ታምራት ተስፋዬ
የቲክ ቶክ አፕሊኬሽን ወይም መተግበሪያ በአሁኑ ሰዓት እጅግ ዝነኛው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ነው። ከሌሎቹ ማህበራዊ መገናኛዎች ለየት የሚያደርገው ደግሞ አጫጭርና እንዲያዝናኑ የታሰቡት ቪዲዮዎች የሚቀርቡበት መሆኑ ነው። እንደ አብዛኛዎቹ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችም ተጠቃሚዎች በቪዲዮዎቹ ላይ መውደድን፣ መጋራት፣ አስተያየት መስጠት ና ማጋራት ይችላሉ።
በተንቀሳቃሽ ስልክ ቪዲዮዎችን ለማጋራት የተፈጠረ ይሕ ማኅበራዊ ሚዲያ አሁን ደግሞ በአንድሮይድ ቴሌቪዥን መተግበሪያ መጥቷል። ‹‹ተጠቃሚዎችም በግዙፍ ስክሪን በቤታቸው ውስጥ ሆነው የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ መመልከት ይችላሉ›› ተብሏል።
የማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ተጠቃሚዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው እንደሚጠቀሙት፣ በአዲሱ በቴሌቪዥን መስኮትም የራሳቸውን ሆነ የሌሎችን ፖስቶች መመልከት እንደሚቻላቸው ታውቃል። በአሁን ወቅትም በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን የቴሌቪዥን መስኮት ጅምሩ እውን መሆኑ ተጠቁማል።
በእንግሊዝ የቲክ ቶክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሪች ወተርዎርዝ፣ ‹‹ቲክ ቶክ በአዲስ መንገድ በቴሌቪዥን መስኮት በግዙፍ ስክሪን ይዘን በመምጣቱ እጅግ ደስተኛ ነኝ፣ የተመረጡ ስራዎችን ማቅረቡም ሰዎች ይበልጥ እንዲዝናኑ ያደርጋል›› ብሏል።
ቲክ ቶክ ተጠቃሚዎቹ በጋራ ሆነው በቤታቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አዳዲስ ልምድና ትምህርቶችን እንዲቀስሙ አሊያም ተመልክተው በሚወዱት ደስታን እንዲያገኙ ማድረጉም አድንቆት የሚያስቸረው መሆኑን ጠቁመዋል።
ይሑንና በአሁን ወቅት ቲክ ቶክ አዲስ አማራጩን ከተወሰኑ አገራት ውጭ በመላ አለም ለሚገኙ ተጠቃሚቹ አልቀረበም። በርካቶች አዲሱን የቲክ ቶክ የአንድሮይድ ቴሌቪዥን መተግበሪያ ለመጫን ፍላጎት ቢኖራቸውም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ እየተናገሩ ናቸው።
አሁን ላይ ቲክ ቶክ አዲስ አማራጩን በመላ አለም የማዳረሱ ጥረቱ በግልፅ አልታወቀም። ይሕ እስከሆነም በመላ አለም እስኪጀመር ተጠቃሚች የተወሰኑ ጊዜያትን መጠበቅ ግድ ይላቸዋል ተብላል። ባሳለፍነው አመት ታህሳስ ወር ላይ በሳምሰንግ ግዜፍ ስክሪን መምጣቱ የሚታወስ ነው። የአሁኑም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነም ተመላክቷል። የመረጃ ምንጫችን ዲጂታል ቲቪ ዩሮፕ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013