አዲስ አበባ፡- 6ኛው ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ኢግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ እንደሚጀመር የፌዴራል ህብረት ስራ ማህበር የግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋዓለም እንየው አስታወቁ።
ዳይሬክተሯ፣ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ የሚካሄደው የኤግዚቢሽኑና የባዛሩ ዋና ዓላማ በህብረት ስራ ማህበራት እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትን የሚያሳይና እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን የሚያመላክት ነው፡፡ እንዲሁም እንደ አገር የህብረት ስራ ማህበራትን ችግር ከመፍታትና የአገር ኢኮኖሚን ከማሳደግ አንጻር በተለይም ግብርናውን ወደ ኢንዱስትሪ ከማሸጋገር አኳያና የስራ እድልን በመፍጠር ያላቸውን ሚና የሚያመላክትና ድጋፍ ቢደረግላቸው ደግሞ የትመድረስ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው።
‹‹ከዚህ ቀደም በተካሄዱ አምስት ኤግዚቢሽንና ባዛሮች አማካይነት የገበያ ሰንሰለቱ አጥሯል፤ ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር መስራት የሚፈልጉ ተቋማት ተገኝተዋል፡፡ የልማት አጋሮች ስራቸውን በማድነቅ ለመደገፍ መነቃቃት አሳይተዋል›› ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በጠቅላላው ህብረት ስራ ማህበራት ፍትሀዊ የገበያ ትስስርን በመፍጠር በኩል ያላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።
ዛሬ በሚቀርበው ኤግቢሽንና ባዛር ላይም ሲምፖዚየም የሚኖር ሲሆን፤ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጽሁፎች ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት በሙሉ እንደሚቀርቡና ውይይቶችም እንደሚደረግባቸው ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይም የህብረት ስራ ማህበራት የሚያቀርቧቸውን ምርቶችና የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በተግባር የሚያሳዩበት ሲሆን፤ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት ከአምራቹ በቀጥታ የሚያገኝበትና የሚገበያይበት ሁኔታም ተመቻችቷል፤ በሌላ በኩልም ወደ ኤግዚቢሽንና ባዛር የሚመጡ አምራቾች የአገራቸው መልክአ ምድር ያፈራውን ምርት ይዘው ከመምጣት ባሻገር ባህላዊ አለባበሳቸውን፣ አመጋገባቸውንና ቡና አፈላላቸውን ይዘው የሚመጡበት በመሆኑ ትልቅ የባህል ልውውጥ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ በየዓመቱ መሰል ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ የዘንድሮውም ለ6ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2011
እፀገነት አክሊሉ