አብነት አባቡ (3ኛ ዓመት የካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ ድህረ ምረቃ ተማሪ)
የንግግር ሕክምና ምንድን ነው? ለምን ይጠቅማል? የንግግር ሕክምና እንደሚያስፈልገን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች በተከታታይ ምላሽ ሰጥተናል። እነዚህን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ መልሼ ከሆነ በቀጣይነት የምናነሳው ማስረጃ፦ የንግግር ሕክምና ውጤታማ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ የሚል ይሆናል። የዛሬው ትኩረታችንም ለዚህ ጥያቄ አጭር እና ግልጽ ምላሽ መስጠት ነው።
ከላይ ያነሳነውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ብንችልም ተመራጩ ራንዶማይዝድ ኮንትሮልድ ቴስት (Randomized Controlled Test) የምንለው ነው። ይህ ዘዴ ተመሳሳይ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው እና ተመሳሳይ የንግግር ሕክምና በሚወስዱ ግለስቦች ላይ የሕክምናውን ውጤታማነት ለመለካት የሚካሄድ ጥናት ነው።
ይህ ጥናት በሁለት የተከፈሉ ቡድኖች ላይ የሚካሄድ ሲሆን ለአንደኛው ቡድን አንድ የንግግር ሕክምናን ስልት የሚከተል ሕክምና ሲሰጠው ለሌላኛው ቡድን ደግሞ ያልተጣራ ሕክምና ይሰጠዋል። አሰገራሚው ነገር ይህ ጥናት ሲካሄድ ምዘናውን የሚያካሂዱትም ሆኑ የሁለቱ ቡድኖች አባል የሆኑ ተጠኚዎቹን ስለ ጥናቱ ምንም መረጃ አይኖራቸውም። በዚህ የጥናት ስልት መሰረት (ከነደካማ ጎኑ) የንግግር ሕክምና ከአማካይ በላይ ውጤት ካገኘ ውጤታማ ይባላል።
ለዚህ ጥናት መወለድ ምክንያት የሆነው የሳይኮአናሊሲስ የንግግር ሕክምና ስልት ነው። ሳይኮአናሊሲስ ባለቤት የሥነ ልቦና አባት ተብሎ የሚጠራው ሲግመንድ ፍሮይድ ነበር። ይሄ የንግግር ሕክምና ስልት አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ያለምንም ተቀናቃኝ በተጽዕኖ ፈጣሪነት የተጓዘ ቢሆንም ሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ግን ብርቱ ሳይንሳዊ ጥያቄዎች ተነስተውበታል።
ለዚህ ዋነኛ መንስዔ የሆነው የተለያዩ የንግግር ሕክምና ስልቶች መፈልፈል እና የሳይኮሎጂ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው የአዕምሮ ችግሮችን ዝርዝር የያዘው መጽሐፍ መውጣት ነው። በዚህ ፉክክር ውስጥም ጠንክረው ለመውጣት የፈለጉ ቡድኖች ሳይንሳዊ መሰረታቸውን ለማጠንክር ፉክክር ገጠሙ።
እንደ ሳይኮሎጂ ቱዴይ ከሆነ በዚህ ወቅት የተካሄዱ በርካታ ጥናቶች የንግግር ሕክምና ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። በመጀመሪያ ደረጃ የንግግር ሕክምና ከሚከተለው ስልት አንጻር በተደረገው ጥናት የጎላ መበላለጥ አልታየባቸውም። በሁለተኛ ደረጃ ከተጠቃሚዎች አንጻር የንግግር ሕክምና በእድሜያቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ልጆች ጀምሮ እስከ አዋቂዎች ድረስ ወጤታማነታቸው በግልጽ ታይቷል።
በሶስተኛ ደረጃ ከሚወስዱት የጊዜ ርዝመት አንጻርም ደግሞ አጭር የሕክምና ጊዜ ከሚወስዱ ሕክምናዎች ይልቅ ረጅም የሕክምና ጊዜ የሚወስዱት ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል። በአራተኛ ደረጃ ከሕመማቸው ጽናት አንጻር የተደረገው ጥናት የንግግር ሕክምና ውጤታማ እንደሆነ ቢመሰክርም ውጤታማነቱ ግን በተለምዶ <የአዕምሮ ችግር> ካለባቸው ይልቅ <ራሳቸውን ለማሳደግ> በሚፈልጉት ላይ ወጤታማነቱ ከፍ ብሎ ታይቷል።
ይሄ ማለት ግን ይህንን ጥናት በተመለከተ የሚካሄደው ሙግት ቆሟል ማለት አይደለም። ከላይ የጠቀስነውን የጥናት ስልት ተከትለው ውጤታማነታቸው በተደጋጋሚ እየተረጋገጠላቸው ያሉ ስልቶች በቁጥር አነስተኛ ጥናት የተደረገባቸውን ስልቶች ሲሞግቱ ይታያል።
ለምሳሌ በአስተሳስብ እና በባህርይ ላይ የሚያተኩር የንግግር ሕክምና (በሀገራችን የተለመደ) በርካታ ጥናት የተሰራበት እና ውጤታማነቱ በተደጋጋሚ የተረጋገጠ ነው። ይህንን ተቃርነው የሚሞግቱ ቡድኖች ደግሞ ይሄ ሕክምና ውጤታማነቱ ሊረጋገጥ የቻለው ብዙ ጥናት ስለተደረገበት እንጂ ከሌሎቹ የበለጠ ወጤታማነት ኖሮት አይደለም። ሄልዝ ዶት ኮምም ከዚህ ጋር በመስማማት ዋናው ስልቱ ሳይሆን የባለሙያው ተሰጥኦ ነው ይላል።
ይህንንም ስር የሰደደ ሙግት፣ የአዳዲስና ውጤታማ ሕክምና ስልቶች እንደ አሸን መፈልፈል ያሳሰባቸው ተቋማት መዘርዝር አዘጋጅተዋል። የአሜሪካን ሳይኮሎጂካል አሶስዬሽን በድረ ገጹ ከሁለት በላይ ሳይንሳዊ ጥናት የተደረገባቸው፣ የስልቱን አጠቃቀም በግልጽ የሚያስቀምጥ መመሪያ ያላቸውን የንግግር ሕክምና ስልቶች ዘርዝሯል። የአሜሪካ ጤናና ሰብአዊ አገልግሎት ተቋምም የንግግር ሕክምናውን ስልት ውጤታማነት ከ 0-4 ድረስ በቁጥር በመግለጥ መዘርዝር አዘጋጅቷል።
ታዋቂው የንግግር ሕክምና ባለሙያ እና “The Great Psychotherapy Debate: The Evidence for What Makes Psychotherapy Work” ብሩስ ዋምፖልድ፣ የንግግር ሕክምና ውጤታማነት በተመለከተ ከበርካታ ዓመታት ልምዳቸው በመነሳት እንዲህ ሲሉ መልሰዋል፦ “የንግግር ሕክምና አሰገራሚ በሆነ ደረጃ ውጤታማ ነው። ለሁሉም የአዕምሮ ሕመሞች የመድኃኒትን ያክል ውጤታማ ነው። ውጤቱንም አስጠብቆ ለረጅም ጊዜ ይቆያል። ሰዎች መድኃኒትን ለመውሰድ ሊቸገሩ ይችላሉ፥ የንግግር ሕክምናን ግን አልፈልግም አይሉም።”
አዲስ ዘመን የካቲት 09/2013