አዲስ አበባ፡- በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሰራር ሥርዓት የቃልኪዳን ሰነድ ተዘጋጀ፡፡
በፖለቲካ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ መካከል የተካሄደውን ውይይቱን የመሩት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሣ እንደገለጹት፤የአሰራር ስርዓት የቃልኪዳን ሰነዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ መንግስቱን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፣ ሕገ መንግስቱን ከሚጻረሩ ድርጊቶችም እንዲታቀቡ ይደነግጋል፡፡ሚዲያና ማህበራዊ ድረ-ገጾችን አጠቃቀም በተመለከተም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ ተቋማትን ነጻነት ከሚጋፋ ማንኛውም ዓይነት ተግባር እንዲቆጠቡ ይደነግጋል፡፡
የቃል ኪዳን ሰነዱ በአገሪቱ ጠንካራ፣ ዘላቂና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ነው ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣አመራሮቻቸው እና አባሎቻቸው የሚያደርጉትን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያግዛል፤ በፓርቲዎች መካከል ሊነሳ የሚችለውን አለመግባባት በጋራ ውይይት ይፈታል፤ የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብት ሳይሸራረፍ እንዲከበርና እንዲረጋገጥ የሚያስችል አሰራርን ይፈጥራል፤መጪው ብሔራዊ እና አካባቢያዊ ምርጫ ነጻ እና ፍትሃዊ እንዲሆን በሚደረገው ዝግጅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ተሣትፎና ሚና ያሳድጋል ሲሉ የሰነዱ አላማዎችን አብራርተዋል፡፡
የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ብሔራዊና አካባቢያዊ ምርጫ እየተቃረበ ነው፡፡ ኢትዮጵያም አሁን የምትገኘው በፖለቲካዊ ሽግግር ላይ ነው፡፡ አለመረጋጋቶች እዚህም እዚያም ይስተዋላሉ፤የፖለቲካ ችግሮች አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን የፖለቲካ ችግሮች ፈትተን፣ሰላምን አስፍነን፣ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂደን በመጨረሻም ሰላማዊና የተረጋጋች አገር እንድትኖረን እንዴት ተግባብተን መስራት አለብን፤ማን ምን መስራት አለበት በሚሉት አንኳር ነጥቦች ላይ ሰነዱን መሰረት በማድረግ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በምርጫውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳንጣላ፣ ህዝብን ለችግር ሳንዳርግ፣ችግሮች ሳይፈጠሩ እንዴት ተግባብተን ማከናወን እንችላለን የሚለውም የውይይታችን ማጠንጠኛ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አብርሃ ደስታ ማብራሪያ፤ ቀደም ሲል የፖለቲካ ፓርቲዎች የግንኙነት ደንብ ምን ችግሮች ነበሩበት የሚለው በምሁራን ቀርቧል፡፡ ይሄን የቃል ኪዳን ሰነድ ማዘጋጀት የሚያስችሉ ሃሳቦች ተነስተው ቀጥሎም የሕግ ባለሙያዎች የተካተቱበት ስብስብ እንዲያዘጋጀው እና በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲቀርብ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ተዘጋጅቷል፡፡
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ ከሕጎችም በላይ የሚጠቅም ነው፡፡ በዚች አገር ዴሞክራሲ ይምጣ ካልን ምን መሆን እንደምንችል ያሳያል፡፡ህግ ከመውጣቱ በፊት ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ መዘጋጀቱ ጥሩ ነው ፡፡ፓርቲዎቹ ከሕግም በላይ ተስማምተውና ፈቅደው ባወጡት መመራታቸውን የሚያሳይ ይሆናል ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችም ሆኑ አባሎቻቸው በዚህ የቃል ኪዳን ሰነድ መሰረት መመራት አለባቸው፤ ሕብረተሰቡም እንዲ ያውቀው ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃልኪዳን ሰነድም በሦስት ምዕራፎችና በአስራ ዘጠኝ አንቀጾች መደራጀቱ ተገልጿል፡፡ ተስማምተው በፈረሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር፣አባላት፣ወኪሎች እና ተጠሪዎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ምርጫ ቦርድ ኃላፊዋ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናግረዋል፡፡
የቃል ኪዳነዱ በሚቀጥሉት ውይይቶች ዳብሮ በፖለቲካ ፓርቲዎች ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 30/2011
ሙሀመድ ሁሴን