መልካምስራ አፈወርቅ
ደንበጫ ልዩ ስፍራው ‹‹ ጠዴ ›. ከተባለ ስፍራ ተወለደ፡፤ ለወላጆቹ ሦስተኛ ልጅ ነው ።የአካባቢው ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የመላክ ልምድ አላቸው ።አብዛኞቹ ነገን በበጎ እያሰቡ ከልጆቻቸው መልካም ፍሬን ይጠብቃሉ ።በርካቶቹ በትምህርት የሚገኘውን ውጤት ያውቃሉና ልጆች ትምህርት ቤት ቢውሉ አይከፋቸውም፡፤
ታደሰ እድሜው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ከእኩዮቹ ጋር ቀለም የመቁጠር ዕድል አገኘ ።በጊዜው ወላጆቹ ያስፈልገዋል ያሉትን አሟሉለት ።ትምህርት ቤት እየዋለ ከቤት ሲመለስ ደስተኛ ሆነ ።ዓመቱን ሙሉ ተምሮ ወደ ሁለተኛ ክፍል ሲሻገር እናት አባቱ ለሚቀጥለው ጊዜ ተስፋን ሰነቁበት፡፡
ቀጣዩ ዓመት እንደባተ ታደሰ ትምህርት ቤት ሊሄድ ደብተሩን አነሳ ።ዘንድሮም ለትምህርት ያደረው ስሜቱ ነቅቶ በአዲስ መንፈስ ቀለም ሊቆጥር ውስጡን አዘጋጀ ።ዓመቱ በመልካም ውጤት ተጠናቀቀ፡፡
ለከርሞ ትምህርት ራሱን ያበቃው ታዳጊ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሆነ ።የዕድሜው ከፍታ እውቀት ጨመረለት ።ከአምና ካቻምናው ተሸሎም ለቀጣዩ ዓመት ጎበዝ ተማሪ ሊሆን ከደብተሩ ተዋደደ ።ዓመቱ በሰኔ ውጤት ሲጠናቀቅ የአራተኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን አረጋገጠ ።ይህኔ በራስ መተማመኑ አደገ ።የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የመሆን እጩነቱን አረጋግጦም ቀጣይ ዓመታትን በተስፋ ጠበቀ፡፡
አሁን ታደሰ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል፤ ዘንድሮ የጀመረውን ትምህርት በድል ካጠናቀቀ ለህይወቱ አዲስ ምዕራፍ ይሆናል፡፤ ቀጣይ ዓመታትን በጉብዝና ተሻግሮም የነገ ህልሙን ያሳካል፡፤
ክረምት አልፎ ተማሪዎች መመዝገብ ሲጀምሩ ታደሰን የቀደመው የለም፡፤ እንደቀድሞው ሁሉን አሟልቶ የቀለም ጥማቱን በአዲስ መንፈስ ጀመረ።ጠዋት ማታ ከደብተሩ አልተለየም፡፤ ጥናቱን በጊዜ ጀምሮ የደረጃ ተማሪ ሊሆን ዕቅድ ነደፈ፡፡
አዲስ ሃሳብ…
የአምስተኛ ክፍል ተማሪው ሰሞኑን በአዲስ ሃሳብ መብሰልሰል ይዟል፡፤ አሁን እንደወትሮው የትምህርቱ ነገር እያሳሰበው አይደለም ።መሽቶ በነጋ ቁጥር ልቡን በሚሰርቀው ጉዳይ መብከንከን መጨነቅ አብዝቷል፡፡
ታደሰ ስለ ትምህርቱ ማሰብ ትቶ ለአንድ ጉዳይ ማተኮር ከጀመረ ቀናት ተቆጠሩ፡፤ አልፎ አልፎ ብቅ በሚልበት ትምህርት ቤት ለወጉ የሚቃኘው ደብተር የተሟላ እውቀት እያደረሰው አይደለም፡፤ ከትካዜ መልስ ውስጡ በተለየ ተስፋ ሲሞላ ገጽታው ፈገግታን ይላበሳል ።መልሶ በሃሳብ ሲሰምጥ ደግሞ መሬት እየቆረቆረ በጭንቀት ይዋጣል ።
አሁን ታደሰ ትምህርት ቤት መሄድ ካቆመ ቀናት አልፈዋል፡፤ ውስጡ ባቀበለው አዲስ ሃሳብ ከራሱ መክሮ ሰለቀጣይ ማንነቱ እያቀደ ነው ።እሱ ካደገበት ቀዬ ብዙዎች ርቀው ሄደዋል፡፤ አብዛኞቹ ተመልሰው ሲመጡ እጃቸው ባዶ አልነበረም፡፤ በአለባበስ አምረው በኑሯቸው ተቀይረዋል፡፡
እሱም ቢሆን ርቀው እንደሄዱት የመንደሩ ነዋሪዎች ተለውጦ ቢመለስ ይወዳል ።ለእጁ የሚመነዝረው ገንዘብ ቢቆጥር ደስታው ነው፡፤ ከመንደሩ የቀድሞ ልጆች ተደምሮ የእነከሌ ልጅ መባል የሁልገዜ ህልሙ ነው፡፡
ከቀናት በኋላ ታደሰና ህልሙ ተገናኙ ።የልቡ ሞልቶ የነገውን ዕቅድ ለማሳካት ቀዬውን ለመልቀቅ ወስኖ ጓዙን ሸክፏል ።እግሮቹ እንደሌሎቹ ወጣቶች አዲስ አበባ ሊያደርሱት አልፈጠኑም ።የእሱ እንጀራ የሚገኘው ወደ ወለጋ ሲሻገር ብቻ መሆኑን አምኖበታል፡፡
በወለጋ ብዙ የአገሩ ልጆች እንዳሉ ያውቃል፡፡ በርካቶቹ ደህና ጥሪት ይዘዋል፡፤ ጥቂት የማይባሉት ከቀያቸው ተመልሰው መተዳደሪያ አፍርተዋል፤ እሱም ቢሆን በእነሱ መንገድ ካለፈ ያሰበውን አያጣም፡፡ገንዘብ ይዞ ጥሪት ቋጥሮ መለወጥን ይሻል፡፤
የትናንትናው ብርቱ ተማሪ ስለ ትምህርት ማሰቡን ትቶ የብር ቁጥርን ያልም ጀምሯል፡፤ ለእሱ ገንዘብ ማግኘት የህይወቱ ለውጥ ነው፡፤ ለዚህ ለውጥ አገር ቆርጦ ወንዝ ተሻግሮ መሥራት አለበት፡፤ ይህ ከሆነ ያሰበው ይሳካል፣ ያለመው እውን ይሆናል፡፡
ህይወት በአዲስ መንገድ…
የደንበጫው ወጣት አሁን የወለጋ ሰው ሆኗል፡፤ ከስፍራው ሲደርስ እንግድነት አልተሰማውም፡፤ ካገሩ ልጆች ደርሶ አካባቢውን ተላመደ፡፤ ታደሰ ኑሮ በወለጋ እንዳለመው አልሆነለትም ።የመጀመሪያ እንጀራው የአረምና የእርሻ ሥራ ሆነ፡፡
ብርቱ ሆኖ ከማደር ውጭ ምርጫ ያልነበረውም ታደሰ ውሎ አድሮ ሥራውን ለመደ ።እስክሪብቶ መጨበጥ የለመዱ እጆቹ ለእርሻ ሥራው አልቦዘኑም። ቀድሞ, የሚያውቀውን ግብርና ሳይሰንፍ ሳይደክም ተያያዘው፡፤ ነገን እያሰበም ገንዘብ መያዝን አወቀ፡፡
ውሎ አድሮ የታደሰ ዕቅድ ተቀየረ ።በጉልበቱ ወዝ የቋጠረውን ጥሪት አገሩ ይዞ የመግባት ሃሳቡን ሰረዘ፡፤ እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ወደ አዲስ አበባ አልፎ የተሻለ ህይወት መኖርን ተመኘ ።ይህ ከሆነ ወደ አገሩ የሚመለሰው በአዲስ አበባ አውቶቡስ ይሆናል ።እንደሌሎች የአገሩ ልጆች ቤተሰቦቹ በደስታ ይቀበሉታል፡፤ እሱም የልቡ ሞልቶ የሃሳቡን ያገኛል፡፡
አዲሱ ሰው በአዲስ አበባ
ታደሰ በእርሻ ሥራው የያዘውን ገንዘብ ቋጥሮ ወደ አዲስ አበባ አቀና፡፤ አዲስ አበባ የሩቅ ዘመዶች እንዳሉት ያውቃል ።አስቀድሞ ለመምጣት ያለማሰቡ አድራሻ እንዳያገኝ ሰበብ ሆኖ በሃሳብ ናወዘ ።‹‹የእኔ›› የሚለው ዘመድ ቢኖረው ማረፊያ አያጣም፡፤ ቀናትን አሳልፎ ሥራ ይፈልጋል፡፤ ሃሳቡን ጥሎ ነገውን ያልማል፡፤
ለታደሰ አዲስ አበባ እንደወለጋ አልሆነም። ግርግሩ፣ የከተማው ስፋትና የሰው ብርካቴ አጨናነቀው፡፤ ይህኔ ‹‹አለሁ›› የሚለውን ናፈቀ።ቀዝቃዛ ውሃ ጠጥቶ ጎኑን ያሳርፍበት ጎጆ ተመኘ ።
አዲስ አበባ አውቶቡስ ተራ የደረሰው እንግዳ ቆም ብሎ ስፍራውን ቃኘ ።የሚያውቀው አንዳችም ሰው የለም፡፤ ባይተዋርነቱ ሳይታወቅ ማረፊያውን ማግኘት እንዳለበት ከራሱ መከረ ።አዲስ አበባ ከጀት የፈጠኑ ሞጭላፎች መኖራቸውን ሰምቷል ።ግራቀኙን እየቃኘ ማደሪያውን ጠየቀ ።ብዙ አልተቸገረም ።በአካባቢው በአነስተኛ ዋጋ የሚታደርበት ማረፊያ እንዳለ ተነገረው፡፡
ታደሰና አዲስ አበባ ከአንድ ውለው ማደር ይዘዋል።በማረፊያ ስፍራው እሱን መሰል ሰዎች መኖራቸውን ያወቀው ወጣት ቀጣዩን ህይወት ለመምራት አሁንም በዕቅድ ላይ ነው ።በዚህ ስፍራ ህይወት ቀላል እንዳልሆነ ሲገባው በሃሳብ ሲናውዝ ውሎ አደረ።ገንዘቡን ሳያጠፋና፣ በሌቦች ሳይነጠቅ ይዞ ለመዝለቅ መበርታት እንዳለበት ገባው፡፡
አሁን ታደሰ ከተማውን በደንብ አውቋል፡፤ በቀን ሥራ ውሎው ከብዙዎች ተግባብቶ ሙያን መልመድ አውቋል ።ሲደክም ውሎ ጎኑን የሚያሳርፍበት ማደሪያ እምብዛም ኪሱን አይጎዳም፡፤ የዕለት ጉርሱን እየቀመሰ ማልዶ ሲነሳ ጉልበቱ አዲስ ሆኖ ያበረተዋል፡፡
ታደሰ ከአገሩ የወጣበትን ዓላማ አልዘነጋም፤ ገንዘብ ይዞ ራሱን የመለወጥ ዕቅዱ ዛሬም ድረስ አብሮት ነው ።የጉልበት ሥራውን እርግፍ አድርጎ ለመተው ባሰበ ማግስት በንግድ ለመሰማራት ወሰነ።ይህ ውሳኔው ለነገው ማንነቱ መሰረት እንደሚሆን አውቋል።ካገሩ ተመልሶ የሌሎችን አይነት መልካም ህይወት መድገምን ይሻል፡፡
የታደሰ ንግድ ክብሪትና የሴቶችን ጫማ በማዞር ተጀመረ ።ብዙዎች ይህን ሥራ በጀመሩ አጭር ጊዜያት ራሳቸውን ቀይረዋል ።ሥራውን በሌላ ንግድ ቀይረውም ብርቱ ነጋዴዎች ሆነዋል፡፡
ታደሰ ጫማውን በአነስተኛ ዋጋ እየተረከበ የተሻለ ትርፍ ያገኛል፡፤ ትርፉን ይዞም ነገን የተሻለ ለማግኘት ይሮጣል ።ጫማዎቹን ለመሸጥ ገዢዎችን ማግባባት ግድ ይለዋል፡፤ እንዲህ በሆነ ጊዜ ገበያው ይደራል፣ ገቢው ይጨምራል ።አሁን የአዲስ አበባን ህይወት በንግድ ሥራ አሟሽቶ ህይወቱን ቀጥሏል፡፡
ታደሰና በየቀኑ የሚሮጥበት ሥራው እምብዛም አልዘለቁም፡፤ ጥቂት እንደገፋ ልፋቱ አሰለቸው፤ እንጀራ ለማግኘት ገዢ መለማመጥ፣ ማቆላመጡ ደከመው። ጅምሩ የንግድ ሥራ ከትርፍ ይልቅ ኪሳራ አስከተለበት። ይህኔ ማሰብ የማይሰለቸው ውሰጠቱ በሌላ ውጥን ተያዘ፡፡
አዲሱ የታደሰ ሃሳብ አልሰመረም፡፤ እስካሁን ያለፈበት መንገድ ውጤት አልባ መሆኑ እያበሳጨው በትካዜ ዘለቀ፡፤ ትካዜው ከሌላ መስመር አላገባውም፤ እስካሁን የሰራበትን ገንዘብ እየተጠቀመ ብቻ ለመኖር ወሰነ፡፤ ውሳኔው ሰምሮ በገንዘቡ ማዘዝ ሲጀምር እንዳሰበው ኑሮ አልቀለለም፡፤ ቀን ሲባዝን ውሎ ለሚያርፍበት ማደሪያ የሚከፍለው እስከሚያጣ ተቸገረ፡፤
ታደሰና ሊሰራ ያሰበበት ገንዘቡ መለያየት ከጀመሩ ቀናት ተቆጠሩ ።ከወራት በፊት እጁ ላይ የነበረውን በርከት ያለ ብር ለአንድ ጉዳይ አውሎታል ።ገንዘቡን ያዋለበት ዕቃ ዛሬ ምግብና መኝታ ሊሆነው አልቻለም፤ ይህን ማድረጉ ባይቆጨውም ግራ እንደገባው ያለመፍትሄ ዘልቋል፤
ኑሮ በጎዳና…
ታደሰ ያለሥራ ያሳለፋቸው ጊዚያት ባዶ ኪስና ተስፋ የለሽ ህይወትን አስረክበውታል፡፤ በድካም ሲንከራተት ውሎ ማደሪያውን የጎዳና ጥግ ካደረገ ቆይቷል ። አሁን እንደትናንቱ ነገን አርቆ አያስብም። ቀድሞ ያለመው አገሩ የመመለስ ውጥን ላይጠገን ተሰብሯል፡፤
ሁሌም ምሽቱን በሚያሳልፍበት የጎዳና ጥግ ከጎኑ የማይርቀው ወጣት የእሱን ስሜት የሚጋራ መሆኑ ለታደሰ መልካም ሆኗል፡፤ ወጣቱ በጨዋታ መሐል የአንድ አካባቢ ሰዎች ስለመሆናቸው ነግሮት ተግባብተዋል፡፡
ታደሰና ይህ ወጣት በጎናቸው ጋለል ብለው የሚያወጉት ጨዋታ ከሌሎች ይለያል ። ስለነገው መልካምነት እያሰቡ ተስፋ ያደርጋሉ ።ዛሬን በአሸናፊነት ቢያልፉ ወደፊት ብሩህ እንደሚሆን ያስባሉ፡፤ ሁለቱም በፈተና ህይወት መመላለሳቸው በአንድ ቋንቋ እንዲያወሩ ምክንያት ሆኗል ።ምክክራቸው መግባባት መጫወታቸው ስሜታቸውን አጣምሯል፡፤
ግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ.ም…
ምሽቱ ገፍቷል ።ቀኑን በቃጠሎ የዋለው የግንቦት አየር ማታ ላይ ቀዝቀዝ ማለት ጀምሯል ።ከጎዳናው ጥግ ያረፉት ባልንጀሮች የትናንትናውን ወግ ቀጥለዋል፤ ዛሬም ጨዋታቸው ስለዛሬ ውሎና ስለነገው የህይወት ለውጥ ነው፡፤ ይህን ሲነጋገሩ ሁለቱም በተለየ ስሜት ይዘፈቃሉ፡፤ ደማቅ ፈገግታ በፊታቸው ይነበባል ።
ድንገት የሁለቱን ጨዋታ የሚረብሽ ድምጽ በአካባቢው ተሰማ ።ይህኔ ሁለቱም የለበሱትን አሽቀንጥረው ፈጥነው ተነሱ። በድንጋጤም ወደ አንድ አቅጣጫ አተኮሩ፡፤ ወዲያው ወደእነሱ እየቀረበ ያለውን ሰው አወቁት ።አብዛኞቹ በተለምዶ አፍራሽ ግብረሃይልና ደንብ አስከባሪ ሲሉ ይጠሩታል፡፡
ሰውዬው አብሮት የነበረውን የታደሰ ጓደኛ እጁን እየወዘወዘ አጥብቆ ሰላም አለው፡፤ ሁኔታውን የየው ታደሰም እንደ ጓደኛው እጁን ለሰላምታ ዘረጋ፡፤ ሰውዬው በግልምጫ አነሳው ።‹‹ምን ያንጠባርርሃል›› ሲልም የተዘረጋ እጁን ገፈተረ፡፡
በዚህ ብቻ አላበቃም ።የታደሰን እጅ እየጎተተ ከተጋደመበት አነሳው፡፤ ታደሰ ፊቱ ተለዋወጠ፤ ሰውዬው ከድርጊቱ ይታቀብ ዘንድም ሊታገሰው ሞከረ፡፤ የውስጡን እልህ እየታገለ ሳለ አብሮት ያለው ሰው ጠጋ ብሎ ከደንብ አስከባሪው ጋር አበረ።
ሁለቱም በወጉ ያልቆመውን የጎዳና ወጣት እየጎተቱ አንገላቱት። ታደሰ ምን እንደበደለ ለመጠየቅ አፉን ከመክፈቱ ሁለተኛው ሰው እንዳይጠጋው እያስፈራራ ቀረበው ።ታደሰ ሰዎቹ ሊያጠቁት ማሰባቸውን ተረዳ።ራሱን እንዲቆጣጠር ጊዜ አልሰጡትም፡፤ እያጣደፉ፣ እያዋካቡ ፋታ አሳጡት ።
አሁን ታደሰ የሰዎቹ ድርጊት የታሰበበት መሆኑ ገብቶታል ።በእነሱ እጅ ላለመውደቅ ብቸኛው አማራጭ አንድ ነገር ማድረግ ብቻ ነው፡፤ ይህ ይሆን ዘንድ ከውሳኔ ደርሷል ። ለአፍታ በአይምሮው ብልጭ ያለለትን መፍትሄ ሊመልሰው አልፈለገም፡፤ ይህን እያሰበ እጆቹን ወደሆዱ አቅጣጫ ሰደዳቸው፡፡
እጆቹ ለዓመታት ደብቆ ያቆየው ድብቅ ሚስጥር ስለመኖሩ አረጋገጡለት፡፤ ያስቀመጠውን ሚስጥር በእጁ እየነካካ መልሶ አሰበ፡፤ ይህ አጋጣሚ እስኪመጣ በዚህ ድብቅ ዕቃ ሊጠቀምበት አቅዶ አያውቅም ።
ሁለቱ ሰዎች ታደሰን ለማነቅ ከፊቱ ቆመዋል።የጎዳና ጓደኛው በድንጋጤ እያየው ይርበተበታል፡፤ ታደሰ እጆቹን ካሰረፈበት አነሳ ።ድንገት የተሰማው ደማቅ የተኩስ ድምጽ በአካባቢው አስተጋባ፡፡
ከታደሰ እጅ የሚታየው ሽጉጥ ከአንደኛው ሰውዬ ግንባር ተነጣጥሮ ተተኩሷል፡፤ የቃታውን መሳብ ያየው ደንብ አስከባሪ አብሮት የነበረው ሰው ከመሬት ወድቆ መዘረሩን አረጋግጧል፡፤ በድንጋጤ እግሬ አውጭኝ ከማለቱ በፊት ታደሰ ትንሸዋን ሽጉጥ ከቦታው መልሶ ከስፍራው ተሰወረ፡፤
ሁለቱ ባልንጀሮች ታክሲ ይዘው ወደመገናኛ አቀኑ፤ አዳራቸውን ከታደሰ ጓደኛ እናት ቤት አድርገውም ሲነጋ በደንበጫ አውቶቡስ ተሳፈሩ፡፤ ግማሽ ቀን ተጉዘው ወደ ታደሰ የትውልድ አገር ሲደርሱ ልባቸው ተረጋገጋ። ጉዳያቸውን በሚስጥር ይዘው ቀናትን ቆጠሩ፡፡
ታደሰ ከዓመታት በፊት ስሙንና መልኩን ከማያስታውሰው ግለሰብ የገዛውን ሽጉጥ ደብቆት ኖሯል ።አንድ ቀን እንደሚጠቅመው ቢያውቅም በዚህ አይነቱ አጋጣሚ ይውላል ብሎ አላሰበም፡፡
የፖሊስ ምርመራ..
ምሽቱን አራዳ ፖስታ ቤት አካባቢ የደረሰው የፖሊስ ቡድን በጥይት ተመቶ የወደቀውን ሰው አስከሬን አንስቶ መረጃዎችን ሰበሰበ ።በስፍራው ከሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ባገኘው ፍንጭም ቀጣዩን ምርመራ ለማካሄድ የፖሊስ ቡድን አዋቅሮ እንቅስቃሴውን ቀጠለ ።በመዝገብ ቁጥር 879/08 የተደራጀው ዶሴ በአዲስ አበባው ፖሊስ መርማሪ ዋና ሳጂን መንግስቱ ታደሰ ተሰንዶ ወደሚመለከታቸው ተለላፈ፡፤
አሳሽ ቡድኑ የተጠርጣሪውን አድራሻ ለይቶ አወቀ፡፤ አባይን ተሻግሮም ወደ ምዕራብ ጎጃም አቀና ። ፖሊስ ተጠርጣሪውን ከተደበቀበት ይዞ ምርመራውን እንደቋጨ ክሱን ከዓቃቤ ሕግ አሳለፈ፡፤
ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ የቀረበውን ማስረጃ መርምሮ ጥፋተኝነቱን አረጋግጧል፡፤ በዕለቱ ባሳለፈው ውሳኔም ታደሰ እጁ ከተያዘበት ጊዜ በሚታሰብ የስድስት ዓመት ጽኑ እሥራት ይቀጣ ሲል በይኗል፡፤
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013