኔም እንዳንቺ አርጎኝ ነበር:: ባይሆን ድንግልናሽ ካለ ደህና ዋጋ ሊያወጣልሽ ይችል ይሆናል!’ አለችኝ::
የመጀመሪያው ቀን ሳንስማማ አደርን:: ግን ከእርሷ መራቅ እንደሌለብኝ ደግሞ አመንኩ፤ ሌላ መጠጊያ አልነበረኝምና:: ከሦስት ቀን በኋላ ግን ረሀብም ሲበዛብኝ፣ ሌላ አማራጭም ሲጠፋ ከእርሷ ጋር ተስማማሁና ተያይዘን ጭፈራ ቤት ሄድን::”
“ከጭፈራ ቤቱ የገባነው አምሽተን አምስት ሰዓት አካባቢ ነው፤ ለወትሮው ገና በአንድ ሰዓት ተኩል ወደ ሥራ የምትሄደው ጓደኛዬ ያን ቀን እኔ ጋር አመሸችና ስለኮንዶም አጠቃቀም፤ ስለ ወንዶች ባሕሪያት፣ ማድረግ ስለሚገባኝ ጥንቃቄ፣ ወደ ሥራው ከገባሁ ይሉኝታና ሀፍረት መኖር እንደሌለባቸው ስትመክረኝ አመሸች:: ከዚያ አንድ መቶ ብር ያዘችና አብረን ጭፈራ ቤት ገባን፤ እሷ ቢራ እኔ ሚሪንዳ አዘዝን:: ወዲያው አንድ ትልቅ ሰውዬ መጣና ከጎናችን ተቀመጠ::
እኔን ለምን ቢራ እንደማልጠጣ ጠየቀኝ:: ጓደኛዬ ‘አትጠጣም፤ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ መምጣቷ ነው! በዚያ ላይ የቤት ልጅ ናት!’ አለችው:: ከዚያ ከጓደኛዬ ጋር ብዙ ሲነጋገሩ ቆዩ፤ እኔ ትኩረቴን ሁሉ ከጭፈራ ቤቱ ውስጥ በየጥጉ ስላለው ሁኔታ ስላደረኩ እነሱን ትኩረት አልሰጠኋቸውም ነበር::” ትላለች ታዳጊ ወጣቷ።
“ከዚያ ወደ ሰባት ሰዓት አካባቢ ሲሆን ጓደኛዬ በጆሮዬ ጠጋ ብላ ‘ሰውዬው ሊወስድሽ ተስማምቷል፤ ለዛሬ ሦስት ሊከፍልሽ ነው:: እንደነገርሽኝ ድንግል ከሆንሽ ደግሞ አይቼ እጨምራለሁ እያለ ነው፤ አለችኝ:: አምኜ የወጣሁበት ጉዳይ ነበርና አብሬው ሄድኩ::” በማለት ትዝታዋን ወደ ኋላ ሄዳ አወጋችኝ።
“እነዚህ ሁሉ ህፃናትን ከቤታቸው አስወጥቶ ጎዳና የበተናቸው ችግር የማን ጥፋት ነው፣ ማንስ ነው ያለእድሜያቸው ለተሸከሙት መከራ ተጠያቂው?” እያልኩ በዚሁ ጉዳይ ላይ የተዘጋጁ ሰነዶችን ማገላበጥ ጀመርኩ።
በሕፃናት ሴተኛ አዳሪነት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ እንደ አዲስ አበባ የሕፃናት ሴተኛ አዳሪነት የተስፋፋበት ከተማ የለም። በተለይ ደግሞ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የነገዋ ተስፋችን ወደሚሏት አዲስ አበባ የሚጎርፉት አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ።
በአዲስ አበባ ጀንበር ዘቅዘቅ ሲል እንደ ፒያሳ፣ ካዛንችስ፣ ሃያ ሁለት፣ ጨርቆስና መርካቶ አካባቢዎች ያሉ ጎዳናዎች በነዚህ ታዳጊዎች ይወረራሉ። ለአካለ መጠን ያልደረሱ፤ የምሽቱን ቅዝቃዜ መቋቋም ያቃታቸው፤ ምን ያጋጥመኝ ይሆን በሚል ጥርጣሬና ስጋት ውስጥ እንዳሉ ፊታቸው የሚያሳብቅ ታዳጊዎች ከምሽቱ አንድ ሰአት አንስቶ ወዲህ ወዲያ ይላሉ።
እንደነአዲስ ያሉ ልጆችም በተለያዩ ቡና ቤቶች ምሽ ታቸውን የሚያሳልፉ መሆኑን ለመመልከት ችለናል። ስለነዚህ ልጆች ተስፋ ማጣት ሀላፊነቱ የማን እንደሆነ ባይገባኝም ይህን ትልቅ ማህበራዊ ክፍተት መድፈን ያለበት ማን እንደሆነ አሁንም ጥያቄ ያጭርብኛል። እነዚህ የተሻለ ህይወት ፈልገው ወደ መዲናይቱ ለሚጎርፉት ሴት ህፃናት መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው።
በዴንማርክ የሕፃናት አድን ድርጅት የተደረገው ጥናት እንደሚያረጋግጠው፤ ሕፃናቱ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆኑን ነው። 43 በመቶ የሚሆኑት በድህነት ተማረው የተሻለ ሕይወትና ሥራ ፍለጋ አዲስ አበባ የከተሙ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከወላጆቻቸው ጋር ባለመስማማታቸው የሚፈጥሯቸው የቤተሰብ ግጭቶች፣ በልጅነት መዳርና የእናት ወይም የአባት ሞት ናቸው።
በተጨማሪም ወደ ከተማ የሚያመጧቸው ደላሎች በዋነኛነት ልጆቹንም ሆነ ወላጆቻቸውን፣ ልጆቹ አዲስ አበባ ቢመጡ መማር እንደሚችሉና ሰው ቤት ትንሽ ሠርተው በርካታ ገንዘብ እንደሚያገኙ ደጋግመው ስለሚነግሯቸው፤ ባልተጨበጠ ተስፋ ስለሚሞሏቸው መሆኑን ያመላክታል።
ነገር ግን ከሕፃናቱ መካከል የትምህርት ዕድል ያገኙት በጣም ጥቂቶቹ ሲሆኑ እነርሱም ቢሆኑ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን እንኳን በቅጡ አላገባደዱም። እናም ሕፃናቱ ተስፋ ያደረጓት አዲስ አበባ ፊቷን ስታዞርባቸው፣ የልጅነት ህልማቸው እንደ ጉም ሲበን ብቸኛ አማራጫቸው የሴተኛ አዳሪነት ሕይወትን መቀላቀል ይሆናል። ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት፤ 60 በመቶ ያህሉ ይህንን አስከፊ የሴተኛ አዳሪነት ህይወት 15 ዓመት ሳይሞላቸው ይጀምራሉ።
እነአዲስ እንደሚሉት ምሽቱ በሙዚቃ፣ በደማቅ መብራቶችና በአልኮል መጠጦች በተሞሉበት የአዲስ አበባ መንደሮች ካሉ ቡና ቤቶች ውስጥ ሰውነታቸውን ለገበያ በማቅረብ የእለት ጉርሳቸውን መፈለጊያ አማራጭ ሲሆንባቸው ከዚያውም ብሶ ስራ የለም በሚል ሰበብ የተወረወረላቸውን ሳንቲም ብቻ ተቀብለው መምጣታቸው ልብ የሚነካ ነው።
እነዚህ ልጆች ማረፊያ ፍለጋ ከመንከራተት ባለፈ በዚህ ስራ ውስጥ የለመዱት ደባል ሱስ አላስቆም አላስቀምጥ ሲላቸው፣ ኑሮው ዳገት ሆኖ አልገፋ ሲላቸው፤ ከረሀቡ፣ ከብርዱና ከችግሩ ጋር መኖር ግድ ሲላቸው ይህም አልበቃ ብሎ አሳዛኝ ወሲባዊ ጥቃቶችንም ያስተናግዳሉ።
ገና ከመነሻው የሕፃናቱ ገላ ለወሲባዊ ግንኙነት ያልጎለበተ ከመሆኑ ባሻገር ሕፃናቱ ገንዘብ ከፍሎ አብሯቸው ከሚተኛው ወንድ በአካል ስለሚያንሱ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረስጋ ግንኙነትን ለመከላከል የሚቸገሩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው።
ይህ ደግሞ ካልተፈለገ እርግዝና በተጨማሪ ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎችና እንደ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ላሉ የጤና ቀውሶች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። ጥናቶች የሚያረጋግጡትም፤ ከመቶ ታዳጊ ሴተኛ አዳሪ ሕፃናት ውስጥ 47ቱ ቢያንስ አንዴ አስገድዶ መደፈር አጋጥሟቸዋል። ከዚህ ውስጥ ግማሾቹ ደግሞ በተደጋጋሚ በወንዶች የተደፈሩ ናቸው።
ከወሲባዊ ጥቃቶቹ ባለፈ ሕፃናቱ ተደጋጋሚ ድብደባና ዘረፋ የዕለት ሕይወታቸው አካል ነው። ባለታሪኮቻችንም እንደነገሩን መደፈር መደብደብ የእለት ከእለት ገጠመኛቸው መሆኑን ነው። አሁን ከሚያርፉበት ድርጅት ኮንዶም ይዞ በመሄድ በተቻላቸው መጠን ራሳቸውን ለመጠበቅ ቢሞክሩም ሌላ የህይወት አመራጭ ስለመኖሩ ግን አስበው የሚያውቁ አይመስሉም።
ግንቦት 1997 ዓ.ም የተሻሻለው የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 634 ላይ እንደተጠቀሰው፤ 18 ዓመት ያልሞላቸው ታዳጊዎችን ለወሲባዊም ሆነ ለሌላ የግዳጅ አካላዊ በደል ያጋለጠ ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቀዋል። የሠራተኛ ሕጉም ቢሆን ታዳጊዎች መሥራት ስለሚገባቸው ሥራዎች በግልፅ ያስቀምጣል።
በተለይ ሕፃናትን በግዳጅም ሆነ በማታለል ለወሲባዊ ጥቃት ያጋለጠ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መሰረት እንደሚዳኝ ይዘረዝራል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንና የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት አነስተኛ የሥራ ዕድሜ ድንጋጌዎች ለሕፃናቱ ከለላ መሆን አልተቻላቸውም።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚቀመጠው ከማታለልና በኃይል ከማስገደድ ባልተናነሰ የኑሮ ሁኔታና ድህነት፣ 18 ዓመት ያልሞላቸውን ሕፃናት ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እንዲገቡ እያስገደዳቸው መሆኑ ነው። ታዲያ ለዚህ ማህበራዊ ችግር ተጠያቂ አድርገን የምንከሰው ማንን ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ሁሉም ሰብአዊ ፍጡር የሚመልሰው ይሆናል።
ከቤት ገፍትሮ አስወጥቶ ለጎዳና ህይወት ከዳረጉ በኋላ ከንፈር መምጠጥ ከችግሩ ምንም ያህል ፈቀቅ ስለማያደርግ፤ ጉዳያቸውን ጉዳዬ ብሎ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ቆም ብሎ ማሰብ የሁሉም ባለድርሻ አካል ሃላፊነት ነው።
ልጆች የጨለመው ተስፋ ፈክቶ ለሃገራቸው ሸክም ሳይሆኑ ሀብቶቿ እንዲሆኑ ከገቡበት የህይወት አዘቅት በማውጣት ችግራቸውን መፍታትና ለሃገር እድገት እንዲተባበሩ ማድረግ እንደሚገባ በማመላከት በዚሁ ላብቃ።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2013