ሙሉቀን ታደገ
የዛሬ የፍረዱኝ ጉዳያችን በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ቡልቡላ ሸማቾች ወይም 93 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ‹‹በሕገ ወጥ መልኩ በወራሪዎች የይዞታ መሬታችንን ተነጥቀናል›› በሚል ፍረዱኝ ያሉ ቤተሰቦችን አቤቱታ እንመለከታለን::
ፍረዱኝ ባዮቹ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፣ እነኝህ ቤተሰቦች ማለትም ወይዘሮ አልማዝ ባዩ፣ ወይዘሮ ቡርሴ ባዩ እና አቶ በቀለ ባዩ ይባላሉ:: እነኝህ ቤተሰቦች ከአንድ አባት እና ከአንድ እናት ተወልደው ያደጉት አሁን ላይ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ሸማቾች ተብሎ በሚጠራው ቡልቡላ አካባቢ ነው::
እነኝህ ቤተሰቦች ማንኛውም ቤተሰብ ለልጁ እንደሚያደርገው ከእናታቸው ወይዘሮ ሚልኮ ቢፍቱ የመሬት ውርስ ያገኛሉ:: በውርስ ያገኙትን መሬት ከለውጡ በፊት የነበረው የህወሓት መራሹ ኢህአዴግ መንግሥት ለልማት በሚል ሰበብ መሬታቸውን የወሰደውን ወስዶ የተረፈውን ይተውላቸዋል::
አሁን ደግሞ በለውጡ በህወሓት መራሹ መንግሥት እርስታቸው የተወሰደባቸው አርሶ አደሮች በመሬታቸው የመጠቀም መብት አላቸው በተባለው መመሪያ መሰረት ለመጠቀም ሲሞክሩ በጉልበታሞች እና ሕግን በረሱ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው የወረሱት የይዞታ መሬታቸው ተወረረ:: በሕገወጦች የተወረረባቸው መሬት ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው ይጠቀሙበት የነበረና ልጆችም ከእናታቸው ከወይዘሮ ሚልኮ ቢፍቱ በውርስ ያገኙት ነበር::
በዚህም ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለከተማ አቤት ቢሉም ሊሰማቸው የቻለ አንድም የመንግሥት አካል አለመኖሩን ይናገራሉ:: አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንዳስረዱትም በደላቸውን ተመልክቶ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ሁልጊዜ አዳማጭና እኔ አይመለከተኝም የሚል መልስ መስጠት ይቀናቸዋል:: የሕዝብን ችግር ይፈታሉ ተብሎ ሕዝብ እና መንግሥት ኃላፊነት የሰጣቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ችግሩን ማስቆም ተስኗቸዋል::
የወረዳ አመራሮች፣ የቀጣና አመራሮች፣ የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤቶች፣ የፍትህ ጽሕፈት ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የሕዝብን ችግር አዳምጠው ሕግ እና ሥነ ሥርዓት ያሰፍናሉ የተባሉ አካላት እንኳንስ የሕዝብን ቅሬታ አዳምጠው የሀገርን ሕግ እና ሥርዓት ሊያስጠብቁ ይቅር እና ከሕገወጦች ጋር እየተባበሩ የምንሻውን ፍትህ ጉድጓድ በመቅበር ለማዳፈን እየሞከሩ ነው የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከቀጣና፣ ወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ያሉ አመራሮች የፈፀሙብንን ግፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ነገሩን ግልፅ ለማድረግ እና ሕዝብ ለፍርድ ይመቸው ዘንድ የተለያዩ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን መሠረት በማድረግ የግለሰቦቹን ቅሬታ ለማጣራት ጥረት አድርጓል::
የወይዘሮ ሚልኮ ቢፍቱ ወራሾች የለውጡ መንግሥት ያስተላለፈውን መመሪያ «አግባብ ባለው አካላት ሳይፈቀድ የተያዙ ቦታዎችን ለማስተካከልና ለመከላከል የወጣ የአፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 16/2006 ይሰኛል:: ይህን መመሪያ ተከተሎ የነሱ መሬት ነበር ከመባል በስተቀር ምንም ጥቅም ሳያገኙለት የቆየውን መሬታቸውን ለመጠቀም የሚስችል ተሰፋ ሰንቀዋል:: ይሁን እንጂ ፈፅሞ ከማያውቋቸው እና በቅርብ አብረዋቸው ሲበሉ ሲጠጡ የነበሩ ሰዎች መሬታቸውን መቀራመት ይጀምራሉ::
በዚህ ጊዜ ነበር 16/09/ 2011 ዓ.ም የወይዘሮ ሚልኮ ቢፍቱ ልጆች ለቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሥራ አስፈፃሚ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጣቸው በጻፉት ማመልከቻ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ሸማቾች እና ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው የወላጅ እናታችን ይዞታ የነበሩ ቦታዎች ያልታወቁ ሰዎች እንደራሳቸው ይዞታ በማድረግ ካርታ ለማውጣት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የወረዳው ጽ/ ቤት ትኩረትሰጥቶ በማየት እልባት እንዲሰጠን ሲሉ አቤት ያሉት:: ከወረቀት ባገኘነው የሰነድ ማረጋገጫ መሠረት የቀጣና አመራሮችም ጉዳዩን በመከታተል በሕጋዊ ወራሾች ይዞታ ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የተሰራውን አጥር ለማፍረስ ሞክረዋል::
ከዚህ በኋላ እንደ ወራሾች ገለፃ በቦታው ላይ ለአራት ጊዜያት ያህል ሕገወጥ ግንባታ ተካሂዶ በወረዳው የደንብ አስከባሪዎች እና በቀጣናው አመራሮች ቢፈርስም ለአምስተኛ ጊዜ አጥር የማጠር ሥራ ሲከናወን ለቀጣና አመራሮች ጉዳዩን መልሰን ብናመለክትም ያጠረውን አካል ማንነት ማወቅ አልቻልንም የሚል የቃል መልስ ከመስጠት ያለፈ መፍትሄ አልሰጡንም::
በመሆኑም የወረዳውን የሥራ አስፈፃሚ የምንጠይቀው ነገር ቢኖር በጉልበት በግለሰቦች የተያዘ ቦታችን እንዲለቀቅ ውሳኔ እንዲያስተላልፍልን ጉዳዩ በወረዳ ደረጃ የማይፈታ ከሆነ ወደ ክፍለ ከተማ ለማለፍ የምንገደድ ስለሆነ ችግራችንን በማየት መፍትሄ እንዲሰጠን ሲሉ ያመለክታሉ::
ውሎ ሲያድር ነገሮች መቀያየር ጀመሩ የሚሉት ሕጋዊ ወራሾች፤ የወረዳ 12 አመራሮች አራት ጊዜ በሕገ ወጥ የተገነባውን ቤት እና አጥር በይዞታችን ላይ የተገነባ እና ሕገ ወጥ አካሄድ በመሆኑ ወራሪዎች የገነቡትን ቤቶች እና አጥር እንዳላስፈረሱ ሁሉ ከጊዜ በኋላ የወረዳ አመራሮች ተገልብጠው ለሕገወጥ ወራሪዎች ሽፋን ለመስጠት በማሰብ ሕጋዊ ወራሽ መሆናችን እየታወቀ ከቤተሰብ እንደወረስን እና የእኛ የይዞታ ቦታ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚል ምስክር እንድናቀርብ በቀን 19/09/ 2011 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የወረዳው አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ዲሮ ደሜ ደበሌ ለቅሬታ አቅራቢውን ቤተሰብ እንደጠየቁ ከወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተላከላቸውን የወረቀት ማስረጃውን በዋቢነት በመጥስ ቅሬታ አቅራቢው ቤተሰብ የደረሰበትን በደል አመላክቷል::
በዚህም አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ ሦስት ምስክሮችን ማቅረብ ቻለ:: ምስክሮችም ለአቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ አዋሳኝ ድንበርተኛ መሆናቸውን የወረዳ እና ቀጣና አመራሮች አስረድተው በ23/09/2001 ዓ.ም መሬቱ የወይዘሮ ሚልኮ ቢፍቱ እንደነበር እና ለልጆቻቸው እንዳወረሱ እና እንዲሁም ይዞታው በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን እና በደቡብ የይዞታው አዋሳኞች ጠቅሰው ገለፁ::
በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኙት መካከል አቶ እሸቱ ግርማ እና አቶ ስንታየሁ የተባሉ የወረዳ 12 አመራሮች እንደሆኑ ከቃለ ጉባኤው መረዳት ይቻላል:: ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የወረዳ 12 አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ዲሮ ደሜ የምስክሮችን ቃል ተሰምቶ ያለውን የምስክሮችን ቃል ሪፖርት እንዲደረግ ባዘዙት መሰረት ያደርጉ ለወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የምስክሮች እማኝነት በቃለ ጉባዔ ተደግፎ ሕጋዊ ወራሽ መሆናቸው እንደደረሳቸው ቅሬታ አቅራቢው ቤተሰብ ይናገራል:: የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የቃለ ጉባኤውን ሰነድ መመልከት ችሏል::
ይህ በእንዲህ እያለ በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለሰነድ አልባ ፕሮጀክት ዴስክ ጽሕፈት ቤት በ30/8/ 2011 ዓ.ም ለወረዳ 12 እና ለሸማቾች አካባቢ የአርሶ አደር ተወካዮች በተፃፈ ደብዳቤ ከሕጋዊ ወራሾች መካከል አንዷ የሆኑትን ወይዘሮ አልማዝ ባዩ የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውን አጣርታችሁ ላኩልን ባለው መሰረት የአርሶ አደር ተወካዮች እና የወረዳ አመራሮች በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለሰነድ አልባ ፕሮጀክት ዴስክ ጽሕፈት ቤት ወይዘሮ አልማዝ ባዩ የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውን ይገልፃሉ::
ውድ አንባቢያን በኋላ ላይ ለግንዛቤ ይረዳችሁ ዘንድ የወይዘሮ ሚልኮ ቢፍቱ ልጅ የሆኑትን ወይዘሮ አልማዝ ባዩ የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውን ሌላኛዋ እህት እና ወንድማቸው ከላይ ለመግለፅ አንደሞከርኩት ሕጋዊ ወራሽ እና በቦታው ነዋሪ መሆናቸውን ካረጋገጡ የአርሶ አደር ተወካዮች መካከል አቶ ካሳሁን ደበሌ፣ አቶ ለማ ውዜ እና አቶ ተሰፋዬ ማሞ ሲሆኑ፤ የወረዳ አመራሮች ደግሞ አቶ እሸቱ ግርማ እና አቶ አድን ሽፈራው መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው:: ምክንያቱም የነዚህን የወረዳ አመራሮች ሕግ እና ሥርዓትን ከማስከበር አንፃር የሄዱበትን አካሄድ ምን እንደሚመስል ከታች መመልከት እንድትችሉ ይረዳል::
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአካባቢውን መሬት በሕገወጥ ወረራ የተለያዩ አካላት መቀራመት ይጀምራሉ:: መሬት ለመቀራመት የመጡት ግለሰቦች የአርሶአደር ልጅ ነን ሲሉ ለቦሌ ክፍለከተማ አስተዳደር ለሰነድ አልባ ፕሮጀክት ዴስክ ጽሕፈት ቤት በ3/10/2011 ከባለ ይዞታዎች መሬት የእኛም አለን ሲሉ ያመለክታሉ::
በዚህ ጊዜ ከላይ የተገለፁት የወረዳ 12 ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ማለትም ወይዘሮ አልማዝ ባዩ፣ ወይዘሮ ቡርሴ ባዩ እና አቶ በቀለ ባዩ የአካባቢው ነዋሪ እና ሕጋዊ ወራሽ መሆናቸውን የመሰከሩት የወረዳ አስተዳደሮች አንደኛው ሰው ተቀይሮ አቶ ስንታየሁ የተባሉ ሰው በወረዳ አስተዳደር አባልነት ተጨምሮ፤ የወረዳው የአርሶ አደር ተወካዮችን ሙሉ በሙሉ በመቀየር እና ሌላ ሰው በመተካት መሬት ለመውረር የመጡት ግለሰቦች ከወይዘሮ ሚልኮ ቢፍቱ ወራሾች መሬት ይገባኛል ሲሉ አመልክተው በወይዘሮ ሚልኩ ቢፍቱ የውርስ ይዞታ ላይ ሌላ ሰው እንዳለ ተደርጎ ወረራው ተጀመረ ሲሉ አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ ያስረዳል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአርሶ አደር ልጅ ያልሆነ በአካባቢው ነዋሪ ቢሆንም እንኳን መሬት የማግኘት መብት የሌለው መሆኑን በመመሪያ መወሰኑን መገንዘብ ያስፈልጋል:: ይሁን እንጂ ይላሉ የአቤቱታ አቅራቢው መሬት ለሚቀራመቱት ግለሰቦች መሬታችንን እንዲቀራመቱ ለማድረግ የወረዳው አመራሮች የአርሶ አደር ልጆች እና ቤተሰቦች አለመሆናቸውን እያወቀ የአርሶ አደር ልጅ እንደሆኑ በማስመሰል መሬታቸውን እንዳስወረረባቸው ይናገራሉ::
ይህን ተከትሎ የወይዘሮ ሚልኮ ወራሽ ቤተሰቦች በ21/10/ 2011 ዓ.ም ለቦሌ ክፍለከተማ አስተዳደር ለመሬት ልማት ማኔጅመንት እና ለወረዳ 12 አስተዳደር ጽ/ቤት በእናታችን ይዞታ ላይ ለሌላ ግለሰብ ካርታ ሊሰራበት እና የመሬት ወረራ እየተካሄደ ነው በማለት ቅሬታ ያቀርባሉ::
ይህን የወይዘሮ ሚልኮ ወራሽ የቤተሰብ ቅሬታ የተመለከተው የቦሌ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ጥላሁን ፍቃዱ የወይዘሮ ሚልኮ ቤተሰቦች ይዞታው የቤተሰቦቻቸው ከሆነ በይዞታቸው መጠቀም ያለባቸው ስለሆነ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በግለሰቦቹ
ይዞታ ላይ እየተደረገ ያለው የመሬት ወረራ እንዲቆም እና ግለሰቦቹ በይዞታቸው እንዲጠቀሙ የሚል ማሳሰቢያ ለወረዳ 12 ደብዳቤ ይልካሉ:: ይህን ደብዳቤ ተከትሎ የወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ዲሮ ደሜ በበኩላቸው በ25/10/2011 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ወረራው ተካሂዶበታል ለተባለው ሸማቾች ተብሎ ለሚጠራው አካባቢ የቀጣና አመራሮች እና ከደንብ ማስከበሮች በጋራ በመሆን እየተካሄደ ያለው የይዞታ ወረራ ወራሪዎችን ከይዞታቸው ላይ አንስታችሁ መሬቱን ለባለይዞታዎች እንድታስረክቡ የሚል ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ::
ነገር ግን ከበላይ አካላት ትዕዛዝ ቢተላለፍም ቅሉ አንድም የቀጣና አመራር እና የደንብ ማስከበር አካል የክፍለ ከተማውን እና ወረዳ አስተዳዳሪውን ትዕዛዝ ሊያስፈፅም የቻለ እና ትዕዛዙን ለማስፈጸም ፈቀደኛ የሆነ አካል አለመኖሩን አቤቱታ አቅራቢዎች ያስረዳሉ::
በ3/11/2011 ዓ.ም የመሬት ወረራውን ሕጋዊ ለማድረግ አንዳንድ ግለሰቦች የቤተሰቦቻቸውን ስም በመቀየር የያዙትን መሬት ሕጋዊ ለማድረግ ምንም ቤት እና አጥር በሌለበት ለቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ሸማቾች ቀጣና አመራሮች የቤት እና የአጥር እድሳት ጥያቄ አቀረቡ::
ይህን ማመልከቻ ተከትሎ አቶ ስንታየሁ ዳንኤል እና አቶ አድን ሺፈራው የተባሉ ግለሰቦች የመሬት ልማት ማኔጅመንት እና መሃንዲሰ ፈቃድ ሳይጠይቁ የአጥር እና ቤት እድሳት እንዲያደርጉ በሕገወጥ መልኩ መሬት እንዲወሩ በወረዳው አመራሮች ተፈቀደ ሲል አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ አመልክቷል::
እነኝህ የወረዳው አመራሮች ከላይ ለግንዛቤ እንዲሆናችሁ ለሕጋዊ ወራሾች ሕጋዊነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የወይዘሮ ሚልኮ ልጅ ከሆኑት አንደኛዋ ልጅ ወይዘሮ አልማዝ ባዩ ለአንገት ማስገቢያ የሆነችውን እና እርጅና የተፈታተናትን ቤታቸውን ለማደስ በ11/11/2011 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ ለወረዳ 12 አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የቤት እድሳት ማድረግ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ::
በዚህ ማመልከቻ መሠረት የቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 12 የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሚገኙት አቶ ደምሰው አበራ የተባሉ የወረዳው መሃንዲስ ወይዘሮ አልማዝ ባዩ ምንም ዓይነት የቅርፅ እና ማቴሪያል ለውጥ ሳያደርጉ ቤት እና አጥራቸውን እንዲያድሱ ፈቃድ ይሰጣሉ::
ይህንን ለሸማቾች የቀጣና አመራሮች እና ደንብ ማስከበር እንዲተባበሯቸው ከወረዳ አመራሮች ትዕዛዝ ተላለፈ:: ይህን ትዕዛዝ ካስተላለፉት የወረዳ አመራሮች መካከል አቶ አድን ሺፈራው እና አቶ ስንታየሁ የተባሉ አመራሮች ይገኙበታል::
እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፉት የወረዳ አመራሮች አንድ ጊዜ ለወራሪዎች ሕጋዊ ፈቃድ እየሰጡ የባለይዞታዎችን መሬት ሲያስወርሩ በሌላ ጊዜ ደግሞ ለሕጋዊ ባለይዞታዎች ምስክር ሲሆኑ እና ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ተባባሪ የማስመሰል ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ::
ነገር ግን ሕጋዊ ወራሽ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ አልማዝ ባዩ ከመሃንዲስ አስፈቅደው ያጠሩትን አጥር አቶ ተሾመ የተባሉ ለጊዜው አቤቱታ አቅራቢው የአባታቸውን ስም የማያውቁት ከየት እንደመጡ የማላውቃቸውን ወጣቶች በማሰባሰብ አጥሬን ነቃቅሎ በመጣል ቤቴን ያለ አጥር አስቀርቶ ለአደጋ አጋልጦኛል ሲሉ ይናገራሉ::
ወይዘሮ አልማዝ ባዩ ይህን የፈረሰባቸውን አጥር አቤቱታ ለማሰማት የወረዳ 12 አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ፍትህ እና መንግሥት ባለበት ሀገር ቦታዬን በመውረር ንብረቴ ላይ ጉዳት ያደረሰብኝ ግለሰብ በሕግ እንዲጠየቅልኝ እና አጥሬን እንዳፈረሰ መልሶ እንዲሰራልኝ ውሳኔ እንዲያስተላልፍኝ ብለው አቤቱታ ያቀርባሉ::
ይህን ቅሬታቸውን በወቅቱ አጥሩ ሲፈርስ በአካባቢያቸው ላለው የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ቢናገሩም ፖሊስ አጥሬን ከጥፋት እንደመከላከል ቆሞ ማየቱን መርጧል ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዋ ይናገራሉ::
የወረዳው አስተዳዳሪ እና አመራሮች የመንግሥት እና የሕዝብ ኃላፊነት እንዳለበት አካል ሕግና ሥርዓትን ከማስጠበቅ ይልቅ ለሕገወጦች ሽፋን በመስጠት ተባባሪ መሆናቸውን ቅሬታ አቅራቢዋ ጠቁመዋል::
የቀጣናው አመራሮች እና የደንብ ማስከበር አካላት አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንዲሉ የደረሰብኝን በደል አንድም የሚመለከተው የመንግሥት አካል አይደለም ችግሬን ተረድቶ ችግሬን ለመፍታት መንቀሳቀስ ይቅር እና ችግሬን በአግባቡ እንኳን መስማትየሚፈለግ አካል የለም ሲሉ ወይዘሮ አልማዝ ባዩ ይናገራሉ::
ተስፋ ያልቆረጡት ወይዘሮ አልማዝ ባዩ ለሦስተኛ ጊዜ አቶ ተሾመ የተባሉ ግለሰብ ያደረሱባቸውን በድል ለወረዳ 12 ሥራ አስፈፃሚ ለሆኑት አቶ ዲሮ ማመልከቻ ያስገባሉ:: ለሦስተኛ ጊዜ አቤቱታ የደረሳቸው የወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ዲሮ ሁኔታው እስኪጣራ ድረስ ምንም ዓይነት ግንባታ በቦታው እንዳይካሄድ ለወረዳው የደንብ ማስከበር በ03/2/2012 ዓ.ም ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ:: ነገር ግን የቀጣና አመራሮች ማንም እንደማይጠይቃቸው ስለተገነዘቡ የተላለፈላቸውን ትዕዛዝ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ማለፋቸውን ወይዘሮ አልማዝ ያስረዳሉ::
የወረቀት ሰነድ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት በጋራም ሆነ በግለሰብ ደረጃ እየተመላለሱ እና በወረዳ እና በቀጣና ለሚገኙ አመራሮች ከዛሬ ነገ ችግራችንን ይፈቱልን ይሆናል በማለት ተስፋ ያልቆረጡት የወይዘሮ ሚልኮ ቤተሰቦች ለደላሎች እና ለወራሪዎች ሲሳይ የሆነውን መሬታቸውን ለማስመለስ በ14/2/2012 ዓ.ም ለወረዳ 12 ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ ያለውን ሕገ ወጥ ወረራ እንዲቆምላቸው በመማጸን አቤት አሉ:: በ14/2/2012 ዓ.ም የተጻፈው አቤቱታም እንደሚከተለው ይተነትናል::
«ከዚህ ቀደም አቤቱታችንን ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ያሳወቅን ቢሆንም ሁነኛ መፍትሄ ሳይሰጡን በመቆየታቸው መንግሥት እና ሕግ ባለበት ሀገር ምንም ዓይነት ካሳ እና ምትክ ያላገኘንበት የይዞታ መሬታችን በጉልበተኞች ተነጥቆ ካርታ እየወጣበት በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ እየተቸበቸበ ይገኛል ::»
እንደ አቤቱታ አቅራቢዎች ገለፃ፤ ይህ ማመልከቻ ለወረዳው የጻፉበት ዋና ምክንያት ከወራሪዎች የቀረውን ሌላኛውን የውርስ መሬት ከወረራ ለማስቆም ነበር:: ነገር ግን ሌላኛው ወረራ ካካሄዱት መካከል አቶ ተካ አለሙ የተባሉት ግለሰብ በወረዳ 12 ውስጥ በሥራ ባልደረባነት እሳቸው እና ልጆቻቸው እየሰሩ በመሆናቸው ስለሁኔታው አቤቱታ ያቀረብንላቸው የወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ዲሮ እና የወረዳው የፍትህ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ አቶ ቆርቾ ለአቤቱታቸው ምንም ዓይነት ምላሽ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ ይናገራል::
በሌላ በኩል ደግሞ የወረቀት ሰነድ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት በ08/04/2012 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ዲሮ ለወይዘሮ ሚልኮ ልጅ ለሆኑት ለአንደኛዋ ለወይዘሮ ቡርሴ ባዩ የሚያቀርቡት የባለይዞታነት አቤቱታ አግባብነት የሌለው ነው የሚል ደብዳቤ ጽፈዋል::
ለዚህም እንደ ምክንያት የተጠቀሰው የወይዘሮ ቡርሴ ባዩ በኃይለሥላሴ ዘመን ባለእርስት የነበሩ እና ደርግ ባወጣው የሰፈራ አዋጁ መሰረት በወቅቱ ለአቶ ተሰማ ገመቹ በሰፈራ የተሰጠ ይዞታ ስለሆነ እኛም የእርስት ይዞታ መመለስ የማንችል መሆኑን እናረጋግጣለን የሚል ነው:: ‹‹ይህ የወረዳው አመራሮች ሸፍጥ በእውነት መሬቱ ለተወረሰበት ሰው ቅስም ሰባሪ እና መንግሥት ባለበት ሀገር ይደረጋል ተብሎ የማይታብ ነው›› ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ያስረዳሉ::
ውድ አንባቢያን እዚህ ላይ አቶ ተሰማ ገመቹ ማን ናቸው የሚለውን ለመረዳት ይቻል ዘንድ አንድ የወረቀት ሰነድ ላይ የሰፈረ እና በምርመራ ያገኘነውን እናካፍላችሁ:: ይህ ሰነድ በ2010 ዓ.ም አቶ ዲሮ፣ አቶ እሸቱ እና አቶ አድን የተባሉ የወረዳው አመራሮች በተገኙበት የተያዘ ቃለ ጉባኤ ነው።
በተጠቀሰው ዓመት አቶ ገመቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ሸማቾች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደርግ ዘመነ መንግሥት በሰፈራ ይመጣሉ:: ነገር ግን በአህአዴግ መንግሥት ቦታው ለልማት ተፈልጓል ተብሎ ምትክ ቦታ ተሰጥቷቸው ሸማቾች ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ይነሳሉ:: የለውጡ መንግሥት መምጣቱን ተከትሎ የተሰጣቸውን ምትክ ቦታ በመሸጥ ደርግ በሰፈራ ወደ ሰጣቸው ቦታ ይመለሳሉ:: ይህን ያየው ከላይ የተጠቀሱት የወረዳ አመራሮች አቶ ገመቹ መኩሪያ ያደረጉት ነገር ሕገወጥ መሆኑን ጠቁመው ምትክ ከወሰዱበት ቦታ በአስቸኳይ እንዲነሱ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል::
ይሁን እንጂ በውል ባልታወቀ ምክንያት አቶ ገመቹ መኩሪያ ምትክ የወሰዱበትን ቦታ ተገን በማድረግ ከሕጋዊ ባለይዞታዎች መሬት በመውሰድ እና ካርታ በማውጣት ይሸጣሉ። ይለውጣሉ:: ነገር ግን ከባለይዞታዎች ውጪ ማንም ምንም ያላቸው አካል አልተገኘም::
እዚህ ላይ ከሁሉም በላይ የሚገርመው ነገር የመሬቱን ወረራ ሕጋዊ ለማድረግ እንዲመች አቶ ተሰማ ገመቹ ሸማቾች አካባቢ ምትክ የወሰደበትን መሬት መያዝ እንደማይችል በ2010 ዓ.ም ወረዳው በፃፈው ደብዳቤ የተሳተፉ የወረዳ አመራሮች የፃፉትን እረስተው መሬቱ ለአቶ ገመቹ መኩሪያ ይገባል ማለታቸው የወረዳ አመራሮችን የሕግ ተጠያቂ ያደርጋል ሲል አቤቱታ አቅራቢው ቤተሰብ ይናገራል::
የወረቀት ሰነዶች እንደሚያመላክቱት መሬታቸውን ሲወረሩ ምንም ምላሽ ያላገኙት ወይዘሮ አልማዝ ባዩ አሁንም በወረዳው አመራሮች ተስፋ ባለመቁረጥ በ25/5/ 2012 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ እየተካሄደ ያለውን ወረራ እንዲያስቆሙላቸው አቤት አሉ:: የአሁኑ የቅሬታ ማመልከቻ ከዚህ በፊት ካሉት ሁሉ የሚለይ ነው::
ምክንያቱም ወራሪዎች ሁሉንም የይዞታ መሬቶች ወረው ሲጨርሱ የወይዘሮ አልማዝ ባዩን መኖሪያቤት ያረፈበትን ቦታ በመተው ያጠሩትን አጥር በማፍረስ መውጫ መግቢያ እንኳን ለሴትዮዋ ሳይተዉ ሙሉ በሙሉ ወራሪዎች የራሳቸውን አጥር ግጥም አድርገው ያጥሩታል:: ሦስት የቆርቆሮ ቤቶችም ይሰሩበታል:: ይህንን አቤቱታ የሰማው የወረዳ 12 አስተዳር ለቀጣና አመራሮች በአስቸኳይ በይዞታቸው
ላይ ከታጠረ እንድታነሱ እና በሪፖርት እንድታሳውቁኝ የሚል የተለመደ የፌዝ ትዕዛዝ ለቀጣና አመራሮች ይፅፍላቸዋል ሲሉ ወይዘሮ አልማዝ ባዩ ያስረዳሉ::
በራስ ንብረት የበይ ተመልካች መሆን የሚፈጥረው ቁጭት ተስፋ ያላስቆረጣቸው የወራሽ ቤተሰቦች በ09/ 07/ 2012 ዓ.ም ለወረዳ 12 ሥራ አስፈፃሚ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ያስገባሉ:: «እኛ የወይዘሮ ቢፍቱ ሕጋዊ ወራሾች የወላጅ እናታችን ይዞታ የሆነው የአርሶ አደር ቦታ በተለያዩ ግለሰቦች መወረሩን አስመልክቶ መንግሥት ከወራሪዎች እንዲያስጥለን ይዞታችንንም በሕገወጦች እንደ ሸቀጥ ከመቸብቸብ እንዲታደግልን እና የይዞታችን ተጠቃሚ እንድንሆን ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ በመሄድ አቤቱታ የአቀረብን ቢሆንም ሕገወጦች ወረው የያዙትን ቦታ እንዲለቁ፤ ወረራው እንዲቆም በተለያዩ ጊዜ የጽሑፍ መመሪያ ቢሰጥም ለአቤቱታችን ትክክለኛ እና ቁርጥ ያለ ምላሽ ከአንድም የወረዳም ሆነ የክፍለ ከተማ አካል ሳይሰጥ ቆይቷል::
ከለውጡ መንግሥት በፊት ባለው መንግሥት የተጎዱ የአርሶ አደር ልጆች በይዞታቸው እንዲጠቀሙ የለውጡ መንግሥት ቢፈቅድም እኛ ብቻ ከሌሎች ተለይተን መሬታችን በጉልበተኞች ተወስዶብን እንገኛለን:: ስለዚህ አሁንም የወረዳው ሥራ አስፈፃሚ የምንጠይቀው ነገር ቢኖር፡-አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት እጅጉን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር በ15/7/2012 ዓ.ም የአርሶአደር ተወካዮች እና የወረዳ ባለሙያዎች በቃለ ጉባኤ ወሰኑ::
አዲስ የተተኩት የገበሬ ተወካዮች ሕጋዊ ወራሽ ተብለው ከቀበሌ እስከ ክፍለከተማ የሚታወቁትን ሕጋዊ ወራሾችን እስከ መፈጠራቸውም አናውቅም ሲሉ ሽምጥጥ አድርገው ካዱ:: ይህን ያዩት ሕጋዊ ወራሾች በመሬቱ ከኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ግብር እየከፈሉ የኖሩበት የይዞታ ቦታ ላይ እስከመፈጠራቸው አናውቃቸውም መባሉ የመረረ ኀዘን እንደፈጠረባቸው አመላክተዋል::
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ይህ ችግር ተፈጠረበት ወደተባለው ቦታ በማምራት የወረዳ አስተዳደሮችን፣ የቀጣና አመራሮችን፣ የቀጣና ደንብ ማስከበር እና የአርሶ አደር ተወካዮች ስለጉዳዩ ለመጠየቅ በአካል የተገኘን ቢሆንም የወረዳ አመራሮች ሁሉም ከወረዳው ከሥራ እንደለቀቁ እና ግማሾች ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ሥራ ውጪ እንደሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ እንደተዛወሩ መረዳት ችለናል::
ይሁን እንጂ አሁን ላይ በወረዳ 12 ምክትል ሥራ አስፈፃሚ የሆኑትን አቶ ዮሴፍ ወንድሙ አግኝተን ስናነጋገር ሰሞኑን በአካባቢዊ ካለው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የቀጣናውን የፀጥታ አካላት እና አርሶ አደር ተወካዮች ማግኘት እንደማልችል እና በሚቀጥሉት ቀናቶች እንደሚያገኙን ነግረውናል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ሥራ ላይ ለማይገኙት ለአቶ አድን እና አቶ እሸቱ ለተባሉ ግለሰቦች ደውለን እነሱ የወረዳ አመራር በነበሩበት ጊዜ ተፈጠረ ለተባለው ችግር መልስ እንዲሰጡን በስልክ አናግረናቸው ነበር:: ይህን ተከትሎ አቶ እሸቱ የተባሉት የቀድሞ ወረዳ 12 አመራር ስለጉዳዩ ስናነሳላቸው ስልካቸውን ዘጉ:: ይሁን እና ሌላው የቀድሞው የወረዳ አመራር የሆኑትን አቶ አድን ደውልን ባነጋገርን ጊዜ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል::
«እኛ በወቅቱ መሬቱን ለተለያዩ ግለሰቦች ስንሰጥ የተለያዩ ነገሮችን ከግምት ውስጥ አስገብተን ነው:: አሁን ቅሬታ አቅራቢዎች የእኛ ነው የሚሉት መሬት የእነሱ አይደለም:: መሬቱ በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የቤተሰቦቻቸው ይዞታ የነበረ ነው:: ይህም የተወሰነው መሬት በደርግ የተወሰደ ሲሆን ቀሪውና የተወሰነው ደግሞ በኢህአዴግ ተወስዶባቸዋል::
ነገር ግን አሁን በለውጡ መንግሥት የአርሶ አደር ቤተሰቦች 500 ካሬ ሜትር ይሰጣቸው በተባለው መመሪያ መሰረት ለእነሱም 500 ካሬ ሜትር ለእያንዳንዳቸው ሰጥተናቸዋል::» ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ‹‹የማናውቃቸው ሰዎች መጥተው የአርሶ አደር ልጅ በሚል ሰበብ ለእያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር ሲሰጥ እኛ ግን የበይ ተመልካች ሆነናል:: መሬትም የለንም ›› ይላሉ ስለዚህ ምን ይላሉ የሚል ጥያቄ ለአቶ አድን ሲነሳ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም በማለት ስልካቸውን ዘግተዋል::
ውድ አባቢያን በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃዎችን መስጠት የሚፈልጉ አካላት ካሉ በቀጣይ እትማችን ይዘን የምንቀርብ መሆኑን እናሳውቃለን::
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013