ተገኝ ብሩ
አዲስ አበባ ለመልሶ ማልማት የፈረሰው ደጃች ውቤ ሰፈር የትውልድ ቀዬው ነው። በልጅነቱ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሰዎች አዝናኝ የሆኑ ትዕይንቶችን ማቅረብ ያዘወትር ነበር። በትክክል ስለ ትወና ባያውቅም በቴሌቪዥንና በተለያዩ መድረኮች ያያቸው ተዋንያን አተዋወን በማስመሰል ለአካባቢው ሰዎች ሲያሳይ አድጓል። እጅግ ተጫዋችና ቀልድ አዋቂ በመሆኑ ብዙዎች ይወዱትም ነበር።
ንፋስ ስልክ አካባቢ የሚገኘው ብልጭታ፣ የተባበሩት መምህራን የሕዝብ ትምህርት ቤትና ቂርቆስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው ፈለገዮርዳኖስ የመጀመሪያ ደረጃና አራት ኪሎ በሚገኘው ዳግማዊ ምኒልክ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፊደል የቀሰመባቸው፤ የልጅነት ሕይወቱን ከመምህራኖቹ ጋር በመልካም መስተጋብር በመልካም ሁኔታ የኪነ ጥበብ ልምምድ በማድረግ ያሳለፈባቸው ትምህርት ቤቶቹ ናቸው፤ በብዙዎች አድናቆትና ዝናን ያተረፈው አርቲስት አበበ ባልቻ ተፈራ።
አካባቢው ላይ አጋጣሚውን ሲያገኝ ውስጡ ያለውን ፍላጎት ለማሳየት በማስመሰል መተወንና ቀልደኛነቱ የተመለከቱ ወይዘሮ ዝናሽ የሚባሉ በአካባቢው የሚኖሩ ግለሰብ ወደ ፊልምና ትያትር ሰሪዎች በመቅረብ ወደ ሙያው እንዲቀላቀል ሀሳብ አቀረቡለት። በተደጋጋሚም ወደ ኪነጥበብ ሙያተኞች እንዲገባ ወተወቱት። ከፍ ብሎም ወይዘሮ ዝናሽም ከሚያውቋቸው የትያትር ባለሙያዎች ጋርም አገናኙት። እሱም ያን ዕድል በሚገባ ተጠቀመበት ሙያውንም ተቀላቀለ።
«የወንደ ላጤው መዘዝ» በተሰኘ የመድረክ ቲያትር ላይ በአንድ ቀን ብቻ አንብቦ ወደመድረክ ወጥቶ ባሳየው ድንቅ ችሎታ የትያትሩ አዘጋጅና ተመልካች አድናቆት ተቸረው። ከዚያን ቀን ወዲህ ከመድረክ ሳይወርድ በትወና የተሰጠውን ክህሎት ለተመልካች በማሳየት ዛሬ ድረስ አለ። ለበርካታ ዓመታት በኪነ ጥበቡ ዘንድ በሚሳትፍባቸው ልዩ ልዩ መድረኮች እውቅናና ዝናም አተረፈ። በ15 ፊልሞች ወጥ ፈልሞች ቁጥራቸው በርካታ በሆነ ትያትሮችና ተከታታይ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ድራማዎች ላይ ሰርቷል።
የማዕከሉ ገሀነም፣ የወንደ ላጤው መዘዝ፣ በደሞዝ ሰሞን ሕይወት በየፈርጁ የመሳሰሉት ከተሳተፈባቸውና ዝናን ካተረፈባቸው ትያትሮች ሲጠቀሱ በፊል ደግሞ ማንቴቆል ፋሪስ፣ የአውሬው እርግቦች፣ ትመጣለህ ብዬ፣ ሰው በልኬ፣ አርፋጅ እና ከተከታታይ ደግሞ ትርታ ተጠቃሾቹ ናቸው። በቅርብ ሕዝብ ጋር የሚደርሱ ከሦስት ያላነሱ የፊልም ሥራዎች ላይ መሳተፉም ይናገራል።
የዝነኛው የእረፍት ጊዜ
በሥራው ታታሪ የሆነው አርቲስት አበበ ከሥራና ከተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ነፃ ሲሆን ብዙ ጊዜውን እቤቱ ማሳለፍ እንደሚወድ ይናገራል። በቤት ውስጥ ሥራዎች ላይ መሳተፍ መዝናኛውም ቤተሰባዊ ሕይወቱን ማጠንከሪያውም ነው። ፊልሞችን በብዛት መመልከትም ያስደስተዋል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን በብዛት የሚታዩት የህንድ ፊልሞች ትኩረት ሰጥቶ የትወና ብቃትና የሲኒማው እድገታቸውን ሁሉ በማሄስ መልክ ይመለከታል። ከፊልም ዓይነቶች የኮሜዲ ይዘት ያላቸው ፊልሞች መከታተል ይወዳል።
ለአገር ውስጥ ፊልሞች ልዩ ፍቅር ያለው አርቲስት አበበ አዲስ የወጡ ፊልሞችን በማደን የእረፍት ጊዜ ቆይታው የተሻለ የማድረግ ልምድ አለው። ከሚመለከታቸው ፊልሞችና የጥበብ ሥራዎች የሚጠቅሙትን እንደ ትምህርት እንደሚወስድና ሙያውን ለማሳደግም ጥሩ ዕድል እየፈጠሩለት መሆኑ ያስረዳል። ቤት ውስጥ ከቤተሰቡና ከሙያ አጋሮቹ ጋር በጨዋታ ማሳለፍ ቆይታውን አስደሳች እንደሚያደርግለትም ይናገራል።
ባገኘው የዕረፍት ጊዜው ማንበብ እንደሚወድ የሚናገረው አርቲስት አበበ እንደዛሬ በእጅ ይዘው በሚዞሩት ስልክ የፈለጉትን መጽሐፍ ከፍቶ ማበብ በማይቻልበት በድሮ ጊዜ እንኳን ከእጁ ላይ የሚያነበው መጽሐፍ በፍጹም የማይጠፋ መሆኑንና የማንበብ ፍቅሩ ፅኑ መሆኑን ያስረዳል። የአገርና የሕዝቦችን በትክክል የሚገልፁና ታሪክ ነክ የሆኑ ልቦለዶች መርጦ የሚያነባቸው ናቸው።
ከማህበረሰቡ የሚያገናኘው የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችላይ ንቁ ተሳታፊ መሆኑን የሚናገረው አበበ ከሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ሌሎችን መርዳትና መደገፍ አብሮነት ማጠናከር እንደሚወድ ይናገራል። ኑሮን ቀለል አድርጎ የመመልከት ልምዱ ሰዎች ጋር በቀላሉ ተግባቢ እንዲሆንም ረድቶታል።
ወደ ተለያዩ ደብሮች ከቤተሰቡ ጋር በመሄድ እራሱንና መንፈሱን አድሶ የመመለስ ልምድም አለው። አጋጠሚውን ሲያገኝም የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚሄድበት ጊዜ በቦታው ላይ የሚገኘው ታሪካዊ ወይም የተለየ ሁነት አይቶ እንደሚመለስም ይናገራል።
የዝነኛው መልዕክት
«ከልጅነታችን ጀምሮ በአብሮነት ተጋግዘን ከጎረቤት ጋር ተዋደን በሃይማኖትና በብሔር ሳንነጣጠል ዛሬ ድረስ ቆይተናል። ዛሬ ላይ ግን ኢትዮጵያዊነታችንን የሚቃረኑድርጊቶችና አመለካከቶች እየተንፀባረቁ ነው።
ይህ እኛን የማይገልፅና የነበረንን አንድነት የሚንድ ነው። ሁላችንም በጋራ በመቆም የሚያጋጥሙን ችግሮችን መጋፈጥ፤ አገራችንን ከችግር ማውጣት ይጠበቅብናል። የእኛ ታሪክ አብሮነት አብሮ መቆም የኢትዮጵያውያን ታሪክ በሕዝቦቿ በአብሮነት የተገነባ ነው።
አገራችን ትናንት በአባቶች ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎባታል። የዛሬው ትውልድ ደግሞ እሷን ጠብቆ ማቆየትና ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል። ሁላችንም ለአገራችን የምንችለውን በጎ ነገር እናድርግ። » በማለት ለማህበረሰቡ መልዕክቶችን አስተላልፏል። እኛም ከዝነኛው አርቲስት አበበ ጋር የነበረንን ቆይታ አበቃን መልካም የዕረፍት ቀን።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2013