መርድ ክፍሉ
ኢትዮጵያውያን ወግና ባህላቸውን፣ የልብ አብሮነታቸውን በተግባር የሚመነዝሩበትን፤ ደስታና ሀዘናቸውን የሚካፈሉበትን ሐቅ በተግባር ቋንቋ ከሚነግሩንና ከሚያስረዱን በርካታ ተግባራት መካከል በማህበራት ተሰባስበው ለወገኖቻቸው ጉልበት እና እስትንፋስ መዝራታቸው አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። ፖለቲካው ዘርቶ፣ አጠጥቶ፣ አብቅሎ፣ ኮትኩቶ፣ ለፍሬ ያበቃቸውን አንዳንድ መጥፎ ድርጊቶች በእምነቶች፣ በብሄረሰቦችና በማህበረሰቡ መካከል የሆኑ፣ የተደረጉና የተፈጠሩ አድርገው የሚነዙ አካላት አይጠፉም። ይህ እኩይ አስተሳሰብ የኢትዮጵያዊነትን የትስስር፣ የመዋደድ፣ የአንድነት፣ የፍቅር ማሰሪያ ውል ጥልቀት በፖለቲካቸው ጮርቃ ሚዛን ከመለካት የሚመነጭ የለጋ እሳቤ ውጤት ነው።
‹‹ከልብ ካዘኑ እንባ አይገድም›› እንዲሉ ከልብ ካዘኑ ሌሎችን ማገዝ የሚያስችል አቅም ከእያንዳንዱ ሰው እጅ ሞልቷል። የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ሐብታም መሆንን አይጠይቅም። ሐብታም እስኪሆኑ ከንፈር በመምጠጥ ማለፍም ለተራበ ሰው ጉራሽ ሆኖ የታጠፈ አንጀቱን አያቃናለትም። ሰዎች ባላቸው አቅም ለችግሮች ለተጋለጡ ወገኖቻችን ለመድረስ ቁርጠኛ ሲሆኑ አቅም ያገኛሉ። ሰዎች ካላቸውና ከራሳቸው ቆርሰው ለሌሎች ሲጋሩ ቅንጣት ታህል የእነሱ አይቀንስም። ይልቁንም በሚያገኙት የመንፈስ እርካታ ሕይወታቸው በብርሃን እንዲሞላ በፍቅር እንዲንበሸበሽ ይሆናል። ለመስጠት የልብ ቁርጠኛ መሆን እንጂ ብዙ የሚሰጥ ነገር መያዝን አይሻም።
ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጠት ባህል የነበራትና በፍጹም ወንድማማችነት ዜጎች የሚኖሩባት ችግራቸውን በጋራ በመተባባር የሚያሳልፉባት ሀገር ነች። ይህ በመስጠት የሚገለጸው በጎ ፈቃደኝነት የሀገሩ ባህል ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት ልማድና ወግም ነበር። ሲወልድ የግምዶ፣ ሲያዝን የዝን፤ ብሎ ከመስጠት ጀምሮ ሲዘምት የስንቅ፣ ሲመለስ የደስታ፤ ሲሾም የምስራች፣ ሲሻር የሹመት አይደንግጥ ብሎ እስከመስጠትም የረቀቀ ነው።
በተለያዩ ዘርፎች ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት መትጋት በጎነትና ልበ ቀናነት የሚፈጥረው የአዕምሮ እሳቤ ውጤት ነው። ከሀሳብም አልፎ በተግባር የሚገለጽ በጎነት በወጣትነት ሲሆን ደግሞ ያስደስታል:: ምክንያቱም ወጣትነት ለመልካም ዓላማ ሲውል አካባቢን አልፎ አገርን ብሎም ዓለምን የመለወጥ አቅም አለውና ነው። በዚህ እሳቤ የተቃኘው ‹‹ከልብ በጎ አድራጎት ማህበር›› የዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
ማህበሩ በኮሌጆች ውስጥ የሚማሩ ችግረኛ ተማሪዎች ላይ አተኩሮ ይሰራል። ለተማሪዎቹ የመማሪያ ቁሳቁሶችን ከማሟላት በተጨማሪ የቤት ኪራይና የትራንስፖርት ገንዘብ እየሰጠ ይገኛል። በዚህም ችግረኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ አድርጓል። በቀጣይም በተለያዩ ኮሌጅ ውስጥ የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎችን ለመደገፍ አላማ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከማኅበሩ መስራችና ሰብሳቢ ወጣት ሳሙኤል ለገሰ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።
የማህበሩ ምስረታና የሰራቸው ስራዎች
ማህበሩን ለመመስረት የተነሱት በሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ ይማሩ የነበሩ በስፖንሰር የመጡ ተማሪዎችን ለመደገፍ ግቢ ውስጥ ጫማ በመጥረግና መኪና በማጠብ ለልጆቹ ድጋፍ በማድረግ ነበር። በሌላም በኩል በግቢው ይማር የነበረ ሰውነቱ መንቀሳቀስ ለማይችል ልጅ ትኬት በመሸጥ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች አድርገዋል። በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ተማሪዎች ከክፍለአገር የሚመጡ በመሆናቸው ብዙ ችግር ያጋጥማቸዋል። በተለይ ሴቶቹ በችግር ምክንያት ወዳልሆነ ነገር ሲገቡ ይስተዋላል። በዩኒቨርሲቲው የነበሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው ሲወጡ ለችግረኛ ተማሪዎች በቋሚነት ለመደገፍ ሀሳብ አመጡ። ተማሪዎቹን ለመደገፍ በማህበሩ ውስጥ የተካተቱ ሰዎች ከደመወዛቸው ማዋጣት ጀመሩ። ማህበሩ ስራውን ከጀመረ በኋላ በተያዘው ዓመት ሁለት ተማሪዎችን ማስመረቅ ችሏል። በአሁን ወቅት አራት ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።
አብዛኛው ተማሪ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በመንግሥት ወጪ ተምሮ ይጨርሳል። የተወሰኑ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ውጤት ላይመጣላቸው ይችላል። በዚህም የግል ኮሌጆች ገብቶ ለመማርም አቅም አይኖራቸውም። በገንዘብ እጥረት ምክንያት የመማር እድል ማግኘት የማይችሉ ሰዎች አሉ። በዚህም ምክንያት ላልተገባ ነገር የሚዳረጉ ወጣቶች እንዲበዙ አድርጓል።
ማህበሩ በቅርብ እንደ አዲስ ራሱን በማዋቀር 50 አባላት ያቀፈና እውቅና ያገኘ ማህበር ሆኗል። ነገር ግን መልካም ስራ ሲከናወን አብዛኛው የመሳተፍ ሁኔታው የቀነሰ ነው። በጥሩ ሁኔታ በማህበሩ የስራ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉት ከአስር ሰው አይበልጥም። ማህበሩን ለማጠናከር ከወርሃዊ መዋጮ በዘለለ በውጭ ከሚገኙ ደጋፊዎች በሚገኝ ገንዘብ ስራዎች እየተሰሩ ነው። በውጭ አገራት የሚገኙ ደጋፊዎች ህፃናትን በመምረጥ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው ጀምሮ በማስተማር ላይ ይገኛሉ።
የኅብረተሰቡ አቀባበል
ማህበሩ መጀመሪያ ስራ የጀመረበት ወቅት በወረዳዎች ወደሚገኙ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ነበር የሚሄደው። ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ህፃናትም ሆነ ወጣቶች ከፅህፈት ቤቶቹ ሞቅ ካለ አቀባበል ጋር ማግኘት ችለዋል። ድጋፍ የሚደረግላቸው ወጣቶች ቤትም በሚኬድበት ሰዓትም የፅህፈት ቤቶቹ ሰራተኞችና አመራሮች አብረው ከማህበሩ አባላት ጋር ይዘዋወራሉ። እገዛም ያደርጋሉ። በአሁን ወቅትም ማንኛውንም ድጋፍ ለማግኘት ወደ ወረዳዎች በመሄድ መማር የሚፈልጉ ወጣቶችን ማግኘት ተችሏል።
በመንግስት ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች ቅዳሜና እሁድ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት እቅድ ተዘጋጅቶ ነበር። ነገር ግን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ተግባር ሳይገባ ቀርቷል። የመንግሽት ትምህርት ቤቶች ሀሳቡን ተቀብለውታል። ነገር ግን ኅብረተሰቡ አካባቢ የተወሰኑ አመኔታ አለመስጠት ሁኔታዎች ይታያሉ። ኅብረተሰቡም በግል በማግኘት ስለ ማህበሩ ስራ ግንዛቤ ሲሰጥ በግላቸው ተማሪዎችን ለመደገፍ ፍላጎት እያሳዩ ናቸው። በቀጣይ ድጋፍ የሚደረግላቸው ወጣቶቸ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁና ተለውጠው ሲመለከቱ የኅብረተሰቡ አመለካከት በደንብ ሊቀየር ይችላል። አንድ ወጣት መርዳትና ካለበት ሁኔታ ማውጣት ቤተሰብን እንደመደገፍ ይቆጠራል።
ተማሪዎቹ የሚመለመሉበት መንገድ
ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለተወሰኑ ተማሪዎች የነፃ ትምህርት እድል ይሰጣል። ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ ሁሉንም ነገር ማሟላት ሲያቅተው ወደ ማህበሩ ይልካል። ከወረዳዎች ከፍለው መማር የማይችሉትን በመውሰድ እንዲሁም ቤት ለቤት በመዞር ድጋፍ የሚደረግላቸውን በመጎብኘት ፎርም እንዲሞሉ ይደረጋል። ከዚህ በኋላ ተማሪዎቹን ወደ መደገፉ ይገባል።
ማህበሩ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች ችግር ቅድሚያ ያጠናል። ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነፃ የትምህርት እድል ይሰጣል። ነገር ግን ተማሪዎቹ ፎቶ ኮፒ፣ ቤት ኪራይና ሌሎች ነገሮች የሚሸፍኑበት ገንዘብ አይኖራቸውም። ይህንን ችግር ለመፍታት ማህበሩ ጥረት ያደርጋል። ማህበሩ ከሚደግፋቸው ውስጥ አንደኛዋ የቤት ኪራይ አጥታ በነበረበት ወቅት ማህበሩ ትምህርቷን እንድትቀጥል የቤት ኪራይ ድጋፍ አድርጓል።
ሌላው ደግሞ ማህበሩ ደግፎ እያስተማረው የሚገኘው ወጣት ቀደም ብሎ የትራንስፖርት ገንዘብ ስላልነበረው ትምህርቱን እንዳያቋርጥ የትራንስፖርት ገንዘብ እየተሰጠው ይገኛል። የትምህርት ወጪያቸውን መክፈል ለማይችሉ ደግሞ ሙሉ ክፍያ ይከናወንላቸዋል። ባሁን ወቅት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ወደ ማህበሩ የመጡት ወጣቶች አብዛኛዎቹ ከፍለው መማር የማይችሉት ናቸው። መክፈል ለማይችሉ ተማሪዎች ክፍያቸው ይከፈላል። በተጨማሪም ፎቶ ኮፒና ለመሰል ነገሮችም ድጋፍ ይደረጋል።
ማህበሩን ያጋጠሙት ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ አጋጥሞ የነበረው ትልቁ ችግር ሰው ድጋፍ ሲባል የሚያስበው የወደቁና የደከሙ ሰዎች ሲረዱ ብቻ ነው። በተጨማሪም ቤት ማደስ ዙሪያ ላይ እንጂ በወጣቱ ችግር ላይ ድጋፍ ማድረግ የተለመደ አይደለም። አብዛኛው ሰው የሚታይና ሁሉን ያሳተፈ ነገር ማህበሩ እንደማይሰራ አድርገው ያስባሉ። በማህበሩ ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶች ቤት ወድቆ የማንሳት፣ የአቅመ ደካሞችን ገላ ማጠብና ከጎዳና ልጆችን ማንሳትን ብቻን እንደ በጎ ስራ የሚያዩት።
ከዚህ ነገር ውጪ በሦስትና በአራት ዓመት ውስጥ ሰዎችን መቀየር የሚያስችል አላማ ተይዞ እየተሰራ ነው። ማህበሩ ከብዙ ማህበራት የተለየ ነገር ነው የሚያከናውነው። አብዛኛው ግን የሚታይ ነገር ማህበሩ አይሰራም የሚል አመለካለት በመያዛቸው የተወሰኑ ችግሮች እያጋጠሙ ነው። ድጋፍ በሚሰባሰብበት ወቅት ቤት ለመስራት ወይም አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ባለመሆኑ ችግሮች ያጋጥማሉ። ማህበሩ ድጋፍ ለወጣቶቹ ሲያደርግ የህሊና እረፍት ያገኛል። ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ውጤታማ ነው።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
ማህበሩ በቀጣይ በርካታ ስራዎችን ለማከናወን አስቧል። የሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚገኘው ጀሞ ኮንደሚንየም አካባቢ ነው። በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ እየተማሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሴቶች ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ናቸው። ሴቶች በዝቅተኛ ዋጋ ቤት ለማግኘት ወደ ጫካ ውስጥ ስለሚኖሩ ለጥቃት ሊጋለጡ ይችላሉ። ይህን ለመፍታት ማህበሩ የተማሪዎች ማደሪያ የመስራት ሀሳብ አለው። ሴት ተማሪዎቹ ከመሸ በኋላ ወደተከራዩት ቤት ለመሄድ በጣም ይቸገራሉ። ይህንን ለማሳካት ኮንደሚኒየም ለመግዛት ሃሳብ አለ። ሌላው የማህበሩ አላማ ወጣቶች ላይ አተኩሮ በመስራት ውጤታማ ማድረግ ነው። በአሁን ወቅት ማህበሩ ድጋፍ እንዲደርግላቸው ከክፍለ አገር ድረስ ጥያቄዎች እየመጡ ይገኛሉ። ተማሪዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች መክፈል ሲያቅታቸው ወደ ማህበሩ የሚመጡበት ሁኔታ አለ።
በቀጣይ በሌሎች ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች ላይ የሚማሩ ተማሪዎችን ለመርዳት እቅድ ተቀምጧል። የማህበሩ አባላት በሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ የተማሩ በመሆናቸው እዛው አካባቢ ያሉትን በመደገፍ ስራውን ጀምረዋል። በቀጣይ ግን በሌሎች ተቋማት ውስጥ የሚገኙትን አቅም የሌላቸውን ከትምህርት ክፍያ ጀምሮ ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን ይሰራል። ተማሪዎች ወጪያቸውን የሚሸፍኑበት ገንዘብ ከሌላቸው በትምህርታቸውን ደከማ ይሆናሉ።
በአየር ጤና አካባቢ የሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የማዳረስ እቅድ አለ። ተቋማቱ የትምህርት ክፍያ ቢችሉ ማህበሩ ደግሞ ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን ያስባል። አለበለዚም ግማሸ ግማሽ ክፍያ የሚችሉበት ሁኔታ ለመፍጠር ታስቧል። አብዛኛው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲከፈቱ የማህበረሰብ አገልግሎት ግዴታ አለባቸው። በዚህም አብዛኛው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች ማስተማር ፍላጎት አለው። ነገር ግን መመዘኛ አውጥቶና ተማሪዎችን ለይቶ ማስተማር ላይ ወደ ኋላ እያሉ ነው። ይህንን ችግር ለመፍታትም ማህበሩ አብዛኛውን ስራ ጨርሶ ወደ ተቋማቱ ለመሄድ እቅድ አለው።
አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013