አዲስ አበባ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) እንደገና ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ትናንት አፀደቀ፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ አገራት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ረቂቅ አዋጆችንም አፅድቋል፡፡
ምክር ቤቱ አራኛ ዓመት ሶስተኛ ልዩ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገና ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅና ከተለያዩ አገራት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ አፅድቋል፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገና ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በዝርዝር ሲመለከት የነበረው የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መካተትና መስተካከል አለባቸው ያላቸው ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂና የሙያ እድገት ጋር የተጣጣመ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ ገቢ የሚያመነጭባቸው ስራዎች ላይ እንዲያተኩር የሚያደርጉ ሃሳቦች ረቂቅ አዋጁ ላይ ተካተዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ፎዚያ ገለፃ፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መንግስት ከሚመድብለት በተጨማሪ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚሰበስባቸውን ገንዘቦች የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ እንደሚወሰን ተቀምጧል፡፡ በዚህም ኢዜአ የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ በሚያስችል መልኩ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ተስተካክሏል፡፡ ምክር ቤቱም ተወያይቶ ረቂቅ አዋጁን አጽድቋል፡፡
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በእንስሳት ሀብት እና አሳ ዘርፍ በትብብር ለመስራት የተደረገ ስምምነት፣ የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት፣ በእፅዋት ማቆያና ጥበቃ ዘርፍ የተደረገ ስምምነት፣ በኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን በትብብር ለመስራት የተደረገ ስምምነት እና ሌሎች የትብብር ስምምነቶች ጸድቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 30/2011
መርድ ክፍሉ