አዲስ ዘመን፡- ሻለቃ ተስፋዬ በእርስዎ በኩል ስለ ጀግኖችና ሕጻናት አምባ ማሕበር የሚያነሱት የሚሉት ነገር ካለ ቢገልጹልን ?
ሻለቃ ተስፋዬ፡- የጀግኖችና የሕጻናት አምባ ድርጅት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ነኝ ። የማሕበሩን አላማና ግብ እንዲሁም በተቋቋመ በሶስት ወር ውስጥ የሠራቸውን ስራዎች በተመለከተ በአብዛኛው በዶ/ር አዳሙ በኩል የተገለጸ ይመስለኛል ።
ምናልባት እኔ ልጨምረው የምፈልገውን ነገር ቅድም ዶ/ር አዳሙ የገለጹት ቢሆንም ትንሽ ነገር ልበል። ወደ 169 የሚጠጉ የቀድሞው ጦር አባላት የሆኑ የጦር ጉዳተኞች በጣም ጠባብ በሆነች ቦታና አኗኗራቸው ጥሩ ባልሆነ መንገድ እዚህ ልደታ አካባቢ አሉ። ከጀግኖች አምባ እንዳፈናቀሏቸው በቀጥታ ልደታ አምጥተው ነው ያጎሩአቸው ። እነዚህ የጦር ጉዳተኞች በማሕበራዊ ጉዳይ ስር ሆነውም እያሉ ዶ/ር አዳሙ በግሉ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርግላቸው ነበር።
እኛንም አንዳንድ ጥያቄዎች እየጠየቅን በአቅማችን ማድረግ የምንችለውን የሚገባንን ነገር እያደረግን ነው የቆየነው። አሁን ያለው የለውጥ መንግስት ከመጣ በኋላ የተለየ ትኩረት ሰጥተውት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ሄደው በቅርብ ግዜ ጎብኝተዋቸዋል ። አሁን በከፍተኛ ደረጃ አዲስ አበባ መስተዳድር፤ ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ መከላከያ ሚኒስቴር ፤የመንግስት ባለስልጣናት ትኩረት ሰጥተውታል ።
የማሕበራችን የጀግኖችና የሕጻናት አምባ የምስረታው አንዱ ነጥብ እዛ ውስጥ ያለን የተሰባሰብን ሰዎች ዋናው ምክንያታችን ከፍተኛ ቁጭት ነው። ብዙ ግዜ የተለያዩ መንግሥታት ይመጣሉ። ይሄዳሉ ። ግን ከእነሱ በፊት የአለፉት መንግሥታት የሰሩትን ጥሩ ነገር እያበረታቱ አይቀጥሉም። አይማሩም። የጀግኖችና የሕጻናት አምባ ከኢሕአዴግ በፊት በነበረው በቀድሞው ሥርዓት የተቋቋመ ነበር ።
በጦር ሜዳ የተጎዱ ጀግኖች የሀገር ባለውለታ ስለሆኑ ተገቢ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የሚያደርግ ጀግኖችን የሚያበረታታ ልጆቻቸውም የሀገር ባለውለታ ልጆች ስለሆኑ የትም ሜዳ ላይ እንዳይወድቁ ይደግፋል ። ያስተምራል ። ያበረታታም ነበር ። አስተምሮም ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ የነበረ ስለሆነ መፍረስ አልነበረበትም ነበር ።
እኔ ራሴ በአይኔ ያየሁትን ስለ ሕጻናቱ ብነግርህ ከሕጻናት አምባ አውጥተው አምጥተው አብዮት አደባባይ ሜዳ ላይ ነበር የበተኗቸው ። እነዚህ ሕጻናት ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። አብዛኞቹ አሁን በዘበኝነት በሾፌርነት ተበታትነው ሁልግዜም ያንን የኢሕአዴግን ሥርዓት እያማረሩ ነው ያሉት።
ሀገሬ ብሎ ለተዋጋ ለቆሰለ ለሞተ ሠራዊትና አባት ላጡ ልጆቹ የኢሕአዴግ መንግስት እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጽም ነበር ። አሁን ያለው ሠራዊት ምን አይቶ ምን አስቦ ነው ሞራል የሚኖረው ? ስትል ለቀደመው ሠራዊት ሲደረግለት ካየው በጎም ሆነ መጥፎ ነገር ጋር ይያያዛል ። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ሲባል እንደሚዋደቅ መስዋዕትነት እንደሚከፍል ይታወቃል ።
የአሁኑም ሠራዊት እንደ ቀድሞው ሁሉ ለሀገሩ መከበርና መታፈር ታላቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል ። ግን ደግሞ የቀድሞዎቹን ሲመለከት አብሮት ሲዋጋ ለሀገር መስዋዕትነት ሲከፍል ሲንከራተት የነበረው ወንድሙ ሜዳ ላይ ወድቆ ሲለምን የሚንከባከበው ሰው አጥቶ ሲያይ ወይንም ሳይኖር ሲቀር ወታደርነትን አይወደውም ።
ውትድርና ሙያውም ሆነ ሠራዊቱ በአጠቃላይ የተወደደ የተከበረ እንዲሆን ነው መደረግ ያለበት ። ለሀገሩ መስዋዕትነትን በሕይወቱ ከሚከፍል ጀግና በላይ የሚከበርስ የሚወደድስ ማን አለ ? ማንም የለም ።
በጦርነቱ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ባደረጉት ንግግር ለመከላከያ ሠራዊታችን 5000 ሰው ለመመልመል ተቸግረን ነበር አሉ ። አንዱ ምክንያት ይሄ ነው ። ለምን ብንል ለሀገር እሰዋለሁ፤ እቆስላለሁ፤ እደማለሁ፤ አይኔ ይጠፋል፤እጄ ይቆረጣል ከዚያ በኃላ የሚቀጥለው ነገሬ በሕይወት ከተረፍኩኝ መንግስት ይንከባከበኛል፤ የሚያኮራ አለኝታ የሆነ ወ
አለኝ ብሎ ሠራዊታችን እንዲያስብ በሀገሩና በወገኑ ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖረው አድርገን መስራት ማነጽ አለብን ። ይሄንን በማሰብ ነው በቀድሞው ስርአት ግዜ የጀግኖች አምባና የሕጻናት አምባ ተብሎ በሕግ ተቋቁሞ ብዙ የጦር ሜዳ ጀግኖችን ተቀብሎ ሲንከባከብ የነበረው። ልጆቻቸውንም እንደዚሁ ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በአጭር ግዜ ውጤታማ ስራ እየሰራችሁ መሆኑን ገልጸውልኛል። የሚጨምሩበት ካለ?
ሻለቃ ተስፋዬ፡- አላጌ ዝዋይ ላይ የቀድሞው የሕጻናት አምባ የነበረበት ቦታ የተወሰነ ብሎክ ተሰጥቶን በመከላከያ በኩል እድሳት እየተደረገለት ሲሆን በቅርቡ ያሉ ጀግኖች እዛ እንዲገቡ ሊደረግ ነው ። ሕጻናት አምባን በተመለከተ በአራቱም አቅጣጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በአዲስ መልኩ ለመስራት እየተዘጋጀን ነው ።
በኮሚቴው ውስጥ ያሉ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ለስራው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው ። ከፍተኛ የሀገርና የሠራዊት ፍቅር ፤ የየራሳቸው ሀገራዊ የአገልግሎት ታሪክ ያላቸው፤በግልም ሆነ በመንግሥት በተለያየ ከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ላይ የሰሩና ያሉም አሉባቸው ። ወ/ሮ ገነት አየለ ፤ ብ/ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ፤ ኢንጂነሮች፤
አርክቴክቶች፤ የሐይማኖት አባቶችም አሉበት ። የታሰበውን የግንባታ ስራ ለመስራትና የጀግኖቹን እንክብካቤ በተሻለ ደረጃ ለማሳካት በቅድሚያ የሀብት ማሰባሰብ ስራ ላይ ነው ያለነው።
አዲስ ዘመን፡- በቅርብ ግዜ ምን እንጠ ብቅ?
ሻለቃ ተስፋዬ፡– በቅርቡ ከህወሓት ጋር በነበረው ጦርነት የተጎዱ ቁስለኞቻችንን ተቀብለን የሚያገግሙበትን ሁኔታ ነው በአፋጣኝ እየሰራን ያለነው። በመከላከያ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ድጋፍ እየተደረገ ነው ። የተሰጠን ስራ አለ ። ያንን ለመስራት ሩጫ ላይ ነን ።
በተለያየ መንገድ መደገፍ ያለብንን ነገር አልጋ፤ ብርድ ልብስ፤ የላውንደሪ ማሽን፤ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ሌሎች ሌሎች ነገሮችንም በሙሉ በአስቸኳይ አስገብተን ድጋፍ ለመስጠት እየሰራን ነው ። ዋናው የተነሳሽነታችን ቁልፍ ነጥብ ቁጭትና እልህ ሲሆን የፈረሰውን መልሶ ለመገንባትና የሀገር ጀግኖች በጦር ሜዳ ጉዳት ሲደርስባቸው አለሁ አይዞአችሁ የሚል የሚንከባከብ የሚደርስላቸው ወገን እንዳለ ለማሳየት ነው። መንግስት መጣ፤ መንግስት ሄደ ወታደር ወታደር ነው ። የሀገሩ ጠባቂና አስከባሪ ነው ። በዚህም ሊከበር ይገባዋል ።
አዲስ ዘመን፡- የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?
ሻለቃ ተስፋዬ፡– እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የክልል መንግስታት፤ዩኒቨርሲቲዎች፤ ባለሀብቶች በከፍተኛ ደረጃ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የሌሎችም ኢትዮጵያዊ ተቋማት ባንኮች ኢንሹ ራንሶች የመንግሥትም ሆኑ የግል ድጋፋቸው እንዳይለየን እንጠይቃለን ። በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጻናትን በተመለከተ የሚሰሩ ድርጅቶችን እያስተባበርን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግና በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ነው የምናስበው ።
ይሄን እንቅስቃሴ የሚመራው ራሱን የቻለ አካል አለ ። ማህበራዊ ጉዳይ ነው የሚሆነው ብለን እናስባለን። በአሁኑ ግዜ ግን በተለይ ተባብረን የምንሰራው ከመከላከያ ጋር ነው ። መከላከያ፤ ማሕበራዊ ጉዳይ፤ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባም እንዲሁ ከፍተኛ ድጋፍና እገዛ እያደረጉልን ነው። በጣም ስኬታማ ስራ እንሰራለን የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፡- በጋራ ስለሰጣችሁን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን።
ዶ/ር አዳሙ አንለይ፣ ሻለቃ ተስፋዬ ወንድሙ፡- እኛም እናመሰግናለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2013