አዲስ አበባ፦ ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሠራ መሆኑን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ ትናንት ተቋሙ ባዘጋጀው ፎረም ላይ እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከህዝብና ንግድ መገናኛ ብዙኃን ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት፤ አገልግሎቱ ምን ያህል ተደራሽ እንደሆነ ክፍተቱን በመለየት አቅሙን ለማጎልበት እየሠራ ነው።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገሪቱ ብቸኛና ቀዳሚ የዜና አገልግሎት እንደመሆኑ መድረስ ካለበት ደረጃ ሊደርስ አልቻለም። በተለይም ከጀርባ ሆኖ ዜና በማቅረቡ ተረስቷል። ህዝቡም ዜናውን የሚያገኘው በሌሎች መገናኛ ብዙሃን በኩል በመሆኑ ይህን ያህል ተፅዕኖ ይፈጥራል ተብሎ አይታሰብም። ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት ተቋሙ እራሱን ችሎ እንዲቆም ባለመደረጉና ከሌሎች ተቋማት ጋር ሆኖ መቆየቱ ወደኋላ ጎትቶታል።
ይሁን እንጂ፤ ተቋሙ እንደ አዲስ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ እንደ ስሙ ግዝፈት ያለውን አቅም ይዞ መቀጠል የሚያስችለውን ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ አዲስ ምዕራፍ እየመጣ ይገኛል። በዋናነትም ጋዜጠኛው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ እንዲሠራና ነጥሮ እንዲወጣ ለማስቻል ሳቢ ደመወዝ በመክፈል የባለሙያ ፍልሰትን ማስቀረት ይቻላል ብለዋል።
በአሁን ጊዜ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ 12 የመገናኛ ብዙሃን ጋር ውል ተዋውሎ እየሠራ ሲሆን፤ ከውጭ ደግሞ ከ10 መገናኛ ብዙሃን ጋር አብሮ እየሠራ ይገኛል። በውጭ ካሉ 10 ሀገራት ጋርም በየቀኑ ዜና ለመላላክ ስምምነት ያለው መሆኑን አቶ በቀለ ተናግረዋል። አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋት በጎረቤት ሀገራት ማለትም በሁለቱ ሱዳኖችና በጅቡቲ፤ አሁን ባለው በአዲሱ ዕቅድና አዋጅ መሰረት በምሥራቅ አፍሪካ፣ በሰሜን አፍሪካ፣ በመካከለኛው አፍሪካና በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፎችን ለመክፈት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት በያዝነው ዓመት ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2011
በፍሬህይወት አወቀ