ጽጌረዳ ጫንያለው
በአገራችን የተፈጠሩ ችግሮችን ስናነሳ ትግራይ ላይ የሆነውን ቀድመን የምናስበው ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ዋጋ የከፈሉበት ቦታ መሆኑን መናገርም ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ብዙ ትግራዊያን የኢትዮጵያን ድጋፍ የሚፈልጉበት እንደሆነ ማንም አይዘነጋውም፡፡ የሰላምና ጸጥታው ሁኔታም ቢሆን እንዲሁ በአንዳንድ ስፍራዎች መታየታቸው እሙን ነው፡፡
የመሠረተ ልማቱ ጉዳይም ሌላው ፈተናቸው ነው:: እንደ አጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ በብዙ ችግሮች ውስጥ ጊዜውን እያሳለፈ ነው፡፡ ለመሆኑ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? ምን እየተደረገለት ነው? ምንስ ያስፈልገዋልና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት በጊዜያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ከአቶ አትክልቲ ኃይለሥላሴ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል፤ ተከተሉን፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሕግ ማስከበሩ ሥራ ከተከናወነ በኋላ የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል:: በዚህ ውስጥ የሕዝቡን ጥያቄ እንዴት አያችሁት፤ ምላሽ ከመስጠት አንጻርስ ምን ያህል እየተጓዝን ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?
አቶ አትክልቲ፡– ሕግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ብዙ ነገሮች አሉ:: የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ አካል ጎድሏል:: በአጠቃላይ የጸጥታና የመረጋጋት ችግርም ነበር:: ሁሉም መሠረተ ልማቶች በሚባል ደረጃ የወደሙበትና መልሶ ለማምጣት ፈተና የታየበትም ነበር::
በተለይ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክና የባንክ ጉዳዮች ምንም ማግኘት ያልተቻለበት ነበር:: ሰዎች ከቤታቸው ወጥተው ለመመለስ እርግጠኛ ያልሆኑበትም እንደነበር ይታወሳል:: የመንግሥትና የሕዝብ አገልግሎቶችም ቢሆኑ ሙሉ ለሙሉ ቆመው ቆይተዋል:: አሁንም እንዲሁ በዚህ ጉዞ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች አሉ::
ችግሩ በዚህ ደረጃ እያለ የመጣ አመራር ብዙ ፈተና ይኖሩበታል:: ሆኖም ከተሰጠ ኃላፊነት አንጻር በተቻለ ሁሉ መስራትና መፍትሄ ማበጀት ግድ ስለሆነ ጥሩ እየተንቀሳቀስን ነው ብዬ አምናለሁ:: ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥት በአጭር ጊዜ ችግሩ እንዲቀረፍ ጥሯል:: በዚህም እንደ መቀሌ ብዙ ለውጦች ታይተዋል::
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሦስት ዋና ዋና ሥራዎች ለመስራት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቷል:: የመጀመሪያው የጸጥታና የመረጋጋት ሥራው ሲሆን፤ ይህም ብዙ ልፋትን የጠየቀ ነው:: ማለትም ፌዴራል ፖሊስ ወደ ትግራይ ለመግባት መንገዱ ሲዘጋበት የተለያዩ ቦታዎች ላይ በተለይ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ የነበሩ የጦር መሣሪያዎች በሌቦች እጅ እንዲገባ ሆኗል::
ሕጋዊ ባልሆነ መንገድም የሚወሰዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ይህ ደግሞ ብዛት ያላቸው ዘራፊዎችና ሌቦች የታጠቁ እንዲሆኑ አድርጓል:: በዚህም ሕዝቡም ሆነ የጸጥታ አካሉ የማይንቀሳቀስበት ሁኔታ እንዲኖር መንገድ ጠርጓል:: ስለዚህም ይህንን የማጽዳት ሥራ ሲሰራ ነበር::
ሌላው አላማው ምን እንደሆነ ያልታወቀውና መጠናት ያለበት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ማን እንደለቀቃቸው በማይታወቅበት ሁኔታ በትግራይ ማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉ ታራሚዎች ሁሉ ተለቀው በቀጥታ መቀሌ ላይ እንዲገቡ ተደርገዋል:: ይህ የሆነውም በአንድ ቀን ውስጥ ነው:: በዚህም ማህበረሰቡ ላይ ሌላ ትልቅ ውጥረት ሲፈጥር ነበር::
የክልል ፖሊስና ሚሊሻ በፈረሰበት ቅጽበት ይህ መሆኑ ደግሞ የአካባቢን ጸጥታ ከማስጠበቅ አንጻር የሚያግዝ ኃይል እንዳይኖርና ሕዝቡ በዘራፊዎች እንዲሰቃይ አድርጎታል:: ነገር ግን ከፌዴራል የጸጥታ አካል ጋር በመሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትጥቅ ከማስፈታት ጀምሮ ሥራዎችን በመስራቱ ነገሮች እንዲቀሉ ሆነዋል:: በዚህም ጥሩ ጉዞ ነበረን ማለት እችላለሁ::
አዲስ ዘመን፡- ሕዝቡ የኤርትራ ወታደር እኛን እያሰቃየን ነው የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ እያቀረበ እንደሆን ይሰማል:: አሁንም ድረስ የመደፈር፤ ዘረፋና ሌሎች ሕገወጥ ተግባራት እየተፈጸመ ነው ይላሉ:: በዚህ ላይ ምን ይላሉ? ችግሩን ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው?
አቶ አትክልቲ፡- እኔ መናገር የምችለው ስለ መቀሌ ነው:: የማስተዳድረውም እርሱን ስለሆነ እንደ መቀሌ ካነሳሁ እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ የለም:: የየትኛውም አካባቢ ሰራዊትም መቀሌ ውስጥ አልገባም:: ከመዘረፍ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የጸጥታ ችግር ግን አሁንም አለ::
30 ዓመት ሙሉ የተሰራ ሥራ በሁለት ወር ውስጥ ይጠፋሉ ተብሎ ሊታሰብም አይችልም:: ሆኖም መጀመሪያ ያጋጠሙ በነበሩበት ልክ ችግሮች አሁን አይፈጠሩም፤ እያጋጠሙም አይደለም:: ማንኛውም ሕዝብ ሰዓት እላፊውን አክብሮ እየተንቀሳቀሰና እየተገበያየ ነው::
ጥያቄውን በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ እንደአለ አመራር በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲነሱ እሰማለሁ:: አሉ ለምን አይወጡምም ይባላል:: እንደ መቀሌ ግን ስለሌሉ በሙሉ እርግጠኝነት ይህ የተባለው ነገር ከእውነት የራቀ ነው እላለሁ::
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አካላት መንግሥትን አለማመን ላይ እንደደረሱ የሚታይበት ሁኔታ አለ:: ይህንን ከመፍታት አኳያ የእናንተ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ አትክልቲ፡– ትልቁ ነገር መተማመን አለመተማመን አይደለም:: እንድንተማመን የሚያደርገን ምንድነው፤ እንዳንታመንስ የሚያደርገው ምንድነው የሚለው ነው:: እንደ ሕዝብ መንግሥት ካደረገው አኳያ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ አለው ብዬ አላምንም:: ነገር ግን ከደረሰበት ችግር አንጻር የሚያሳየው ነገር ይኖራል:: መሠረተ ልማት ሙሉ ትግራይ ላይ በሌለበት ሁኔታ፤ ሰብዓዊ እርዳታው ሳይደርስለት፤ ቤተሰቡን ተነጥቆ ባለበት ሁኔታ ላይ ለምን ይህ ስሜት ይሰማዋል ማለት ትክክል አይደለም::
ሰው በነበረው ላይ ጨምሮ ባረካበት ሁኔታ ያለውን ተነጥቆ የሚኖር ሕዝብ ቢከፋ ትክክል አይደለምም አይባልም:: ይህ ባህሪም ሊገመት የሚገባውና የሚጠበቅ ነው:: ስለዚህም ለመተማመኑም ላለመተማመኑም መንስኤው ችግሩን ለመቅረፍ ያለ ተነሳሽነት፤ ተግባርና ችግሮቹ እየተፈቱ የሚሄዱበት ደረጃ ይሆናል::
ለምሳሌ መቀሌ ቶሎ ወደነበረበት ሁኔታ የተመለሰው የፌዴራል መንግሥት በፍጥነት በየትም አቆራርጦ የሰጠው ምላሽ ነው:: ሕዝቡ የሚፈልገው ተጨባጭ ሥራ ነው:: ከሥነልቦና ጫና ውስጥም የሚወጣውና ሌላውን እያመነ የሚሄደውም ከሚደረግለት አንጻር እየለካ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ሕዝቡ አሁንም ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እንዳይቀራረብ የሚያደርጉ አገር ጠል ሰዎች በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ አሉ ይባላል:: እነዚህ አካላት የባሰ ችግር እንዳይፈጥሩ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ አትክልቲ፡- የትግራይ ሕዝብ ማንነት በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍታም ዝቅታም በህወሓት ማንነት አይገለጽም:: ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገር መገንባቱ፤ በሥርዓቱ፣ በፖለቲካው፣ በባህልና እሴት ግንባታውም የራሱን አሻራ ሲያሳርፍ እንደቆየ ሁሉ የትግራይ ሕዝብም ይህንን ሲያደርግ የኖረ ነው::
ስለዚህም የትግራይ ሕዝብም ከዚህ አንጻር መታየትና ለሌላው ሕዝብ ያለው ፍቅር እንደነበር እንደሆነ ሊታሰብ ይገባዋል:: ሆኖም ምልከታው የተዛባ የሚያስመስሉ ነገሮች በጭላንጭል ደረጃ ይታያሉ:: ግን ልክ አይደለም:: ማንም ማንንም አይጠላም::
የህወሓት ውድቀት መሠረታዊ ነገር የትግራይ ሕዝብና የእርሱን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አንድ ማድረጉ ነው:: ሰዎችም በዚህ እሳቤ ውስጥ ከሆኑ የህወሓት ዕጣፈንታ አይገጥማቸውም የሚል እምነት የለኝም::
እናም ሁሉም ዛሬ ላይ የትግራይን ሕዝብ ሲያስብ የ30 እና የ40 ዓመት ቆይታን አጉልቶ ሳይሆን ለሺህ ዓመታት የነበረውን አበርክቶ በማየት መሆን አለበት:: የትግራይም ሕዝብ ቢሆን እንዲሁ ሌላውን ብሔረሰብ ሲመለከት በቀደመው መልካም ተግባሩ መሆን ይገባዋል:: ይህም ስለሆነ የሚያቀራርበው::
በህወሓት ሴራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከፍሏል:: በተለይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ የበለጠ ዋጋ የከፈለ ነው:: አሁንም ክፈል የበላኸው ነው በሚል አስተሳሰብ መወጋትና መመታት የለበትም:: ሕዝቡ ጥናት ያስፈልጋል እንጂ አንዳንድ ችግሮቹ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ልቀው የወጡና የተለዩ ናቸው::
በኢኮኖሚ ብቻ አይደለም በደሉ:: ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሥነልቦናዊ ጫናም ተፈጥሮበት ሲኖር የቆየ ነው:: ከፖለቲካው ጋር በተያይዞ ብቻ ቢነሳ የትኛውም ክልል ላይ ያልሆነ ትግራይ ላይ ተከስቷል:: ለአብነት ትግራይ ላይ ተቀዋሚ መሆን አይፈቀድም:: ቢሮ መክፈትም እንዲሁ አይቻልም:: ተቀዋሚ ሆነ ከተባለ ቤት የሚያከራየው አይኖርም፤ ቤተሰቡም በነፃነት መንቀሳቀስ አይችልም::
መንግሥት ሥራ ላይ መቀጠርም ይከለከላል:: ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ድሮም የተጎዳ እንጂ የተጠቀመ አይደለም:: አሁንም ጉዳቱን የሚያባብስ ነገር ተጨመረለት እንጂ አልተጠቀመም:: የተሰራው ሥራ በመንግሥትም ላይ ሆነ በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ እምነት እንዳያሳድር ብዙ ነገሮች አድርገውታል::
ሕግ ከማስከበሩ ጋር ተያይዞ ጭምር አሁንም ቢሆን ችግሮችን የሚጨምሩ አልጠፉበትም:: ስለሆነም የቱን ማመን እንዳለባቸው ግራ ስለሚጋቡ ለማቀራረብ ያስቸግራል:: ለአብነት ከአማራ ክልል ጋር የሚነሱ ነገሮች ሲባል የነበረውን ነገር የሚያረጋግጥ ነው:: ሊወሩህ ነው፤ መሬትህን ሊቀሙህ ነው ሲባል የነበረ ሕዝብ በተግባር ሲያየው ህወሓት ልክ ነበር የሚለውን አስተሳሰብንም እንዲከተል ይሆናል::
ይህ ደግሞ አለመረጋጋቶች እንዲንሰራፉ መንገድ ይከፍታል:: በተለይ በየጊዜው ለመነካካትና አዲስ ችግር ለመፍጠር ያሰፈሰፉ አገር ጠል ፖለቲከኞችና ጥቅመኞች መኖራቸው ለአመራሩ ሥራውን ያከብድበታል:: ሆኖም ውጥረቱ እንዲረግብ ለማድረግ እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው::
ውዥንብር ለመፍጠር የሚጥሩ አካላት በእኔ እይታ ጊዜያዊ ናቸው:: ምክንያቱም በሳል የሚባለው የማህበረሰብ ክፍል ይህንን አስተሳሰብ ያከሽፈዋል:: ያለውን ኢትዮጵያዊነት አጉልቶ ስለሚያወጣውም በሚመጡ ቅጽበታዊ ግጭቶች እንዳይሸረሸር ያደርገዋል:: እነዚህ ሰዎች በፈጠሩት ድርጊትም ላለመበከል ይጥራል::
ምክንያቱም ድርጊቱ አሁን ተነቅቶበታል:: ከዚህ በፊት መላው ኢትዮጵያ ዋጋ የከፈለበትን ዳግም በሚያውቀው ነገር አይደግመውም:: በተለይ ትግራዊያን በዚህ ችግር ዳግም አይበሉም:: ምንም ዓይነት ፖለቲካው ውስጥ የሌለው ሰው ትግሪኛ ስለተናገረ ብቻ እንዲገለል ተደርጓል፤ ሥነልቦናዊ ጫና ደርሶበታል፤ ተዘርፏል ተደብድቧል::
እናም ያንን ዳግም ችግር መቅመስ ለማይፈልግ ወግድ ማለቱ አይቀርምና ለአመራሩ ይህም ያግዛልና በውይይት ይህንን አስተሳሰብ እንዲያሰፋ እየተሰራ ነው::
የተፈጠረውን አለመረጋጋት፤ የሥነልቦና ጫና ለማርገብም ቢሆን የፌዴራል መንግሥት ከሚሰራው ሥራ በተጓዳኝ የአገር ሽማግሌዎችን፤ የከተማው ወጣቶችን በማሳተፍ ሕዝቡ የራሱን ጸጥታ እራሱ እንዲያስከብር የማድረግ ሥራም እየተሰራ ነው:: ችግሩ በጣም የከፋና ስር የሰደደ በመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ያለበትን ሁኔታ ተገንዝቦ ከአገዘው ደግሞ ይበልጥ እንደሚበረታና ወደቀደመ የልማት ሥራው እንደሚመለስ እምነት አለኝ::
ለዚህም ማሳያው ብዙዎች እየደረሱለት በመሆኑ አሁን ሜጋ ፕሮጀክቶችን የማሰብና ተቋርጠው የነበሩት የውሃ ፕሮጀክት ዓይነት ተግባራት እንዲጀመሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው:: ብዙ የልማት ጉዞዎች አሉብንና ይህ ድጋፍ ሊቀጥል ይገባል::
አሁን በደረሰው ችግር ምክንያት የትግራይ ሕዝብ መገፋት እንደደረሰበት ሁሉ ከለላም አልተደረገለትም ተብሎ ሊወሰድ አይገባውም:: ምክንያቱም ብዙ ክልሎች ላይ መልካም አመለካከት ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ሕዝቡና ተሳታፊው ተለይቶ ደህንነቱ ተጠብቋል::
እናም እዚህ ላይም ቢሆን ከለላውን ማስጠበቅና እርስ በእርሳችን መተሳሰባችንን ማጠናከር ከምንም በላይ ያስፈልገናልና ለመቀራረባችን መሠረት እናድርገው ሳልል አላልፍም::
አዲስ ዘመን፡- በአማራና በትግራይ መካከል ያለው የመሬት ጥያቄ አሁን መነሳቱ ወቅቱ ነው? ለትግራይ ሕዝብ መሬት ወይስ ዳቦ ዛሬ ላይ የሚያስፈልገው?
አቶ አትክልቲ፡- እንደኔ ጉዳዩ መነሳቱ ወቅታዊ ነው የሚል እምነት አለኝ:: ምክንያቱም በዘመቻ ስም ምንም ዓይነት ተቃውሞ የሚያስነሳ ተግባር መከናወን የለበትም:: ችግር የሚፈጥሩ ነገሮችም መነሳት አልነበረባቸውም:: ነገር ግን በዘመቻ ስም የመጣው ነገር መልስ እንድንሰጥ የሚያስገድድ ስለነበር ሆኗል::
ዘመቻው በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በትግራይ ሕዝብም በሙሉ ልቡ የሚታመንበት ነው:: ምክንያቱም እዚያ የነበረው ኃይል አጥፊ ስለነበር ከዚያ ሊወገድ ይገባዋል:: በዚህም ሕግ ለማስከበር ዘመቻው ተካሂዷል:: ሕግ የጣሱ ሰዎችንም በሕግ ቁጥጥር ስር ለማዋል ተሞክሯል:: ነገር ግን ዘመቻው ላይ አብሮ የሄደ ሰው መሬት መውሰድ አይገባውም ነበር::
ዘመቻው ራያን ለማስመለስ፣ ወልቃይትን ለመውሰድ አይደለም:: አሰላለፋችንም እንዲህ አይሆንም:: ስለዚህም ከዘመቻው ጋር ታኮ የመጣን አደጋ መታገስም አይገባውም:: ክልሎች ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል::
ግን ጥያቄው ደግሞ በሁለቱም በኩል ያለና በፌዴራል መንግሥት የተያዘ ነው:: ጥያቄው መነሳቱም ስህተት አይደለም:: ስህተቱ የሚሆነው ጥያቄው የሚስተናገድበትን መንገድ አለመለየቱ ላይ ነው::
እዚያ አካባቢ ያለው ኃይል ተዳክሟል፣ ሕዝቡም ችግር ላይ ነው ብሎ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ የመሬት ወረራ ማድረግ የሚያስተዛዝብ ነው:: በወቅቱ ጥያቄውን ማንሳትም ተገቢነት አለው:: በእርግጥ ይህንን ያደረጉት አንዳንድ ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ ይመስሉኛል::
በትግራይ ሕዝብና በአማራ ሕዝብ መካከል ያለው አቋም ግልጽ በሆነበት ሁኔታ ይህንን ማንሳቱ ሁለቱ የበለጠ እንዲካረሩ ተፈልጎም እንደሆነ እገምታለሁ:: በዚህም በተያዘው አካል በጊዜው መታየት ስላለበት ወቅታዊ ምላሽና ሁሉም እንዲያውቀው የማድረግ ሥራ ተሰርቷል::
መሬታችን እየተያዘ ነው መባሉ ብዙ ሕዝቦች እየተፈናቀሉ ስላሉ ነው:: መሬት ሲባል አፈር አይደለም:: ቦታው ላይ ሰው አለ:: ስለዚህም በችግር ላይ ችግር እየተደራረበበት አትጠይቅ ማለት ደግሞ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው የሚል እምነት የለኝም:: ቦታው ላይ ያለው ሰው የጸጥታ፣ የአስተዳደር፣ የመሠረተ ልማት ጥያቄ አለው::
በየትኛው እንደሚተዳደር ግራ ገብቶታል:: ይህንን ለማረምም ነው ድርጊቱ ትክክል እንዳልሆነ የማስገንዘብ ሥራ የተሰራው:: ለዚህም ነው ወቅቱን ጠብቆ የተነሳው ነው ብዬ በሙሉ ልብ እናገራለሁ::
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የትግራይ ነዋሪዎች ኩርፊያ ላይ ናቸው ይባላል:: ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ አትክልቲ፡- ከሕግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞ በመጡ ችግሮች ምክንያት ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል:: የተካሄደው ጦርነት በመሆኑም ተጨማሪ ችግሮችን ይዞ መጥቷል:: በዚህ ችግር ውስጥ ያለ ሕዝብ ደግሞ አፋጣን ምላሽ የሚሰጠውን አካል ቢናፍቅና ቢያኮርፍ ችግር ነው ብዬ ልወስደው አልችልም::
በየደረጃው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ያረፉበት አካል ብዙ ጥያቄዎች ይኖሩታል:: ምላሹን በሚፈልገው መጠንና ፍጥነት ካላገኘም ቢያኮርፍ ችግር አለው ብዬ አላስብም:: ነገር ግን ኩርፊያው ማን ላይ ነው የሚለው መታየት አለበት::
መልስ የማይሰጠው ላይና ለምን ተነካሁ በሚል ስሜት ከሆነ ትክክል አይደለም:: አስተሳሰቡም ከህወሓት የሚለይ አይሆንም:: ይህ የፖለቲካ ውግንና ነውም ሊባል የሚችለው:: ስለዚህ ህወሓት ለምን ተወገደ ብሎ ያኮረፈ ካለ የማኩረፉ ምንጭ ፖለቲካው ይሆናል:: ይህ ደግሞ ትልቅ ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰድ አይሆንም::
ምክንያቱም ህወሓት የተወገደው የፖለቲካ አስተሳሰቡ ለሕዝብ የሚመች ባለመሆኑና ራሱን ስለሚያይ ነው:: አሁንም ለምን ጥቅማችን ተነካ የሚል ካለ መወገዱ አይቀርምና ሊያሳስብ አይገባም:: ግን የግጭት መንስኤ ለመሆን እየተንቀሳቀሱ ከሆነ ይህ ኩርፊያ ትክክልም፤ የሚሞትም እንደሚሆን ማሰብ የአኩራፊው አካል ይሆናል::
አሁን ያለውን ችግር እንዲፈታ የሚጠበቀው አካል ህወሓት ሳይሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሆነ ግልጽ ነው:: ስለሆነም ሁለቱን ነጥሎ ማየት ያስፈልጋል:: አኩራፊው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ቶሎ ምላሽ ባለመስጠቱ የተከፋና ያደረገው ከሆነ ይህ ትክክለኛ ነው:: አንድም መንግሥትም ሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለምላሹ እንዳይዘገይ ያበረታዋል::
በሌላ በኩል ደግሞ የአመራሩን ሥራና ቸልተኝነት እንዲታይ ያደርጋል:: ስለዚህም ይህ ኩርፊያ ከሚጠበቀው አካል የሚጠበቀውን ያህል ማግኘት ሳይቻል ሲቀር የሚመጣ ሆኖም ምላሹ በተገቢው ሁኔታ ሲሰጥ የሚፈታ ነው:: አሁን ያለውም አንዳንዶች አኩርፈዋል የሚባለው ከዚህ የተነሳ ሊሆን ይችላል::
ህወሓትን እንደገና እመልሳለሁ ብሎ አኩርፎ የተቀመጠው ግን የተለየና ማንም ትኩረት የማይሰጠው እንደሆነ ሊወሰድ ይገባል:: በዚህ መልኩ ያኮረፉም እንዳሉ ይሰማኛል:: ምክንያቱም ኩርፊያው ስላለ ትናንት ጠዋት ብዙ ነገር አድርገዋል:: ዛሬም ያደርጋሉ:: ምልክቶችም አሉ::
የእኛ ጥያቄ ግን ይህ ሊሆን አይገባም:: ሕዝብ እንደሕዝብ ተበደለ እንጂ በነበራቸው ኔትወርክና በነበራቸው ቡድን ኢኮኖሚያቸው የጠነከረ፣ ብዙ ሀብትና ንብረት ያካበቱ፣ ተጠቃሚነታቸው የተረጋገጠላቸው ማለቱ ላይ አይሆንም::
ነገር ግን እነርሱንም ዝም ብሎ ማየት አይገባም:: መረጋጋት ካለ እነርሱ እንደሚነኩ ስለሚያውቁት የቀደመ ነገራቸውን ለማግኘት የማይቆፍሩት ድንጋይ አይኖርም:: ለዚህም ማሳያው አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆነው መከላከያ ላይ ሳይቀር ጦር ሰብቀዋል::
ጥቅማቸው ሲነካ ኔትወርካቸው የሚፈርስባቸው፤ ትናንት እንደ ልባቸው ይረግጡት የነበረ ሕዝብ ከጎንህ አይደለንም ብሎ ሲያገለውም መነሳቱ አይቀርምና አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል:: እናም ኩርፊያውን በየአቅጣጫው እያዩ መፍትሄ መስጠቱ ይበጃል እንጂ አኮረፉ ብሎ ማወዛገቡ ተገቢነት የለውም::
አዲስ ዘመን፡- አንድ ሚዲያ በጠራው አመጽ ንግድ ቤቶች ጭምር መዘጋታቸው ይገለጻል:: የዚህ ማሳያው ምንድነው፤ ቅድሚያ ጥቆማ ደርሶ ዝም ተብሏል ይባላልም:: ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ አትክልቲ፡– ሚዲያው በራሱ ችግር ያለበት ነው:: መሬት ላይ የሌለ ነገር ማውራትንም ይመርጣል:: ሰውን ወደ ሥራ እንዳይመጣ የሚያደርግ ተግባር የሚያከናውን ነው:: መረጋጋትና ሰላም በትግራይ እንዳይኖርም የሚፈልግ ዓይነት አካሂድ ይከተላል:: ነገር ግን ሙሉ ነን ማለት አይደለም፤ ችግሮች የሉም ማለትም አይደለም:: ብዙ ችግሮች አሉ::
ብዙ ጥያቄዎችም በሕዝብም ሆነ በጊዜአዊ አስተዳደሩ ደረጃ ይነሳሉ:: በየደረጃው በየጊዜውም ለሚመለከተው አካል ይቀርባሉ:: ስለዚህም ጥያቄ ማቅረብ መቼም መከልከል የለበትም:: ነገር ግን ሥርዓቱን በጠበቀና ሂደቱን በአማከለ መልኩ መሆን ይኖርበታል:: ከዚያ አቅም በፈቀደ መልኩ ጥያቄው የቀረበለት አካል መፍትሄ መስጠት ይገባዋል:: ከዚያ ውጪ ጥያቄን በአሉታዊ መልኩ መጠቀም ተገቢነት የለውም::
የትግራይ ሚዲያ ሀውስ ጥያቄን ወደ አመጽ መቀየር መፈለግን ያሳየ ነው:: ትናንት በነበረው ችግር የተካሄደው ዘመቻ ብዙ ዋጋን አስከፍሏል:: ከተጎዳ ሥነልቦና ጀምሮ እስከ ሕይወት ማጥፋት ድረስ ትልልቅ ችግሮች ተፈጥረዋል:: አሁንም እርሱን ሊደግም በሚችል መልኩ መንቀሳቀስ ደግሞ ይበልጥ አደጋ ነው:: ለሕዝብ ማሰብም አይደለም:: የሕዝብ ወገንተኝነትን ማሳየትም አይደለም::
እንደ ሚዲያም ሙያዊ ሥነምግባርም አይደለም:: ከዚህ አንጻር የእነርሱን ሀሳብ የሚከተሉ ይኖራሉና እንደነዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ሊያደርግ አይገባውም ነበር:: በእርግጥ ትናንት ሕዝቡን ደም እያስለቀሱ፤ በዘርና በኔትወርክ ተደራጅተው ሲዘርፉ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ይፈልጋሉ ማለት ሞኝነት ነው:: ምክንያቱም ሕዝቡ ተረጋግቶ ወደ ሥራ ከገባ መጠየቅ ይጀምራል:: ስለዚህም ላለመጠየቅ የቀደመ ተግባራቸውን ያከናውናሉ::
መቼም ቢሆን አንድ ነገር አምናለሁ:: ጥያቄዎቹ ስህተት ናቸው አልልም:: ትክክል ናቸው:: በአመራርም ደረጃ የሚነሱ ሊሆኑ ይችላሉ:: ነገር ግን አጠያየቁና ስሜቱ የሚገለጽበት ነው ትክክል ያልሆነው::
ጥንቃቄንም ይጠይቃል:: መልሰን ዋጋ በምንከፍልበት መልኩ መጠየቅ የለባቸውም:: ሚዲያው ግጭት የሚመስሉ ቅስቀሳዎችን ሲያደርግ ነበር:: ሆኖም ሕዝቡ እርሱን ተከትሎ ምንም ያደረገው ነገር አልነበረም:: ወደፊትም ቢሆን ተከትሏቸው እንደማይሄድ አምናለሁ::
አዲስ ዘመን፡- አዲሱ መዋቅር ምን ያህል የተናበበ ሥራ እየሰራ ነው?
አቶ አትክልቲ፡- ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከተቋቋመ በጣም አጭር ጊዜ ነው የሆነው:: ሁለት ወራት ነው የሞሉት:: ከችግሩ ስፋት አንጻር ሁሉንም ችግሮች ለማድረስ አልቻለም:: ያልተፈቱ፣ ያልተስተካከሉ ብዙ ችግሮችም አሉበት:: መስተዳድር ማደራጀት በራሱ ብዙ ሥራንና መናበብን የሚጠይቅ ነው:: ስለዚህም አንዳንድ ቦታዎች ላይ በሚገባው ፍጥነት ያልሄዱ ሥራዎች እንዳሉም እናምናለን::
በዚያው ልክ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ልቀው የሄዱም ይኖራሉ:: እርስ በእርስ ለመገማገምና ሥራዎቻችንን ተናበን እየሰራን ነው ለማለት ገና ብዙ ጊዜያት የሚቀሩን ይመስለኛል::
በቂ ጊዜ ላይ ነን ተብሎም ለመውሰድ ያዳግታል:: ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምን ሊሰራ ተቋቋመ፣ ምንስ ሰራ፣ አልተናበበም ወዘተ የሚሉትንም ለማስቀመጥ ያልሰራን መናገር ስለሚሆን ጊዜ ወደፊት የሚናገረው ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከህወሓት የተሻለ ሥራ እየሰራ አይደለም ትባላላችሁ:: እንዲያውም የእነ ስብሃት ቡድን ነው ይሏችኋል:: በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ አትክልቲ፡- አንድ ነገር ጠንከር ብሎ መወሰድ አለበት:: ነው አይደለም የሚል ላይ ባልደረስንበት ነባራዊ ሁኔታ መናገርም ተገቢነት ያለው ጉዳይ አይደለም:: ትልቅ እውነት እንዳለ ግን አምናለሁ:: ይህም የትግራይ ሕዝብ ከዚህ በኋላ የቡድንተኝነት፣ የዘርና የዘመድ ተግባርንንም ፖለቲከኛንም ይቀበለዋል ብዬ አላስብም::
የሚያስብም ካለ ከእኛ ወገን አይደለህም እንደሚለው አምናለሁ:: ምክንያቱም በዚህ ሴራ ብዙ ነገሩን አጥቷል:: እኔም እዚህ ላይ ስወጣ ይህንን በማሰብና በማለም ስለሆነ እታገለዋለሁ፤ ሕዝቡም ይታገለዋል::
ዛሬ እንዲህ የወረደ አስተሳሰብ ላይ የደረስነው ይህ አመለካከት በእንጭጩ መቀጨት ስላልቻለ ነው:: ዘመድ ዘመዱን ሳይሆን ኢትዮጵያዊነቱን ያስቀድም ተብሎ ውግንናችን ከሰው ሁሉ ጋር ቢሆን ኖሮ ማንም ማንንም ባልነካ ነበር::
ተው የሚል ኃይል ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ብሔርተኝነት አይንሰራፋም ነበር:: ትግራይ ያሉ ነዋሪዎችም ሆኑ ሌሎች ክልሎች ላይ ያሉ ነዋሪዎች ይህንን ዋጋ አይከፍሉም ነበር::
አዲስ ዘመን፡- እንደ አጠቃላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት ዕድሉን ልስጥዎት?
አቶ አትክልቲ፡– ሦስት መሠረታዊ ነገሮች መልዕክት ቢሆኑልኝ እደሰታለሁ:: የመጀመሪያው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲሆን፤ ይህ ችግር የትም ቦታ ላይ ሊያጋጥም የሚችል ነው:: ችግሩን እንደ ትግራይ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ችግር አይቶ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ በመሆኑ አመሰግናለሁ::
ነገር ግን ያጋጠመው ችግር መጠነ ሰፊ በመሆኑ ሁኔታውን አይቶ ይህንን ድጋፉን ሳይታክት አጠናክሮ እንዲቀጥልና ሕዝቡን ከችግሩ እንዲታደገው እጠይቃለሁ::
ሁለተኛው በየትኛውም የዓለም አገራት ላይ ለሚቀመጡ ትግራዊያን የማስተላልፈው መልዕክት ሲሆን፤ በተለይ ዲያስፖራዎች ችግር አለ ብሎ ሁልጊዜ ስለችግሩ ብቻ ማውራት መፍትሄን አያመጣምና ችግሩን ከማውራት በላይ ድጋፉ ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነው:: ችግሮች መፈታት የሚችሉትም በየደረጃው በሚመለከታቸው አካላት እንደሆነ መገንዘብ ይገባቸዋል::
ችግርን አግዝፎ ወይም አሳንሶ በማቅረብ መፍትሄ አይመጣምና የተረጋጋ ሰው ተመልሶ ወደ ብጥብጥ እንዲገባ ማድረግ የትግራይን ሕዝብ መውደድ አይደለምና በዚህ ድርጊት ላይ የሚሳተፉ አካላት እጃቸውን ቢሰበስቡ:: እወደዋለሁ፣ እታገልለታለሁ የምትሉት ሕዝብ መጀመሪያ ልትደርሱለት የሚገባው መሠረተ ልማት በማሟላት ነው:: እናም ይህንን በማድረግ አግዙት::
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋናው ትኩረቱ ሕዝብን መታደግ እንጂ ፖለቲካ ማስፈጸም አይደለም:: የአንድ ፓርቲ አመራርም አይደለም:: የአንድ ፓርቲን አመለካከት የሚያሰርጽም አይደለም::
በመሆኑም አሁን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፖለቲካ ሳይሆን ሕዝብን የመታደግ ሥራ እያከናወነ በመሆኑ ሕዝቡ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር፣ የሥነልቦና ችግር፣ የመሰረተ ልማት ችግር፣ የሰብዓዊ እርዳታ ችግር ለመፍታትም እንደ ኢትዮጵያዊ ሁሉም ከጎኑ በመሰለፍ ሊያግዘው ይገባል::
ሁሉም ሰው የፈለገ የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረውም ሰው መታደግ ግን አንድ የሚያደርግ መሆኑን ማመን ይገባል:: ስለዚህም ፖለቲካው ይቆየንና ትግራይን እንታደገው::
ሦስተኛው ለሚዲያው የማስተላልፈው መልዕክት ሲሆን፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ ችግር ሆኗል:: አንዳንዱ ተጨባጭ ያልሆነ ችግር ፈጥሮና ተፈጠረ ብሎ እወቁልኝ ይሰራል:: ሌላው ደግሞ ያለውንም በደንብ አይዘግብም::
ግልጽ ማብራሪያ ከሚመለከተው አካል አይጠይቅም:: ያለውን ችግርም ቢሆን እንዳይታወቅ በማድበስበስ ሌላ ችግር ይፈጥራል:: በዚህም ሕዝቡ እንዲወናበድና እውነታው የቱ ላይ እንዳለ እንዳይረዳ አድርጎታል::
አዲስ ዘመን፡- ከመቀሌ ድረስ መጥተው ላቀረብናቸው ጥያቄዎች ምላሽ ስለሰጡን እናመሰግናለን::
አቶ አትክልቲ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2013