ውብሸት ሰንደቁ
አቶ ጌትነት አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዋድላ ወረዳ ከአባታቸው ዓለሙ ፈንቴ እና ከእናታቸው መልካም ገላው ከተወለዱ አራት ልጆች ውስጥ የመጀመሪያው በመሆን በ1969 ዓ.ም ይህችን ምድር የተቀላቀሉ ሰው ናቸው።
አሁን ወይዘሮ መሥከረም አማረን አግብተው ወልደውና ከብደው አዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ነው የሚኖሩት። በአሁኑ ጊዜ አቶ ጌትነት የሦስት ልጆች አባት ናቸው።
አቶ ጌትነት ከየት ተነስተው የት እንደደረሱ አንድ በቅርብ የሚያውቃቸው ሰው ሹክ አለኝና ነው በስኬት ዓምድ ላቀርባቸው ወስኜ ሃሎ ያልኳቸው። በሥልክ ከተነጋገርንበት የቀጠሮ ሰዓት ሽራፊ ሰከንድ ሳይቆርሱ ቦታው ከተፍ ሲሉ አስደምመውኝ የነበረው ቅንነታቸውና ወንድማዊ አቀራረባቸው ደግነትን ገልጦ ከሚያስነብብ ገፅታቸው ጋር ሲታዩ ትንሽ ጥሪት ሲቋጥር ደረቱን የሚነፋን ሰው ያስንቃሉ።
አቶ ጌትነት በትምህርት ደረጃ ብዙም አልገፉም፤ ባለፉት ውጣ ውረድ የበዛው ሕይወት ውስጥ መማር የቻሉት እስከ ሥምንተኛ ከፍል ነው። የትምህርት ጥማቴን ልጆቼን በማስተማር የምበቀለው ይመስለኛል ሲሉ ይናገራሉ። ለአቅመ አዳም ሲደርሱ በጉርምስና ዘመን የማደግ ፍላጎት ጨመረና ወደ አዲስ አበባ መጡ።
ሆኖም አዲስ አበባ ጥንትም ይሁን ዛሬ ኑሮን ከዜሮ ለሚጀምር ሰው ምቹ መደላድል ይዛ የምትጠብቅ ከተማ አይደለችም። እናም ለመለወጥ የሚደረግ ትግል የተጀመረው በቀን ሠራተኝነት ሕይወት ነው። ከዚያም ወፍጮ ቤት ተቀጥሮ እህል ማበጠር ሥራ ላይ ተሠማርተው ሠርተዋል።
በዚህ ሰዓት ደመወዝ ብሎ ነገር አይታሰብም። በሠራኽው ልክ ታገኛለህ ተብዬ ተቀጠርኩ ይላሉ አቶ ጌትነት። ሴቶች ወፍጮ ቤት መጥተው የመረጡትን እህል ማበጠር፤ አበጥሮ ማስፈጨት የየዕለት ተግባራት ናቸው። ከዚያም የሚስፈጩት ሰዎች በጥቂት ብሮች ክፍያ ይከፍላሉ። ያች ናት ለዕለት ጉርስ የምትበቃዋ ገንዘብ።
ከዚያም ወደ መሳለሚያ እህል በረንዳ በማምራት በወዛደርነት ሥራ ተሠማራ። ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረግ መፍጨርጨር ውስጥ ከዚያች ገቢ ላይ እንኳን ቁጠባ ማድረግን አልረሳም። በወዛደርነት ሥራ ጥቂት ጊዚያትን አሳልፎ ትንሽ ብሮች በእጁ ሲያድሩለት በዚሁ አካባቢ በንግድ ሥራ ተሠማራ። ይህ የሆነው በ1994 ዓ.ም ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አቶ ጌትነት የራሱን የንግድ ሥራ ጀመረ።
የጀመረው የእህል ንግድ ሥራ ለብቻ የሚቻል አልነበረምና ከጓደኛው ጋር ያለቻቸውን ጥሪት በማዋጣት ነው ንግዱን የጀመሩት። እንደ ዛሬው የብር አቅም አልተልፈሰፈሱምና ንግድ ለመጀመር ያዋጡት ገንዘብ 2500 ብር ከእያንዳንዳቸው ነበር። ይህች ብር በእርግጥም በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ በብዙ መጠን ማደግ ችላ ነበር። ቀጥላ በተለያዩ ምክንያቶች መሽቆልቀቆል ጀመረችና ኪሣራ ውስጥ ገቡ።
ቆይተው ከጓደኛው ጋር በማንኛውም ንግድ ሥራ ውስጥ እንደሚፈጠረው አለመግባባት ተፈጠረና በሰላም ተለያይተው ወደየራሳቸው የሕይወት መሥመር አመሩ። ብሩም ጠፍቶ ከጓደኛ ጋርም መስማማት ሳይቻል ሲቀር እንደገና ወደ ሌላ የሕይወት መንገድ ሙከራ መግትባት ግድ ነበርና አቶ ጌትነት ወደ ድለላው ዓለም ዘው ብለው ገቡ።
ከዚህ ቀደም ከድለላ ሙያ ጋር የተያያዘ ልምድ ባይኖራቸውም የእህሉን ንግድና የስንዴውን ገበያ አጣርተው ያውቁት ነበርና በዚሁ በስንዴ ንግድ በተለይም የስንዴ ምርትን እንደ ግብዓት ለሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ከተለያዩ ቦታዎች ስንዴ አቅርቦቶችን በማገናኘት የድለላ ሕይወት አሃዱ ተባለ።
ከእህል ነጋዴዎች የስንዴ ምርትን ለፋብሪካዎች በማቅረብ በሚገኙ ሽርፍራፊ ሳንቲሞች ሕይወት እንደገና ከዜሮ ተጀመረች። ይህም ቆይቶ ተቀይሯል እናም አቶ ጌትነት እንዳቅሜ ያልሞከርኩት ነገር የለም ይላሉ።
በጉልበት የመሥራትና ጠንክሮ የማደር አባዜ ቀለል እያለ ሲመጣ አቶ ጌትነት በ1996 ዓ.ም ወደ ትዳር ዓለም ተቀላቀሉ። ባለቤቴ በሕይወቴ እጅግ ታላቅ ቦታ ያላት የሕይወቴ መሪ ነች። ሁሌም ከጎኔ ሆና አይዞህ በማለትና በማበረታታት ለስኬቴ ወደፊት እንድራመድ አበርችዬ ናት። በፀሎትና የመፍትሄ ሃሳቦችን በማመንጨት ከጎኔ የማትለይ ሴት ናት ይላሉ ስለ ሕይወት አጋራቸው ሲናገሩ።
ሰውዬው አልጨበጥ ባላቸው የስኬት ጉዞ ውስጥ የኮንስትራክሽን ሥራ ውስጥ ተሳተፈውም አልሆን ሲል ጥለው ወጥተዋል። በተለይ በዚህ ዘርፍ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን በማቅረብ ለሁለት ሦስት ዓመት ሠርተው አይተውታል። ይህ የጠበቁትን ያህል ውጤት አላመጣ ሲል አንድ ሁለት መኪኖችን በመግዛት እስከ ጅቡቲ ድረስ የሚዘልቅ ደረቅ ጭነት አገልግሎት ላይ በመሰማራት ወደ ትራንስፖርት ዘረፉ ተቀላቀሉ።
ከዚህ ሁሉ ሕይወት ውጣ ውረድ በራሴ ጥረት ነው ልወጣ የቻልኩት። ይህንን ረድቶኛል ብዬ የምጠቅሰው ሰው የለኝም። ፈጣሪዬን አምን ነበርና ከእሱ በስተቀር ማንም ከጎኔ አልነበረም ይላሉ አቶ ጌትነት።
ይህን የሕይወት ልምድ ከማካበት ቀጥሎ ነገሮች እየገቧቸው በመጡ ጊዜ ሥራዎቻውን ከባንክ በሚገኝ ብድር ማገዝ ጀመሩ። በቅርቡም የተወለዱበት አካባቢ ላይ የኢንቨስትምንት ዕድል አለ ሲባል በመስማታቸው ሳያመነቱ እትብታቸው ወደተቀበረበት ምድር በማምራት ኢንቨስት የማድረግ ሃሳባቸውን በየደረጃው ለሚገኙ ባለሥልጣናት አስረዱ።
በዚህ ዕቅዳቸው መሠረትም ዋናው ዓላማቸው አካባቢያቸው ላይ በገፍ ይመረት የነበረውን የስንዴ ምርት ከአምራቹ በመረከብ እርሳቸው ተጠቅመው ሌሎቹም እንዲጠቀሙ ያለመ ነበር። በአካባቢው የነበሩ አመራሮችም ሆነ የዞንና የክልል አመራሮች ጥያቄውን ምንም ሳያቅማሙ ተቀብለው አፀደቁት።
ከልማት ባንክ ከተገኘ ብድርና ከአቶ ጌትነት ፋብሪካውን ለማቋቋም ከአጠራቀሙት ገንዘብ ጋር ይህ 17 ሚሊየን ብር ያስመዘገበ ካፒታል የፈሰሰበት ፋብሪካም ዕውን ሊሆን በቃ። 2009 ዓ.ም ላይ የኢንቨስትመንት መሬቱን ተቀብለው፤ 2010 ዓ.ም ላይ የግንባታ ሂደቱ ተጠናቆ 2011 ዓ.ም ላይ ምርት ተጀመረ።
በእርግጥ የፊኖ ዱቄት ዘርፍ ብዙ ውድድር ያለበት ዘርፍ ነው። አዲስ ምርት በመሆኑ ለትውውቅ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው። አሁን አሁን ግን እየታወቀና ተወዳዳሪ ምርት እያመረትን በመሆኑ ጥሩ ደረጃ ላይ ነን ይላሉ።
ይህ ፋብሪካ አካባቢው ስንዴ አምራች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የስንዴ ምርትን ከአርሶ አደሮች በመቀበል ፊኖ ዱቄት በማምረት ለገበያ ያቀርባል። ይህ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። አንድም የአካባቢው ሰው ከዚያው የፊኖ ምርት በቅርቡ ያገኛል።
በሌላ በኩል አምራቾች ሳይንከራተቱ የስንዴ ምርታቸውን ለፋብሪካው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ ይረዳቸዋል። በእርግጥ ከአምራች ገበሬዎች ውጪም መንግሥት ስንዴ ያቀርብ ነበረ። በወርም እከስከ ሁለት ሺህ ኩንታል ስንዴ ከመንግሥት ያገኙ ነበር። በመንግሥት በኩል ስንዴ መቅረብ በማቆሙ እንደማንኛውም ስንዴን እንደግብዓት እንደሚጠቀም ፋብሪካ የስንዴ እጥረት ተፈጥሮባቸዋል።
ፋብሪካው ጋሸና ዱቄት ፋብሪካ ይባላል። በሥሩ በቋሚነትና በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚሠሩ ከ35 በላይ ሠራተኞች አሉ። ዘንድሮ ማንኛውም የዱቄት ፋብሪካ ላይ የግብዓት እጥረት አለ። ሰውም በዚህ ዙሪያ እሮሮ እያሰማ ይገኛል። ፍላጎትና አቅርቦት ስላልተመጣጠነ የስንዴ አቅርቦት አለመኖሩ ሥራቸው ላይ ጫና አምጥቷል።
አቶ ጌትነት ከዱቄት ፋብሪካው ጋር በተያያዘ የስንዴ አምራች ገበሬዎቹ ምርት ሁልጊዜ በአቅርቦት ሊያረካ ስለማይችልና ጥራቱንም ማሳደግ ስለሚያሥፈልግ እዚያው ፋብሪካው አካባቢ የእርሻ ቦታ በኢንቨስትመንት በመረከብ ስንዴ የማምረት ሃሳብ አላቸው።
ባለሃብቱ ስኬትን አጣጥሚያለሁ ብለው አርፈው የተቀመጡ ሰው አይደሉም፤ እጃቸው ላይ በርካታ መሥራት የሚያስቧቸው ዕቅዶች አሏቸው። በወጪና ገቢ ንግድ ዘርፍ ለመሳተፍ እንደሚፈልጉም አጫውተውኛል። ሌሎች በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ማህበረሰቡን ጠቅሜ መጠቀም እፈልጋለሁ ይላሉ።
ለመሆኑ የመዝናኛ ጊዜዎትን የት ያሳልፋሉ ስል ላቀረብኩላቸው ጥያቄ አቶ ጌትነት እንዲህ ብለውኛል ሻይ ቡና እያልኩኝ ከጓደኞቼ ጋር ለመዝናናት የምመርጠው ፀጥ ያለ አካባቢ የሚገኙ ካፌዎችን ነው። ከልጆቼና ከባለቤቴ ጋር በምንዝናናበት ጊዜም እንደዚሁ ፀጥ ያለ ቦታ መርጠንና ሰላማዊ የሆን ከባቢያዊ ሁኔታ ባለባቸው አካባቢዎች ነው።
ከዚህ በተረፈ ቤተክርስቲያን እሄዳለሁ። የሆነ ነግሮች በሚወሳሰቡ ጊዜና ልቤን የሆነ ነገር በሚሰማኝ ጊዜ ፀጥ ያለ ሁኔታ ውስጥ ተቀምጨ ራሴን ማረጋጋትና ልቤን ከፈጣሪ ጋር ለማገናኘት እሞክራለሁ። ይህ ሁኔታ ደሥተኛ ኑሮ እንደመራ አስችሎኛል።
አቶ ጌትነት እንዲህ ይላሉ፡- በሕይወት ውስጥ አሳዛኝና አስደሳች ነገሮች ይፈራረቃሉ። ሁሉን በልኩ ማድረግ ግን ከሰው ልጆች ይጠበቃል። ደስታን ብቻ ሲያጣጥም ኑሮ ያለፈ የለም፤ መከራውን ብቻ ቀምሶ ያለፈም አይኖርም። ሁሉም በጊዜው ይመጣና ይሄዳል። በዚህ ረገድ እኔ ያሳለፍኳቸውን አስከፊና አሳዛኝ፤ አስደሳችና ተስፋ ሰጪ ነገሮች በቅጡ እየመራሁ ባልመጣ አሁን የደረስኩበት ደረጃ አልደርስም ነበር።
ለሥራዬ ታማኝ ነኝ፤ በገንዘብ ደረጃም እንደዚሁ ታማኝ ነኝ። የሰው አደራ የማይበላ፤ የሰው ገንዘብ የማይነካ ሰው ወድቆ ይቀራል የሚል ዕምነት የለኝም። ከሰዎች ጋር አወንታዊ የሆንና ዘላቂነት ያለው ወዳጅነት ነው የምመሠረተው።
ሰዎችን ላለማስከፋት ጥረት አደርጋለሁ። ይህን የማደርገው ሰዎችን በማስደሰት ፈጣሪን ማስደሰት ይቻላል ብዬ ስለማምን ነው። እነዚህ ነገሮች በሕይወቴ ውስጥ ለተንፀባረቀው ስኬት ትልቅ መሰረት ናቸው ብዬ አምናለሁ ይላሉ።
ተቻችሎና አብሮ የመኖር ፀጋ አለኝ ሲሉም ይናገራሉ። ከአውሬ ጋር መላመድ የሚችሉ የሚባሉ ሰዎች ውስጥ የምመደብ ሰው ነኝ። ብዙ ጓደኞች አሉኝ። ጥሩ ቀረቤታም አለን። ነገር ግን ጌትነት ከ 11 ሰዓት በኋላ ጓደኛ የለውም። ከዚህ በኋላ ያለው ሰዓት ለቤተሰቦቼ የምሰጠው ጊዜ ነው። ጌትነት አምሽቶ ተገኘ ከተባልክ ትልቁ ሰዓትም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ነው የሚሆነው።
ልጆቼና ለባለቤቴ ያለኝን ፍቅርና ክብር በገንዘብ መግለፅ አልችልም፤ ከአለኝ ጊዜ ላይ ለእንሱ በማጋራት እንጂ። ከእኔ ሰዎች እንዲማሩ የምፈልገው አንደኛው በሰዎች ዘንድ ታማኝ መሆንን ነው።
መልካም መሆንና ለሰዎች ማሰብም ከጥሩ ደረጃ የሚያደርሱ መሰላሎች ናቸው። እነዚህን ስታደርግ ስኬታማ ትሆናለህ ሲሉ መልዕክታቸውን አጋርተውናል። እኛም ቀሪ ዘመናቸው የተባረከ፤ ስራቸው ለሀገርና ለወገን የሚተርፍ እንዲሆን ተመኘን።
አዲስ ዘመን የካቲት 09/2013