ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀሳቤቅ አባት)
እንደነገርኳችሁ እግረኛ ነኝ…ተሽከርካሪ አልጠቀምም..አካባቢዬን ማህበረሰቤን እያየሁና እየቃኘሁ መሄድ ደስ ይለኛል። ህይወትን፣ ኑሮን..ደስታና ውጣ ውረዱን እያየሁ እየታዘብኩ መራመድ ያስደስተኛል። ካየሁት ከታዘብኩት..ወይ ጉድ ካስባለኝ የመዲናችን ጉዶች ውስጥ አንዱን እንደሚከተለው አስቃኘኋችሁ።
የአፍሪካ መዲና፣ የአለም የዲፕሎማሲ መቀመጫ አዲስ አበባ..በውስጧ ከአምስት ሚሊየን ህዝብ በላይ ይኖርባታል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪም በርካታ አህጉራዊና አለም አቀፍ ስብሰባዎችን የምታስተናግድ ትልቅ ከተማ ናት። በዚህ ሁሉ ገናናነቷ ውስጥ ውብ መልኳን የሚያጠይሙ አያሌ እንከኖች አሏት። ከዚህ ውስጥ አንዱ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዐት አለመኖር ነው። እንደ ዋና ከተማነቷ የስሟን ያክል ውብና ጽዱ ከተማ ናት ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።
በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሾችን ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ብዙዎች የሚስማሙበት የከተማዋ የጽዳት ሁኔታ ከትላንት ጀምሮ እልባት ሳያገኝ ዛሬ ላይ ደርሷል። በየሰፈሩ፣ በየአስፓልቱ፣ በየክፍለከተማው በየትኛውም ቦታ የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ ብዙ አይነት በካይ ቆሻሻዎች እዛም እዚም ይስተዋላሉ። በአጠቃላይ በቆሻሻ የተከበበች ከተማ ናት ብሎ መናገሩ ይቀላል። እንዳውም አንዳንዴ የዝባዝንኬ እቃ ቤት ትመስለኛለች።
አለም ላይ ያለ ቆሻሻ ሁሉ አዲስ አበባ ላይ የሚጣል እንዲህም ይመስለኛል። ጓዳ ጎድጓዳዋ ሁሉ እጣቢና ጥራጊ የሞላበት ነው። ይሄን ሁሉ ክብርና ማዕረግ ይዛ..የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሆና የውበትና የጽዳት ባይተዋር መሆኗ ይገርማል። ቀን በቀን ከአዲስነቷ እኩል አሮጌነቷን የሚያጎሉ እንከኖቿ እየበዙ መጥተዋል። ዘመናዊነቷን ከሚያጎሉ ህንጻዎቿ ጋር፣ ዘመናዊነቷን ከሚመሰክሩ ቴክኖሎጂዎች ኋላ አብሮ ጉድፏም እየበረከተ ነው።
የከተማዋ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት ኋላቀር ከመሆኑም በላይ ለአንድ ዋና ከተማ የማይመጥን ሆኖ እናገኘዋለን። ከተማን ከተማ ሊያስብለው ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ውበት ነው። ሁሉም ነገር ውበትን ተከትሎ የሚመጣ ነው። ባልጸዳና ባላማረ ከተማ ላይ የፎቅና የመኪና ብዛት ትርጉም አለው ብዬ አላምንም።
ሁላችንም ፎቅ መስራት ላይ አስፓልት መገንባት ላይ ነው ያተኮርንው። ሌላው ቢቀር ለግንባታ ተብለው በየመንገዱ ተደፍተው አስፓልት ያበላሹ መንገድ የዘጉ አሸዋና ድንጋዮች ሀይ ባይ እንኳን የላቸውም። በየመንገዱ በየህንጻው ጥግ ላይ በፔስታልና በጨርቅ የሚሰሩ የመንገድ ላይ ቤቶች በመንግስት እልባት ቢሰጥባቸው ባይ ነኝ። ከከተማዋ የህዝብ ቁጥር ጋር የሚስማማ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዐት ያስፈልጋል። ማህበረሰቡን ስለ ከተማ ጽዳት እውቀትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀዳሚው ጉዳይ ነው። በየመንገዱ የህዝብ መገልገያ መጸዳጃ ቤቶች መሰራት ቢችሉ ቢያንስ ጎዳና ላይ ያለውን የከተማ ውበት መጠበቅ እንችላለን ብዬ አምናለው። ሁሉም ሰው ለምንም ነገር መንግስትን የሚጠብቅ ነው። መንግስትን ከመጠበቅ ባለፈ ለከተማዋ ጽዳት ሀላፊነት የሚሰማው ግለሰብ እስካሁን አላየሁም።
ካለም ጥቂት ነው። አብዛኛው ሰው ስለ ሚኖርበት ቤት እንጂ ስለሚጠራበት ከተማ ግድ ሲኖረው አላየሁም። ብዙሃኑ የቤቱን ቆሻሻ አስፓልት ዳር የሚደፋ ነው። አብዛኛው ሰው መንገድ ላይ የሚጸዳዳ ነው። ከተማ ሳይጸዳ ሰፈርና መንደር መጽዳቱ ትርጉም እንደሌለው እንዲገባን እፈልጋለው። እኛው በደፋነው ቆሻሻ በየመንገዱ አፍንጫችንን እየያዝን እየሄድን፣ ለጉንፋንና ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጥን ቤትና ሳሎናችንን ማጽዳቱ ጥቅም የለውም። ከተማ ሳይጸዳ፣ በየቦታው የቆሻሻ ክምር እያየን ፎቅ መገንባት ትርጉም አለው ብዬ አላምንም። አንድ ከተማ ከህንጻና ከመኪና ሰልፍ ባለፈ ውብና ጽዱ መሆን ግድ ይለዋል። በአራቱም የከተማዋ አቅጣጫ በጣም የሚገርመው ደግሞ ትላልቅ ህንጻዎች አጠገብና የህብረተሰብ መገልገያ አካባቢዎች ላይ ሳይቀር የቆሻሻ ቁልል መኖሩ ነው።
እኔ ከምኖርበት ጊቢ ፊት ለፊት አንድ ሴት አለች.. አሁን ላይ ሳስበው ለአዲስ አበባ መቆሸሽ ግንባር ቀደም ተጠያቂ እሷ ትመስለኛለች..እንዴት አትሉኝም? ቀን ጊቢዋን ስታጸዳ ውላ ቆሻሻውን በማዳበሪያ በማስቀመጥ ማታ መሸትሸት ሲል ከልጆቿ ጋር ተጋግዛ አስፓልት ዳር ትጥለዋለች። አንድ ቀን ጥላ ስትመለስ መንገድ ተገናኘን.. እንደዛ ቀን ደንግጣ የምታውቅ አይመስለኝም። ለምን እንደደነገጠች ገብቶኛል..መልሱን ባውቀውም ከእሷ ልስማ ብዬ ‹ምን አስደነገጠሽ? ስል ጠየኳት። ‹ቀበሌዎች የመጡ መስሎኝ ነው› አለችኝ።
ከሰው ይልቅ የህሊና ወቀሳ እንደሚበልጥ አታውቂም?
በማሽሟጠጥ ‹ክፍለ ከተማ ነህ እንዴ? አለችኝ።
‹ህግን ለማስከበር የመንግስት አካል መሆን አይጠበቅብኝም። ሁላችንም ለዚች ሀገር መንግስት ነን። የምሰሪው ነገር ልክ አይደለም..ለከተማችን ውበት ሁላችንም ሀላፊነት መውሰድ አለብን። እኔና አንቺ ቆሻሻችንን በአግባቡ ማስወገድ ካልቻልን የመንግስት ጥረት ብቻውን ዋጋ የለውም። ለውጥ ከራስ ይጀምራል። አልኳት። ከዛን ሰዐት ጀምሮ ሰላም ብላኝ አታውቅም። እኔም ሰፈር ቀየርኩ።
አዲስ አበባ የቆሸሸችው በእኛ ነው። እኛ ለከተማችን ሀላፊት ቢሰማን ኖሮ የአፍሪካ መዲና የሆነችው ከተማችን በዚህ ልክ አትቆሽሽም ነበር። የቆሻሻ ገንዳ እያለ እንኳን ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ቆሻሻ የምንጥል ሰዎች ነን። የተስተካከለ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዐት ያስፈልጋል። ህንጻው አስፓልቱ የቤታችንን ጥራጊ መድፊያ ሆኖ እንዴት ነው ስለ ውበት የሚገባን። በየመንገዱ ለደረቅ ቆሻሻ ተብለው የተቀመጡ ኮንቴኔሮች እያሉ እንኩዋን ቆሻሻዎቻችንን በየመንገዱ ነው የምንጥለው። የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች ተገብተውልን አጥር ጥግ ነው የምንጸዳዳው። ለመገረም ዝግጁ ከሆናችሁ በርካታ የሚያስገርሙ ነገሮችን ታያላችሁ። በየሀይላንዱ ሽንት ሸንተው መንገድ ላይ የሚጥሉ፣ ምግብና አላስፈላጊ ነገሮችን በፔስታል አድርገው የሚጥሉ በርካታ ግለሰቦች አሉ።
ዘመናዊነት የፎቅ ብዛት ብቻ አይደለም..ዘመናዊነት የከተማ ውበትም ጭር ነው። ሀዋሳ ና ባህርዳር የብዙዎቻችንን ቀልብ ስበው የቆዩት በውበታቸው ነው። አዲስ አበባ ሲሆን ግን በክረምት ጎርፍ በበጋ ቆሻሻ በዚህ ሁሉ ውስጥ መኖር ነው። የአዲስ አበባ ኑሮ እንባና ሳቅ ይመስለኛል ዘመናዊነቷ ደስ ሲልህ በጎን ደግሞ በቆሻሻዋ ታስመርርሀለች። ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ ነውና… እስኪ አዲስ አበባን በክረምት ሰሞን እንዴት ትገልጧታላችሁ? አስቸጋሪ ናት አይደል? አስፓልት ላይ የሚወርደው ጎርፍ አባይና ጣናን ያስታውሳል። ጫማ አውልቆ፣ ሱሪ ጠቅልሎ መሻገር፣ መኪና ያሰመጠ፣ .መንገድ የዘጋ ጎርፍ..ቆሻሻና ጥራጊ ይዞ የሚሄድ ዝናብ ውሀ እንዲህ ነች አይደል?..በጋ ሲሆን ደግሞ እንደምታውቁት እዛም እዚም ቆሻሻ፣ እዛም እዚም ሰገራ፣ እዛም እዚም ሽታ፣ እዛም እዚም በሽታ.. የአፍሪካ መዲናዋ..የአለም የዲፕሎማሲ መቀመጫዋ ሸገር አዲስ አበባ ክረምትና በጋ ይቺ ናት። አንድ ኮሜዲ በአዲስ አበባ ላይ ሲቀልድ ሽታዬ ብሎ ነበር የቀለደው። አዲስ አበባ እንደ ስሟ አበባ እንድትሆን የሁላችንም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል።
መንግስት ብቻውን የሚፈጥረው ተዐምር የለም። በቅርቡ በተጀመረው የሸገር ማስዋብ ፕሮግራም ላይ ሁላችንም ባለድርሻ ሆነን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን። አዲሲቷን በሁሉ ነገሯ ውብ የሆነችውን አዲስ አበባ ለመፍጠር ትክክለኛ ጊዜ ላይ እንገኛለን። የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል። ጽዳትን ከቤታችን በመጀመር..አካባቢያችንን ማስዋብ ከጀመርን ከተማችን የማትዋብበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ለሀገራችን የቤትና የአካባቢያችን ጽዱ መሆን አስተዋጽኦ አለው። ጽዱ አካባቢ ከከተማነት ባለፈ በርካታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። የመጀመሪያው የገጽታ ግንባታ ነው ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ማህበረሰባዊ እሴቶችም አሉት።
ጽዱ በሆነ አካባቢ የሚኖሩ፣ የሚማሩ የሚጫወቱ፣ የሚያድጉ ህጻናት ስብዕና ግንባታቸው ላይ ከፍተኛ ዋጋ አለው። የከተማን ጽዳት ከራስ ጽዳት ጋር ማያያዝ እንችላለን…ከተማ ጸዳ ማለት በዚያው ልክ አስተሳሰባችንም ተስተካከለ ማለት ነው። ባልጸዳና ባላማረ አካባቢ መኖር በራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍ ያለ ነው። ለራሳችን ለሌሎችም ስንል ከተማችንን ውብና ጽዱ ማድረግ ይኖርብናል። መልካም ህይወት ከመልካም ኣካባቢ የሚወጣ ነው። መልካም አመለካከት ከመልካም አካባቢ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ጽዳት የዘመናዊነት አንዱ መገለጫ ነው። ከተሞቻችን መጠሪያዎቻችን ናቸው። አለም ኢትዮጵያን ከምታውቅባቸው አጋጣሚዎች አንዷ አዲስ አበባ ናት።
በርካታ የውጪ ሀገር ዜጎችን ተቀብላ የምታስተናግድ ከተማ ናት። በሁሉ ነገሯ ምቹ መሆን ይኖርባታል። ጽዳት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ይሄ ሁሉ ባይሆን እንኳን ዜጋ ሆነን እስከኖርን ድረስ ሁላችንም አካባቢያችንን ከብክለት የመጠበቅ የዜግነት ግዴታ አለብን። ያልታጠበ የቆሸሸ ልብስ መልበስ የሚፈልግ አለ? የለም አይደል..አካባቢም እንደዛ ነው ቤታችን ጸድቶ አካባቢያችን ካልጸዳ ዋጋ የለውም።
ቤትና አካባቢያችን ጸድቶ ከተማችን ካልጸዳ ትርጉም የለውም። ሰፈርና መንደር የከተማ ውጤቶች ናቸው። ሁሉም ነገር የሚሆነው ከተማ ሲጸዳ ነው..ማጽዳት ባንችል እንኳን ለመቆሸሹ ምክንያት አንሁን። ከተማችንን በአግባቡ መያዝ ሳንችል ሌሎች ሀላፊነቶችን እንወጣለን ብዬ አላምንም። በአእምሮ ውብ ነገር ይፈልጋል..ውብ ነገር ማየት መንፈስን ያድሳል። በተባበረ ክንድ ሁላችንም የከተማችንን ውበት እንጠብቅ እላለው። እንደተለመደው በሁለት ስንኝ ግጥም ትዝብቴን እቋጫለው።
‹ምን ብናምር ብንደምቅ ብንዘምን በአለም
ከተማ ሳይጸዳ ስልጣኔ የለም።
አዲስ ዘመን የካቲት 02/2013