አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን የ2009 ዓ.ም የቀን ገቢ ግምትን በተመለከተ ቅሬታ ላቀረቡ ግብር ከፋዮች ውሳኔ መስጠቱን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረ ስላሴ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የ2009 ዓ.ም የቀን ገቢ ግምትን አስመልክቶ ግብር ከፋዮች ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ያስተላለፈውን ውሳኔ መነሻ በማድረግ ለቅሬታ አቅራቢዎቹ ውሳኔ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ሺሰማ ማብራሪያ፤ ከቀን ገቢ ግብር ጋር በተያያዘ በግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ አቤቱታ ያቀረቡና ክርክር ላይ የሚገኙ አራት ሺህ 41 ግብር ከፋዮች የከፈሉት ሃምሳ በመቶ ፍሬ ግብር በቂ ሆኖ ወለድና ቅጣትን ቀሪ በማድረግ ወይም የቀን ገቢ ግምታቸው ሃምሳ በመቶ ተስተካክሎ እንዲሰራ፤ ክርክሩም ተቋርጦ የንግድ ፈቃዳቸውን ያላደሱ እንዲያድሱ ተወስኗል፡፡ በዚህ የውሳኔ ሃሳብ ያልተስማሙና ክርክራቸውን መቀጠል የሚፈልጉ ካሉም በክርክሩ የመቀጠል መብታቸው የተከበረ ነው፡፡
በሌላ በኩል የፍሬ ግብሩን ሃምሳ በመቶ መክፈል ባለመቻል ግብር ይግባኝ መሄድ ያልቻሉ አንድ ሺህ 59 ግብር ከፋዮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ እነዚህም በጀመሩት ንግድ የመቀጠል ፍላጎት ያላቸው ግብር ከፋዮች ንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያድሱና ንግድ ፈቃዳቸውን መመለስ የሚፈልጉትም ደግሞ ከገቢያቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ግብር መክፈል የሚያስችላቸውን ግምት የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊነት ወስዶ እንደሚሠራና እንደሚያስፈጽም አቶ ሺሰማ ገልፀዋል፡፡
‹‹የገቢ አሰባሰባችን በሚፈለገው ደረጃ እየተከናወነ አይደለም››ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ችግሮችን ለመፍታት ተቀራርቦ መነጋገርና አዳዲስ ታክስ ከፋዮችን ወደ ሥርዓቱ በማካተት ዜጎች አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የከተማ ግብር የሚሰበሰብባቸው አርዕስቶችንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ የተጀመረው የታክስ ንቅናቄም ግቡን እንዲመታ ሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅበትን ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 30/2011
ኢያሱ መሰለ