አስናቀ ፀጋዬ
በኢትዮጵያ 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው 92 ሺ የህብረት ስራ ማህበራት እንዳሉና የማህበራቱ አጠቃላይ ካፒታልም 28 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱ ከፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
በነዚሁ ህብረት ስራ ማህበራት ስር 1 ሺ 60 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ መሆኑንና ከ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም በነዚሁ የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የስራ እድል መፈጠሩን መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
በሀገሪቱ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የገበሬ ህብረት ስራ ዩኒየኖች ለተመሳሳይ ዓላማ የተቋቋሙ ቢሆንም አንዳንዶቹ ግን የራሳቸውን ፋብሪካ በመገንባትና አባላት ወደነዚሁ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ውጤታማ ስራዎችን ሰርተዋል።
አርሶ አደሮችና ህብረት ስራ ማህበራት ምርቶቻቸውን ሰብስበው በተሻለ ዋጋ እንዲያቀርቡና ከሚያመርቷቸው ምርቶችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከወለድ ነፃ የብድር አገልግሎት ከማቅረባቸውም ባሻገር ህብረት ስራ ማህበራቱ ሂሳባቸውን እንዲያውቁ የኦዲት አገልግሎት በመስጠት አባላቶቻቸው እንዲጠቀሙ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።ከነዚህ ውስጥም በሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ የሚገኘው ቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ተጠቃሽ ነው።
አቶ ደረጀ አባቡ የቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒዩየን ስራ አስኪያጅ ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት የቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በ 17 ህብረት ስራ ማህበራት አባላትና 35 ሺ በሚሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች 105 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ይዞ ከሚመለከተው የመንግስትና ህብረት ስራ ማስፋፊያ ቢሮ ሁለት ሰራተኞች ተመድበውለት በ1997 ዓ.ም ተመስርቷል።ይህም ብር ከሼር ሽያጭና ከመመዝገበያ ተገኝቷል።
ዩኒየኑ ሲመሰረት ዋነኛ ዓላማውም አባላት የግል ችግራቸውን በራሳቸው ከመፍታት ይልቅ አንድ ላይ ሆነው ህብረት ስራን በማደራጀት በፋይናንስ፣ በጉልበትና በእውቀት እንዲፈቱ ነበር።የግብርና ግብዓቶችን ለህብረተሰቡ ማቅረብ፣ ለአባላቱ የፋይናንስ ምንጭ መሆን ወይም የብድር አገልግሎት መስጠትና የገበያ ትስስር መፍጠር ዩኒየኑ ሲመሰረት ይዞ ከተነሳቸው ተጨማሪ ዓላማዎች ውስጥ ይገኙበታል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ በአሁኑ ወቅት ዩኒየኑ አንድ መቶ ሰላሳ ሶስት የመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት አባላት አሉት።99 ሺ የሚጠጉ አርሶ አደሮችም የዩኒየኑ አባል ናቸው።የካፒታል መጠኑ ወደ 59 ሚሊዮን ብር አድጓል።አጠቃላይ ንብረቱም ወደ 72 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተጠግቷል።በሰሜን ሸዋ ዞን አስራ ሶስት ወረዳዎች ላይና በልዩ ዞን ደግሞ በሱሉልታና ሙሎ ወረዳዎች ላይ አግልግሎት ይሰጣል።
የምርት ማሳደጊያዎችን በጥራትና በብዛት እያቀረበ የሚገኘው ዩኒየኑ ለአባላት ስልጠናዎችን ከመስጠት በዘለለ አርሶ አደሩ ወይም ህብረት ስራ ማህበሩ ምርቶች ሰብስቦ በተሻለ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ እንዲችል ከወለድ ነፃ የብድር አገልግሎት በማመቻቸት የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።እንዲሁም ህብረት ስራ ማህበራት ሂሳባቸውን እንዲያውቁ የኦዲት አገልግሎትም ይሰጣል።
ዩኒየኑ የሚገኝበት ሰላሌ በተለይ በወተት ሀብት የሚታወቅ ከመሆኑ አኳያም ወተቱ በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ ከአርሶ አደሩና ከአባላቱ ተቀብሎ ለገበያ ያቀርባል።አርሶ አደሩ ልምድ የሚያገኝበትን የከብት ማደለቢያ ማእከል ከፍቶ ከዘርፉ እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ስልጠና በመስጠት ላይም ይገኛል።
የሰላሌ አካባቢ በከብት እርባታም ስለሚታወቅ ምጥን የከብት መኖ ማምረቻ ፋብሪካ በፍቼ ከተማ በ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር አቋቁሞ ለአርሶ አደሩ በተሻለ ዋጋ ያቀርባል።ፋብሪካው ሰሜን ሸዋ አካባቢ ላሉ አርሶ አደሮች ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ሌሎች አርሶ አደሮችም ከሌሎች የኦሮሚያ ዞኖች እየመጡ እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ስራ አስኪያጁ እንደሚሉት በአብዛኛው አርሶ አደሩን የሚገጥመውና ምርቱን ካመረተ በኋላ ለገበያ የማቅረብ ወይም የመሰብሰብ ችግር ቢሆንም ይህ ችግር በቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ውስጥ አለመታየቱ ከሌሎች ተመሳሳይ ዩኒየኖች ለየት ያደርገዋል።ባለፈው ዓመት ብቻ አርሶ አደሮች ምርቶቻውን ሰብስበው ለገበያ የሚያቀርቡበት 24 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ከወለድ ነፃ ብድር ማመቻቸቱም ለልዩነቱ የእሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።ይህም ዩኒየኑ በሞዴልነት እንዲጠቀስ አድርጎታል።
በሌላ በኩል ደግሞ አምና በሀገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ ዩኒየኑ ከህብረተሰቡ ጎን በመቆም የሳሙናና ሳኒታይዘር ዋጋን በማረጋጋት ህብረተሰቡ ምርቶቹን በተመጣጣኝና በተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ አድርጓል።እነዚህን ምርቶች ከሚያመርቱ ፋብሪካዎች ጋር በመነጋገርም ለአርሶ አደሩና ለከተማው ነዋሪ ምርቶቹን በራሱ መሸጫ ሱቆች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ አድርጓል።
በተለይ ደግሞ እነዚህን ምርቶች 200 ለሚሆኑ የመግዛት አቅም ለሌላቸውና ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በእርዳታ መልክ በማቅረብ አበረታቷል።በእርዳታ የቀረበው የምግብ፣ የሳሙናና ሳኒታይዘር ምርት አጠቃላይ ዋጋም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ይገመታል።
ገበያን ከማረጋጋት አኳያም ለአብነት ከምስራቅ ሸዋ የተለያዩ ዩኒየኖች ጋር በመሆንና የገበያ ትስስር በመፍጠር የፍራፍሬ ምርቶችንና ሽንኩርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርስ አድርጓል። የተለያዩ ሌሎች ምርቶችንም ከአርሶ አደሩ ተቀብሎ በመሸጥ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝም አስችሏል።
ተጠቃሚም ምርቱን በተሻለ ዋጋ እንዲያገኝና የምርት ዋጋ ከፍ በሚልበት ወቅት በተለይ የመንግስት ሰራተኞች የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፎላቸው ገንዘብ ተበድረው በሶስት ወር ውስጥ እንዲከፍሉም ጥረቶች ተደርገዋል።በአዲስ አበባም ሆነ ፍቼ ከተማ የአርሶ አደሩን ምርት በመሰብሰብ በተሻለ ዋጋ ማንኛውም ሰው በሚፈልግበት ወቅት እንዲያገኝም አድርጓል።
በአሁኑ ጊዜ ዩኒየኑ የከብት ማድለቢያ ማእከል በሰሜን ሸዋ ዞን ያዮ ጉለሌ ወረዳ ያስገነባ ሲሆን ማእከሉ በዘመናዊ መልኩ የተሰራና የተደራጀ በመሆኑ ሌሎች መሰል የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ለልምድ ልውውጥና ተሞክሮ መቅሰሚያነት እየተገለገሉበት ይገኛሉ።
ዩኒየኑ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ችግሮችም ያጋጠሙት ሲሆን ለአብነትም በወተት ንግድ ላይ የተሰማሩ የተለያዩ ህገወጥ ነጋዴዎች በመኖራቸው አርሶ አደሩ የለፋበትንና የሰራበትን ዋጋ እያገኘ አለመሆኑን ይናገራሉ።
በህገ ወጥ ነጋዴዎች ምክንያትም አርሶ አደሩ በሌሎች ምርቶችም የለፋበትንና የሰራበትን ዋጋ ማግኘት አልቻለም።ምርቶችን ከአርሶ አደሩ መሰብሰብ ቢቻልም ምርቱን የሚቀበልም ሸማች ማህበራት በብዛት ባለመኖራቸው ችግሩ ጎልቶ መታየቱን ነው የጠቀሱት።
እነዚህን ችግሮችን ለመፍታትም ዩኒየኑ ምርቶቹን በስፋት ከሚያቀርብለት የኦሮሚያ ህብረት ስራ ፌዴሬሽን ጋር እየሰራ ይገኛል።ፌዴሬሽኑም የተለያዩ የገበያ ትስስሮችን እየፈጠሩ በእነሱ በኩል ወደ ውጭ ሀገራት ምርቶች እየተላኩ ነው።በተመሳሳይ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ኤጀንሲም የገበያ ትስስር እየፈጠረ ዩኒየኑ ምርቶችን ለአዲስ አበባ ሸማች ማህበራት እያቀረበ ቆይቷል።
ይሁንና ዩኒየኑ ይህን ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ ወይም እዚህ በቦታው ላይ ያለውን እምቅ አቅምና የአርሶ አደሩን ምርት ወደ ገበያ ሙሉ በሙሉ የሚቀርብበት ሆኖ አላገኘውም።አዲስ አበባና እዛ ያለው ገበያ ብዙ ጊዜ የተለያየ ነው።ገበያውን በማዛባት በኩልም ህገ ወጥ ነጋዴዎች ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ስራ አስኪያጁ እንደሚገልጹት ዩኒየኑ በቀጣይ 70 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ትልቅ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በፍቼ ከተማ ለመገንባት በሂደት ላይ ይገኛል። በቀጣዩ ዓመት ስራውን ለማስጀመርም እቅድ ይዟል። በአሁኑ ወቅትም ግንባታውን ለማከናወን ከዞኑ አስተዳደር መሬት ጠይቆ የግንባታ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
ዩኒየኑ የወተት ላሞችን አዳቅሎ በማርባት ለአርሶ አደሮች በማከፋፈል ከእነርሱ ደግሞ መልሶ ወተት በመቀበል ወደ ፋብሪካው የመሰብስብ ተያያዥ እቅድ አለው።አርሶ አደሩን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሌሎች እቅዶችም ያሉት ዩኒየኑ በተለይ ደግሞ የአርሶ አደሩን ምርቶች በመሰብሰብ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ የሚያስችለውን የተለያዩ መጋዘኖችን በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለመገንባትም ውጥን ይዟል።መጋዘን ከሚገነባባቸው አካባቢዎች ውስጥም አንዱ አዲስ አበባ ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ የገበያ ማእከል ለመገንባት ቦታ ተረክቧል።
ይህም በሂደት ላይ ያለ ሲሆን ሂደቱ እንደተጠናቀቀ የገበያ ማእከሉ ተገንብቶ ዩኒየኑ ራሱን ጠቅሞ ሌሎች ዩኒየኖችም እንዲጠቀሙበት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ተዘጋጅቷል።
‹‹በአስራ ስድስት ዓመት ቆይታው ቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ውጤታማ ነው›› የሚሉት የዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ በዘንድሮው በጅት ዓመት ባሰራው የሂሳብ ኦዲት መሰረት 27 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንና ይህም የውጤታማነቱ አንዱ ማሳያ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
የተለያዩ ንብረቶችን በማፍራትም ዩኒየኑ ውጤታማነቱን ማረጋገጥም ችሏል የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ የአርሶ አደሩን ምርቶችና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በራሱ ተሽከርካሪዎች እንደሚያጓጉዝና በራሱ ቢሮ በመገልገል ከኪራይ ነፃ መሆኑንም ይገልፃሉ።በተለያዩ ቦታዎች ላይ መጋዘኖችን በራሱ ገንብቶ እንደሚጠቀምና በዚህም ከተለያዩ ወጪዎች ራሱን ማዳኑንም ይጠቅሳሉ።
በአሁኑ ወቅትም ዩኒየኑ 11 የጭነት ተሽከርካሪዎችና ለእርሻ አገልግሎት የሚውሉ ሁለት ትራክተሮች፣ አንድ ሳር ማሰሪያ ማሽንና 7 ክሬሼሮች እንዳሉትም ስራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ።ይህም ዩኒየኑ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን ተጠቅመው ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ እያደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑንም ያስረዳሉ።
የህብረት ስራ ማህበራት ሲደራጁ የህብረተሰቡን አቅምና ጉልበት አሰባስበው ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ በመሆኑና ዩኒየኖችም ሆኑ ህብረት ስራ ማህበራት ደግሞ አንድ ላይ ሆነው ያደራጁት ታች ያሉ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ስለሆኑ ቢፍቱ ሰላሌ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበርም ታች ያሉ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲያድጉና ዩኒየኑን እንዲያጠናክሩት በተለያየ የአሰራር ዘዴ፣ ማቴሪያልና ፋይናንስ እንደገፋቸውም ስራ አስኪያጁ ያብራራሉ።
ታች ያሉ አባል አርሶ አደሮች ባደጉ ቁጥር ምርታቸውን በብዛትና በጥራት ለዩኒየኖች ማቅረብ ስለሚችሉና ይህንንም ተከትሎ ዩኒየኖችም ስለሚያድጉና ምርቶችን በበለጠ ጥራት ለሚመለከታቸው ድርጅቶችና ለህብረተሰቡ ማቅረብ ስለሚችሉ በተመሳሳይ በሀገሪቱ የሚገኙ ሌሎች የገበሬ ህብረት ስራ ዩኒየኖችም ተያይዞ የማደግን መንገድ መከተል እንደሚኖርባቸውም ያሳስባሉ። አቅም ባፈሩ ቁጥርም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ።
አቶ ደረጄ አባቡ፤
አዲስ ዘመን የካቲት 06/2013